አዲስ አበባ:- ከተማን ቀስፎ የያዛትን የትራንስ ፖርት ችግር ይፈታል ተብሎ የተዘረጋው የቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ 41 ባቡሮችን ይዞ ነበር ወደ ሥራ የገባው፡ ፡ ሆኖም የቀላል ባቡር ትራንስፖርት ያለበት ሁኔታ አሳሳቢና ፈጣን መፍትሄን የሚሻ ነው።
ለምሳሌ፣ የትራንስፖርት ዘርፉ በሁለት መስመሮች (ምስራቅ-ምእራብ እና ሰሜን-ደቡብ) በመሰማራት በየቀኑ በአማካይ እስከ 120ሺህ መንገደኞችን የሚያጓጉዝ ሲሆን፤ የእለት ገቢውም በአማካይ ከብር 480ሺህ በላይ እያስገባ መሆኑ ሲነገርለት የነበረው ቀላል ባቡር፤ ዛሬ ወደ ብር 330ሺህ እስከ 350ሺህ መውረዱ ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ሥራው ሲጀመር በየስድስት ደቂቃ ቆይታ ለተጠቃሚው ይደርስለታል ተብሎ የተነገረለት «ፈጣን» ዘርፍ ዛሬ ከ15 እስከ 25 ደቂቃ ሰዎችን ሲያንቃቃ ስለመዋሉ ተጠቃሚዎች በኀዘኔታ እየ ተናገሩለት ነው። ይህ ብቻ አይደለም፤ በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡት ከ22 እስከ 26 ሲሆኑ ሌሎቹ ከአገልግሎት ውጪ ሆነው ቆመዋል፡፡ ይህ ለምንና እንዴት ሆነ? የኮርፖሬሽኑ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ደረጀ እንደሚሉት፤ የትራንስፖርት ዘርፉን የፊጥኝ የያዙት ችግሮች በርካታ ናቸው። ለአብነት፣ ለዘርፉ ቃል የተገባለት ድጎማ መቅረቱ ዋንኛው ችግር ነው፡፡
ይህ ደግሞ በዋናነት የአዲስ አበባ አስተዳድርን ይመለከታል። ምክንያቱም ባቡሩ ወደ ሥራ ሲገባ ከአስተዳደሩ ጋር በተደረሰው የድጎማ ስምምነት መሰረት በየዓመቱ 1ነጥብ5 ሚሊዮን ብር መክፈል ቢጠበቅበትም እስካሁን ይህ አልተደረገም። ይህም የቀላል ባቡር ትራንስፖርቱ በሙሉ አቅሙ እንዳይሰራ ማነቆ ሆኖበታል። በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየ ቅናቸው በአዲስ አበባ አስተዳደር የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ ግን በዚህ አይስማሙም። በርግጥ «ኮርፖሬሽኑ ድጎማው ይከፈለኝ ብሎ ጥያቄ አቅርቧል፤ እኛም ምን ያህል መከፈል እንዳለበት ከነልዩነቱ አጥንተን የውሳኔ ሃሳብ ለሚመለከተው አካል አቅርበናል።»
የሚሉት ምክትል ኃላፊው፤ «ኮርፖሬሽኑ የይከፈለኝ ጥያቄውን ያቀረበው ባለፈው ዓመት ነው፤ ይሁን እንጂ ችግሮች ሳይለዩ፣ ምን የማን ኃላፊነት እንደሆነ እና ትርፍና ኪሳራው ሳይታወቅ እንዲሁ መክፈል ስለማይቻል ይህን ለማጣራት ሲጠና ነው የቆየው» ሲሉም ያስረዳሉ።የኮርፖሬሽኑ መረጃ እንደሚያስረዳው በዘርፉ ያለውና ተግባሩን እየተገዳደረው የሚገኘው፤ ሌላው ትልቅ ችግር ሜቴክ ሰራሽ ኬብሎች መቅለጣቸውና እነሱን ለመተካት የውጭ ምንዛሪ እጥረት መግጠሙ ነው። ሥራ ላይ የዋሉት ኬብሎች በቱርክ ኩባንያ እና በኢትዮጵያዊው ሜቴክ የተመረቱ ሲሆን፤ የሜቴክ ምርት የሆነው ኬብል ባልተጠበቀ ዕድሜው በመቅለጡ በሥራው ላይ ከፍተኛ እንቅፋትን ፈጥሯል።
የተሳፋሪዎች ኃላፊነት የጎደለው አጠቃቀምም ሌላው ፈተና መሆኑን ነው ኃላፊዎቹ የሚናገሩት። ከተገኘው መረጃ መረዳት እንደተቻለው የቀላል ባቡር ትራንስፖርት ታሪፍ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የተጠቃሚውን ህብረተሰብ አቅም በማየት ለመደጎም በማሰብ ነው፡፡ በመ ሆኑም ታሪፉ ሁለት፣ አራት እና ስድስት ብር እንዲሆን ተደርጓል። ይሁን እንጂ ይህንን የሚገ ዳደሩና ኮርፖሬሽኑን ለኪሳራ የሚዳርጉ፤ ቲኬት ማጭበርበርን የመሳሰሉ አስነዋሪ ተግባራት ባንዳ ንድ ተሳፋሪዎች በኩል ሲፈፀሙ ይታያል፡፡
ይህም የአጭር ርቀት ቲኬት እየቆረጡ ረጅም ርቀት በመጓዝ፤ ጭራሹንም ሳይቆርጡ መግባት እየተለመደ ነው። አቶ ደረጃ እንደሚሉት፤ ችግሩን ለመከላከል ቲኬት ሳይዙ ለሚጓዙ 100 ብር፤ የአጭር ረቀት ገዝተው ረጅም ርቀት ለሚጓዙ የ30 ብር ቅጣት የተቀመጠ ቢሆንም ተጠቃሚው በቅጣት ሳይሆን በአግባቡ ከፍሎ በመጠቀም ማመን አለበት፡፡ ህብረተሰቡ በተለይም የትራንስፖርቱ ተጠቃሚ የባቡር ትራንስፖርት ዘርፉ ከሚሰጠው አገልግሎት ጎን ለጎን ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅና የፋይናንስ አቅምን የሚፈለግ መሆኑን መረዳት ይኖርበታል፡፡
ታሪፉ ራሱ ዝቅተኛ ሆኖ ሳለ በዚህ ላይ ማጭበርበር ሲታከልበት የኮርፖሬሽኑን ገቢ እጅጉን ስለሚጎዳውም ይሄን የሚያደርጉ ወገኖች ከዚህ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል፡፡ ይህን የማጭበርበር ተግባር ለመቆጣጠርም ኮርፖሬሽኑ ዘመናዊ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ለመጠቀም የሚያስችለውን ጅምር ጥናት እንደተጠናቀቀም ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ ለጊዜው ስሙ እንዲገለፅ ያልፈለገ ተቆጣጣሪ፣ ችግሩ መኖሩን በማረጋገጥ የእርሱንም ገጠመኝ ይናገራል፡፡ ቲኬት ሳይዙ እጅ ከፍንጅ የያዛቸው ተሳፋሪዎች የሰጡትን ምላሽ በማስታወስ ሳቅና ንዴት በተቀላቀለበት ስሜት ሲገልጽ፤ «ለቻይና ልትሰጠው ነው፣ እኛ ወገኖችህ አይደለንም፣ አንተ ኪስ ይገባል፤…» እንደሚሉት ይናገራል፡፡
ይህ ድርጊት ካልቆመም ለድርጅቱ አደጋ በመሆኑ ሁሉም የእኔነትና የኃላፊነት ስሜት ሊኖረው፣ለህግ መገዛትና ሥነ-ሥርዓት ማክበር እንዳለበት ይገልጻል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ባልደረባና ተቆጣጣሪ እንደሚ ገልፀው፤ «በኮርፖሬሽኑ ማናጅመንት በኩል ከፍተኛ የሆነ ድክመት አለ፡፡ የሠራተኛ አስተ ያየት እንኳን ለመቀበል የሚፈልግ የለም። አንድ ሠራተኛ ከተናገረ በተለያየ ዘዴ ከሥራ እንዲለቅ ይደረጋል። ሆኖም አዲሱ አመራር የሠራተኛውን ችግር ለመለየት የሚያስችል 35 ጥያቄዎችን የያዘ መረጃ መሰብሰቢያ መጠይቅ ማሰራጨቱ ችግሩ ይፈታል የሚል ተስፋ አሳድሮባቸዋል። ለሁለት ዓመት በደንበኝነት የዘለቀው ወጣት ስፖርተኛ ኡመር ሀሰን በበኩሉ፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ የትራንስፖርቱ መኖር የሚደነቅ ነው፡፡ ሆኖም የመጠበቂያ ጊዜው በየጊዜው እየጨመረ በመሄዱ አሁን ላይ እስከ 25 ደቂቃ መጠበቅ እየተለመደ መምጣቱን ይናገራል፡፡
ባጠቃላይ ሲታይ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት ዘርፉ በበርካታ ችግሮች የተተበተበ እንደመሆኑ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተግባብተውና ከችግር ጸድተው በመቀናጀት በባለቤትነት ስሜት ከሰሩ ችግሩን መፍታት ይቻላል፡፡ የቆሙት ባቡሮች ተነስተው፣ የትራንስፖርት ችግሩም ተቀርፎ፤ ኮርፖሬሽኑም ከኪሳራ ተርፎ ማየት ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2011
በግርማ መንግሥቴ