ሕወሓት በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ላይ ሰፊ ጉዳቶችን ማድረሱ ተደጋግሞ ይገለፃል። ከአመት በፊት በትግራይ ክልል በደረሰው የኤሌከትሪክ መሠረተ ልማት ጉዳት 11 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ውድመት መድረሱ መገለጹ ይታወሳል::
በቅርቡ በአፋርና አማራ ክልሎች ላይ ባካሄደው ወረራም በርካታ የመሠረተ ልማት ውድመቶች የደረሱ ሲሆን፤ ከአገልግሎት ዘርፍ መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል ውድመት አንዱና ዋናው ነው።
በዚህ ጉዳትም ኅብረተሰቡ ከስድስት ወር ላላነሰ ጊዜ በጨለማ ውስጥ እንዲያሳልፍ ተገዶ ቆይቷል። በኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ ኢንሱሌተሮች፣ ኮንዳክተሮች፣ ምሰሶዎችና ሌሎች የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ በደረሰው ጉዳት ተቋሙ በርካታ ሚሊዮን ብሮችን እንዳጣ ይገመታል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በተቋሙ ላይ ስለደረሰው ኪሳራ ብሎም አሁን ላይ ኅብረተሰቡ ተቋርጦ የነበረውን ኃይል እንዲያገኝ የተሠራውን ሥራና የተገኘውን ውጤት አስመልክተው ይህንን ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን፦ በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ምክንያት በአፋርና አማራ ክልሎች ላይ የደረሰው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ውድመት ምን ያህል ነው?
አቶ ሞገስ፦ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ተቆጣጥሯቸው በነበሩ አካባቢዎች ላይ በርካታ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፤ ከእነዚህም መካከል አንደኛው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ነው።
ይህንን ውድመት በዓይነት ስናየው ደግሞ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የማስተላለፊያ መስመሮች (ኮንዳክተሮች) ተቆርጠዋል፡፡ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ አንድ ኃይል የሚያልፍበት መስመር ከሌላው ጋር እንዳይነካካና ኤሌክትሪክ መቋረጥ ፈጥሮ ችግር እንዳይከሰት የሚያደርጉ ስኒዎች (ኢንሱሌተር) የተሰባበሩበት ሁኔታ አለ።
ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ የኤሌከትሪክ ምሰሶዎች (ታዎሮች) የወደቁበት ቦታ ከመኖሩም በላይ ዳታና ድምጽን ለማስተላለፍ የሚያስችል ኦፕቲካል ግራውንድ ፋይበር ሁሉ ለከፍተኛ ጉዳት ተዳርገዋል።
በጠቅላላው ግን መስመሮች ተበጣጥሰዋል፤ ታወሮች ወድቀዋል፤ ኢንሱሌተሮች ተሰባብረዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች መስመሮቹ ባይበጠሱም በጥይት ስለተመቱ ኤሌክትሪክ ተሸክመው ማስተላለፍ አይችሉም። አሁን ላይ ጉዳቱ ከሙላ ጎደል የሚመስለው ይህንን ነው።
አዲስ ዘመን፦ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቱ ላይ የደረሱት ጉዳቶች በገንዘብ ሲተመኑ ምን ያህል ዋጋ አላቸው?
አቶ ሞገስ፦ እውነት ለመናገር የጉዳት መጠኑ በገንዘብ ደረጃ እስከ አሁን ድረስ ተሰልቶ አላለቀም። ምክንያቱም አንደኛው አካባቢ ላይ ያለው መስመር ሌላኛው አካባቢ ድረስ የሚዘልቅ ነው። ለምሳሌ እስከ ወልዲያ ድረስ ያለውን ጨርሰናል፤ መረጃውንም ይዘናል።
ነገር ግን ከወልዲያ ቆቦ አላማጣ ያለው መስመር ምን ያህል ጉዳት ደረሰበት? የሚለው ሳይጠናቀቅ የመስመሩ አንድ አካል የሆነው የተወሰነ ክፍል ብቻ ይህንን ያህል ነው ማለት የተሳሳተ ግምት ያስወስዳል በሚል መረጃዎች ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቁ ድረስ እየጠበቅን ነው። እዚህ ላይ ግን ከኮምቦልቻ በባቲ ወደ ሚሌ አድርጎ ሰመራ ድረስ የሚዘልቀው የኤሌክትሪክ መስመር ጉዳት ከደረሰባቸው ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡ በዚህ መስመር ላይ ሁለት ታዎሮች ወድቀዋል።
በዚህ ብቻ ጉዳቱ ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ነው። ሌሎች አካባቢዎች ግን ለምሳሌ ከደብረሲና፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ እንዲሁም ወልዲያ አካባቢዎች ጉዳቶቹ በዓይነት ተለይተዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም የተጠናቀቀ ካለመሆኑም በላይ ገና የኢንጂነሪንግ ግምት አልተሠራላቸውም። በመሆኑም መግለጽ ይከብዳል ።
ጋሸና ላይም የደረሰው ጉዳይ የሚመዘዘው ከደብረ ታቦር ጀምሮ ነው፡፡ በዚህም ገረገራ ጋሸና ድረስ ያለው ተጠናቋል፡፡ ግን ደግሞ ቀሪ ሥራዎችም በመኖራቸው የጉዳቱን መጠን በገንዘብ ማስቀመጥ ከባድ ነው።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል የሚባልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ማለት ይቻላል?
አቶ ሞገስ፦ አዎ! ጋሸና ድረስ ያለው ሙሉ በሙሉ ሊያስብል በሚችል ተጠናቋል። ነገር ግን እዚህ ድረስ ተጠናቀቀ እንጂ ገና ቀሪ ሥራዎች አሉ። ለምሳሌ ዋግ ኽምራ ላይ ያሉ የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም የኤሌክትሪክ አገልግሎት አላገኙም። በሌላ በኩል ደግሞ በምዕራብ በኩል ያለው የአማራ ክፍል ማለትም ወልቃይት ሁመራም አሁን ኤሌክትሪክ እያገኙ አይደለም።
እነሱ እንዲያውም ችግር ውስጥ ከገቡ ከአንድ አመት በላይ ሆኗቸዋል። እነ ላሊበላም አሁን ላይ ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ የሆነው በአማራጭ ማለትም ከገናሌ ዳዋ 3 ላይ ጀነሬተር ወስዶ በመተካት ነው፤ እንጂ ሥራው ተጠናቆ ጥገናው ሙሉ በሙሉ አልቆ በነበረበት ተመልሶ አይደለም። በመሆኑም በዋግኽምራ ዞን ሰቆጣ አካባቢ ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል።
አዲስ ዘመን፦ በእነዚህ አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ ችግሩን ለመቅረፍ ጊዜ እየወሰደ ያለው ጉዳቱ ከፍ ያለ ስለሆነ ነው?
አቶ ሞገስ፦ ይህ አካባቢ ኤሌክትሪክ ያገኝ የነበረው ከአላማጣ በሚወጣ 66 ኪሎ ቮልት መስመር ነበር፡፡
አሁን የሠራነው እስከ ወልዲያ ነው፤ እስከ አላማጣ ድረስ ሄዶ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ከአላማጣ ደግሞ ወደላሊበላና ሰቆጣ የሚሄደውን መስመር መሥራትም ያስፈልጋል። እነዚህ ሲሠሩ ደግሞ ዋጋቸው ስለሚታወቅ ተቋሙን ምን ያህል ኪሳራ ውስጥ አስገብተውታል የሚለውም በዚያው ተጠናቆ ይገለጻል። በሌላ በኩል በእነዚህ አካባቢዎች እስከ አሁን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማስጀመር ያልተቻለው የመጀመሪያው አካባቢዎቹ ነጻ የወጡት ከሁሉም በኋላ በመሆኑ ነው፡፡
ሁለተኛ ደግሞ የጥገና ቡድኖቻችን ወደሌሎች አካባቢዎች የሚሄዱት ቀድመው ነጻ በወጡ አካባቢዎች ያሉ ሥራዎችን እየጨረሱ ነው፡፡ አገልግሎቱ የዘገየው በእነዚህ ምክንያቶች ነው፡፡ ቀጥሎ የሚሆነው ሥራ አሁን ወልዲያ ላይ ተደርሷል፡፡ በሁለቱም መስመር ያሉ ቀሪ ሥራዎች ላይ ባለሙያዎች ይሰማራሉ።
አዲስ ዘመን፦ እነዚህን ጉዳቶች ግን በከተማ ደረጃ ማስቀመጥ ይቻል ይሆን? ምን ለማለት ፈልጌ ነው በአማራ ክልል ይህንን ያህል ከተሞች ላይ ወድመት ደርሷል፤ በተመሳሳይ በአፋር ክልልም እንዲህ ሆኗል ሊባል የሚችል ነገር ካለ ?
አቶ ሞገስ፦ ይህንን ለመግለጽ ያስቸግራል፤ ምክንያቱ ደግሞ የእኛ ከፍተኛ የኃይል ማሰራጫ መስመሮች በብዛት ያሉት ከከተማ ወጣ ባሉ መስመሮች ላይ ነው፡፡ ትልልቅ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ካልሆኑ በቀር ከተሞች ላይ ሌሎች ነገሮች የሉንም።
ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎቻችን ላይ ደግሞ ብዙ የደረሰ ጉዳት የለም። ነገር ግን በከተማ ደረጃ በአፋር በኩል ካሳጊታ ቡርቃ አለ ውሃ በሚባሉ አካባቢዎች የደረሰው ጉዳት በጣም ከፍተኛ ነው። በጋሸና መስመርም በተመሳሳይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።
በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ያለው የመልሶ ግንባታ ሥራ ቢጠናቀቅም በኃይል ዘርፉ ብቻ የሚሠራው ሥራ ኅብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሊያደርገው ስለማይችል፤ የስርጭት መስመሮች ደግሞ መጠገን ነበረባቸው። ይህም ቢሆን ግን የአገልግሎት ዘርፉ ባለሙያዎች በዛ ፍጥነት ገብተው ሥራውን ሊያጠናቅቁ ስለማይችሉ የነበረው አማራጭ የእኛ ባለሙያዎች ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በተመሳሳይ የአገልግሎት ዘርፉን ሥራ የማገዝና እንዲፋጠን የማድረግ ከተሞቹም ኤሌከትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል።
መጠቀስ ያለበትና ትልቅ ጉዳት ደርሶብናል ብለን የምንለው ወልዲያ «ዶሮ ግብር» በሚባለው አካባቢ ላይ ያለው 230 ኪሎ ቮልት አቅም ያለው ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የደረሰው ጉዳት ነው፡፡
ይህ ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ ሙሉ በሙሉ ተነቅሎ ተወስዷል፡፡ ከውስጡ አንዲት ቡሎን እንኳን እንዲተርፍ አልተደረገም። መከላከያ ወልዲያ ነጻ መውጣቷን ቅዳሜ ቀን ተገልጾ፤ እኛ እሁድ ቦታው ላይ ስንደረስ እጅግ በጣም በሚያስደነግጥ መልኩ ማከፋፈያ ጣቢያው ተነቅሎ ሄዷል።
ሌሎች አካባቢዎች ላይም የተወሰኑ ዝርፊያዎች ነበሩ፡፡ የመቆጣጠሪያ ማሽኖች (ብሬከሮች) መውሰድ፡፡ የሚሠሩ ትራንስፎርመሮችን ፈትሾ ይዞ በመሄድ ትልቅ ጥፋት ተፈፅሟል። እዚህ ግን ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያው ተነቅሎ መሄዱ እጅግ በጣም ትልቅ ጉዳትም ድንጋጤም አድርሶብናል።
አዲስ ዘመን ፦ ከተሞች ነጻ ከወጡ በኋላ እንደተቋም የሄዳችሁበት የመልሶ ጥገና ሥራ በጣም ውጤታማ እንደሆነ ታዝበናል፡፡ ሥራው ሲታሰብ ከእቅድ ጀምሮ እስከ አፈጻጸም ድረስ የነበረው ሂደት ምን ይመስላል?
አቶ ሞገስ፦ በዋናነት ሕወሓት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ላይ ኅብረተሰቡ የደረሰበትን ጉዳት እንደማንኛውም ሰው የተቋሙ አመራሮችም ሆነ ማኔጅመንቱ ሲሰማ ከፍተኛ የሆነ ደንጋጤና ኀዘን ተሰምቶናል፡፡
በዚህ ጊዜ ማኔጅመንቱ ተቀምጦ የወሰነው ውሳኔ መንግሥት አካባቢዎቹን ነጻ ሲያወጣቸው ምን ዓይነት ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል? በሚለው ላይ በመወያየት መደረግ ስለሚገባቸው ድጋፎች ልየታ ተከናውኖ ለሥራው የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች ሲካሄዱ ነበር።
እንደ ተቋም ሕወሓት ይህንን ያህል ገፍቶ ደብረሲና ደርሶ ያንን ያህል በመሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ያርሳል የሚል ግምት አልነበረም። ነገር ግን ሊመጣ የሚችለውን ችግር በቶሎ ቀርፎ ኅብረተሰቡ በቶሎ ወደመደበኛ ሕይወቱ የሚገባበት ነገር ላይ መሥራት አለብን ተብሎ በማኔጅመንት አቅጣጫ ከተቀመጠ በኋላ የሚመለከተው ዘርፍ የራሱ የሆነ ዝግጅት ሲያደርግ ነበር። የዘርፉ ዝግጅት የጀመረውም ዘጠኝ ሪጅኖች አሉ፡፡ በእነዚህ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች አስፈላጊ የሆኑትን ዝግጁ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል።
ከዚህ በተጨማሪ ለጥገናው የሚሆኑ ዕቃዎችን ከመጋዘን (ስቶር) የማሰባሰብ፤ በዚያ የሌሉትን ደግሞ ሪጅኖች ላይ ያሉ ማቆያዎችና ለጊዜው ለሌሎች ጥገናዎች ዝግጁ ሆነው ከተቀመጡት የማሰባሰብ ሥራዎች ተከናውነዋል። መከላከያ ኃይላችን ደብረሲናን ጨምሮ የሸዋሮቢት አካባቢዎችን ነጻ እያወጣ መሄድ ሲጀምር፤ እኛም በማግስቱ እየተከተልን ወደ ሥራ ገብተናል። ሥራው ሲጀመር ለባለሙያዎቻችን ፈታኝ ሆኖ የነበረው፤ በመንገዶች ላይ በርካታ አስከሬኖችን ማለፍ ነበረባቸው እንዲያውም የመጀመሪያ ቀናቶች ላይ ለመቅበር ሙከራ አድርገው ነበር፡፡ ነገር ግን ከብዛቱ የተነሳ ስላልተቻለ እሱን በመተው ወደ ጥገና ሥራቸው ገቡ፡፡
በተሠራው ሥራ ግን በየከተሞቹ ውጤቶች ሲታዩ የኤሌክትሪክ መጀመር ማህበራዊ መስተጋብሮችን ማንቀሳቀስ ሲጀምር ሠራተኞቻችንም ይበልጥ እየተበረታቱ መጥተዋል ። እውነት ለመናገር ሥራው ሲጀመር ለምሳሌ ሸዋሮቢት ሙሉ በሙሉ የወደመች ከተማ ነች፡፡ ሠራተኛው ሥራውን የሚሠራው ከከተማ ውጪ ነው፡፡
ጠዋት ወጥቶ ማታ እስከሚመለስ ምግብ እንኳን ቢፈለግ ከተማ ወጥቶ እመገባለሁ ሊል የሚችልበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሠራተኞች በትዕግስትና በትጋት እናልፈዋለን በሚል ስሜት በመነሳሳት ጥሩ ውጤት ለማግኘት ተችሏል።
በሌላ በኩል ለሥራ በገባንባቸው አካባቢዎች ላይ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች እገዛ ማድረግ ጀመሩ፡፡ በተቻለ መጠን ከፍ ያለ ጉዳት ያልደረሰባቸውን አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለማንቀሳቀስ ተሞከረ፤ ይህ ደግሞ የበለጠ ኃይል እየሆነ የበለጠ ውጤት እያመጣ ሄደ። እዚህ ላይ ተቋሙ ሁሉንም የወደሙበትን መሠረተ ልማቶች በአንድ ጊዜ ጠግኜ አገልግሎት አስጀምራለሁ ቢል ኖሮ ምናልባትም ኅብረተሰቡ ለተጨማሪ ከሦስት እስከ ስድሰት ወራት ድረስ በጨለማ ውስጥ መክረም ይኖርበት
ነበር፡፡
ነገር ግን ለምሳሌ ከአንድ ከተማ እስከሚቀጥለው ድረስ ያለውን መጀመሪያ በመስራት እየተሳካና ውጤቱ ከታየ በኋላ ደግሞ ከዚህኛው ከተማ እስከሚቀጥለው ድረስ ያለውን የመጠገን ሂደት ነበር፡፡ ልክ ከሚሴ ከታለፈ በኋላ ኤሌከትሪክ በመገኘቱ ኅብረተሰቡ ተደሰተ፡፡
አንዳንድ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሲነቃቁ፤ ኅብረተሰቡም ጋር መረጃዎች ሲደርሱት ሕዝቡም ለተቋሙ ያለውን ስሜት ሲገለጽ ሠራተኞቹ በመነቃቃት ከተማው ዛሬ ኃይል ሳያገኝ አያድርም እያሉ እልህ ውስጥ ገብተው እንደውም እስከምሽት ድረስ በሥራው ላይ በመቆየት ሰርተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሕዝባችን በመጠኑም ቢሆን ችግሩ ቀለል እንዲልለት አድርጓል። ለምሳሌ በኮምቦልቻና በደሴ መካከል ያለው ርቀት ትንሽ ነው፡፡ ነገር ግን መስመሩ ከዋና መንገድ ውጪ ስለሆነ ተራራ ቁልቁልት ሁሉ ማለፍ ነበረባቸው፤ ያንን ሁሉ ተቋቁመውና እኛ ደርሰን አንድ ቀን እንኳን በጨለማ ማለፍ የለበትም በማለት ሠርተው ወደ አራት ሰዓት አካባቢ መብራት ማብራት ችለዋል።
ይህ የሠራተኛው ትጋት እንዳለ ሆኖ የውስጥ አመራሩም ጭምር ከፍተኛ ትኩረት ከመስጠቱም በላይ ቢሮ ቁጭ ብሎ ይህንን አድርጉ ያን ስሩ የሚል ሳይሆን በተለይም በቀጥታ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች በቦታው ላይ በመገኘትና ከሠራተኞቹ ጋር እኩል እየሠሩ አቅጣጫ በመስጠት ስለመሩት የሠራተኛውም ትጋት በዚህን ያህል ተገልጿል። የኅብረተሰቡን ችግር በጋራ ለመቅረፍ ጥሩ የሆነ የመናበብ ሥራ በመሥራት በጋራ ክንድ ውጤት ማግኘት ተችሏል።
አዲስ ዘመን፦ በዚህ ሥራ ላይ ለተቋሙ በጣም ፈታኝ የነበረው የሥራ ዓይነት ምን ነበር? እንዴትስ ታለፈ?
አቶ ሞገስ፦ በጣም ፈታኝ ነው ብለን የምንወስደው ጦርነት ተካሂዶ ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች ነጻ ወጡ ተብሎ ከተነገረ በኋላ፤ እኛም በነጋታው ሥራ ለመጀመር ስንሄድ የምናየው የሰው ልጆች ሕይወት መጥፋት፤ የንብረት ውድመት ብቻ በአጠቃላይ አካባቢው ላይ ያለው መጥፎ ሁኔታ በጣም ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የሚከት ነበር።
እውነት ለመናገር አንዳንድ ሠራተኞቻችን ራሳቸውን እንኳን መቆጣጠር የማይችሉበት ሁኔታ ሁሉ ተፈጥሯል። ይህ ደግሞ ሠራተኞቻችን ራሳቸው የምንቀጥለው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው? እስኪሉ የሚያስጨንቅ ነበር። ከዚህ ውጪ ልክ ሥራውን ለመጀመር ስንንቀሳቀስ መከላከያ የራሱን ራሽን ይዞ ይሄዳል፡፡ የእኛ ሠራተኞች ደግሞ ሥራ ተላኩ እንጂ ስለ ቀለባቸው ምንም የታሰበ ነገር አልነበረም።
የታሰበው ከተሞች ላይ አንዳንድ አገልግሎት የሚሰጡ የምግብ ቤቶች ይኖራሉ የሚል ነበር፤ ግን የሆነው በተቃራኒው ነው። ምንም ዓይነት ምግብ ማሰብ ከባድ ከመሆኑም በላይ ሰዎቹ ራሳቸውን ለማቆየት የሚሆን እንኳን ምግብ አልነበራቸውም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሥራ መስራት ትንሽ አስቸጋሪ አድርጎታል። ከዚህ ውጪ እንደ ተቋም በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶቻችን ላይ የደረሰው ጉዳት ይህንን ያህል የከፋ ይሆናል ብለን በፍጹም አላሰብንም።
ከዓመት በፊት ትግራይ ላይ በነበረውና በተለይም በወልቃይት በሽሬ አካባቢ ለመጠገን የተሞከረውን ብናስታውስ ትልቅ ኢንቨስትመንት የጠየቀ ስለነበር ለጥገና የሚሆኑ እቃዎች በሙሉ ጥቅም ላይ ውለው ነበር፡፡
አሁን በዚህ ደረጃ ይመጣል ተብሎ ያልታሰበ ችግር ሲመጣ ሁኔታውን ፈታኝ አድርጎታል። በመሆኑም ወደ ሥራ የተገባው ተቋሙ በማከማቻ ክፍሎቹ ያሉት እንዲሁም በየዲስትሪክቱ የተቀመጡ መለዋወጫዎችን በሙሉ በማሰባሰብና በመያዝ ነበር፡፡ ይህም ከፍተኛ የሆነ የሀብት ኪሳራን አስከትሏል። ምናልባትም ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ነገር ቢያጋጥም አሁን በተሠራበት ፍጥነት ልክ ለመስራት ይቻላል ወይ?
የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው። ብዙ ለመጠባበቂያ ጥገና ሥራ ይውላሉ ብለን የያዝናቸውን መለዋወጫዎችን በሙሉ ለጥገናው ተጠቅመንባቸዋል፡፡ አብዛኞቹ ከውጭ የሚገቡም በመሆናቸው አሁን ላይ እነሱን ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ትልቅ ፈተና ነው።
ይህ ደግሞ አሁን ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩም ጊዜ ፈተና ይሆናል ብለን እየፈራን ነው። በሌላ በኩል እንደ ተቋምም ትርፍ ያገኘንበት ጊዜም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ተቋሙ ኅብረተሰቡ ጋር ያለውገጽታ መገንባት ያስቻለም ጊዜ ነበር።
ሰዎች የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መለየት የቻሉበት ጊዜ የተፈጠረበት ነው። ሁለቱ ተቋማት የዛሬ ስምንት አመት ገደማ አንድ ላይ ነበሩ፡፡ ብዙ ሰዎች የሚያውቋቸው በአንድነታቸው ነበር፡፡
ነገር ግን ሁለቱም ተቋማት አንድ ካለመሆናቸውም በላይ ከፍተኛ የኤሌከትሪክ ኃይል መስመሮች ለሥራ ዝግጁ ቢሆኑም፤ የስርጭት መስመሮች ዝግጁ ካልሆኑ ምንም ትርጉም እንደሌለው ኅብረተሰቡ እንዲረዳ መስሪያ ቤቶቹንም ማወቅ እንዲችል ለማድረግ አስችሏል። አዲስ ዘመን፦ የእናንተ ተቋም ሁለት ጊዜ ነው የተጎዳው በመጀመሪያው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅትም በመልሶ ግንባታ ላይ የነበሩ ባለሙያዎቻችሁ እንደተጎዱ ይነገራል፡፡
ይህ ሁኔታ ዛሬ ላይ ለሠራችሁት ሥራ ተጽዕኖ አልነበረውም ማለት ይቻላል? አቶ ሞገስ፦ ሥራ ሲሠራ ጉዳቶች ያጋጥማሉ፡፡ ነገር ግን ዛሬ ላይ በሠራነው ሥራ የሕይወት ዋጋን የጠየቀ ሁኔታ በፍጹም አልገጠመንም። በሥራ ላይ ሆነው ለምሳሌ ሽቦዎች ሲወጠሩ ተመልሰው ረግበው ባለሙያዎች ግራር እሾህ ላይ ወድቀው የተወጋጉ ነበሩ፡፡
እነሱም ቢሆን የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና ተደርጎላቸው ተመልሰው ወደ ሥራ ገብተዋል። የአገልግሎት ሰጪውን መስሪያ ቤት መስመሮች በሚዘረጉበት ወቅት ያረጁ ምሰሶዎች እየወደቁ የተወሰነ ጉዳት አድርሰዋል እንጂ፤ ከባድ ጉዳት ብለን ልንገልጸው የምንችለው ችግር አላጋጠመንም።
የሚገርምሽ ነገር ባለሙያዎቹ የዛሬውን ሥራ ሥሩ ሲባሉ የባለፈውን እያስታወሱ መቆዘምና መፍራት ሳይሆን እየታየባቸው ያለው ፍጹም ተነሳሽነት፣ እልህና ቁጭት ነው፡፡ በሌላ በኩልም እኔ ለሥራው እንዴትና ለምን አልተመረጥኩም እንዴት እቀራለሁ የሚሉ ባለሙያዎች ብዙ ነበሩ። ከሠራተኞቹ ባሻገር እንዲያውም አንድ ወጣት በግል ስልክ ደውሎ የተማርኩት «ፓወር ኢንጂነሪንግ» ነው፡፡
የምትሠሩት ሥራ ስላስደሰተኝ እኔም መሳተፍ እፈልጋለሁ ብሎ ጥያቄ አቅርቦልኝ ነበር፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የተፈጠረው ችግር በሌሎች ወገኖች ላይ ቁጭትን መፍጠሩን የሚያሳይ ነው፡፡
ይህ ቁጭት ደግሞ የወደመውን መልሶ ወደነበረበት ለመመለስ ሁላችንም እንሳተፍ የሚል ስሜት ፈጥሯል ማለት ይቻላል። አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ የጦርነት ቀጣና ሆነው የቆዩት የአማራና አፋር አካባቢዎች የመብራት አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ ይህ በጣም ጥሩ ነገር ነው፤ ነገር ግን በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ ኢንዱስትሪዎችም እንደገና ወደነበሩበት ለመመለስና አመርተው እንደቀድሞው ለመቀጠል ኤሌክትሪክ ያስፈልጋቸዋል፡፡
በዚህስ ላይ የታሰበው ምንድን ነው? አቶ ሞገስ፦ መጀመሪያ ኅብረተሰቡ የዕለት ጉርሱን እንዲያገኝ መብራት ወሳኝ በመሆኑ እነሱን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ለምሳሌ ከደብረሲና ጀምሮ ሸዋሮቢት፣ ኮምቦልቻ እያልን ስንሠራ በአካባቢው ኤሌክትሪክ የሚያገኘው በሁለት መስመር ነው፡፡
አንደኛው 132 ኪሎ ቮልት የምንለው መስመርና 230 የሚባለው መስመር ናቸው። 230 ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች የሚያገኙት ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከ230 ወደ 132 ኪሎ ቮልት ኃይል እንዲገባ እያደረግን ነው። ነገር ግን አካባቢውን አላማ አድርገን ስንነሳ መጀመሪያ ኤሌክትሪክ ማግኘት ያለበት ሕዝቡ ነው፡፡
ሕዝቡ ሳያገኝ ፋብሪካዎች እንዲያመርቱ የሚያስችል ኤሌክትሪክ መስጠት እርስ በእርሱ የሚቃረን ነው፡፡ መጀመሪያ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የ132 ኪሎ ቮልት መስመር እንጠገን ተብሎ መጀመሪያ የተጠገነውና ከተሞቹም ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ የሆነው በዚህ ነው።
በመቀጠል የተሠራው ግን የ230 ኪሎቮልት መስመሩን ሙሉ ጥገና ነው፡፡ በዚህም እስከ ደሴ ባሉ ከተሞች ላይ ከፍተኛ ኃይል የሚፈልጉ ኢንዱስትሪዎች ቢኖሩ ለእነሱ ኃይል ማቅረብ የሚቻልበት ሁኔታ ዝግጁ ነው፡፡
ምንም ችግር የለብንም። አሁን ትልቅ ችግር ይኖራል ብለን የምንጠብቀው እስከ ወልዲያ ድረስ ባለው ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ኤሌክትሪክ የሚያገኙበት የ230 ኪሎቮልት ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ ሙሉ በሙሉ ተነቅሎ ስለተወሰደ ከዚያ ኃይል ማግኘት አይችሉም።
በመሆኑም መሠረተ ልማቱ ቢኖርም ጣቢያው ስለሌለ ኃይል መስጠት አይቻልም። እዚህ ላይ አሁን እራሱ አካባቢው ኃይል እንዲያገኝ የሆነው በአማራጭ ነው። ምናልባት ከዚህ በኋላ በፈረቃ ኃይል ሊያገኙ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
አዲስ ዘመን፦ የተዘረፈውን የማከፋፈያ ጣቢያ መሣሪያ ሊተካ የሚችል ሥራስ አልታሰበም?
አቶ ሞገስ፦ አዎ ታስቧል፤ እርሱን ሊተካ የሚችል ትራንስፎርመር ወደቦታው ወስዶ ተክሎ አገልግሎት ለማስጀመር እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ይህ ምናልባት አራትና አምስት ወር ገደማ ሊፈልግ ይችላል። አዲስ ዘመን፦ በመጨረሻም እርስዎ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ? አቶ ሞገስ፦ ማስተላለፍ የምፈልገው ሁለት ነገር ነው።
አንደኛው የወደመው በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ የደረሰው ውድመት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ላይ ብቻ የደረሰ ጉዳት ሳይሆን የኅብረተሰቡና አገር አንጡራ ሀብት ነው።
ይህንን ለመተካትም የቻልነውን ያህል ጥረት አድርገናል፤ ብዙ ቦታዎች ላይም ሕዝቡ ኤሌከትሪክ ኃይል ማግኘት ችሏል። ነገር ግን እንደ ተቋም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የገቡ መጠባበቂያዎቻችንን ሁሉ አሟጠን እንድንጠቀም ተገደናል፡፡
የመንግሥትና የሌሎች በጎ ፈቃደኞችን ትኩረት የምንፈልግበት ጊዜ ላይ ነን ብዬ አስባለሁ። በመሆኑም አስተዋጽዖ ማድረግ የሚፈልጉ አካላት ካሉ ተቋሙን መደገፋቸው ኅብረተሰቡን መደገፍ መሆኑን ተገንዝበው በድጋፋቸው መቀጠል አለባቸው። የሽብር ቡድኑ በዚህ መልኩ መሠረተ ልማቶችን ማውደሙ እንዳለ ሆኖ በሌሎች አካባቢዎች ላይ ደግሞ የመሠረተ ልማቶቹን ዝርፊያም በከፍተኛ ሁኔታ ስላለ በእንደዚህ ዓይነት እኩይ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስባለሁ።
ምናልባት እነሱ በጥሰው አገልግሎቱን አቋርጠው የሚወስዱት ነገር ለእነሱ ጥቅሙ ከዕለት የማያልፍ ነው፤ ለተቋሙና ለአገር ግን ብዙ ሚሊዮን ብሮችን የሚያስወጣ በዚያው ልክ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች እነሱን ጨምሮ በኃይል ማጣት ምክንያት ችግር ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግ መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ሞገስ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥር 16/2014