«እማዬ ለምን ‹‹ሰላም›› ስትይ ስም ሰጠሽኝ?» ልጅ እናቷን ትጠይቃለች። እናት «ሰላም እኮ የሁሉ ነገር መሰረት ነው። የምንፈልገውን ማግኘት፤ እምንመኝበት መድረስ፣ የምናልመውን መሆን የምንችለው ሰላም ሲኖር አይደል?።
ስለዚህ ይህን አስቤ የልጄን ስም ሰላም፣ ሰላሜ ብል ምን ከፋሽ?» ልጅ ዝም ብላ በጥሞና ነገሩን የምታላምጥ ይመስል አንገቷን እንዳዘነበለች ከእናቷ የሚወጣውን የቃላት ማር ወደ ህሊናዋ ታንቆረቁራለች። ነገሩ የገባት ይሆን ግራ ያጋባት ብቻ ከአጎነበሰችበት ቀና ብላ « እና እንዳሰብሽው ሰላምን አገኘሽ ?»ስትል ድንገታዊ ጥያቄዋን ቀጠለች። « አዎ! ልጄ አንቺ ሰላማዊ ነሽ፤ የእናትሽን ምክር የምትሰሚ፣ ሰው የምታከብሪ፣ ትምህርትሽን ለነገ የሚበጅሽን የምታስቀድሚ ነሽ፤ ነገ ደግሞ ትልቅ ደረጃ ትደርሻለሽ። ለሀገር ለወገን የምትተርፊ ዜጋ ትሆኛለሽ። የእኔ የእናትሽንም ምክር ሰምተሽ ነገ ታኮሪኛለሽ ፤ ታስደስችኛለሽ…» ፈገግ አለች።
ይሄን መሆን እዚህ መድረስ የማይፈልግ ማን አለ? ልጁ እንዲህ እንዲሆንለት የማይመኝ ማነው?… ለሁሉም ግን የሀገር ሰላም ቀዳሚ ነው። እናትና ልጅም በዚህ ሀሳብ ተግባብተዋል። ወጥቶ ለመግባት፤ ሰርቶ ለማደር፣ አርሶ ለመብላት፣ ነግዶ ለማትረፍ … በሶስት ፊደላት አንሳ የምትታየን ግን የምድር ስፋቱ፣ የሰማይ ርቀቱ የማይገድባት ሰላም ለሁላችንም ታስፈልገናለች። ዋጋዋም ከስም በላይ የገዘፈ ነው። ሰላም ከሌለስ? ሰላማችንን የሚያደፈርስ ካለስ ? ብለን አስበን ሊሆን የሚችለውን አርቀን ገምተን ይሆን? ይሄን ካላደረግን ሁላችንም ተሳስተናል። ከስረናል።
እምንመኘው ቦታ የምንደርሰው፣ ይሄ ለእኔ ያኛው ለእከሌ የምንባባለው በሀገር ላይ ሰላም ሲኖር ብቻ ነው። እንኳን እንዲሆንልን የምንመኘውን ያለንም የእኛ ሆኖ የሚቀጥለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው። ካልሆነ ምንም የማንም የሚሆን ነገር አይኖርም። አርሶ አደሩ አርሶና አምርቶ ጎተራ የሚሞላው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው። በሁሉም መልኩ ሰላም ካልሆነ የተዘራውን አዝመራ ሰብስቦ እንብላ ማለት አይቻልም። ከተማ ወስዶ መሸጥና መለወጥ፤ ለነገ የተሻለ ዕድገትና ልማት ማሰብ አይቻልም። ልጆቼን አስተምሬ፣ ከዩኒቨርስቲ አስመርቄ፣ ድሬ ኩዬ… ማለት ቀድሞ አይታሰብም።
የሰላም አለመኖር የወጣው እንደወጣ የሚያስቀር፣ በቤት ያለውንም በሩ እንደተዘጋ የሚያለያይ አጸያፊ ነገር ነው። እናት ልጇን ከትምህርት ቤት ይመጣልኛል ብላ ስትጠብቅ በድን የምትታቀፍበት፣ አልቅሳ እርሟን አውጥታ መቅበር የማትችልበት በጣም በጣም አስፈሪ ነገር ነው። መግቢያ ወገን የሚያሳጣ፣ ከአገር የሚያሰድድ፣ ሰውን በሰው ላይ የሚያጨካክን ለሰው ልጆች መቼም በምንም ምክንያት ሊሆን የማይገባው ነው የሰላም ማጣት። በዚህ ደግሞ ዋነኞቹ ተጠቂዎች እናቶች ናቸው። ህፃናት ናቸው። አረጋውያን ናቸው። ይሄንን በቅርቡ ከሶሪያውያን ስደተኞች አይተናል።
የነደበቡ ሱዳንን ጉዳይ አስተውለናል። ሌሎችም በሰላም ማጣት የተተራመሱ የዓለም አገራት ኢኮኖሚያቸው ምን ያህል ደቆ፣ ኢኮኖሚያቸው ተራቁቶ፣ ህዝባቸው ተጎሳቁሎና ተበትኖ ለስቃይና እንግልት እንደተዳረገ አይተናል። አይተን አዝነናል። በእኛም ሀገር ይሄ እንዳይደገም ከእነዚህ መማር ይገባናል። ስለዚህ ሁሉም ወገን ሊያስብና ሊያስቀድም የሚገባው የሰላምን ጉዳይ ነው። ሰላምን ማደፍረስ ቀላል፤ መመለሱ ግን ክንድን የሚያዝል ነው። የሰላም ጉዳይ የፖለቲካ ትርፍ ከማግኘትም በላይ ነው። እመራዋለሁ ብሎ የሚያስበውን ህዝብ እና ሀገር እንደ ሀገር የሚቀጥለው ህዝቡ ተረጋግቶ መኖር ሲችል ብቻ ነው።
ይሄ የምንመኘው ጠዋት ማታ የምንወተውትለት፤ እንዲሆንልን የምንፀልይለት ሰላም በሀገራችን ሲሰፍን ነው። የሰላም ማጣት የሁሉንም ቤት ያንኳኳል። ሰላም ከጠፋ የእኔ ብሄር፣ ሃይማኖት፣ ፆታ ከዚህ ነፃ ይሆናል፤ ከዚህ ያተርፋል የሚባል አይሆንም። ምክንያቱም የማይቆረቆር ቤት አይኖርማ። ስለዚህ ለሰላም መሰዋዕትነት መክፈል የግድ ይላል። አንዴ ከእጅ ከወጣ በኋላ መመለሱ ከባድ ነውና። በሀገር ላይ ሰላምን ለማስፈን መነጋገር፣ መደማመጥ፣ መተሳሰብ ፣ መከራከር እና በሀሳብ ልዕልና መሸናነፍ መኖሩን ማወቅ ያስፈልጋል።
በአመጽ፣ በጉልበት… የሚሆን ነገር ሁሉ ከትርፉ ይልቅ ኪሳራው እንደሚያይል መገንዘብ ይገባል። ሁሉም በተሰማራበት መስክ ሰላምን መስበክ ፣ለሰላም መስራት ይኖርበታል። በተለይ እናቶች የሰላም እጦት የመጀመሪያዎቹ ገፋት ቀማሾች ናቸውና በሀገር ላይ ሰላም እንዲሰፍን የእናትነት ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። አውቅውም ይሁን ሳያውቁ በጥፋት አጀንዳ የሚቀላቀሉ ወጣት ልጆችን በመገሰፅ፣ መሪዎችን በመምከርና በመማፀን፣ አጥፊዎችን በመቃወም ለሀገራችን ሰላም ጠንክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል። የሀገር ሰላም «ሰላም» ብሎ ልጅን ከመጥራትም በላይ ነውና።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2011