አዲስ አበባ፡- የአፍሪካውያንን ችግ ሮች መፍቻ እና ሰላምን ማስፈኛው መን ገድ ማህበረሰባዊ ቁርኝት ያለው በመሆኑ የምዕራባውያኑን የሰላም ማስፈኛ መን ገድ መከተል አዋጪ አለመሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።
የአፍሪካ ጥናትና ምርምር ባለሙ ያዎች ማህበር ጉባዔ ላይ የቀረበው ይህ ጥናት እንዳመለከተው የአፍሪካ ሰላም ከምዕራባውያኑ የሰላም ጽንሰ ሃሳብ ምልከታ ጋር ቅርርብ ቢኖረውም አገራዊ እውቀቶችን የያዘና የተለየ ባህሪ ያለው በመሆኑ ካለው ባህሪ አንጻር ታይቶ ሊሰራበት ይገባል ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናትና ምርምር የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪና የጥናቱ አቅራቢ አቶ ፍስሃ ሞረዳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በአፍሪካም ይሁን በምዕራቡ ዓለም ሰላም ከማህበረሰቡ ፍልስፍናዊና ፖለቲካዊ እሳቤ ጋር የተቆራኘ ነው።
ሆኖም የአፍሪካ የሰላም ጽንሰ ሃሳብ ከዚህ ልቆ ትኩረቱ በተለይ ከማህበረሰቡ ባህላዊና ትውፊታዊ ዳራዎች ጋር ይሆናል። በሰዎች ሥነልቦናዊ መስተጋብር ላይና በሞራል ልዕልና ላይ በመሆኑ ቅኝቱ በራሱ እንጂ በምዕራቡ ሊታይ አይገባውም ብለዋል። «የምዕራባውያን የሰላም ጽንሰ ሃሳብ ብልጽግና፣ የህግ የበላይነት፣ መረጋጋት በሚሉት ላይ ይታጠራል» ያሉት ጥናት አቅራቢው፤ ቁሳዊ ብልጽግናን ብቻ መሰረት ያደረገና ከግል ያልዘለለ ባህሪን ከአፍሪካ ሰላም ጽንሰ ሃሳብ ጋር ማወዳደር ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል።
የምዕራባውያኑ የሰላም ጽንሰ ሃሳብ ያለንን ሊያሳጣ ስለሚችል መጠንቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል። አፍሪካውያን ሰላምን ከፈጣሪና ከራሱ ከሰው እንደሚያገኙት ያምናሉ፤ ሰላም መንፈሳዊና ሞራላዊ እሴቶች አሉት፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገርም ነው ብለው ስለሚያምኑም የሚገጥማቸውን ችግር ከባህላዊ ትውፊታዊ እምነቶች አንጻር እንደሚያዩት ጠቅሰዋል። ችግራቸውንም በማህበረሰባቸው ይፈታል፤ ከማህበረሰብ ሲጣሉ ሰላማቸውም ይጠፋልና ሰላም ሲፈለግም ይህን እያዩ መሆን እንዳለበት ይገልጻሉ።
የአፍሪካ የሰላም ጽንሰ ሀሳብ ማህበራዊ ትስስር ያለው ቢሆንም ብዙጊዜ ጥናቶች ትኩረታቸው የምዕራባውያኑ በመሆናቸው ትኩረቱ ይቀየራል የሚሉት አቶ ፍስሃ፤ የግጭት አለመኖር ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ መተሳሰር ከሌለ በአፍሪካ ደረጃ ሰላም አይኖርም። ስለሆነም መረዳዳት፣ ወንድም አማችነት የሚሉት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት ብለዋል። አፍሪካውያን «እኔ በሰው ውስጥ ሰዎችም በእኔ ውስጥ ነው የሚንጸባረቁት» ሲሉ ሰዋዊነትና ሰብዓዊነት ላይ ትኩረታቸውን ያደርጋሉ ምዕራቡ ደግሞ «እኔ ራሴን ስመረምር መኖሬን አወቅሁ» ነው ምልከታው።
ስለሆነም የአፍሪካ ሰላም ብዙ የሚልቁና ሊሰራባቸው የሚገባ ባህሪያት ስላሉት የራሱን በራሱ ጠብቆ ማስተግበር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ብዙ ጊዜ ሰላም የሚገኘው ከውጪ ነው የሚለው ሃሳብም መወገድ እንዳለበት አሳስበዋል። የተለያዩ ስምምነቶች ሲደረጉ ያለን ሳያዩ የውጪን ተቀብሎ መተግበር ላይ ትኩረት ስለሚደረግ ይህ አንጻራዊ ምልከታ ሊኖረው ይገባል። የማህበረሰባችንን ልዕልና የሚያረጋግጠውን ማህበራዊ መስተጋብር መተው እንደማይገባ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ፍስሃ ገለጻ፤ ግጭቶችን መመርመር የመጀመሪያ ተግባር ማድረግ፤ ማህበራዊ ትስስር ላይ ትኩረት መስጠትና በየጊዜው ከማስታረቅ ቅድሚያ ችግሩ ከምን እንደመነጨ ማጥራት፣ሞራላዊ አስተሳሰብ እንዲዳብር ማድረግም ያስፈልጋል። መልካም ጉርብትና በፍትሐዊነትና በልግስና ማጠናከርና መጠበቅን የሚይዘው የአፍሪካውያን የሰላም ጽንሰ ሀሳብ ትኩረት ማግኘት አለበት። ሰላም በአፍሪካ ሰዎች ዘንድ መስተጋብር ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሳይሆን የሰው ልጅ ከአካባቢው ጋር ያለው መስተጋብር፣ ከቀደምት አባቶች ጋር ያለው ትስስርንም ይይዛልና የአፍሪካ ሰላም በምድር ላይ ለመኖር እንደመጨረሻ ግብ ወይም አጋጣሚ ብቻ የሚቆጠር ባለመሆኑ የሰውን ልጅ ለተሻለ ህይወት ማብቃት ላይ ጽንሰ ሀሳቡን መከተል ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል።
ባህላዊ እሴቶች፣ እምነቶችና ወጎች ላይ ከተሰራ የአፍሪካ ሰላም ይረጋገጣል። ለዚህም የኦሮሞ ገዳ ሥርዓትንና የኡቡንቱ ጥንታዊ የአፍሪካ ማህበረሰባዊ ፍልስፍና ማሳያ ነው። በኡቡንቱ ፍልስፍና ታማኝነትና አብሮነት ቀዳሚ ተግባራት ናቸው፤ በገዳም እንዲሁ። ስለዚህ እነዚህ ላይ እንጂ የምዕራባውያኑ የሰላም ጽንሰ ሃሳብ ላይ በመንጠልጠል ሰላማችንን እንዳናጣ መጠንቀቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2011
በጽጌረዳ ጫንያለው