ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው በርካታ እሴቶች መካከል አንዱ ብሔር ብሔረሰቦቿና መላው ማህበረሰቧ የሚጠቀሙት ባህላዊ አልባሳት ነው። ይህ ከየትኛውም የዓለም ክፍል ያልተቀዳ በራስ ማንነት የተቀነበበ እሴት ታዲያ ለልጆቿ ውበትን የሚያጎናፅፍ ለሚያየው የሚማርክና ማንነትን፣ አገርን ባህልንና ሃይማኖትን በአንድነት ጠቅልሎ የሚያሳይ ሃብት ነው።
በሁሉም አካባቢ ያሉ ኢትዮጵያውያን የማንነታቸው መገለጫና የውበታቸው ማድመቂያ የሆነ አልባሳት እንዲሁም የአለባበስ ስርዓት አላቸው። በደስታ፣ በበዓላት፣ በሃዘንም ሆነ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ሁሉ ይህ የራስን ማንነት አጉልቶ የሚያሳይ ማጌጫ ጥቅም ላይ ይውላል። ባሳለፍናቸው ሁለት ሳምንታት ውስጥ የነበሩትን ሁነቶች ብንመለከት እንኳን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የተከበረውን የገናንና የጥምቀትን ክብረ በዓል ተከትሎ ባህልን የሚያሳይ፣ ሃይማኖትን የሚገልፅ እንዲሁም ውበትን አጉልቶ የሚያወጣ እጅግ በርካታ ማራኪ ልብሶችን እና ጌጣጌጦችን እናስተውላለን።
ከሰሞኑ በተለያዩ የዓለም ክፍላት በተደረገው ኢትዮጵያዊነትን የማጉላትና የሌሎች አገራትን ጣልቃ ገብነትና ጫናን የመቃወም የ “በቃ” ንቅናቄ ላይ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያኑ ማንነታቸውን በሚያጎሉ የራሳቸው አልባሳትና እሴቶች ተውበው “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” ሲመቱ ተመልክተናል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን “ወደ አገራችሁ ኑ” የሚል ጥሪ ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ዲያስፖራዎችም በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ የባህል አልባሳት ሱቆች ጎራ እያሉ ባህላቸውን ከማወቃቸው በላይ ለውበታቸው ካባን እየደረቡ ወጥተዋል፤ አሁንም ያሻቸውን እየሸመቱ ነው።
በአገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ባህላዊና የሸማ አልባሳት ዲዛይን የሚያደርጉና የሁሉንም ፍላጎት የሚያረኩ የእጅ ጥበበኞችም የገበያውን ፍላጎት ለማሟላት አይቦዝኑም። በአገር ውስጥ ለቁጥር የከበዱ ሱቆችን በመክፈት የአገር ውስጥ ፍላጎትን ከማርካትም ባለፈ ትእዛዝ ለሚልኩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተለያዩ
አማራጮች ኤክስፖርት የሚያደርጉ በርካቶች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በአዲስ አበባ አራት ኪሎድንቅ ስራ ህንፃ ውስጥ የባህላዊ አልባሳት በአገር ውስጥና በውጪ ላሉ ደንበኞቿ የምታቀርበው አምሳል ባዬ “ቶቤል የአገር ባህል ልብስ ቤት” በሚል ሱቅ ከፍታ የኢትዮጵያውያንን ባህላዊ አልባሳት በመሸጥና በማስተዋወቅ ላይ ትገኛለች። የዝግጅት ክፍላችንም ወቅታዊውን ገበያና ባህላዊ አልባሳትን የማዘውተር ፍላጎትን በሚመለከት አጭር ጭውውት አድርጎ እንደሚ ከተለው ሃሳቧን ይዞ ቀርቧል።
የቶቤል የአገር ባህል አልባሳት ባለቤቷ አምሳል ባዬ ይህን ስራ ከጀመረች ሶስት ዓመታትን እንዳስቆጠረች ትናገራለች። ወደ ዚህ ስራ ለመግባት ምክንያት የሆናትም የአገሯን አልባሳት በእጅጉ ከመውደዷና አዘውትራ ከመልበሷ የተነሳ መሆኑን በመግ ለፅ ይህ ጅማሮ ለቀሪው ወገኗ በስፋት ለማስተዋወቅ፣ በውጪ አገራት ለሚገኙና በቀላሉ ምርቱን ለማግኘት ለሚቸገሩ ወገኖቿ እድሉን ለማመቻቸት በማሰብ መሆኑን ትገልፃለች።
ኢትዮጵያውያን የአገር ልብሳቸውን በተለያዩ ግዜያት በማዘውተር ባህል ባይታሙም አሁን አሁን አልባሳቱን በቀላል ዋጋ ማግኘት ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህንን አስመልክቶ ላነሳንላት ጥያቄ አምሳል ስትመልስ “አሁን አሁን ጥሬ ዕቃ በጣም ውድ ነው። ከጥለት ክር ጀምሮ እያንዳንዱ ነገር ጨምሯል። ጠላፊም ሆነ ሸማኔ ስራቸውን ሲያከናውኑ ጥሬ ዕቃውን ለማግኘት ይቸገራሉ” ብላናለች። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ባህላዊ አልባሳትስለሚወዱና ስለሚያከብሩ ጫናውን እየተቋቋሙም ቢሆን እንደሚሸምቱ ነግራናለች።
“አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በዓላትና የተለዩ ዝግጅቶች ላይ ነው አልባሳቶቹን የሚጠቀማቸው” የምትለው የቶቤል የአገር ልብስ ቤት ባለቤቷ፤ በጥምቀት እንዲሁም በገና ሰሞን ስራውና ፍላጎቱ ጫን እንደሚል ትናገራለች። በተለይ የጥር ወቅት የሰርግ ሰሞን ከመሆኑ የተነሳ እጅግ የበዛ የገበያ ፍላጎት መኖሩን ትመሰክራለች ። ይሁን እንጂ ከዓመት እስከ ዓመት የአገር ባህል ልብስ በርካታ ፈላጊዎች መኖራቸውን መዘንጋት እንደሌለበት ትናገራለች። የእርሷ ደንበኞች በስፋት ውጪ አገራት ያሉ ሲሆኑ “በዲ.ኤች.ኤልና” በተለያዩ የመላኪያ አማራጮች ወዳሉበት አገራት ትልካለች። አሁን ወደ አገር ውስጥ የገቡ ዲያስፖራዎችም ምርቶቿን ፈልገው እንደሚመጡና ለባህላዊ አልባሳቶቹና ለባህላቸው ያላቸው ቀናኢነት እንደሚያስደስታት ትናገራለች። ሰሞኑንም ከመጡት ዲያስፖራዎች ትእዛዝ መቀበሏንና በቅርቡ እንደየፍላጎታቸው አልባሳቶቹን እንደምታቀርብ ገልጻልናለች።
በቶቤል የአገር ባህል ልብስ ቤት የወንድ፣ የሴት፣ የእናቶችና የወጣቶች የተለያዩ የአገር ባህል አልባሳት እንደሚገኙ ትናገራለች። ቀሚስ ከነነጠላው፣ ስካርፍ (የአንገት ላይ ልብሶች) ቲሸርቶች እና መሰል በርካታ ባህላዊ አልባሳት በተለያዩ ቀለማትና የጥበብ ክር ደምቀው መደርደሪያዎች ላይ ተሰቅለዋል። ሁሉም ሰው በፈለገው ዲዛይንና ቀለም አልባሳቶቹን ሸማኔዎችን አዛ ታዘጋጃለች። እንደየ ጥራትና መጠናቸው ዋጋቸውም እንዲሁ እንደሚለያይ ትናገራለች። ከአራት ሺህ ብር አንስቶ እስከ ሃያ ሺ ብር የሚደርሱ ከዚያም የሚያንስና የሚበልጥ ዋጋ ያላቸው ባህላዊ አልባሳት መኖራቸውን አጫውታናለች።
አምሳል “ሁሉም ሰው አገሩን፣ ባህሉን እንዲወድ እፈልጋለሁ፤ የዚህ መገለጫ የሆኑትን አልባሳት በእለት ተእለት እንቅስቃሴው ውስጥ እንዲጠቀምም መልዕክት አስተላልፋለሁ” ትላለች። ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአገሩ ምርት፣ ባህልና እሴቶች ሊኮራና ለቀሪው ዓለም ሊያስተዋውቅ ይገባል የሚል አቋምም አላት። በቅርቡ ወደ አገራቸው የገቡ ትውልደ ኢትዮጵያውያንም በቶቤል የባህል አልባሳት ቤት መጥቶ ትእዛዝ ቢሰጥ እንደየፍላጎታቸው ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን በመናገር ሃሳቧን ቋጭታለች።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥር 16/2014