በገና መዳረሻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የ100 ቀናት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን የስራ አፈጻጸም ለመገምገም ካቢኔያቸውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሚገኝበት ጉባ መሰብሰባቸው ግድቡ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን የሚያበስር ከመሆኑ ባሻገር በአገሪቱ ህልውና ላይ ተደቅኖ የነበረው አደጋ መቀልበሱን የሚያውጅ ነው። የስብሰባ ቦታው ጉባ የሆነው በአጋጣሚ አይደለም። በመንግስት ዘንድ የተፈጠረን በራስ መተማመን ለወዳጅም ለጠላትም ከመግለጥ በላይ ታሪካዊ ጠላቶቻችንና ቡችሎቻቸው ኢትዮጵያን ከሕዳሴዋ እንደማያቆሟት ግልጽ መልዕክት ያስተላለፈም ነበር ።
ግብጽ ይህ አገራዊ ፕሮጀክት እንዲኮላሽ ያልፈነቀለችው የውክልና ግጭትና ጦርነት ፣ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲና የሚዲያ ድንጋይ የለም ። ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በአገሪቱ አራቱም ማዕዘናት ከተቀሰቀሱ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ግጭቶች ፤ አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ አገራችንን ለማፍረስ ከከፈቱት ጦርነት ፣ ከሱዳን ወረራ እና ምዕራባውያንና አሜሪካ ከከፈቱብን የሚዲያና የዲፕሎማሲ ግንባር በስተጀርባ ረጅሙ የግብጽ እጅ አለበት ። ሰሞኑን ይፋ የሆኑ አስደንጋጭ መረጃዎች እንዳመለከቱት ግብጽ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ አድርጋለች ። በገንዘብ ያልተተመነው ዙሪያ መለስ ጫናዋ ሳይዘነጋ ። በጉባ የተካሄደው የካቢኔ ስብሰባ አገራችንን ለመበተን በህቡዕም ሆነ በአደባባይ የተንቀሳቀሱትን ዕቅዳቸው መክሸፉን ያረዳ መራራ ኩነት ነበር ።
ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ በሁለቱ ተርባይኖች 760 ሜጋ ዋት ለማመንጨት በተዘጋጀበትና የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በመዲናችን አዲስ አበባ ሊካሄድ ቀናት በቀሩት በዋዜማው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሐሙስ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ፤ “The GERD as a site of cooperation”/ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እንደ ትብብር ማዕድ/ በሚል ርዕስ ባስተላለፉት መልዕክት ፤ ከድህነትና ከኋላቀርነት የተላቀቀችና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የኤሌክትሪክ ኃይል ወሳኝ ሚና አለው ። ለናይል ወንዝ 85 በመቶ የሚሆነውን ውሃ የምታበረክት አገር ከህዝቡ 53 በመቶ ወይም 60 ሚሊዮን የሚሆነው ያለ ኤሌክትሪክ በጨለማ ነው የሚኖረው ። ይህን ያህል ህዝብ በኩራዝና በጭስ እየተጨናበሰ ብልጽግናን ማለም አይቻልም ። ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በዓመት 15ሺህ 700 ጊጋዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ።
እንደ ሕዳሴው ግድብ ያለ ታዳሽ ኃይል አገሪቱን እቅፍ ድግፍ አርጎ ይዞ ለመነሳት ካለው ሁለንተናዊ አስተዋፅኦ በላይ የካርቦን ልቀትን ወደ ዜሮ ለማውረድና ብዝሀ ህይወትን ለመጠበቅና ለማበልጸግ ጥርጊያውን ያመቻቻል ። ግድቡ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ 10 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን በካይ ጋዝን ይቀንሳል ። ለግርጌ የተፋሰስ አገራትም ከዓመት ዓመት አስተማማኝ ውሃ ለመልቀቅና በተለይ በሱዳን በየዓመቱ የሚከሰተውን ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ጉዳትና የውሃ እጥረት ለማስቀረት የሚያስችል መደበኛ ፍሰት እንዲኖር ያደርጋል ። በግብጽ ግድቦች በብዙ ቢሊዮን ሜትር ኩብ የሚገመት ውሃ በትነት ሲባክን ፤ በአንጻሩ በሕዳሴው ግድብ ትነቱ እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑ ባሻገር ዓመቱን ሙሉ መደበኛ ፍሰት እንዲኖር ስለሚያስችል የአስዋን ግድብ ከመጥለቅለቅ ይታደገዋል ።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በግርጌ ተፋሰስ አገራት የጎላ ጉዳት ሳያደርስ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ፤ የትበብር መርህን የሚያበረታታ እንጂ የግጭትና የስጋት ምንጭ ሊሆን አይገባም ሲሉ ወቅቱን የዋጀ መልዕክት አስተላልፈዋል። ወዲያው ወዲያው የመርሳት አባዜ ስላለብን የቀጣናውን ጂኦፖለቲክስ በአዲስ የበየነው ይህ የብልጽግና ማርሽ ቀያሪ ሜጋ ፕሮጀክት እንዴት ከለየለት ክሽፈት እንደተረፈና አገሪቱን የአህጉሩ የጂኦፖለቲክስ ከባድ ሚዛን ተጫዋች እንዳደረጋት እንመልከት ።
በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር አመራር ግድቡ ገጥመውት የነበሩ ስር የሰደዱ ብልሹ አሰራሮች ፣ ሙስናና ደካማ የኮንትራት አስተዳደር ተለይተው የእርምት እርምጃ መወሰዱ ታላቁን የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ከክሽፈትና ከለየለት ውድቀት ከመታደግ አልፎ ኢትዮጵያውያን የእፍታው ተቋዳሽ ሊሆኑ ከጫፍ ደርሰዋል ለለውጥ አመራሩም ትልቁን የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያን ስዕል እየተመለከተ ብልፅግናዋን እውን ለማድረግ አቅም ይሆነዋል ቅኝ ካለመገዛት ጋር ብቻ ተያይዞ የነበረውን ነጻነትና ሉዓላዊነት በኢኮኖሚያዊ ብልፅግና ለመድገም መስፈንጠሪያ ሠሌዳ ( ስፕሪንግቦርድ ) በመሆን በድህነትና በተመፅዋችነት አንገታቸውን ደፍተው የነበሩ ዜጎች አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት እንዲራመዱ የሚያደርግ ብሔራዊ (ፍላግሺፕ)ፕሮጀክት ነው ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ እንዳሉት በድህነትና በኋላ ቀርነት የሚማቅቅ ህዝብ የተሟላ ሉዓላዊነት ሊኖረው አይችልምና ስንዴ እየለመኑ ፣ እየተመጸወቱ ሉዓላዊነቷን ያላስደፈረች፤ በነጻነት ታፍራና ተከብራ የኖረች ብሎ መመጻደቅን ምሉዕ አያደርገውም።
አገራችን ኤርትራን ፣ ቀይ ባህርንና የባህር በሯን በግብፅና በተላላኪዎቿ ደባ ከተነጠቀች በኋላ በቀጣናው ያላትን ጂኦፖለቲካዊ ስፍራዋን ላለፉት 30 አመታት ተነጥቃ ኖራለች ቀይ ባህርን በመነጠቋና የባህር በር የሌላት መሆኑ በቀጣናው ያላትን የጂኦፖለቲክስ ሚና ሲያኮሰምነው ኖሯል ። የሕዳሴው ግድብ የነበሩበት የሙስና ፣ የብልሹ አሰራርና ውስብስብ የቴክኒክ ችግር ተቀርፎ ለዚህ መብቃቱ እና ከናይጀሪያ ቀጥሎ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት አገር መሆኗ ላለፉት ዓመታት አጥታው የነበረውን ሞገስ ያስመልስላታል ።
የአረቡ ዓለም የነዳጅ ባለቤት መሆኑ ከተረጋገጠ ፣ እ.ኤ.አ በ1948 ዓ.ም እስራኤል የአይሁዶች መንግስት ሆና ከቆመች ፣ ከ1993 ዓ.ም የመስከረም 1ቀን የሽብር ጥቃት በኋላ የአሜሪካ ፣ የምዕራባውያንና የዓለም አቀፉ ተቋማት የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ማጠንጠኛ ነዳጅ ፣ የእስራኤል ደህንነት እና የጸረ ሽብር ዘመቻ ሆነ ለእነዚህ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ተግባራዊነት ደግሞ ከአረቡ ዓለም ግብፅ ቀዳሚዋ ስትራቴጂካዊ አጋር ሆና ተመርጣለች ግብፅን ተመራጭ ያደረጋት ለምዕራባውያን የጡት ልጅ እስራኤል ጎረቤት ፤ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ በተለይ የስዊዝ ቦይ ባለቤት ፤ የእስላማዊ ትምህርት ማዕከል እና የአረብ ብሔርተኝነት አቀንቃኝ መሆኗ ፤ ዜጎቿ ከሌላው የአረብ ዓለም ጋር ሲነጻጸር በዓለማዊም ሆነ በእስላማዊ ትምህርት የገፉ በመሆናቸው በምዕራባውያንም ሆነ በእስላማዊው ዓለም ዘንድ ሞገስ አግኝታለች ይህን ሞገሷን የአረቡን ዓለም ጨምሮ የአረብ ሊግን እንዳሻት ለማሽከርከር ትጠቀምበታለች በልዩነትና በክፍፍል ከሚንጠራወዘው የአረቡ ዓለም ግብፅ ከፍ ብላ እንድትታይ ረድቷታል።
ይህን መከፋፈል እስራኤልን ጨምሮ አሜሪካውያን ሆኑ ምዕራባውያን ይፋ ባያወጡትም የሚደግፉት ስለሆነ ግብፅ ሽብልቅ ሆና እንድታገለግል አሞሌ እያላሱ (ብድርና እርዳታ እየሰጡ በአናቱ የጦር መሳሪያ እያስታጠቁና ወታደራዊ ስልጠና ፤ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ድጋፍ እያደረጉ ይንከባከቧታል ይለባኟታል ከእስራኤል ቀጥሎ ከፍተኛ እርዳታና ብድር የምታገኘው ግብጽ ናት ።
ግብፅ በአጸፋው ይህን ውለታ ከግምት ያስገባ እና እ.ኤ.አ በ1979 በአንዋር ሳዳትና በእስራኤል መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት መሰረት ያደረገ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀርጻለች የአገሪቱን ኢኮኖሚ ፣ ደህንነትና ፖለቲካ በመዳፉ የጠቀለለው የግብፅ ጦርና ደህንነት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ተገባራዊነት ያረጋግጣል በአይነ ቁራኛ ይከታተላል ከአረቡ አብዮት በኋላ በምርጫ የፈርኦኖችን በትረ ስልጣን ጨብጠው የነበሩ የመጀመሪያው የእስላም ወድማማቾቹ አባል ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሙርሲ እንኳ የድርጅታቸውንም ሆነ አክራሪ እስላሞች ግፊት ተቋቁመው የግብፅና እስራኤልን የሰላም ስምምነት ማክበር ችለዋል።
መጀመሪያ በመፈንቅለ መንግስት በኋላ በምርጫ ወደ መንበሩ የመጡት ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲም ከሳዳት ፣ ከሙባረክና ከሙርሲ በላይ የሰላም ስምምነቱን እያስፈጸሙ ነው የእስራኤል ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው አስኳል ነው ማለት ይቻላል ከእስራኤል ጀርባ ደግሞ አሜሪካ አለች ግብፅ ናይል የህልውናዬ ጉዳይ ነው ብላ በሕገ መንግስቷ ብታካትተውም ፤ በውስጠ ታዋቂ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ የማዕዘን ራስ ቢሆንም በግላጭ ትኩረቱ እስራኤል ፣ ፍልስጤምና አሜሪካ ላይ ነው።
ግብፅ አባይን ከምንጩ ለመቆጣጠር፣ አገራችንን ቅኝ ለመግዛት እና ጠንካራ ሉዓላዊ አገር ሆና እንዳትወጣና ይህ ቀን (አባይ የሚገደብበት ቀን) እውን እንዳይሆን ከ11 ጊዜ በላይ ወራናለች በስውር ደግሞ ምን አልባት ለሺህ ወይም ለሚሊዮን ዓመታት አሲራለች በተለይ ከ20ኛው መ.ክ.ዘ ወዲህ ደግሞ በእነ ሶማሊያ ፣ ሱዳን ፣ ጀብሀ ፣ ሸዓቢያ ፣ ትህነግ ፣ ኦነግና የኦጋዴን ነጻ አውጭ በመጠቀም የውክልና (proxy) ጦርነት በማካሄድ አገራችንን ስታዳክም ኖራለች ይህ እኩይ አላማዋ ከሞላ ጎደል በመሳካቱ የቤት ስራዋን በማጠናቀቋ ዝቅ አድርጋ ስታየን ኖራለች።
ከታሪካዊዋ ሀምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሁኔታዎች ተቀይረዋል፤ በሴራና በደባ በቀጣናውም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ ያሳጣችን ጂኦፖለቲካዊ እና ስትራቴጂካዊ ስፍራ ከ30 አመታት በኋላ መልሰን ተረክበናል ፤ምርኳችን ተመልሷል ፤ የቀጣናው ጂኦፖለቲካዊ አሰላለፍ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ እንደ አዲስ ተበይኗል ፤ ተፐውዟል ፤ ከዚህ በኋላ የአገራችን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና ጂኦፖለቲካዊ ስፍራ ከ1983 ዓ.ም በፊት ወደነበረው ከመመለሱ ባሻገር ከግብፅ የሚተናነስ አይደለም ቢባል ማጋነን አይሆንም።
አሸባሪው ሕወሓት እንደለመደው አገርን ለመሸጥ ተስማምቶ በግብጽ የእጅ አዙር የገንዘብ ፣ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ድጋፍ ፤ በምዕራባውያንና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲሁም እንዳሻቸው በሚጠመዝዟቸው ሚዲያዎችና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነን ባዮች ወከባ አፈር ልሶ ተነስቶ የነበረው፤ አሁን በመማጸኛ ከተማው የመሸገው አሸባሪው ሕወሓት ፤ አንድ ጊዜ ተሽጧል ሌላ ጊዜ ለፖለቲካዊ ጥቅም ተለውጧል እያለ የውሸት መዓት ሲነዛበት የኖረው የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኃይል ለመስጠት በዋዜማ ላይ ከመሆኑ ባሻገር የሕዝቡንና የመንግስትን የመፈጸም አቅም ለዓለም አሳይቷል ።
ኣገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ፈጣሪ አብዝቶ ይባርክ ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም