ምስራቅ አፍሪካ በዓለም ላይ ካሉ ቀጣናዎች በቀዳሚነት በርካቶችን ትኩረት ሰቅዞ የያዘ ቀጣና ስለመሆኑ ዓለም የሚያውቀው እውነታ ነው ቀጣናው በዓለም ላይ እጅግ ስትራቴጂክ ከመሆኑም ባሻገር በዚያው ልክ ብዙ ፈተናዎችንና ችግሮችን የሚያስተናግድ ነው በተለይም ኢትዮጵያ የበርካቶች ዓይን ማረፊያ ስለመሆኗም ታሪክም፣ ክስተቶችም ሕያው ምስክር ናቸው።
የምስራቅ አፍሪካን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን መዘወር አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ኢትዮጵያ የቀጣናው ማዕከላዊ ሥፍራ ወይንም የስበት ማዕከል ሆና ማገልገሏ ሐቅ ነው ስለ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ሰላምና መረጋጋት፣ ስኬትና ውድቀት ሲነገር ቀጣናው ጭምር ታሳቢ ያደረገ ነው።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት ተሰሚነት፣ የቆዳ ስፋት፣ የሕዝብ ቁጥር ብዛት፣ ታሪካዊ እሳቤዎችና ሌሎች ክስተቶችን በበላይነት ያካተተ ነው ይህም ጽሑፍ በዋናነት ኢትዮጵያ ላይ ያተኮረ ቢሆንም ቀጣናውንም ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው ጉዳዩን ለማብራራት ይረዳ ዘንድ ስለአገሪቱ አሁነኛ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ እውነታ በጥቂቱ ለመዳሰስ ልሞክር።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ኮቪድ-19 በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ኑሮ ላይ የሚስከትለውን ተጽዕኖና መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች ጠቋሚ ምልከታ በሚል ባሰፈረው ሃሳብ፤ ኮቪድ-19 ተያያዥነት ያላቸውን የጤና መታወክና ሕይወት ማጣትን፣ የምርት አቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣምን እንዲሁም የፋይናንስ ቀውሶችን ብሎም የአጠቃላይ ኢኮኖሚ መቀዛቀዝን ያስከተለ የዘመናችን አስከፊ ክስተት መሆኑን ያትታል።
ድንበር ተሻጋሪው ወረርሽኝ ከጤና ወደ ኢኮኖሚ ብሎም ማኅበራዊ ቀውሶችን ከመፍጠሩም በላይ ተጽዕኖውን ለማርገብ የሚያስችል አቅምን ተፈታታኝ እንደሆነ ያስቀምጣል ጥናቱ ወረርሽኙ ሊቆይ የሚችልበት የጊዜ ርዝማኔና የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የሚወሰዱ እርምጃዎች የሚያስከትሉት ውጤት የጉዳቱን ስፋትና ጥልቀት የሚወስኑት ቢሆንም ወረርሽኙ የአገራችንን የኢኮኖሚ እድገትን በመግታት ድህነትን ሊያባብስ እንደሚችል ያስገነዝባል።
እንደ ጥናቱ ከሆነ ‹‹የወረርሽኙ የቆይታ ጊዜ እየተራዘመ በሄደ ቁጥር ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ቅነሳ ሊያስከትል ይችላል በዚህም የተነሳ ወረርሽኙ በሠራተኛ ቅነሳና መፈናቀል ላይ በሚያስከትለው ተፅዕኖ በኢኮኖሚዉ ላይ እስከ 200 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ሊያስከትል ይችላል። የወረርሽኙ ስርጭት መራዘምና መስፋፋት የሚያስከትለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ በከተማና በገጠር ድህነትን ማስከተሉ ነው።
በአገር ዓቀፍ ደረጃ ከድህነት ወለል በታች የሚኖረው ዜጋ እስከ 38.4 በመቶ ሊያሻቅብ እንደሚችልና ይህም በገጠር፣ በአነስተኛ ከተሞችና በከተሞች ሲተነተን የሚኖረው ድህነት መጠን በቅደም ተከተል የ42.1፣ 29.1 እና 20 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው ተመልክቷል ሲል ያትታል።
በመሆኑም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያስችሉ አፋጣኝና የተቀናጁ የመከላከል እርምጃዎችን መውሰድ ካልተቻለ ዘርፈ-ብዙ የሶሽዮ-ኢኮኖሚ መዛባትን በመፍጠር መውጫ ወደሌለው የቀውስ አዙሪት መግባት አይቀሬ ነው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰርቶ አደሮች ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የኑሮ ሁኔታ የሚገኙበት የአገራችን ኢኮኖሚ ወረርሽኙ በተጨማሪ የሚፈጥረው ጫና ከሥራ መፈናቀልን ካስከተለ በእነዚህም ሆነ በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ የሚያስከትለውን አስከፊ ጉዳት መገመት አያዳግትም›› ይላል።
ከዚህ ሃሳብ መረዳት የሚቻለው በሽታው የሚያስከትለው ጫና ኢትዮጵያ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ሁኔታዎች አስቸጋሪ ናቸው በተለይም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በአሸባሪዎቹ ኦነግ ሸኔ እና ሕወሓት ጦርነት ከፍተውባት በተጨማሪም ሌላ ጫና ለመሸከም አስቸጋሪ የሚሆን ይመስላል አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች በእጅጉ የበረቱባት በመሆኑ ነው ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ጫና እና መፈረካከሶችም ቀጣናውን ሳይነካኩ የማያልፉ እንደሆኑ ይታመናል።
ለችግሩ እንደየፈርጃቸው መፍትሔ ማፈላለግ አስፈላጊ ነው በመሆኑም ፈጣንና ሁሉን አቀፍ የመከላከልና የማገገሚያ መርሐ-ግብር በመዘርጋትና በመተግበር ጊዜያዊ የሆነው የጤና መታወክ ዘላቂና የከፋ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ቀውስ እንዳያስከትል ማድረግ አማራጭ የሌለው ተግባር ስለመሆኑም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ምክረ ሃሳቡን ያስቀምጣል በተጨማሪ የፖለቲካ ሜዳውን ለማስተካከል መፍትሔዎች እየቀረቡ እንዳሉት ሁሉ ለኢኮኖሚ ተግዳሮቶች ዓይነተኛ መፍትሔ የሚጠቁሙ መድረኮች በስፋት ሊመቻቹ እንደሚገባም ያሳያል።
ሌላኛው ኢትዮጵያን እየፈተኑ ካሉ ውጫዊና ውስጣዊ ክስተቶች እና ሁኔታዎች ሌላኛው ደግሞ ሽብርተኝነት ሆኗል መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በርካታ ደህንነት ተንታኞችና ባለሙያዎች እንደሚሉት ሽብርተኝነት በአፍሪካ ውስጥ በፍጥነት ስር እየሰደደ እየመጣ ነው ። የበርካቶችን ሕይወት እያመሳቀለና ቁሳዊ ውድመት እያስከተለ ይገኛል።
በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ ቦኮሃራም የተባለው አሸባሪ ቡድን አናሳ ክርስቲያኖችን የሚገድሉበት ክስተት የበርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አውታሮች ጆሮ ማሞቂያ ከሆነ ሰነባብቷል ሶማሊያ በአል ሻባብ አሸባሪዎች ፍዳዋን መብላት ከጀመረች በርካታ አስርተ ዓመታት ተቆጥረዋል ይህ ቡድን በሶማሊያ ብቻ የተገደበ ሳይሆን መቀመጫውን በሶማሊያ በማድረግ በመላው ምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል የሶማሊያ የባህር ወንበዴዎች፣ የህንድ ውቅያኖስ ምስራቃዊ ጠረፍ የሚያቋርጡ መርከቦችን ለማፈን ከዓለም አቀፍ የሽብር መረብ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው እየሰሩ እንደሆነም በስፋት እየተነገረ ነው።
የአልሻባብ ጥፋት በተወሰነ ቦታ የተገደበ ባለመሆኑም ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት ከፈጠሩ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው ። በተደጋጋሚ ጥቃት የማድረስ ሙከራዎችን አካሂዷል ይህም ስጋት በአገሪቱ ላይ የሚፈጥረው ጫና አደገኛ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሞቃዲሾ ድረስ እንዲዘምትና የአገር ሉዓላዊነትን እንዲያስከብር በማሰብ ብሎም ሽብርተኛውን ቡድን በሩቁ ለማክሰም እዚያም በመፋለም ይገኛል አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ በአገር ውስጥ አሸባሪዎቹ ኦነግ ሸኔ እና አሸባሪው ሕወሓት አማራጮችንና እድሎችን ካገኘ ሙሉ ለሙሉ ከአልሻባብ ጋር ተናበው መሥራታቸው አይቀሬ ነው።
ይህ ሁሉ ሲታይ ኢትዮጵያ በውስጥም ይሁን በውጭ በአሸባሪዎች ከበባና ስጋት ውስጥ ያለች አገር መሆኗ መታሰብ አለበት በመሆኑም የአገሪቱን ህልውና የሚያጠብቅ ሠራዊትና እና ሕዝብ በኢትዮጵያ ቁመና ልክ መገንባትና የሥነ-ልቦና ትጥቅ ማበጀት ለይደር የማይተው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።
ከእነዚህ ችግሮች በተጨማሪ አገራዊ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ የሰላም እጦትና የዜጎች በየጊዜው መፈናቀል እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሯል ታዲያ ይህን ታሳቢ ያደረ የፖለቲካ ሪፎርም ማድረግ ይገባል።
ከእነዚህ ችግሮች በተጨማሪም ኢትዮጵያ በርካታ ቀጣይ ፈተናዎች የሚጠብቃት አገር መሆኗ ሊታሰብ ይገባል በመሆኑም መንግሥት እነዚህን ችግሮች አሻግሮ መመልከት እና ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ያስገባ እንቅስቃሴ ማድረግ አለበት።
ከምጣኔ ሃብት ዕድገት ጋር ያልተናበበ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት፣ ከፍተኛ የሆነ የወጣቶች ቁጥርና ሥራ አጥነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትሏቸው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች የኢትዮጵያ ቀጣይ ፈተናዎች መሆናቸውን አይቀርም። ችግሮቹን ታሳቢ ያደረጉ መፍትሄዎችን ከወዲሁ ማፈላለግ ተገቢ ነው ችግሮቹን ቀድሞ በአግባቡ በመረዳት ወደ መልካም አጋጣሚዎች የመቀየር ዕድሉ እንዳለም ማስተዋል ተገቢ ነው።
እነዚህ ችግሮች ቀድሞ መገንዘብ ሁኔታዎችን መተንበይ ብሎም መፍትሔ መዘጋጀት ከተቻለ እነዚህ ፈተናዎች የማያልፏት ግን ደግሞ ኢትዮጵያን የሚጠነክሯት ፈተናዎች እንደሚሆኑ ማሰብ የሚከብድ አይደለም ነው።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም