አዳማ፡- በአገራችን በገፀ ምድርና በከርሰ ምድር ውሃ ሊለማ የሚችለው አጠቃላይ የመስኖ መሬት አምስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር እንደሆነ ቢገመትም፣ እስካሁን የለማው ከ20በመቶ እንደማይበልጥ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት፣መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ከትናንት በስቲያ በአዳማ ድሬ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ እንደተናገሩት፣ በሀገራችን ለመስኖ የሚውል ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ቢኖርም ልማት ላይ የዋለው ግን እጅግ አነስተኛ ነው።
የመስኖ ልማት አንዱና በቀዳሚነት ትኩረት ተሰቶት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ መስኖን ማል ማት በተቆራረጠ ዝናብና በድርቅ ወቅት መደበኛ ምርት ለማግኘት፣ የድርቅ ተጋላጭነትን በመቀነስ የኢኮኖሚና አካባቢ ጉዳት እንዳይደርስ ለማድረግ እንዲሁም ብዙውን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። እምቅ ሃብታችንን በማልማት በሌላ በኩል ደግሞ እያደገ የመጣውን የአገራችንን ህዝብ ቁጥር ተከትሎ እየተከሰተ ያለውን የሥራ አጥነት መቅረፍ ወቅታዊ አጀንዳ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ነጋሽ ይህንን አቅጣጫ ተከትሎ የሚሰራው ሥራ ፍሬያማ እንዲሆን የቋሚ ኮሚቴው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝ በዋል፡፡
የምክክሩ ዋና አላማ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ክትትል፣ ድጋፍና ቁጥጥር የሚያደርጉ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ስለ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ችግሮች፣ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ከመስሪያ ቤቱ አመራሮች ጋር ተግባብተው መስራት የሚያስችል አቋም ለመፍጠር መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአዲስ መልክ ስለተደራጀ ወደ መሥሪያ ቤቱ የተቀላቀሉ አዲስና ነባር ተጠሪ ተቋማት በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን አሰራር ለመፈተሸና ከቋሚ ኮሚቴው የሚደረጉ ድጋፎችም ወደ መሥሪያ ቤቱ የተቀላቀሉ ተጠሪ ተቋማትን ከግምት ያስገባ እንዲሆን ጭምር ነው፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለሥራው ተግዳሮት ናቸው ብሎ የለያቸው የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት፣ያሉትም ቢሆኑ በቂ ክፍያ የሌላቸው በመሆናቸው ፍልሰት ፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪና በጀት ዋነኛው መሆናቸውን አመል ክተዋል። እነዚህን ችግሮች እንዲፈቱ በማድረግ በኩልም ቋሚ ኮሚቴው ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
በምክር ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት፣መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈቲሀ የሱፍ በበኩላቸው፤በተቋሙ ያለውን ክፍተት በመፈተሽ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ቋሚ ኮሚቴው አዲስ ስለሆነ ስለ መስሪያ ቤቱ ግንዛቤ ማስጨበጥና ስለ ሥራው በጥልቀት አውቆ መፍትሄ በማምጣት ተቋሙን ውጤታማ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2011
በሞገስ ጸጋዬ