አንድ ሰሞን በመገናኛ ብዙኃን ላይ አንድ ዜማ በተደጋጋሚ እሰማ ነበር፤ በቅርቡም ይህን ዜማ ማለዳ ከቤቴ ስወጣ በሬ ላይ ከቆመ ሚኒባስ ሰማሁ። ዜማው በውስጣችን አንዳች ተስፋ እንድንሰንቅ የሚያደርግ ነው። አለ አይደል ውስጣዊ ስሜትን ሰቅዞ ይዞ ብዙ የሚያሳስብ።
ብዙ ጊዜ ጠዋት የሰማነው ድምፅ ከእዝነ ሕሊናችን አይጠፋም። ይህን ድምጽ ርቀንውም ደጋግመን እናስታውሰዋለን። እናም ያን ማለዳ የሰማሁት ዜማ በእዝነ ሕሊናዬ ታትሞ ከውስጤ ሳይጠፋ ቢሮ ደረስኩ።
ዜማው “ጀምረናል ጉዞ ጀምረናል፣ ወደኋላ ማን ይመልሰናል፤ ጀምረናል ጉዞ ጀምረናል” የሚል ነበር። ይመስለኛል ዜማው የህዳሴ ግድብ ግንባታን አስመልክቶ ታዋቂ ድምፃውያን በጋራ ያዜሙት ነው። በዜማው ውስጥ አገሬን በሰፊው አየኋት። ይህች ታላቅ አገር በፈተናዎች ውስጥም ሆና በተስፋ የተሞላች ናት። እቅድዋን ማሳካት የምትችል ድንቅ አገር መሆኗን ከትናንት እስከ ዛሬ ያለችበትን ሁኔታ መልስ ብዬ በመመልከት ተረዳሁ።
ራዕይዋን፣ እቅድና ተስፋዋን አሁን ያለችበትን አጠቃላይ ሁኔታ አጤንኩት። ከወራት በፊት በብዙ ጫናና ፈተናዎች ውስጥ ነበረች፤ እንዲያም ሆኖ ግን በልጆቿ ብርታት ብቻዋን ቆማ እነዚህን ፈተናዎች እንደምታሸነፍ በተደጋጋሚ አረጋግጣ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሯም ይህን በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል።
እንዳለችውም ከባድ የሚባሉ ፈተናዎችን አልፋ በጠላቶቿ ላይ ድሎችን ተቀዳጅታለች። ጠላቶቿ ሰላሟን ለማደፍረስ፣ ሕልውናዋን ለማሳጣት ያደረጉትን ሙከራ ሁሉ አምክናለች። ነገሮች ጠላቶቿ እንዳቀዱላት ሳይሆኑ እሷ እንዳቀደችው ሆነው ዘልቀዋል፣ ዛሬም አለች፤ በእርግጥም ነገም ትቀጥላለች።
እኛ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ብለን ልታሸንፍ የምትችልባቸውን እቅዶች ነድፈን፤ አሸንፈንም። የአገር ውስጥ እና የውጭ ጠላቶቻችን ደግሞ የማትሸነፈዋን ለማሸነፍ ከንቱ ተመኙ፤ ዕቅዳቸውንም አውጥተው የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ አሴሩ፤ ተገበሩ። ይህ እቅድና ሴራቸው ግን በጀግኖች ኢትዮጵያውያን አንድነት ተመታ፤ ከሸፈ። እንደ እነሱማ ቢሆን ዛሬ ኢትዮጵያ የምትባለዋ የምስራቅ አፍሪካዋ ታላቅ አገር የጦር አውድማ ሆና ነበር።
ጠላቶቻችን አቤት ስንቱን አቀዱልን? ስንቱን አሴሩብን! ስንቱንም ተገበሩብን! በእዚህች አገር ላይ ተዶልቷል፣ ተዝቷል ፤ ተዘምቷል። በዚህች አገር ላይ በሐሰተኛ መረጃ ያልተሰራ የለም። ከሀዲው ትህነግና የውጭ ኃይሎች አብረው ኢትዮጵያውያንን እና አገራቸውን በተለያየ መንገድ ለማንበርከክ ሞክረዋል።
ኢትዮጵያውያን ግን ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ ብለው ባሰቡት ጸኑ። ፍትሕና እውነት ከእነሱ ጋር ነውና የአሸናፊነት ስነ ልቦና አላቸው፤ አገሪቱም የአሸናፊዎች ምድር ናት።
የዓለም ኃያላን የሚባሉት የምዕራባውያን አገሮች መንግሥታት ‹‹ዜጎቻችን ሆይ ይህቺ አገር በመበታተን የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ትገኛለችና ትታችሁዋት ውጡ›› በማለት ደጋግመው ጥሪ አቅርበዋል። ተባባሪዎቻችን ያሏቸው ሌሎች አገሮችም ይህን ሰምተው ሊተገብሩ ሞክረዋል፤ ከእነዚህ አንዷም ሁሌም እየታመሰች የምትገኘው ሱዳን ናት።
ምዕራባውያኑ በአንድም ሆነ በሌላ የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ አይነተ ብዙ ማዕቀብ ጥለዋል፤ ጫና ፈጥረዋል። የዓለም ታላላቅ የሚባሉት ሚዲያዎች ገበናም ዘንድሮ ነው የታየው። ዘዋሪዎቻቸው ምዕራባውያኑ እንደሆኑና የምዕራባውያኑን ሐሰተኛ መረጃ ሲያሰራጩ ነበር። የሐሰተኛ መረጃ ቋት መሆናቸው ታውቋል። በኢትዮጵያውያን መከራ ሊሳለቁ፣ በአገራችን መፍረስ ሥራቸውን ሊያደምቁ፣ የቆሙላቸውን ምዕራባዊያን ዓላማ ሊያሳኩ ብዙ ሠርተዋል፤ እነ ትህነግና ተባባሪዎቹ የሚሰሩትን ወንጀል ባሓላየ እያለፉ፣ ኢትዮጵያን ባልዋለችበት አውለዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት ጠላቶቻችን ኢትዮጵያ መንግሥት አልባ አገር ልትሆን ነው፤ እዚያች አገር ላይ መልካም የሚባል ዜና ሊርቅ አፍታ ነው የቀረው ብለው አሟርተዋል። ምዕራባውያን እና ለፍትሕ የቆሙ ናቸው የምንላቸው የዓለማችን ትላልቅ ተቋማት መሪዎች ሳይቀሩ በእዚህ ቅሌት ውስጥ ተገኝተዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት ፀጥታው ምክር ቤትም ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት በምዕራባውያን ተጠልፈዋል።
ምዕራባውያኑ በተለይ አሜሪካ የኢትዮጵያን ጎረቤት አገሮች መሬት በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ልትሰነዝር የሚሉ ዘገባዎች ተሠርተዋል። ለዚህም ይሁን ለሌላ የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ አገራችንን እንደ ጦስ ዶሮ ዞሯታል። አንዴ ጅቡቲ ሌላ ጊዜ ኬንያ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሱዳን ሲመላለስ ነው የሥራ ዘመኑን የጨረሰው። ከዚያም ደግሞ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ያደርጋሉ በሚባሉት አገሮች ይሄዳል፤ አትደግፉ ለማለት እንጂ ሌላ ምንም ምክንያት የለውም።
በእዚህ ላይ ጎረቤት አገር ሱዳን የተሰጣት የቤት ሥራ አለ። የሰሜን ዕዝ ላይ በትህነግ ክህደት መፈጸሙ ሰርግና ምላሽ ሆኖላታል፤ ከኢትዮጵያ ጋር ስትወዛገብበት የነበረውን መሬት በኃይል ይዛለች። ይህ ድፍረቷ አንሶ ኢትዮጵያን ለማስፈራራት ከግብጽ ጋር የምታደርገውን አጥታለች። በእዚህ ላይ የትህነግን ታጣቂዎች በማስጠለል፣ በማሰልጠን፣ በማስታጠቅ ወደ ኢትዮጵያ ሰርጎ እንዲገባ ድጋፍ ታደርጋለች።
ሁሉም የጠላቶቻችን ዘመቻዎች የተቀናጁ ናቸው። በዘፈቀደ የተሠራ አንድም የጥፋት ተግባር የለም። ይህ በራሱ ለኢትዮጵያ አንድ ፈተና ነበር። ይሁንና ይህ ዘመቻ በኢትዮጵያውያን የአንድነት ክንድ ተደቁሷል። በኢትዮጵያውያን እቅድ የሴረኞቹ እቅድ መክኗል። ልትፈርስ የቀናት ዕድሜ ቀራት ያሏት ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትህነግና ተባባሪዎቹ ውርደትን ተከናነቡ። ኢትዮጵያ እቅዷን በተሳካ ሁኔታ ስለመፈጸምዋ፣ ወደፊትም የምትፈፅም ለመሆንዋ በርካታ ሌሎች ጥቂት ማሳያዎችን እንመልከት።
በምዕራባውያን ድጋፍ ግብፅ እኔ ሳልፈቅድ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ውሀ ትሞሉትና ወዮላችሁ አለችን፤እኛ ደግሞ ውሃው የተፈጠረበትን ምድር አጥግቦ ነው ከአገር የሚወጣው ብለን ዛቻና ማስፈራሪያውን ትተን የግድቡን ሁለተኛ ዙር ውሀ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ ፈጸምን እቅዳችንን አሳካን።
በመረጥነው መንግሥት ለመተዳደር ምርጫ ለማድረግ ወጠንን። ጠላቶቻችን በፍፁም ምርጫው መካሄድ የለበትም፤ ለማካሄድ ቢሞከር እናውካለን አሉ። አገራችን ግን ካለፉት ምርጫዎች ሁሉ የተሻለ ምርጫ አደረገች፤ በአዲስ ዓመት መግቢያ ላይም አዲሱን መንግሥት በመመስረት የምርጫ እቅዷን አሳካች።
አዲስ ዘመንዋን ለማወክ ብዙ ጣሩ፤ ሕዝቧ ግን አዲስ ዘመንን በአዲስ ምዕራፍ ጀመረ። አዲስነት መቀበሉን ይፋ አድርጎ፣ የጠላቶቹን አሮጌ ምልከታ እንደማይቀበል አረጋገጠ። ይህቺ ተአምረኛ አገር ጠላቶቿ እንደሚሉት ሳትፈርስ ልጆቿ እንደሚሉት በአሸናፊነት መራመዷን ቀጠለች። በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርስነት የተመዘገበውን የደመራ እና መስቀል በዓልን በድምቀትና በሰላም አከበረች።
ከሀዲው ትህነግ በአማራና አፋር ክልሎች ላይ ወረራ መፈጸሙ አልበቃህ ብሎት አዲስ አበባን እይዛለሁ እያለ ሲዝት፣ ተባባሪዎቹም ምዕራባውያን ይህንኑ አብረው ሊያስፈጽሙ ሐሰተኛ መረጃ ሲፈበርኩና ሲያሰራጩ ቢቆዩም፣ በዘመቻ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ድል የኢትዮጵያውያን ሆነ።
በአልሞት ባይ ተጋዳይነት እየተንከላወሱ ያሉት ትህነግና ሸኔ በገናና ጥምቀት በዓላችን ላይ ማሴር ጀመሩ። ይህም እንደ እነሱ ሳይሆን እንደ እኛ ሆነና በዓላቱ በሰላምና በደማቅ ሁኔታ ተከበሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለገናና ጥምቀት በዓል ጥሪ ያደረጉላቸው ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችም አገራቸው መጥተው የመጡበትን ዓላማ እያሳኩ ይገኛሉ።
ይህቺ አገር እቅዷ ዓላማዋ ማደግ ነውና ይህም በብርቱ ልጆቿ ተስፋና ራዕይ መሳካቱ አይቀሬ ነው። እቅዶቿን በመፈጸም በኩል ፈተና ሊገጥማት ይችል ይሆናል። ይህን ፈተና ለማለፍ የሚገጥማትን ችግር ሁሉ ለመሻገር የሕዝቧ አንድነት እንደ ትናንቱ ሊቀጥል ግድ ይላል። አንድ ሆነንና እንደ አገር በኅብረት ቆመን ያሰብነውን አሳክተናልና በቀጣይም ያሉብንን በርካታ ግዙፍ ሥራዎች በእቅዳችን መሠረት ለማሳካት ሁሌም አንድነታችን ላይ መፅናት ይኖርብናል።
ኢትዮጵያውያን ያሰብነውን የምናሳካ ፣የወጠነውን የምንፈፅም ነን። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አንድ መሆናችን ነው። በእርግጥም አንድ ሆነን የማንወጣው ችግር ፈፅሞ አይኖርም። ይህ ዘመን ደግሞ ይህን በሚገባ አሳይቶናል። አበቃሁ፤ ቸር ያሰማን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥር 14/2014