ቃል ቢጠፋንi?
የአገሬ ፈተናዋ ሙሉ ለሙሉ ታርሞ ተጠናቋል ማለት አይደለም። ጊዜ የሚጠይቁና ትዕግሥትን የሚፈትኑ በርካታ ቅሪቶች እዚህም እዚያም በስፋት እየተስተዋሉ ነው። ሕወሓት ይሉት የክፋት ጎሬ ሲያቅድና ሲተገብር የኖረው ቢያንስ ለመቶ ዓመታት “ዙፋኑን” ለማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን የዚያኑ ያህል በመቶ ዓመታት የማይጠገን ስብራት ለመፍጠር ጭምር እየቃዠ ነበር።
ቅዠት ለሚቃዠው ግለሰብ ብቻም ሳይሆን የሰላም እንቅልፍ ለሚናፍቀው አብሮ ነዋሪም የሚበጅ አይደለም። የቅዠት ችግር ያለበት ሰው ከመኝታው ላይ እየባተተ ሲደነባበር ሌሊቱን የሚያነጋው በአዕምሮው ስውር ክፍል (subconscious) የተጠራቀመው ክፉ ስብስብ ጤና ስለማይሰጠው ብቻ ሳይሆን በማይገባ ጉዳይ መማለልም በራሱ የቅዠት ምክንያት ሊሆን ይችላል። ቅዠታም የሚሰብረውና የሚደፋው የቤት ውስጥ መገልገያም ሌላው ጉዳት ነው።
የሌሊት ቅዠት ክፋቱ ከጭለማው ጋር እብስ ብሎ ያለመጥፋቱ ነው። ሌሊት በምናቡ ሲፋጭና ሲጋጭ የሚያድር ሰው ቀኑን የሚያሳልፈው በፀፀትና በእፍረት አንገቱን በመሳቀቅ እንደደፋ ነው። ቅዠት በሕክምና ርዳታ መፍትሔ ይኑረው አይኑረው እርግጠኛ አይደለሁም። ባዕዳን በሃሳብ ጭልጥ ብሎ መንጎድንም “Daydreaming” ‹የቁም ቅዠት› እያሉ ይገልጹታል። ዞሮ ዞሮ ቅዠት፤ ቅዠት ነው።
የአሸባሪው ሕወሓትን እኩይ የግፍ ክምር በቅዠታምነት የበየንነው ቢቸግረን ነው። እኩይ ድርጊቶቹን ለመዘርዘር ቃላት እስከማጣት እንደሚቸግር ከአሁን ቀደም ደጋግሜ ገልጫለሁ። የቅዠቱ እውነታ ራሱንም ሆነ እወክለዋለሁ የሚለውን ሕዝብ አንኮታኩቶ መቀመቅ ውስጥ መክተቱን እስካሁን ባንኖ አልተረዳውም፤ ወይንም ከቅዠት ድብርቱ ዛሬም አልተላቀቀም።
አገር በእንደዚህ መሰል ፈተና ውስጥ እያለች ይህ ጎደለ? ይህ አነሰ? ብሎ ማማረር አግባብ ላይሆን ይችላል። መልከ ብዙው ጦርነት ገና እንዳልተጠናቀቀም ማንም ዜጋ ያውቀዋል። ያም ቢሆን ግን ይህንን አጋጣሚ እንደ ደህና መመከቻ ጋሻ እየተጠቀሙ በመሐል አገር ያለውን ሕዝብ ባልተገባ ሁኔታ ማማረሩ አግባብ ነው ተብሎ አይታመንም።
ጦርነቱ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በበርካታ ዘርፎች አቅም እንዳሳጣ ሳይነግረን ያለፈ አንድም ባለሥልጣን አላየንም። እኛ ዜጎችም ቢሆን የአገራችን መከራ ገና እንዳልተጠናቀቀ መቼ ጠፋን? መከራ የወደቀበት ቤተሰብ “ዕልል በል” ሊባል እንደማይችል ሁሉ ዜጎችም አገራቸው ታማ ለቅንጦት ኑሮ ይጮኻሉ ብሎ መገመት ያዳግታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ መከራ ቻይነት ተደጋግሞ ስለተወደሰ ደግመን አንባቢን አናሰለችም። መከራን የቻለ ሕዝብ አሸናፊ እንደሚሆንም ታሪካችንና ባህላችን በሚገባ አስተምረውናል። ሙግቱ ሊሆን የሚገባው በመከራ መካከልም ቢሆን ተስፋ ሊጎላ፣ ሕይወትም መቀጠል እንዳለበት መታወቁ ላይ ነው።
እውነቱን እንነጋገር ከተባለ መንግሥት ልቡ ስሱ ሆኖ መጨከን ያቃተው ራሱ በሚመራው ቢሮክራሲ ላይ ጭምር እንደሆነ በብዙ ማስረጃዎች ማሳየት ይቻላል። ከበርካታ የመንግሥታዊና የአካባቢ አስተዳደሮች እስከ ሕዝባዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ድረስ ትዝብታችንን እንዘርግፍ ብንል ስፋቱና ወርዱን መሰብሰብ እንቸገር ካልሆነ በስተቀር መዘርዘሩ አይሳነንም።
አንዲት ዘለላ ጉዳይ ለአብነት ልጥቀስ። በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ምክንያት መሠረተ ልማቶች የወደሙባቸው አካባቢዎች ተጠግነው አገልግሎት እንዲጀምሩ የተደረገበት አኩሪ ገድል በእጅጉ የሚያስገርምም የሚያስመሰግንም ነው። በተለይም የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን የመብራት አገልግሎቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ ያደረገው ርብርብ በእጅጉ ያስደንቃል። እኛ ዜጎች በዚህ ተግባሩ ኮርተንበት ነበር። የባለሙያዎቹ የቀንና የሌሊት ተግባርም እንዲሁ የሚቀጥል መስሎን ለእኛ ለመሐል አገር ነዋሪዎችም “ነግ ለእኛም” ተስፋው አሙቆን ነበር።
እውነታው ግን እንደተመኘነው ሊሆን አልቻለም። የችግሩ ስፋት ባይጠፋንም በመሐል ከተሞች ያለው የኃይል መቆራረጥ ግን የኃይል እጥረት ብቻ ሳይሆን የተቋሙ ሠራተኞች ልግመትና ዳተኝነት መሆኑ ከእለት ወደ እለት ጥርት ብሎ እየተስተዋለ ነው። ይህ አምደኛ ይህንን ጽሑፍ የጻፈው የሳምንት ጨለማ በዋጠው ክፍል ውስጥ ሻማ እየተጠቀመ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ በደቂቃዎች ውስጥ ሊፈታ የሚችልና በመኖሪያ ቤቱ አካባቢ ያለ አንድ መለስተኛ ትራንስፎርመር ችግር ደርሶበታል የሚል ነው።
ለችግሩ መፍትሔ ለማግኘት የአካባቢው ነዋሪዎች ተሰባስበን ወደ ዋና ዋና ኃላፊዎች ዘንድ አቤቱታችንን ለማሰማት ያደረግነው ሙከራ ሊሳካ አልቻለም። “የሆነ ነገር አሰባስባችሁ ሸጉጡላቸው እንጂ ያለበለዚያ የበዓሉን ቀናት በጨለማ ውስጥ ማሳለፋችሁ ነው” ብለው ምክሩን ሹክ ያሉን የራሱ የተቋሙ ሠራተኞች ናቸው። እንዳሉትም ትንቢታቸው ሰምሮ በበዓል ደስታችን ላይ ጭካኔ ተፈጽሞብን እስካሁንም በተመከርነው መሠረት እጃችንን ለመዘርጋት ኅሊናችን ስላልፈቀደልን ጨለማችን አልተገፈፈልንም።
ይህ አንድ ተራና ትንሽ ምሳሌ ነው። እንደ አንድ ገጠመኝ ታይቶም የድርጅቱን ክብር እንደመንካት ሊያስቆጥር አይችልም። እንቆጣ ብለው ቢከራከሩም የሚያዋጣቸው አይሆንም። ድምጻችንን ሰጥተን ወንበሩን ላደላደልንለት መንግሥታችን አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ጨከን ብለን ብናቀርብለት ለውሳኔ አሰጣጥ ሊረዳው ስለሚችል ጆሮ ሰጥቶ ይስማን።
መንግሥታችን ሆይ! Persona non granta ያዋጣ ይሆን?
ባለ ቋንቋዎቹ ላቲኖች ያወረሱትን ሆሄያትና ሐረግ እንደወረደ የማስተዋውቀው ሃሳቡ የአማርኛ ፍቺ ይኑረው አይኑረው እርግጠኛ ስላልሆንኩ ነው። Persona non granta የተለመደ የዲፕሎማቶች መግባቢያ ነው። አንድ አገር ወደ ሁለተኛ አገር የሚሲዮን መልዕክተኛውን በሹመትም ሆነ በምደባ ሲልክ ሙሉ ለሙሉ መልዕክተኞቼን ይቀበልልኛል ብሎ በማሰብ አይደለም። ምክንያቱ እንዲህና እንዲህ ነው ብሎ ማብራራት ሳያስፈልገው ተቀባዩ አገር ለላኪው አገር መንግሥት ዲፕሎማትህን ወደ አገሬ እንዲገባ አልፈቅድለትም ወይንም የሹመት ደብዳቤውን (Credential) አልተቀበልኩም በማለት ብቻ ከደጃፍ ሊመልሰው ወይንም ሥራ እንዳይጀምር ሊያደርገው ይችላል። ሌሎች የአተገባበር ዝርዝሮችም ስላሉ ለጊዜው ይኼው ይበቃ ይመስለናል።
Persona non granta ከዲፕሎማሲ የአጠቃቀም ይዘቱ ሰፋ ብሎ ለዕለት ተዕለት ማኅበራዊ አገልግሎቶችም ወደማደግ ተሸጋግሯል። ለምሳሌ፤ ነፃ ማኅበራዊ ግልጋሎት የሚሰጥ የአንድ ክለብ አባል ለመሆን የሚጠይቅ ግለሰብ የጀርባ ታሪኩ ተጠንቶ “ስለ አንተ/አንቺ በቂ ማጣሪያ አድርገን በባህርይም ሆነ በችሎታ የአቅም ውስንነት ይኖራል ብለን ስለገመትን ለክለባችን አባል ልናደርግህ አንችልም” ተብሎ ጥያቄው በጎ ምላሽ ላያገኝ ይችላል። Persona non granta! ከጉዳያችን ጋር እናያይዘውና ሥልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ፓርቲ ወይንም መንግሥት ለከፍተኛም ሆነ ለመለስተኛ ተቋማቱ ወይንም በየደረጃው ለሚመድባቸው አመራሮች ሕዝቡ በአሜንታ እንዲቀበላቸው ብቻ ሳይሆን የሥነ ምግባርና የብቃት ድክመትና ስንፈት ሲስተዋልባቸው ወይንም ሹመቱ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ተጣርቶ የማይመጥኑ ከሆነ የ Persona non granta ውሳኔ ተገልጋዩ ራሱ እንዲያስተላልፍባቸውና “ሹመትህን/ሹመትሽን አልተቀበልነውም” እስከ ማለት ለሕዝቡ መብት ቢሰጥ ክፋት ይኖረዋል? ይህን መሰሉ ውሳኔ ከፍ ከፍ ላሉት ሹማምንት በተወካዮች ምክር ቤት እንደሚተገበር ጭምጭምታ እየሰማን ነው። ለሕዝቡ ግልጥልጥ ተደርጎ እንዲያውቀው ስለመደረጉ ግን እርግጠኞች አይደለንም።
ሆደ ባሻ ሆኖ መንግሥታችን አይቀየመንና በርካቶቹ የአገራችን ባለሥልጣናት ሕልማቸውና ቅዠታቸው ከወንበራቸው ሥር የሚፈልቀው የጥቅማ ጥቅም ምንጭ ይታያቸው ካልሆነ በስተቀር ላባቸውን ጠብ እያደረጉና ሕዝቡን እያከበሩ በንጽሕናና በትጋት ለማገልገል የትናንትናና የዛሬውን ፍሬያቸውን በማየት ብቻ ወደ እውነት መቃረብ ይቻላል። እርግጥ ነው የሕዝብ ፍቅር ያላቸው ጥቂቶች ይጠፋሉ ማለት ግን አይደለም።
Persona non granta ለአዳዲስ ሹመኞች ብቻም ሳይሆን ወንበራቸው ላይ ለተቀመጡት “ትጋት ብርቁዎችና ሕዝብ ናቂታዎችም” መተግበሩ ስለማይከፋ ፀባዖትን በሥዕለት ከመማጸናችን አስቀድሞ መንግሥታችን ብሶታችንን ሰምቶ ምላሹ ቢፈጥንልን ለአፋችን እንኳን ቢቀርበት አንጀታችን ግን ቅቤ መጠጣቱ አይቀርም ነበር።
ለምሳሌ፤ Persona non granta ቢሮዎቻቸው በተገልጋዩ ዕንባ ከራሰው ተቋማት መካከል ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው ከመብራት ኃይል አከፋፋዩ ተቋምና የዜጎችን ግብርና ታክስ እንዲሰበስብ አገር አደራ ከጣለችባቸው መ/ቤት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ቢጀመር ጥሩ መነሻ ሊሆን ይችላል። መብራት ኃይልን በተመለከተ መሠረታዊ አገራዊ ችግሮችን ሳንዘነጋ የአቅሙን ያህል እንኳን እንዲያገለግለን ጮኸን ጮኸን የሚሰማን ስላጣን “ሆድ ይፍጀው” ብለን ትተንዋል። 905 ቁጥራቸውም ሆነ ኃላፊዎቻቸው ባህርያቸው አንድ ዓይነት ስለሆነ ይለወጣሉ የሚለው ተስፋ ከሕዝቡ ውስጥ ከተሟጠጠ ሰነባብቷል። እነዚህን መሰል ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ለPersona non granta ውሳኔ እንዲቀርቡ መንግሥታችን ዕድል ቢሰጠን የምናጨበጭብለት ከወንበራችን ተነስተን በሆነ ነበር።
የአገሬን ግብር ሰብሳቢ መ/ቤት ጥረት ሳንዘነጋ፣ ዜጎችም የግብር ግዴታቸውን መወጣታቸው ግድ መሆኑን ሳንረሳ ሁለቱንም ጽንፎች አቻችለን አቤቱታ ብናቀርብ የሚያስኮርፍ አይመስለንም። የንግድ ፈቃድ ለማውጣት ያለው ፍጥነትና በኪሳራ ምክንያት የንግድ ተቋሙን ለመዝጋት የሚታለፍበትን “የሲዖል መንገድ” ለማነጻጸር በፍጹም የሚቻል አይደለም። ፍቃድ ለማውጣት አቤት ፍጥነት! ድርጅቱን ልንዘጋ ነው ሲባል ደግሞ አቤት መከራ! ይህንን ኮስተር ያለ ብሶት ለማረጋገጥ ሰሞኑን በተለያዩ ወቅታዊ ፈተናዎች ምክንያት በኪሳራ ድርጅታቸውን ለመዝጋት በተቋሙ ግቢዎች ውስጥ ሽቅብ ቁልቁል እያሉ እምባቸውን ከሚያፈሱት “ምንዱባን” መካከል መቶ ያህሉን ብቻ ለውይይት ጠርቶ ቢደመጡ ማረጋገጫውን ማግኘት ይቻላል።
ለአወያይነት የሚመደበው ሰው ግን ከብሶተኞቹ ጋር አብሮ የሚነፋረቅ ስሜተ ስሱ መሆን እንደማይገባው ከወዲሁ መጠቆም ይቻላል። ይህ ጸሐፊ በልበ ሙሉነት የተቋሙን የተለመደ ገመና ይፋ የሚገልጠው መንግሥት በፈቃደኝነት አገልግለኝ ብሎ ባሸከመው “የታክስ አምባሳደርነት” አደራው ጭምር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ውይይቱ በሚካሄድበትም ዕለት ቢሆን ይህ ጸሐፊ በአስረጂነትም ሆነ በተሳታፊነት ለመገኘት ሙሉ ፈቃደኛ ነው።
በሦስተኛ ማሳያነት የየክፍለ ከተሞች አሠራር ቢፈተሽልን አንጠላም። ከሁለት ሳምንት በፊት በተመደበ በአንድ ወሩ ከተገልጋዮች ብር አምስት መቶ ሺህ ጉቦ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ የተያዘው የመዲናችን የወረዳ ሹም ብዙዎቻችንን ማስደንገጡ አልቀረም። በአንድ ወር እንዲህ ያደረገ አንድ ዓመት ቢቆይ ምን ሊሰራ እንደሚችል ስናስብ መደንገጥ ብቻም ሳይሆን “በማማተብ” ጭምር ስሜታችንን ገልጸናል። በተለይም የመታወቂያ ዕደላ እድሳት ጉዳይ ሲጀመር ምን ይገጥመን ይሆን በማለትም መሳቀቃችን አልቀረም። በእነዚህ መሰል ተቋማትም Persona non granta ተጠናክሮ ቢጀመር አይከፋም። እነዚህ ጥቂቶች ለማሳያነት ስለሚበቁን ሃሳባችንን ወደመጠቅለሉ እንሻገር።
የግንባሩ ፍልሚያና ድል በመሐል የአገሪቱ ክፍሎችም ይተግበር ብለን መንግሥታችንን የ Persona non granta ሃሳብ ያቀረብንለት ቢቸግረን ነው። የሥልጣን ምንጭ ሕዝብ ከሆነ ዘንዳ እንዲህ ዓይነቱን ኮስተር ያለ ሃሳብ የምናቀርበው የምርጫ ካርዳችንን እንደጣልንበት ተዓምረኛ ሳጥን (Ballot box) ተስፋችንም እንዳይቆለፍበት አደራ በማቅረብ ጭምር ነው። እየረሳነው ተቸገርን እንጂ ለካንስ ታክስ ከፋይነታችንም የልባችንን እንድንተነፍስ ይፈቅድልናል!? ሰላም ይሁን።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥር 14/2014