የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ከስምንት ዓመታት በኋላ ተሳታፊ ከሆነበት የአፍሪካ ዋንጫ አንድ ነጥብ ብቻ በማስመዝገብ ከምድቡ የመጨረሻውን ስፍራ ይዞ ውድድሩን ማጠናቀቁ ይታወቃል።
በጨዋታው አዘጋጇ ካሜሮን፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኬፕ ቨርዲ ወደ ሚቀጥለው ዙር ሲያልፉ፣ ዋልያዎቹ ባንድም ጨዋታ ሳያሸንፉ ነው ከታላቁ የአፍሪካ መድረክ የተሰናበቱት።
ቡድኑ በምድቡ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ላይ መልካም እንቅስቃሴዎችን ቢያሳይም ፣ በአንጻሩ ጎልተው የታዩ ክፍተቶችም ነበሩበት። የአካል ብቃት፣ የአለም አቀፍ ጨዋታ ልምድ ማነስ፣ ተረጋግቶ መጫወት አለመቻል የሚሉት በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ በተደጋጋሚ ሲነሱ የነበሩ አስተያየቶች ናቸው።
በተለይ በአካል ብቃት ላይ የጎላ ክፍተት ታይቷል። ቡድኑ በጨዋታዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ የሚያሳየውን የአካል ብቃት በሁለተኛው ማሳየት ሲያዳግተው ተስተውሏል። በተቃራኒ ቡድን የጨዋታ ብልጫ የሚወሰድበት እንዲሁም ተጨማሪ ግቦች የሚቆጠርበትም በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ጊዜ መሆኑ ታይቷል።
ይህ የአካል ብቃት ጉድለት ፊትም የነበረ፣ ዛሬም ሊቀረፍ ያልቻለ ትልቅ ችግር ነው ቢባል ስህተት አይሆንም።
በስፖርተኝነት እንዲሁም በስፖርት ባለሙያነት ለረጅም ዓመታት ያገለገሉት፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሰሩበት ኤክሰርሳይስ ፊዚዮሎጂ የእግር ኳስ ተጫዋቾች አካል ብቃት ላይ ብዙ የሰሩት ከፍተኛ የስፖርት ዘርፉ ባለሙያ ዶክተር ኤሊያስ አቡ ሻክር በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ ቡድኑ በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ ተደጋጋሚ ጥፋቶችን ሲሰራ ተመልክተዋል።
በጨዋታዎቹ ለመታዘብ እንደቻሉት ቡድኑ ከ60 ደቂቃ በላይ የሚጫወት አልነበረም። እሳቸው በዚህ ሙያቸው ማገልገል ከጀመሩ 12 ዓመት እንደሆነ ጠቅሰው፣ አካል ብቃትን በሚመለከት ሰሚ እንዳላገኙና እስካሁንም ያልተፈታ ችግር መሆኑንም ይገልጻሉ።
ዶክተር ኤልያስ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾችን የአካል ብቃት መለካታቸውን አስታውሰው፣ አንዳቸውም የአፍሪካን ደረጃ እንደማያሟሉ ማረጋገጣቸውንም ያመለክታሉ።
በተመሳሳይ በሊጉ ተሳታፊ ከሆኑት ክለቦች መካከል የአካል ብቃት አዘጋጅ ባለሙያ እንደሌለም ይጠቁማሉ። ይህም ለአካል ብቃት ምንም ዓይነት ትኩረት እንደማይሰጥ በግልጽ የሚያመላክት ነው ያሉት ዶክተር ኤልያስ፣ ሌላው መታወቅ ያለበት ከቡድኑ ጋር የሚጫወቱት ቡድኖች ተጫዋቾች አፍሪካዊ ስምና መልክ ብቻ ያላቸው እንጂ አብዛኛዎቹ በአውሮፓ የሚጫወቱ መሆናቸው ነው ሲሉ ያብራራሉ። 28 የውጭ ተጫዋቾች ያሉትን የሴኔጋል እንዲሁም 27 የአውሮፓ ሊግ ተጫዋቾች ያሉትን የናይጄሪያን ቡድን ለማሳያነት በማንሳት ያብራራሉ።
‹‹በኢትዮጵያ ሊግ ተጫዋቾች የተዋቀረ ቡድን እንዴት ከአውሮፓ ሊግ ጋር ይጋጠማል?›› በሚል ለሚነሳው ጥያቄም ከእነሱ ጋር ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው እነሱን የሚመጥን ቡድን ይዞ በመጓዝ መሆኑን ያስገነዝባሉ። ዶክተር ኤልያስ በሰውነት ውስጥ የሚኖር የስብ መጠን፣ የልብ ትርታ፣ የፍጥነት ብቃት መለኪያና የመሳሰሉት ሌሎች የመለኪያ መንገዶችን በመጠቀምም ቡድኖችን በተደጋጋሚ መመዘን ችለዋል።
የተለያየ ውጤት ይገኝ እንጂ በአማካይ የኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች የመጫወት ብቃት በሰዓት ሲለካ ከ60-70 ደቂቃ መሆኑን ይናገራሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በበርካታ ጨዋታዎች እንደሚስተዋለው ከሆነም ቡድኑ በርካታ ግብ የሚቆጠርበት ከተገለጸው ደቂቃ በኋላ ተጫዋቾች ስለሚደክሙ ነው። አሰልጣኞች የኳስ ቅብብላቸው በቁጥር ማደጉን እንደስኬት ቢገልጹም ቡድኑ ጠንካራ ሊባል የሚችለው ግን ከአካል ብቃት ጋር ቢያያዝ ነው።
መተኮር ያለበት የ90 ደቂቃ የጨዋታ ሰዓት ብቻ አይደለም፤ በእኩል ውጤት ጨዋታው ተጠናቆ ሌላ 30 ደቂቃ ሊጨመር እንደሚችልም ገምቶ መስራት ያስፈልጋል። በእዚህ መልኩ ካልተሰራ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ያለ ጥርጥር አደጋ ነው። ብሄራዊ ቡድኑ በብዛት እንደሚታየው ወደኋላ በመጫወት ላይ ያተኩራል፤ ይህም የሚሆነው ወደፊት ለመጫወት ፍጥነትና ጉልበት ስለማይኖረው ነው የሚሉት ዶክተር ኤልያስ፣ ተጫዋቾች የሚመርጡት በቅብብል መሄድን ቢሆንም /ይህም በጣም የዘገየ ነው/፣ ይህም በተቃራኒ ቡድን አስቀድሞ ስለሚገመት ብልጫ ይወሰድበታል።
ብሄራዊ ቡድኑ በጨዋታው እንደሚሳተፉት ሌሎች ብሄራዊ ቡድኖች ፈጣንና ጠንካራ እንዲሆን በአካል ብቃት ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚገባ ዶክተር ኤልያስ አጽንኦት ሰጥተው ያስገነዝባሉ።
‹‹ሳይንስ ዘረኛ አይደለም›› የሚሉት አንጋፋው ባለሙያ፤ በአውሮፓ ሊጎች በአካል ብቃት ከኢትዮጵያውያን የሚያንሱ ነገር ግን ኮከብ መሆን የቻሉ ተጫዋቾችን መኖራቸውንም ያመለክታሉ። ‹‹አካል ብቃት በሳይንሳዊ መንገድ ከተሰራ ከፍተኛ ለውጥ ይመጣል። የሚጀመረው ደግሞ በወጣትነት እድሜ ነው።›› ሲሉ ተናግረው፤ እዚህ አገር ግን አካል ብቃትን ለስሙ እንጂ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራበት ቡድን የለም ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ከ17ዓመት በታች ቡድን አካል ብቃት ስለካ አራት የሚሆኑ ተጫዋቾች 30 ሜትሩን በአራት ሰከንዶች ብቻ መሮጣቸውን ተመልክቻለሁ›› ያሉት ዶክተር ኤልያስ፣ ከወራት በኋላ በድጋሚ ስለካቸው ግን ከአራት ደቂቃ በላይ ነበር የሮጡት፤ ይህም አካል ብቃት ላይ እንደማይሰራ አመላካች ነው›› ሲሉ ያስረዳሉ።
አሰልጣኞች የስነ ምግብ፣ ስነልቦና፣ አካል ብቃት፣… ለሙያተኛው ሳይተው ሁሉንም ጠቅልለው የሚይዙ እስከሆነ ድረስ በእግር ኳሱ ለውጥ ሊመጣ አይችልም ሲሉ ነው ያስገነዘቡት። በአካል ብቃት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራ ግን ከሌሎቹ እኩል ለመሆን የማይቻልበት ሁኔታ እንደሌለም አረጋግጠዋል።
ሌላው ትኩረት የሚፈልገው ጉዳይ ቡድኑ የሚገጥማቸውን ቡድኖች መለየት መሆኑን ተናግረው፣ አብዛኛዎቹ የቡድኑ አባላት በአውሮፓ ሊጎች የሚጫዋቱ ቡድኖች ከሆኑ እስከ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ድረስ ከባድ እንደሚሆኑ መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለመሻሻል መድረግ ያለበት ሌሎች ቡድኖች የሚያደርጉትን ማድረግ መሆን እንዳለበት የአካል ብቃት ሙያተኛው ዶክተር ኤሊያስ አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 13/2014