የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክስዮን ማኅበር የ2016 ዓም ውድድር ዘመን የክለቦች ዓመታዊ ትርፍ ክፍፍል ተከናውኗል። በየዘርፉ የዓመቱ ኮከቦችን ሽልማት መርሐግብር አከናውኖም ለክለቦች፣ አሠልጣኞች፣ ተጫዋቾች፣ ዳኞች እንዲሁም አስተናጋጅ ከተሞች የገንዝብ ሽልማት እና እውቅና ተበርክቶላቸዋል፡፡
አዲሱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዓመት ትናንት በድሬዳዋ ስታዲየም በተካሄዱ ጨዋታዎች ተጀምሯል፡፡ ከውድድር ዓመቱ መጀመር አስቀድሞ ያለፈው ዓመት ኮከቦች ምርጫ፣ የክለቦች ዓመታዊ የትርፍ ክፍፍል፣ የማጠቃለያ እንዲሁም የ2017 ዓም ውድድር ማስጀመሪያ መርሐግብር ተከናውኗል፡፡ በሥነ ሥርዓቱም ላይ ለክለቦች እንደየደረጃቸውና ድርሻቸው የገንዘብ ክፍፍል ተደርጎላቸዋል፡፡
16ቱ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች የውድድር ዓመቱን በፈጸሙት ደረጃቸው መሠረት የገንዘብ ክፍፍል ሲደረግላቸው፤ ሻምፒዮኑ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጨማሪ የገንዘብ ሽልማት አግኝቷል፡፡ ከቴሌቪዥን መብት ሽያጭ እና ከሌሎች ገቢዎችም የሊጉ ተሳታፊ ለሆኑት 16ት ክለቦች 195 ሚሊዮን ብር የትርፍ ክፍፍል መደረጉ ተገልጿል፡፡ በዚህም የውድድሩ አሸናፊ የሆነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብርን ጨምሮ በአጠቃላይ 18 ሚሊዮን ብር ተበርክቶለታል፡፡ በብርቱ ተፎካካሪነት ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው መቻል 17 ሚሊዮን ብር አግኝቷል። የኢትዮጵያ ዋንጫ ሻምፒዮኖቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች 16 ሚሊዮን ብር ሲያገኙ፤ ወራጆቹ ሻሸመኔ ከተማ እና ሀምበርቾ ዱራሜ እያንዳንዳቸው 8 ሚሊዮን ብር የትርፍ ተካፋይ ሆነዋል፡፡ ከአራተኛ እስከ 14ኛ የተቀመጡት ክለቦችም ከ15 ሚሊዮን እስከ 9 ሚሊዮን ብር ወደ ካዝናቸው አስገብተዋል፡፡
በ7 ዘርፎች የዓመቱ ኮከቦች ሽልማት የተከናወነ ሲሆን፤ የዓመቱ ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋቾች፣ አሠልጣኞችና ዳኞችም ከፍተኛ የሆነ የማበረታቻ ገንዘብ ተሸልመዋል፡፡ የሊጉ ሻምፒዮን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዓመቱ የኮከቦች ሽልማት በሦስት ዘርፎች አሸናፊ ሊሆን ችሏል። የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች፣ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ፣ ተስፈኛ ወጣት ተጫዋች እና የዓመቱ ኮከብ በረኛ በሚልም ሽልማቱ ተሰጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት በዓመቱ ኮከብ ተጫዋችነት ጋናዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመሐል ሜዳ ተጫዋች ባሲሩ ኡመር የ210 ሺ ብር ተሸላሚ ሆኗል፡፡ የአዳማ ከተማው ቢኒያም አይተን የዓመቱ ወጣት ኮከብ ተጫዋች ሆኖ በመመረጥ 105 ሺ ብር ተበርክቶለታል፡፡ በ2015 ዓም ዮሴፍ ታረቀኝ የሊጉ ወጣት ኮከብ ተጫዋች በመሆን ከተመረጠ በኋላ ቢንያም አይተን ሁለተኛው የአዳማ ከተማ ተሸላሚ ወጣት ተጫዋች ሆኗል፡፡ የ2016 ዓም የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ማጠናቀቅ የቻለው ኤርትራዊው የሃዋሳ ከነማ ተጫዋች አሊ ሱሌማን ደግሞ 200 ሺ ብር ተሸልሟል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግብ ጠባቂ ፍሬው ጌታሁን የዓመቱ ኮከብ ግብ ጠባቂና የ150 ሺ ብር ተሸላሚ መሆኑም ተረጋግጧል፡፡
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከከፍተኛ ሊግ በማሳደግ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ያበቃው አሠልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ኮከብ አሠልጣኝ ሆኖ ተመርጧል፡፡ ክለቡ የመጀመሪያውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ እንዲያነሳና የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ያደረገው አሠልጣኝ በፀሎት 200 ሺ ብርም ተሸልሟል። ምስጉን ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ምርጥ ዋና ዳኛ በመሆን እያንዳንዳቸው 105 ሺ ብር መሸለም ችለዋል፡፡
የ2016 ዓም የውድድር ዓመት መዝጊያ እና የ2017 ዓም የውድድር ዘመን ማብሰሪያ በድሬዳዋ ከተማ የተካሄደውም የከተማ አስተዳደሩ ለስታዲየም ግንባታ የሰጠውን ትኩረት ለማበረታታት እና እውቅና ለመስጠት እንደሆነም የአክስዮን ማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ተናግረዋል። በዚህም ባለፈው የውድድር ዓመት የሊጉን ጨዋታዎች ያስተናገዱት አዳማ፣ ሃዋሳና ድሬዳዋ ከተሞች 10 ሚሊዮን ብር እንደሚከፋፈሉም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
19 ክለቦች የሚፋለሙበትና አምስት ክለቦች የሚወርዱበት የ2017 የሊጉ መርሐግብር ትናንት ሁለት ጨዋታዎችን በማስተናገድ ተጀምሯል። ውድድሩ ዛሬም በሁለት ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲካሄድ እሁድ እና ሰኞም በተመሳሳይ ሁለት ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ፡፡ የዘንድሮው የሊጉ ቆይታ 38 ሳምንታት የሚፈጅ ሲሆን 342 ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡ በቀን ሦስት ጨዋታዎች እየተካሄዱ አንድ አራፊ ቡድን ሆኖ በተመረጡት ከተሞች እስከ ዓመቱ ማጠናቀቂያ የሚቀጥልም ይሆናል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም