የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያ ነው፡፡ የሬክታንግል ቅርጽ አለው፡፡ ስሪቱ ከብረት ነክ ነገሮች ነው፡፡ አፍ ላይ ከወዲያ ወዲህ በማንቀሳቀስ ድምጽ እንዲያወጣ ይደረጋል፡፡ በዚህ መሣሪያ ጨዋታ ውስጥ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት ከንፈርና ምላስ ናቸው፡፡ አጨዋወቱም አየር በማስገባትና በማስወጣት ነው፡፡ ይህ የሙዚቃ መሳሪያ ‹‹ሀርሞኒካ›› ይባላል፡፡ ቃሉ ‹‹ሀርፕ›› ከሚለው የፈረንሳይኛ ቃል የመጣ ሲሆን፣ የአፍ ክፍል እንደ ማለት ነው፡፡ መሣሪያውም በአፍ ብቻ የሚጫወቱት ነው፡፡
ሀርሞኒካ በተለያዩ የዓለም አገራት የታወቀ ቢሆንም፣ መነሻው አውሮፓና አሜሪካ ውስጥ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ተወዳጅነት ባላቸው የብሉስ፣ ፎክ ሙዚክ፣ ክላሲክ ሙዚክ፣ ጃዝ እና ሮክ ሙዚቃዎች ላይ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ እናም ሀርሞኒካ መነሻው ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያ ነው፡፡
ይህን ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያ ከኢትዮጵያዊው አገር በቀል ዋሽንት ጋር እስቲ እናነጻጽረው፡፡ ዋሽንት የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያ ነው። የሚሰራው ከሸንበቆ ሲሆን፣ ከብረትና ከፕላስቲክ መሠራት ከጀመረም ቆያይቷል፡፡ ዋሽንት አራት ወይም አምስት ቀዳዳዎች ያሉት ሲሆን፤ ዋሽንት ተጫዋቾች እንደሚሉት የተለያየ ዜማ መፍጠር የሚቻለው ቀዳዳው ላይ የሚያርፉ ጣቶችን ምት በመቀያየር ነው፡፡ አጨዋወቱም ሙሉ በሙሉ በትንፋሽ ነው፡፡
ተጫዋቾች የቀዳዳዎችን ምት በመቀያየር በፈለጉት ቅኝት ይጫወቱታል፡፡ ሀርሞኒካን ከዋሽንት ጋር ለምን አነፃፀርከው? ትሉኝ ይሆናል፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ ትናንት ጥር 11 ቀን የጥምቀት በዓል ነበር፡፡ የጥምቀት በአል የሚከበርባቸው ስፍራዎች በተለመደው አካሄድ ጥምቀተ ባህር ተብለው ይጠራሉ፡፡ በእነዚህ ስፍራዎች ወንዞችና ሌሎች የውሃ አካላት ይኖራሉ፡፡ ጥምቀቱም የሚፈጸመው በእዚህ ስፍራ የሚገኘው ውሃ በሃይማኖታዊ ሥርዓት ጸሎት ተደርጎና ተባርኮ ነው፡፡ በከተሞች የቧንቧ ውሃ ለእዚህ ተግባር ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ ይገኛል፡፡ ውሃው በገንዳ እንዲጠራቀም ተደርጎ ወይም በቀጥታ የጥምቀቱን አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ በዓሉ በእነዚህ የጥምቀተ ባህር ሥፍራዎች ከዋዜማው አንስቶ በደማቅ ሥነሥርአት ይከበራል፡፡ በአዲስ አበባ በዓሉ በደማቅ ሥነሥርዓት ከሚከበርባቸው ስፍራዎች ጃንሜዳ ይጠቀሳል፡፡ ጃንሜዳ እጅግ ሰፊ ስፍራ ነው፡፡ በዚህ በዓል ወቅት ጀንሜዳ ከጫፍ እስከ ጫፍ ይደምቃል፡፡ በሃይማኖታዊ ሥርዓቱ መሠረት የሚደረግ መንፈሳዊ ሥነሥርዓት ዋናው ድምቀቱ ሲሆን፣ ከበዓሉ ጎን ለጎን ባህላዊ ሥነሥርዓትም ይካሄዳሉ፡፡ ዘፉኑ፣ ውዝዋዜው፣ አለባበሱ ልዩ ነው፡፡ በዚህ አደባባይ ወጣቶች እዚህም እዚያም ክብ ሠርተው ሲጫወቱ ይታያሉ፡፡ በዚህ ስፍራ ወጣቶች ጨዋታዎቻቸውን በሀርሞኒካ ሲያደምቁ ማየት የተለመደ ነው፡፡ እንዲያውም በአገራችን ሀርሞኒካ የሚታይበት ቀን ቢኖር ይህ የጥምቀት በዓል ነው፡፡
በአገራችን ሀርሞኒካ ከተቀመጠበት የሚወጣው በእዚህ የጥምቀት በዓል ነው። እዚህ ቦታ ላይ እንደ አታሞ እና ዋሽንት የመሳሰሉ አገር በቀል የሙዚቃ መሣሪያዎች አይታዩም፡፡ ስለ ባህላዊው ሥነ ሥርዓት ነው እየገለጽኩ ያለሁት፡፡ ሀርሞኒካ የሚነግስበት ወቅት ይህ ጥምቀት ብቻ ነው፡፡ ለእዚያውም በጃንሜዳ ነው የሚታየው፡፡ ሀርሞኒካ የጥምቀት መለያ ሆኗል፡፡
የሬዲዮም ሆነ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የጥምቀት ሰሞን ከመንፈሳዊና ባህላዊ ሥነሥርዓቶቹ ቀጥለው የሚያሰሙንና የሚያሳዩን በሀርሞኒካ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ነው፡፡ በዓመት አንዴ የሚካሄድ ጨዋታ ስለሆነና በወጣቶች በእጅጉ ስለሚወደድ ሊሆን ይችላል ምርጫቸው ያደረጉት፡፡
ወጣቶቹ ይህን የሙዚቃ መሳሪያ መምረጣቸው ምንም ችግር የለውም፤ ለአጨዋወትም ቅልጥፍና ያለው ቀላል መሣሪያ ስለሆነ ሊሆን ይችላል፡፡ የሙዚቃ መሣሪያው ግን በዚህ በዓል ላይ የአባቶች ጥበብ የታየባቸውን የአገራችን የሙዚቃ መሣሪያዎች ሙሉ በሙሉ እየዋጣቸው ነው፡፡ በጥምቀት በዓል ላይ አገር በቀል የሙዚቃ መሣሪያ ያልሆነው ሀርሞኒካው ብቻ አይደለም፤ የሚጫወቱት
ጨዋታም ከአገሪቱ ወግና ባህል ወጣ ያለ ነው፡፡ እርግጥ ነው እነዚህን ጨዋታዎች ራሱ ሀርሞኒካው አላመጣቸውም፤ ግን ሀርሞኒካውን ሲጠቀሙ የመዘመንና የመሰልጠን ምልክት ስለመሰላቸው ጨዋታውንም ቀይረውታል ማለት ይቻላል፡፡
አለባበሳቸውና ለጨዋታ የሚጠቀሟቸው ቃላት በኢትዮጵያ ወግና ባህል ውስጥ ያልተለመዱ ናቸው፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ ጥናትም ተሰርቷል፡፡ ‹‹ወደ ዘመናዊነት ሽግግር እና ባይተዋርነት በጃንሜዳ ሀርሞኒካ ቃል ግጥሞች ክዋኔ›› በሚል ርዕስ ሕሊና ሰብስበው ጥናት አካሂደዋል፡፡ አጥኝዋ አዲስ አበባ ውስጥ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ወጣቶች የሚጫወቱትን ጨዋታ በማስተዋል አነጋግረው ነው ጥናቱን የሰሩት፡፡
በጥናቱ ላይ የተጠቀሱት የቃል ግጥሞች እንደሚያሳዩት፤ አንዳንዶቹ ከዚህ በፊት የነበሩ የስነ ቃል ግጥሞችን ለዘመኑ በሚሆን መልኩ ቀይረዋቸዋል። ጨዋታውን የሚያካሂዱትና የሚያደምጡት አካላት ባሉበት ዘመን የሚታየውን ነባራዊ ሁኔታ እንዲገልጹ ብለው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በታዋቂ ዘፋኞች የሚታወቁ የዘፈን ግጥሞችን አንደኛውን ስንኝ በመቀየርም ይጫወታሉ፡፡ እንግዲህ በዚህ ቦታ ላይ ያሉት ወጣቶች ስለሆኑ፤ በዚያ ላይ የጥምቀት ጨዋታ ስለሆነ፤ ዋና ዓላማው መዝናናት እንጂ ማስተማር ስላልሆነ ሊሆን ይችላል በዚህ መልኩ መጫወታቸው፡፡ ለምሳሌ የአብርሃም በላይነህን ‹‹ውበቷ ውበቷ የዚች ልጅ ውበቷ›› የሚለውን ዘፈን ‹‹ውሸቷ ውሸቷ የዚች ልጅ ውሸቷ›› እያሉ ይዘፍናሉ፡፡
አንዳንዴ ለማሳቅ ተብሎም ነውር ተብለው የማይጠቀሱ ቃላት ይገቡበታል። በእርግጥ እነዚህ የወሲብ ቃላት መተኪያ የሚሆን የ‹‹አራዳ›› ቃላት የሚሏቸውን ፈጥረው ይጠቀማሉ፡፡ እነዚህ ወጣቶች ጨዋታና ዋዛ ፈዛዛ ብቻን ሳይሆን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችንም ያነሳሉ፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ የነበሩ የስነ ቃል ግጥሞችን በዚህኛው ዘመን አውድ ይቀይሯቸዋል፡፡ ለምሳሌ አሥር ሳንቲም ያለው አይባልም ድሃ አምስቷን ለዳቦ አምስቷን ለውሃ
ይባል ነበር፡፡ ይሄ ግጥም የተፈጠረው በአምስት ሳንቲም ዳቦ መብላት ይቻል በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ አሥር ሳንቲም ያለው የተሻለ ስለሆነ ድሃ አይባልም ነበር ማለት ነው፡፡ አሁን ላይ በዚህ ግጥም መዝፈን የድሮውን ለማስታወስ ካልሆነ በስተቀር የዚህን ዘመን ሰው ብሶት ሊገልጽ አይችልም፡፡ እናም በዚህ ጥናት ላይ እንዲህ ተብሎ እናገኘዋለን፡፡ ወጣቶች ራሳቸው እየፈጠሩ (ከዘፈኖች እያገጣጠሙ) አስተዳደራዊ ሥርዓቶችንና የተቋማትን የአሠራር ውጣ ውረድም ይተቻሉ፡፡ ለምሳሌ
ባናገርኩሽ ቁጥር አትበይ ባሌ ባሌ አታካብጅ ነገሩን ልክ እንደ ቀበሌ
በጥምቀት በዓል ላይ ስልክሽን ስጭኝ ወይም እንጫወት ብሏት ‹‹ባል አለኝ›› ብላ እምቢ ላለች ሴት የተዘፈነ ነው፡፡ ባል ባይኖራትም ለመግደርደር ‹‹ባል አለኝ›› ልትል ትችላለች፡፡ በትክክል ያገባች ብትሆንም ደግሞ የወጣትነት ነገር ነውና ‹‹ታዲያ ብታገቢስ ምን ችግር አለው?›› በሚል ስሜት ነው ‹‹ምን ታካብጃለሽ!›› የተባለችው፡፡
እንግዲህ በዚህ ጨዋታ ውስጥ ነው ላነሳው ጥያቄ ያገኘውን ምላሽ ከቀበሌ አሰራር ጋር ያነፃፀረው። ቀበሌ የሚለው ለግጥሙ ቤት መምታት ቢመረጥም ሁሉንም ተቋማት ይወክላል፤ ሲቀጥል ደግሞ ቀበሌ ውስጥ ጉዳይ ስለሚበዛና ቶሎና በአግባቡ የማስተናገድ ችግርም ስለሚስተዋል የባለጉዳዮች መጉላላት ይበዛል፤ ግልጹን እንናገር ከተባለ ደግሞ የቀበሌዎች አሠራር የዘመነ አይደለም፤ ለትንሽ ትልቁ ቀጠሮ ይበዛበታል፡፡ አጥኝዋ በጥምቀት ላይ ያስተዋሉት ነገር ባህላዊም ዘመናዊም እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ ወጣቶቹ ከፊልምና ከተለያዩ ነገሮች ያጠረቃቀሙትን ነው ጉራማይሌ አድርገው የሚታዩት፡፡
የሚጠቀሙት ግጥም ሳይቀር ጉራማይሌ ነው፡፡ ድሮ የነበረውን የመጨረሻ ስንኙን በመቀየር ነው የሚጫወቱት፡፡ ወጣቶቹ የሂፕሆፕና ራፕ ዘፋኞች፣ የሆሊውድ ፊልሞች ላይ ከባባድ ወንጀል የሚፈጽሙና የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን አለባበስም ይከተላሉ፡፡ የሀርሞኒካ ከዋኞች እነዚህን አካላት ስለሚያደንቋቸው ብቻ እንጂ መልዕክቱ ገብቷቸው አይደለም አለባበሳቸውን መከተላቸው፡፡ ማፈንገጣቸውም በውጫዊ ተፅዕኖ ምክንያት እንጂ በእውቀትና በይሁንታ አይደለም፡፡
በሀርሞኒካ ጨዋታ ነውር የሆኑ ነገሮችን እያነሱ መጫወትም ይታያል፡፡ ነውሩ ቃላቱ ላይ ሳይሆን ድርጊታቸው ላይ የሚታይ ነው፡፡ አጥኝዋም ይህን ‹‹ነውር›› ሲሉ ገልጸውታል፤ በነገራችን ላይ እነዚህ ነውር የሆኑ ድርጊቶችን የተጠቀሙት ለማሞካሸት ወይም ለማበረታታት ላይሆን ይችላል፡፡ እንዲያውም እየሰከሩና እያጨሱ ከሚተወንበት ፊልም የእነሱ አቀራረብ ይሻላል፡፡
ግጥሙን የሚሰማ ታዳሚ እየተዝናና ነውርነቱንም ማሰብ ይችላልና፡፡ ለምሳሌ እንዲህ ይባላል፡፡ ያሙናል ያሙናል ይመለከቱናል ጫት ቤት ይውላሉ ይሉናል አዎ ያሙናል እኛ ተሻሽለን ሽሻ ጀምረናል፡፡ በዚህ ግጥም ውስጥ ምፀት ይታያል፡፡ እርግጥ ነው ድርጊቱ ነውር መሆኑን የሀርሞኒካ ተጫዋቾችም አምነዋል፡፡ አምነውም ነው ‹‹ያሙናል›› ያሉት፡፡ ‹‹እኛ ተሻሽለን ሺሻ ጀምረናል›› ሲሉ በምፀት ሽሻ ከጫት በላይ ነውር መሆኑን እየተናገሩ ነው፡፡ የምናገኘው መልዕክት እንደ አረዳዳችን ሊለያይ ይችላል፡፡
ብዙ ጊዜ ግጥም በቀጥተኛ መልዕክት አይገለጽም፡፡ ምናልባት ግን ይሄኛው የዘፈን ግጥም ስለሆነ ያን ያህል ይራቀቁበታል ብሎ ለማሰብ አያስኬድ ይሆናል፡፡ የሆነው ሆኖ ግን ከጫት ወደ ሽሻ መሄድ ከሱስ መላቀቅ ነው ብሎ የሚያስብ አይኖርም፡፡
ከዚህ ይልቅ ነውር የሚሆኑት በዕድሜ የገፉ ሰዎችን የሚሳደቡ የግጥም ዘፈኖች አሉ፤ (ግጥሞችን እዚህ አልጠቅሳቸውም)፡፡ በአካላዊ ሰውነታቸው ማሸብሸብና እንደ ወጣት ሴቶች ማራኪ ባለመሆናቸው በእድሜ በከፉት ላይ የሚሰነዘሯቸው ቃላት ነውር ናቸው። በሌላ በኩል አዛውንቶችን በቀጥታ ከማናገር ይልቅ በ‹‹አራዳ›› ቃላት ለማናገር መሞከርም ሌላው ነውር ነው፡፡
‹‹ላሽ ይበሉ፤ ዱቅ ይበሉ›› የሚሉ ቃላት ስድብ ይሁኑ አድናቆት አዛውንቶች ሊያወቁ አይችሉም። ቃላቱን የሰሙ ሌሎች ወጣቶች ስቀው ከሚሰጡት ምላሽ ተነስተው አንድ የማይገባ ነገር ተነግሯል ብለው ይገምቱ ይሆናል፡፡ ሌላው የሀርሞኒካ ጨዋታ ደግሞ በሰፈር መወዳደስ ነው፡፡
በነገራችን ላይ በሰፈር መወዳደስ በገጠር አካባቢም ተለምዷል፡፡ የመጡበትን አካባቢ በመጥቀስ በጀግንነት ወይም በሥራ ሙያ ወይም በእንግዳ ተቀባይነት ይወዳደሳሉ፤ በወጣቶች ግን ብዙ ጊዜ የሚዘወተረው ጀግንነትን መሠረት ያደረጉ ዘፈኖች ናቸው፡፡
የአዲስ አበባውም ለዚህ የቀረበ ነው፡፡ ተወልደን ተወልደን ተወልደን አራዳ አምልጠን የለም ወይ ቦምብ ሲፈነዳ ተወልደን ተወልደን ተወልደን ጉለሌ መልሰን የለም ወይ የእርዳታውን ስንዴ ተወልደን ተወልደን ተወልደን ማርገጃ እምቢ ያልን እንደሆን ማምለጫውን እንጃ እምቢ እንጃ እምቢ እንጃ! እያሉ ይጫወታሉ፡፡ አጥኝዋ ስለሀርሞኒካ ጨዋታዎች ፋይዳ እንደጠቀሱት፤ ለከዋኞች ስነ ልቦናዊ እርካታና ማኅበራዊ ትስስርን ይፈጥራል፡፡
የውድድር መንፈስን ያጠነክራል፤ ፈጠራን ያበረታታል፡፡ ፋይዳው ለከዋኞች ብቻ ሳይሆን ለአስተዳደር አካላትም እንደሆነ ነው አጥኝዋ የሚጠቁሙት፤ ይሄውም የዘመናዊነትን ምንነት ለመተግባር የወጣቱ ማኅበራዊ ስነ ልቦና ምን እንደሚመስል ያሳያል። ለፖሊሲ አውጪዎች አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ራሱ የሀርሞኒካው ጨዋታም የቱሪዝም መስህብ ይሆናል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
የአጥኝዋ ጥቆማ ተግባር ላይ ቢውል ጥሩ ግብዓት ነው፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በየጊዜው ‹‹መጤ ባህሎች›› እያለ ጥናትና ውይይት ያካሂዳል፡፡ ዳሩ ግን አዳራሽ ውስጥ ከሚደረግ ውይይት ባለፈ እንዲህ አይነት ሁነቶችን መከታተል ላይ እምብዛም ነው፡፡ ትክክለኛው የወጣቶች ስሜት የሚታወቀው ደግሞ በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ እንጂ ከየቀበሌው ለስብሰባ ከተጠራ ወጣት አይደለም፡፡
ለጥናት የሚሰማሩ አካላትም እንዲህ አይነት ቦታ ላይ ሄደው መረጃ ቢሰበስቡና ቢያጠኑ ትክክለኛውን ክዋኔ ያገኙታል፡፡ መጠይቅ አዘጋጅቶ በማሰራጨት ትክክለኛውን ክዋኔ ማግኘት አይቻልም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ አገር በቀል የሆነውን ወግና ባህል ማስተዋወቅ የሚቻለውም በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ነው፡፡ ዓመታዊ የባህል ፌስቲቫል ከማዘጋጀት ይልቅ እንዲህ አይነቱ የሕዝብ በዓል ላይ ማስተዋወቅ የበለጠ ተደራሽ ያደርገዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መገናኛ ብዙኃንና የአስተዳደር አካላት ሊሰሩበት ይገባል፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥር 12/2014