የሐብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 668/2002 ወጥቶ በሥራ ላይ ከዋለ ከስምንት ዓመታት በላይ ተቆጠረ። ምዝገባው የተጀመረ ሰሞን ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጀምሮ ከፍተኛ መንግሥት ባለሥልጣናትና ተሿሚዎች ሐብታቸውን ስለማስመዝገባቸው አይተናል፣ ሰምተናል። ሁነቱንም ተመልክተን «ግልጽነትና ተጠያቂነት በዚህች አገር ሰፈነ፣ መጣ» ብለን ተደስተናል። ግን ዓመታት ቢነጉዱም ሥራው ግን ከምዝገባ ፈቅ ማለት አለመቻሉ ዛሬ የዘገየ ጥያቄ እንዳነሳ ምክንያት ሆኖኛል።
በአዋጅ ቁጥር 668/2002 መሠረት ሐብት የመመዝገብ ሥልጣን የተሰጠው የፌደራል የሥነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ነው። ኮሚሽኑ ምዝገባ ከጀመረበት ከህዳር ወር 2003 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ብቻ 2 ሺ 934 ተሿሚዎች፣ 628 የህዝብ ተመራጮች፣46 ሺ 639 የመንግሥት ሠራተኞች በአጠቃላይ 50 ሺ 201 ዋና ዋና የሚባሉ የባለሥልጣናትንና ተሿሚዎችን ሐብት መዝግቧል። የቅርብ ጊዜ የኮሚሽኑ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከጋምቤላና ከሶማሌ ክልሎች በስተቀር በሁሉም ክልሎች የሐብት ማስመዝገብና ማሳወቅ አዋጁን ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑንና ሐብታቸው የተመዘገበው ባለሥልጣናት፣ ተሿሚዎችና የመንግሥት ሠራተኞች ቁጥር በድምሩ 150 ሺ ደርሷል።
ሐብት ምንድነው?
የተለያዩ ድርሳናት እንደሚጠቁሙት «ሐብት» የምንለው በእንግሊዝኛው (Asset) የሚባለውን ሲሆን በግለሰብ ወይንም በቡድን በይዞታነት የሚገኝ ማንኛውም የማይንቀሳቀስና የሚንቀሳቀስ ግዙፍነት ያለው ወይም ግዙፍነት የሌለውን እንዲሁም የመሬት ይዞታንና ዕዳን ይጨምራል። በተለመደው አጠራር ሐብት/ንብረት የሚገለፀው በገንዘብ፣ በቤት፣ በመኪና እና በመሳሰሉት ሲሆን የሕግ ባለሙያዎች ንብረት የሚለውን አገላለፅ ለሁለት ከፍለው ይመለከቱታል።
ይኸውም የሚንቀሳቀስ እና የማይንቀሳቀስ /ቋሚ/ በማለት። የሚንቀሳቀሱ /ተንቀሳቃሽ/ ንብረቶች በተፈጥሯቸው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ፀባያቸውን ሳይለቁ መንቀሳቀስ የሚችሉ ናቸው። የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች እንደገና ግዙፍነት ያላቸውና የሌላቸው በመባል በሁለት ተከፍለው ይታያሉ። ግዙፍነት ያላቸው የሚባሉት የሚታዩ፣ የሚዳሰሱ እና የሚጨበጡ ንብረቶች ሲሆኑ ግዙፍነት የሌላቸው የሚባሉት በተቃራኒው ለመታየትና ለመዳሰስ የማይችሉ ለምሳሌ የአዕምሮ ንብረቶችና የመሳሰሉትን ያጠቃለለ ነው። የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በባህሪያቸው መንቀሳቀስ የማይችሉና ቢንቀሳቀሱም እንኳን የመጀመሪያ ፀባያቸውን በማጣት /በመፍረስ ወይም በመበላሸት/ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ናቸው። መሬትና ቤቶችን በምሳሌነት ማቅረብ ይቻላል።
ሐብት ለምን ይመዘገባል?
የመንግሥትን አሠራርን በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ ለማድረግ ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ ሐብትን ማሳወቅና ማስመዝገብ ነው። ሐብት ማስመዝገብ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከልና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። በአጭሩ ከገቢ በላይ ሐብት የሚያፈሩ ሹማምንትን ተጠያቂ ለማድረግ አንዱ መንገድ ሐብትን መዝግቦ መያዝና ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ነው። በዚህ መሠረት ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግስት ሠራተኛ በራሱና በቤተሰቡ ባለቤትነት ወይም ይዞታ ሥር የሚገኝ ሐብት፣ የራሱንና የቤተሰቡን የገቢ ምንጭ የማሳወቅና የማስመዝገብ ግዴታ እንዳለበት በአዋጁ ተደንግጓል።
የሐብት ማሳወቅ ሶስቱ አንኳር ጥቅሞች
ከሐብት ማሳወቅ ጥቅሞች የመጀመሪያውና ዋንኛው ሙስናን አስቀድሞ መከላከል (Preventive functions) ነው። ሁለተኛው የሙስና ወንጀልን ምርመራ ማቀላጠፍ (investigative function) ሲሆን ሶስተኛው የሕዝብ አመኔታን መፍጠርና ማጠናከር ናቸው። በነዚህ ዙሪያ ሊታዩ የሚችሉ በርካታና ዝርዝር ጥቅሞችም ሊጠቀሱ ይችላሉ።
ለምሳሌ፡- የህዝብ ተመራጮች፣ በመንግስት የተመደቡ ኃላፊዎች፣ ተሿሚዎችና ሠራተኞች ሀብት አስቀድሞ በመመዝገቡ ምክንያት ግለሰቦቹ በሚገጥማቸው የጥቅም ግጭት ወቅት ትክክለኛ ውሳኔ እንዲኖራቸው ያግዛል። ለምሳሌ ስጦታና ተመሳሳይነት ያላቸው የገንዘብ ጥቅሞች መቀበልን አስመልክቶ ዜጎች ትኩረት ለሰጧቸው ህዝባዊና መንግሥታዊ ኃላፊዎችና ሠራተኞችን ሐብትና ንብረት በግልፅ በማወቃቸው በህዝባዊና መንግስታዊ አስተዳደሩ ላይ እምነት ያዳብራሉ።
የሐብት ማሳወቅ ለምን?
ከፌደራል የሥነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የተገኙ መረጃዎች እንደሚያስረዱት የሐብትን ማስመዝገብ ሥራ፣ ለሕዝብ ከማሳወቅ ጋር ተቆራኝቶ ካልተተገበረ ለመልካም አስተዳደር እውን መሆን የሚኖረው ፋይዳ ዝቅተኛ ነው። ሐብት ተመዝግቦ መረጃው ለሕዝብ ክፍት የሚሆንበት ሁኔታ ከሌለ የሚጠበቀው ግልፅነት፤ በሚፈልገው ደረጃ ካለመፈጠሩም በላይ ተጠያቂነት የሚተገበርበትን መንገድ ያጠበዋል። በዚህም ምክንያት ሕዝብ በመረጣቸው ተመራጮች፤ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ የሚኖረውን ቅሬታና ጥርጣሬ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
የውጭ አገራት ልምዶች ሲዳሰሱ
ሐብት በመመዝገብና ማሳወቅ ጋር በተያያዘ የላቲን አሜሪካ ሀገራት የሐብት ምዝገባ ፋይሎችን ይፋ ያደርጋሉ። ለምሳሌ በሀማስ የተጨመቀ (summarized) የሀብት ማሳወቂያ ምዝገባዎች በጋዜጣ እንዲወጡ ሲደረግ፤ በኢኳዶር ደግሞ ሁሉም የሐብት ማሳወቅ ምዝገባዎች ሕዝብ እንዲያውቃቸው ወይም በሕጋዊ አካል እንዲረጋገጡ ይደረጋል። በተጨማሪም በአርጀንቲና ከሚዲያ አካላት በስተቀር ሌሎች የተመዝጋቢ ግለሰቦችን የተመዘገበ ሐብት መረጃ ለማግኘት ከፈለጉ በጽሁፍ ጥያቄው ለሚመለከተው ክፍል ቀርቦ ሊሰጥ ይችላል። በፔሩ ደግሞ ደመወዝን ጨምሮ የመንግሥት ኃላፊዎችን ሐብት ሕዝብ የማወቅ መብት እንዳለው በሕገ መንግስታቸው ተደንግጓል።
በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካም የዚህ ምዝገባ ዝርዝር ለስድስት ዓመታት ለሕዝብ ክፍት ከመሆኑም በላይ የምዝገባው ሪፖርት በድረ-ገፅ ተጭኖ ይገኛል። በአውሮፓ ሀገራትም የተመዘገበው ሐብትና ንብረት መረጃ ህዝብ እንዲያውቀው ይደረጋል። በደቡብ አፍሪካ ከተመዘገበው ዝርዝር ሐብትና ንብረት ውስጥ ከተወሰኑት በስተቀር (የደመወዝ መጠን፣ መኖሪያ አድራሻ፣ በቤተሰብ አባላት ስም ከተመዘገበ ሐብትና ንብረት) ሌላው ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል። በኤስያና ፓስፊክ የተመዘገበን ሐብትና ንብረት ለህዝብ የማሳወቅ ሁኔታም ከህንድ በስተቀር በተጠቀሱት ሁሉም ሀገራት በይፋ ለሕዝብ ክፍት ነው። በህንድ ግን አስመዝጋቢው ኃላፊ ወይም ሠራተኛ ሐብቱንና ንብረቱን የሚያሳውቀው በታሸገ ፖስታ በማቅረብ ሲሆን፤ ፖስታው መከፈት የሚችለው በፍርድ ቤቶች ነው።
ሐብቱ ተመዘገበ፤ ከዚያስ?
የፌደራል የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን በአዋጁ መሠረት የሚመለከታቸው ባለሥልጣናትና ተሿሚዎች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ሠራተኞች ሐብት መዝግቦ ለመያዝ ባለፉት ስምንት ዓመታት ብዙ መልፋቱ እውነት ነው። ግን ኮሚሽኑ አሁንም በአዋጁ መሠረት የመዘገበውን ሐብት የማጣራትና ለሕዝብ ይፋ የማድረጉ ስራ ላይ ጥርስ የሌለው አንበሳ ሆኖ ታይቷል።
በሐብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 668/2002 መሠረት የምዝገባው መረጃው ለሕዝብ በቀላሉ ተደራሽ ሊሆን በሚችል መልክ የተዘጋጀ አለመሆኑ የኮሚሽኑ ቁርጠኝነት ላይ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን እያስነሳበት ይገኛል። መረጃው በይፋ ባለመገለጹ ምክንያትም ባለሥልጣናትና ተሿሚ ዎች በገቢያቸው ልክ እየኖሩ ስለመሆኑ፣ ትክክለኛ ሐብታቸውን ስለማስመዝገባቸው ሕዝብ እንዳ ያውቅና አውቆም ተጨማሪ መረጃ እንዳይሰጥ አግዷል።
በአሁኑ ወቅት በተለይ በማህበራዊ ድረገጾች «እገሌ ከገቢው በላይ ሐብት አፍርቷል፣ በሙስና ተዘፍቋል» እየተባሉ የሚነገሩ፣ የሚሰሙ ነገሮች አሉ። እነዚህ በአሉባልታ መልክ የሚነገሩ፣ ነገርግን ሲደጋገሙ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን አመኔታ ሊጎዱ የሚችሉ መረጃዎች ማጥራት የሚቻለው የሐብት ምዝገባ መረጃውን በወቅቱ ይፋ ማድረግ ቢቻል ነበር። ይህ አለመሆኑ ከገቢያቸው በላይ ሐብት የሚያፈሩ፣ ምንጩ ያልታወቀ ሐብት ይዘው የሚገኙ ግለሰቦችና ሹማምንት እንዲበራከቱ፣ ሰርቀው በነጻነት እንዲኖሩ ትልቅ በር ከፍቷል።
ሐብት ምዝገባ እና ሙስና
በህብረተሰባችን «ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል፣ የኢህአዴግ ሹመት የዛፍ ላይ እንቅልፍ አንድ ናቸው…» የሚባሉ አባባሎች ሙስና ለመዋጋት በሚደረገው ትግል ላይ ውሃ የሚቸልሱና ስርቆትን የሚያበረታቱ ናቸው። እገሌ በዚህ መስሪያ ቤት ዕቃ ግዥ ባለሙያ (purchaser) ነው ከተባለ «አለፈለት» የሚለው ሰው ቁጥር የትየለሌ ነው። ይህ አስተሳሰብ ደግሞ ሌቦችንና የሌብነት ሥነልቦናን ያጀግናል። በአንጻሩ የጸረ ሙስና ትግሉ ትልቅ አጋዥ መሣሪያ የሆነውን የሐብት ማሳወቅና ምዝገባ ፋይዳ ያኮስሳል። የፌዴራሉ የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን በተለይ በሀገራችን ሙስና ከተንሰራፋባቸው ዘርፎች አንዱ ከግዥ ጋር የተያያዙ ናቸው ይላል።
«የሙስና ተግባር የሚፈጸመው በተወሰኑ ተቋማት ወይንም ሥራ አካባቢዎች ብቻ ነው ብሎ መደምደም ባይቻልም ከተገልጋዮች ጋር የዕለት ተዕለት ግንኙነት የሚያደርጉ ተቋማትና የሥራ አካባቢዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት በጀት የሚመደብላቸውና የመንግሥት ጥቅም (በግዥ፣ ቀረጥና ታክስ በመሰብሰብ ወዘተ) ከማስከበር ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የሚሰሩ ተቋማትና የሥራ አካባቢዎች ይበልጥ ለሙስና ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመስኩ ላይ የተጻፉ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከዚህ አንጻር ግዥ ለሙስና ተጋላጭ የሥራ ዘርፍ እንደሆነ መገመት አያዳግትም። በአንዳንድ አገር ውስጥ ለመንግሥት ግዥ የሚመደብ በጀት ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ከ15 በመቶ እስከ 30 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ይጠቁማል። ይሁን እንጂ ዘርፉ ለሙስና ተጋላጭ ከመሆኑ የተነሳና ግዥዎቹ በውል መሰረት ባለመፈጸማቸው ከ10 እስከ 25 በመቶ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ በሙስና እንደሚመዘበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። በአጠቃላይ ለፌዴራል መንግሥት ከሚመደበው ዓመታዊ በጀት ውስጥ ከ60 እስከ 70 በመቶ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ደግሞ ደግሞ እስከ 15 በመቶ የሚሆነው ግዥ ላይ እንደሚውል ጥናቶች ያሳያሉ። በዚህ ዘርፍ ላይ በቀጥታ የተሰማሩ ኃላፊዎችና የመንግሥት ሠራተኞች ሐብት መዝግቦ መያዝና ማሳወቅ ተገቢ የሚሆነው ምንጩ የማይታወቅ ሐብት እንዳያፈሩ ለመከላከል ነው። በአጭሩ በብድርና በዕርዳታ የሚገኘው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ሥራ ላይ እንዲውል ሙስናና ብልሹ አሰራር መገታት አለበት።
እንደመውጫ
የሐብት ምዝገባው የዜጎች ሐብት የማፍራት መብትና የግል ሕይወት ላይ ያነጣጠረ አይደለም። ይልቅስ ዜጎች በመንግሥታዊ ሥልጣን ወይንም ኃላፊነት ባልተገባ ሁኔታ ከገቢያቸው በላይ ሐብት የሚያፈሩበት በሌላ አነጋገር የመንግስት ሥልጣንን ለግል ሐብት ማከማቻ እንዳያውሉ ልጓም ለማበጀት ያለመ ነው። አሠራሩ በብዙ አገራት ተሞክሮ ውጤታማነቱ የተረጋገጠም ነው። ይህም ሆኖ ባለፉት ስምንት ዓመታት የመንግሥት ተሿሚዎች፣ የተመራጮችና የመንግሥት ሠራተኞች የሐብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 668/2002 ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ ለማዋል ኮሚሽኑ አልቻለም።
ሕግ አውጪው ፓርላማ እና ሕግ አስፈጻሚው አካል በተዋረድ ሕጉን ለማስፈጸም የድርሻቸውን አልተወጡም። በሕጉ መሠረት የሚመለከታቸውን ባለሥልጣናት፣ተሿሚዎችና የመንግሥት ሠራተኞች ሐብት መመዝገብ አንድ የተሳካ ሥራ ሆኖ ይህንን መረጃ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አለመቻሉ የምዝገባውን ፋይዳ ጭምር ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚጥል ጉዳይ ሆኗል። በአጠቃላይ መንግሥት፤ ተቋማቱ ተግባራቸውን በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ ላይ ተመስርተው ማከናወናቸውን፣ የመንግሥት ሐብትና ንብረት በተገቢው መንገድ ለታለመለት ዓላማ መጠቀማቸውን ሊከታተልበትና ሊቆጣጠርበት የሚችለውን አንድ መሣሪያውን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ይህ መሆኑ ደግሞ አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች ከትልልቅ አክስዮኖች፣ ንግዶች ጀርባ ስለመኖራቸው፣ እንደ ህንጻ የመሳሰሉ ግዙፍ ሐብቶችን በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም ስለማፍራታቸው፣ በአጠቃላይ ከገቢያቸው በላይ ሐብት ስለማካበታቸው በስም እየተጠቀሰ ጭምር በህብረተሰቡ ውስጥ ቅሬታዎች እንዲሰሙ፣ እንዲጎለብቱ ዕድል ሰጥቷል። ይህ ደግሞ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ሊኖር የሚገባውን መተማመን እየጎዳ ያለበት ነባራዊ ድባብ ተፈጥሯል። ሌላው የዘርፉ ባለሙያዎች ሁልጊዜም የሚመክሩት አስፈጻሚው አካል የአመራሮች (ባለሥልጣናት) የሥነምግባር ደንብ ያለመኖሩ ጉዳይ ነው።
ይህ ሥነምግባር ደንብ (መመሪያ) ቢቀረጽ ባለሥልጣናት ምን ዓይነት የሥነ ምግባር መመሪያ ማሟላት እንዳለባቸው፣ ከጥቅም ግጭት አንጻር ምን ሁኔታዎችን መስራትና አለመስራት እንዳለባቸው፣ ከመንግሥት ሥራ ውጭ ምን ዓይነት ተግባራት ላይ እንደሚሳተፉ ወይንም እንደማይሳተፉ በግልጽ ለመደንገግ ከማስቻሉም በላይ ተጠያቂነትን በየደረጃው ለማስፈን ቀና መንገድን ይፈጥር ነበር። ይህ የአስፈጻሚ አካላት የሥነምግባር ደንብ አሁንም ሊታሰብበት የሚገባ ዐብይ ጉዳይ ይመስለኛል።
የሐብት ምዝገባውን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ያልቻለበት ምክንያት በተደጋጋሚ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ አለመዘርጋት ጋር እና ሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች በኮሚሽኑ በኩል ሲሰጡ ቆይተዋል።ይሁን እንጅ ማስተባበል የማይቻለው ብቸኛና ትክክለኛ ምክንያት የቁርጠኝነት ማነስ መኖሩ ነው።
በዚህም ምክንያት አዋጁ በተሟላ መልኩ ላለመተግበሩ በጥቅሉ አስፈጻሚው አካል ብቻ ሳይሆን ሕግ አውጪው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለምን አዋጁ መተግበር ተሳነው? በሚል መጠየቅ፣ መከታተል ባለመቻሉም ከተወቃሽነት አያመልጥም። (የጸሐፊው ማስታወሻ፡- ይህን ጹሑፍ ለማጠናቀር አዋጅ ቁጥር 668/2002፣ የፌደራል የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን የተለያዩ ሕትመቶች፣ የኮሚሽኑ ቅርበት ያላቸው ምንጮች፣ የሰንደቅ ጋዜጣ የተለያዩ ሕትመቶች፣ የኢዜአ ዜና…በግብዓትነት ተጠቅሜያለሁ)
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት30/2011
በፍሬው አበበ