ከዛሬ አንድ መቶ ሃምሳ ዓመታት በፊት ነው። ዘመኑ የመሳፍንት የመኳንንቱ ክብር የሚገለጥበት ፣ ሹመኞች በማንነታቸው መንበር ኃይላቸውን የሚያሳዩበት ጊዜ ነው። ይሄም ኢትዮጵያ አገራችን በባላባቶች የኃይል ግዛት እንድትከፋፈል እድል የሰጠ ሲሆን፤ መላው ህዝብም በእነዚህ ኃያላን እግር ስር ከመንበርከክ ሌላ ምርጫ አልነበረውም። የተባለውን ያደርጋል፣ የታዘዘውን ይፈጽማል።
በዘመነ መሳፍንቱ አገዛዝ በህዝቡ ላይ የሚፈጽመው ግፍና መከራ በእጅጉ የበዛ ነበር። ህዝቡ ስለገዢዎቹ ማንነት ሲል ሀብትና ንብረቱን፣ ዕድሜና ጉልበቱን ይሰጣል። ዘረ መሳፍንቱም ዘመኑ በዋጃቸው ስልጣን ተጠቅመው ራሳቸውን ከከፍታ ያስቀምጣሉ። በርካቶችን እንዳሻቸው እየረገጡም በአገልጋይነት ያስገብራሉ።
ኃይል ስልጣናቸውን ተጠቅመው እንዳሻቸው የሚሆኑበትን ህዝብ አያደርጉት አልነበረም። ከእነሱ እኩል እንዳልተፈጠረ እንደሸቀጥ ይቸረችሩታል። ‹‹ባሪያ›› ይሉት ስያሜን ችረውም ለንዋይ ጥቅም ይለውጡታል።በወቅቱ ለነበሩት መኳንንቶች ይህ አይነቱ የባሪያ ፍንገላ የክብራቸው መገለጫ ሆኖ ዘልቋል። እንደከብቶች በሚያስቆጥሯቸው ነፍሶች ልክ ክብራቸውን አስጠብቀው ስማቸውን ሲያስከብሩ ኖረዋል።
ይህ ዘመናትን የቆጠረ እውነታ በገዢው መደብ አስገዳጅነት በአገራችን ዕድሜውን ሲያራዝም ኖሯል። የኃይልና ክብር መገለጫው ከፈጣሪ የተሰጠ እስኪመስልም ትዕዛዛቱ ሁሉ ሊፈጸሙ ግድ ነበር። ኢትዮጵያ ዘመኑ ባፈራቸው መሳፍንቶች ተከፋፍላ በየአቅጣጫው ትገዛ ዘንድ የኋላ ታሪኳ እየገፋት ነበር።
የገዢው መደቦች ህዝቡን በስልጣናቸው በሚረግጡበት፣ የመኳንንቱ ዘሮች የበታች የሚሏቸውን እንዳሻቸው በሚያስተዳድሩበት በዛን ዘመን አንድ ድንገቴ እውነታ ተከሰተ። በውትድርና ዘመኑ ታላቅ ጀብዱን በመፈጸም የሚታወቀውና በብዙ ተከታዮቹ ዘንድ የሚወደሰው የቋራው ደጃዝማች ድምጽ ከሌሎች ጎልቶ ይሰማ ያዘ።
የቋራው ሹም፣ አንደበቱ የሰላ፣ሀሳቡ የጠነከረ፣ ውሳኔው የበረታ ነው። ቴዎድሮስ ከአንገቱ አልፎ ከትከሻው በወደቀ ቁንዳላው ይለያል። እንደቁንዳላው ሁሉ በተለየ ስሜት የሚያፈልቃቸው ጽኑ ሀሳቦች ከሌሎቹ ባላባቶች ይነጥለዋል።
ባለቁንዳላው ቴዎድሮስ ተለምዷዊውን የመሳፍንት አገዛዝ በጽኑ መቃወም መጀመሩ በብዙሀኑ ዘንድ አስመርጦታል። የልብ ፍም ሆኖ የተዳፈነው ስሜትም ትኩረት አግኝቶ ጆሮ እንዲቸረው ሆኗል። ቴዎድሮስ በህዝቡ ዘንድ ከመደመጥ ተሻግሮ እልፍ ተከታዮችን እያፈራ ነው። ሁሌም በወኔና ጀግንነቱ ፣ በቆራጥ አይበገሬነቱ ውስጥ ስለ አንድነት ይሰበካል። ህዝብና አገርን በእኩል ስለማዋሀድ ያለው እሳቤ ምጡቅ ነው።
የዘመነ መሳፍንቱን ስርአት በመቃወም ለህዝቡ አንድ መሆን የወገነው ቴዎድሮስ በወቅቱ ከጀመረው ግስጋሴ የመለሰው ሀይል አልተገኘም። በገዢዎች ፍላጎት በየአቅጣጫው የተዋቀረውን የከፋፍለህ ግዛ መስመር ለማቃናት በሰሜኑ ይዞታ አንድ ሲል እርምጃውን ጀመረ።
የአንድነት ጽንሰቱን ዕውን ባደረገበት ስፍራ በርካቶች ሊቃወሙት ቃጡ። የብዙሀን ድምጽ የነበረው ቴዎድሮስ ግን በቀላሉ አልተበገረም። በትግል የገጠሙትን ሁሉ ድል እየነሳ የአሸናፊነት ወኔን ይጎናጸፍ ያዘ።
ቴዎድሮስ የገጠሙትን ሁሉ እያሸነፈ ታላቅነትን መያዝ ሲጀምር በብዘዎች ልቦና እውቅና ተቸረው። ራስ ተብሎ ከተሾመ በኋላ ለንግስናው እምብዛም አልዘገየም።በመሳፍንት መኳንንቱ አገዛዝ ተበታትና የቆየችውን አገር አንድ የማድረግ አእምሮው ብሩህ ሆኖ ቀጠለ።
አርባ ሺህ የጦር ወታደር፣ ስምንት ሺህ ባለጠመንጃ ተዋጊ ፣ አራት ሺህ ፈረሰኞችን አስከትሎ አማቹን ደጃች ውቤን ድል በነሳ ማግስት የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ሆኖ በክብር ተሾመ።አጼ ቴዎድሮስ አገሩን ሊያስተዳድር በስልጣኑ ከተቀመጠ በኋላ የዙፋን ወንበሩን ለክብር አላስቀደመም።ትናንት ሲያስበው የቆየውን ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ህልም ዕውን ለማድረግ ተነሳ።
ባለቁንዳላው ንጉስ በስርአተ ንግስናው ዘመን የመሳፍንቱን ቅጥ ያጣ አገዛዝ ፈር ለማስያዝ ሌት ተቀን ባተለ። ተንሰራፍቶ የቆየውን የባሪያ ንግድ ለማስወገድ የሚስችል አዋጅ አጽድቆም በስራ ላይ አዋለ። ለአገሩ ይበጃሉ ያላቸውን የስርአተ ንዋይና ፖለቲካውን በማዕከላዊ መንገድ የማወቀር ሂደትን ተገበረ።
ቴዎድርስ በባላባቶች ፍላጎት ተከፋፍላ የቆየች አገሩን በማቃናት እርስ በርስ ጦርነትን ሊገድብ የሚችል ብሄራዊ ውትድርናን ለመተግበር ቀዳሚው ንጉስ ሆነ። እሱ ከቁንዳላው ስር ያለው አዕምሮ ከሌሎች ሁሉ ይለያል። ሁሌም ቢሆን የእሳቤው መሰረት አንድነትን፣ አብሮነትን ማቀንቀን ብቻ ነው።
ይህን ፈጣንና አስገራሚ ለውጥ ያስተዋሉ ባላባቶች የባለቁንዳላውን ታላቅ ግስጋሴ አልወደዱትም።የየዕለት እርምጃው የእነሱን ምቾትና ክብር ተጋፍቷልና በግልጽ ተቃወሙት።በርካቶቹ መሳፍንቶች ህዝቡን መክረው አመጽ አነሱበት፤ የባለቁንዳላው ንጉስ አዕምሮ ግን ስለህዝብ መብትና ፍላጎት ሲል ያቀደውን ከማሰብ አልታቀበም።
ቴዎድሮስ ከቤተመንግስት ምቾት ይልቅ የምስኪኑን ህዝብ ፍቅር መረጠ።የዙፋን አልጋውን ለመደላደያ አልፈለገውም። ክብሩን ዝቅ አድርጎ ከገበሬዎች ዋለ። አገሩን አንድ የማድረግ ህልሙን እየፈታ ሀሳቡን ሲተገብር የኢትዮጵያን ስልጣኔ በጽኑ ተመኘ።
የአገሩ ዕድገትና ለውጥ እውን ይሆንለት ዘንድ እንቅልፍ አልነበረውም። አሁንም ከቁንዳላው ስራ ያለው ብሩህነት ባህር ተሻግሮ መጠቀ። በዘመኑ ወዳጅ አገራት ከነበሩት ሩሲያና እንግሊዝ ጋር መጻጻፉን ቀጠለ። የዓለምን ስልጣኔ ለአገሩ ለማድረስ የሚያደርገውን ጥረት አላቆመም።
ቴዎድሮስ በአስራ ሶስት አመታት የንግስና ቆይታው በውስጥና በውጭ ሀይሎች የበረታ ትግል ገጥሞታል። አይበገሬው ንጉስ ግን ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ በነበረው ጽኑ ተጋድሎ የጠላቶቹን ክንድ ለመስበር አልሰነፈም። ሁሌም ለውድ ሀገሩ መልካሙን እየተመኘ ለስልጣኔዋ ይተጋል።
ባለሹርቤው ንጉስ ከቁንዳላው ስር ያለው እሳቤ ከሌሎች ሁሉ ይለያል። በርካቶቹ ነገስታት የዙፋናቸውን ክብር ሲያስቀድሙ የእሱ ክብር ለውድ አገሩ ብቻ ሆኗል። አብዛኞቹ መሳፍንቶች ህዝቡን በግፍ ሲገዙ ቴዎድሮስ ነጻነትን እየሰበከ የፍትህ መንገድን አሳይቷል። በአገሩ ጉዳይ እልኸኛና ቁጡ ነበር። ያሰበውን ለማሳካት የጠየቀውን ለማግኘት ፈጣን ምላሽን ይፈልጋል።
ስለመድፍ አሰራር ዕውቀት ፈልጎ እንግሊዞችን ምክር በጠየቀ ጊዜ ነጮቹ እንዳሻው አልሆኑለትም። እልኸኛው ባለቁንዳላ ንጉስ እነሱን ለመለመንና ለመለማመጥ ትዕግስቱ አልነበረውም። በአገሩ የነበሩ እንግሊዛውያንን በማሰር አገታቸው። የወገኖቻቸውን መታሰር ያወቁት እንግሊዞች ወደኢትዮጵያ ለመገስግስ የበረከተ ጦራቸውን አደራጁ።
ሰላሳሁለት ሺህ ዘመናዊ ወታደር ይዞ የኢትዮጵያን ምድር የረገጠው የእንግሊዝ ጦር የንጉስ ቴዎድሮስን እጅ ለመያዝ ከመቅደላ አፋፍ ደረሰ።ባለቁንዳላው ንጉስ ዙሪያውን በጠላቶቹ መከበቡን ባየ ጊዜ ወደጦሩ በኩራት ቀረበ ። እጅ ሊሰጠን ነው ያሉት እንግሊዞች በግንባር ሊያገኙት ወደ እርሱ ተጠጉ።
አጼ ቴዎድሮስ ከጠላቶቹ ለመተያየት ጊዜ አልነበረውም። እጅ መስጠት ፣ ሽንፈት መጎንጨት የእሱ ታሪክ አይደለም። ሽጉጡን መዞ ፣ በራሱ ላይ ተኮሰ። ህይወቱ በሞቱ መለወጡን ለጠላቶቹ አሳየ።በቁንዳላው ልክ ለአገሩ ክብር የፈሰሰውን ደም ያዩት እንግሊዞች ባልተያዘው ክንድ ምትክ የጀግናውን ቁንዳላው በምርኮ ወሰዱ።
ዘመናት አልፈው ዘመናት ቢተኩ የነበርን እውነታን መቀየር አይቻልም።ይህን ድንቅ እውነታ በአይናቸው ያረጋገጡት እንግሊዛውያን በወቅቱ ከወሰዱት ቁንዳላ ስር የነበረውን ድንቅ እሳቤ አሳምረው ያውቁት ነበር።ከቁንዳላው ስር የተቀረጸው ብሩህ አዕምሮ ስለኢትዮጵያ አንድነት ሲባል የተሰራ ነው። በቁልዳላው ስር የነበረው እውነታ የአገርን አንድነት፣የህዝቦቿን ሰላምና ህልውና ያዋቀረ ነው።
የዛኔ እንግሊዞቹ የጀግናውን ሹርባ እንጂ የአንድነቱን መሰረት አልወሰዱም። ባይገባቸው እንጂ የእያንዳንዷ ቁንዳላ መጠላለፍ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ አንድነትና ዝምድና አመላካች ነበር። ከአንድ መቶ ሃምሳ ዓመታት በኋላ የወሰዱትን ምርኮ ሲመልሱ አንድ የመሆንን እውነታ ጭምር አረጋግጠዋል። እነሆ ዛሬ የጥምቀት በዓል ነው።የጀግናው ንጉስ ቁንዳላ ከተወሰደበት ምድር ተመልሶ የአንድነቱን ሀይል ከሚያረጋግጥበት ስፍራ በክብር ደርሷል።
ዛሬም በባህረ ጥምቀቱ የኢትዮጵያውያን አንድነት ዳግም ይረጋገጣል። ከቁንዳላው ስር የተነደፈው አንድ የመሆን እሳቤ ተመልሶም የቴዎድሮስ ራዕይ ይተገበራል።ትናንት ከጀግናው ቁንዳላ ስር የታተመው ህብር ቀለማቱ ደምቋል፣ ሰንሰለቱ ጠብቋል። ጥምቀቱ በፍቅር፣ በሰላም፣ በአንድነት ይገለጣል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም