«አንተ ሲሉኝ ደስታ ይወረኛል፤ አንቱ ሲሉኝ ግን ፍርሃት ይሰማኛል» ይላል። ወላጅ አባቱን በስም እንጂ መልኩን አያውቅም። የክርስትና አባቱ ናቸው እንደአባት ሆነው ያሳደጉት። በልጅነቱ እግር ኳስ መጫወት ይወዳል። በትምህርት ቤት ብዙውን ጊዜ ዓርብ ከሰዓት በኋላ የስፖርት ክፍለ ጊዜ ስለነበር ‹‹ቡሬ ቡሬ ነይ ውጪ ወደ ድሬ›› እያለ ኳሷን ሊያጫውታት ይቻኮላል። ወደ ውትድርና የዘመተው እናቱን ለማገዝ ነበር።
1974 ዓ.ም ሥልጠና ላይ ስለነበር በወር 17 ብር ለኪስ ይሰጠው ነበር። ሥልጠናውን ካጠናቀቀ በኋላ በወር ደመወዙ 85 ብር ሆነለት። በየሁለት ዓመቱም በደመወዙ ላይ አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ይጨመርለት ነበር። «ጊዜ ደጉ» እንዲሉ ከ85 ብር ላይ ለክርስትና አባቱና ለእናቱ ተቆራጭ ያደርግ ነበር። እናቱ እንደነገሩት ከሆነ ወላጅ አባቱ መንገሻ ወልደማርያም ይባላሉ። ግን ውልደታቸው አማራ ክልል መርሃቤቴ እንደሆነ ነግረውታል። ለእናቱ የመጀመሪያ ልጅ ነው። አንድ ታናሽ ወንድምና እህት ነበሩት ይሁን እንጅ ሁለቱም በሞት ተለይተው ብቸኛ አድርገውታል። ከጦር ሜዳ ሲመለስ እንደ አባት ሆነው ያሳደጉት ክርስትና አባቱም በህይወት አልነበሩም።
ውትድርና
የዛሬ ‹‹እንዲህም ይኖራል›› አምድ ባለታሪክ ጌታቸው ገብረሚካኤል ይባላል። 1953 ዓ.ም በደቡብ ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ይርጋለም ከተማ ነው የተወለደው። 1974 ዓ.ም ከ10ኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ውትድርና ገባ። አየር ወለድ ምድብ የነበረ ሲሆን፤ በልምምድ ወቅት ሰባት ጊዜ በፓራሹት ተምዘግዝጎ ወርዷል። አምስቱ በቀድሞ አጠራሯ ደብረዘይት በአሁኗ ቢሾፍቱ ከተማ የአየር ኃይል ሲሠለጥን የዘለለው ሲሆን፤ ሁለቱን ዝላዮች ደግሞ በአስመራ ነበር ያከናወናቸው። ውትድርናን ፈልጎት የገባበት ሙያ ነው። አየር ወለድ ማለት አገርን ከጠላት የሚጠብቅና ዓለም አቀፋዊ ግዴታ መወጣት ዋነኛ ተልዕኮ በመሆኑ ከልቡ ሽቶት እንደገባበት ይናገራል። ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን በብቃት በመወጣት የውጭ ወረራን መመከት፣ በሚለው እሳቤ ደስታው ወደር አልነበረውም።
ሕይወት በቀትር
ጌታቸው በ1983 ዓ.ም የውትድርና ሕይወትን ተሰናብቶ ወደ ትውልድ ቀየው ተመለሰ። ከዚያን በኋላ ለዓመታት ተሰናብቶት ከነበረው የእውቀት ገበታ መመለስ ቢፈልግም፤ አቅም አጣ፤ እጅ አጠረው። አሳድጎት የነበረው የክርስትና አባቱም ሞት ስለነጠቀው ሰውን ማስቸገር ከበደው። ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ላይ አተኮረ። እራሱን ለማሸነፍ ሲል ቀለም ቀቢነትን ሥራዬ ብሎ ተያያዘው። ገቢው ግን ከዕለት ጉርስ የሚያልፍ አልሆነም። የወጣበት የቤተሰብ መሰረትና ያልተመጣጠነ ገቢ በሚፈለገው ጊዜ ወደ ትዳር ተንደርድሮ እንዳይገባ አድርጎታል።
ስለትዳር ቢያስብም፤ እስከ ጥቅምት 1999 ዓ.ም ድረስ የውሃ አጣጩን ሊያገኝ አልቻለም። ቤት ኪራይ ጫናም ፋታ አሳጣው። ከማን ተገኘሁ፤ ምን ዓይነት ሕይወት አሳለፍኩ የሚሉ ጥያቄዎች እያጣደፉት ዕረፍት ነሱት። እርሱ ግድግዳ ቀለም እየቀባ፤ አኗኗሩ ደግሞ በዥንጉርጉር ሃሳቦች እየቀባው እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ በዚሁ ሥራ ላይ ቆየ። ቀለም ሲቀባ ብዙም ጥንቃቄ ስለማያደርግ ጤናው ላይ እክል ይፈጥርበት ጀመር። በመሆኑም ሌላ ሥራ መዘየድ ግድ ሆነበት። ቀደም ሲል መንፈሳዊ ሕይወትን የሚያስታውሱ ጥቅስ ያለባቸውን ልብሶች ይለብስ ነበር።
«ፈጣሪ ከዚያን እሳት መልሶኛልና ላመስግነው» በሚል እሳቤ ጭምር ነበር ልብሱን የሚለብሰው። ዘወትር መንፈሳዊ ጥቅስ ያለባቸውን ቲሸርቶች ለብሶ መታየቱ ለየት ያለ ሰው አድርጎታል። ከሥራው ጎን ለጎን ኳስ በአየር ላይ በማንቀርቀብ ወይንም በማንጠባጠብ ልምምድ ያደርግ ነበር። ብዙ ሰዓትም ማንቀርቀብ ጀመረ። ረጅም ኪሎ ሜትርም ኳስ መሬት ሳይነካ መጓዝ ተሳካለት።
ታዲያ አዘውትሮ ከሚከተለው አለባበስ የኳሱን ጥበብ አክሎበት ተንቀሳቃሽ ማስታወቂያ ባለሙያ ለመሆን አሰበ። በሚለብሳቸውን ቲሸርቶች የድርጅቶችን ስም እያሳተመ፤ «ኳስ ማንቀርቀብና በመሬት ላይ በማንከባለል በከተማ እየዞሩ ማስተዋወቅ» የሚለውን የፈጠራ ሃሳብ በሚገባ ወደ ተግባር ቀየረው። ቀለም ቀቢ ሆኖ ቀለም በተደጋጋሚ ይሸምትበት ከነበሩት ሱቆች ጋር ተነጋገረ። እነርሱም አላሳፈሩትም ድርጅቶቻቸውን እንዲ ያስተዋውቅ ፈቀዱለት። በዚህም በመጀመሪያ ሁለትና ሦስት ድርጅቶች ጋር ወረቀት ላይ ያልሰፈረ ግን በልብ የተፃፈ ውል ይዞ ሥራውን ጀመረ። በሂደት አሁን የሚያስተዋውቃቸው ድርጅቶች በረከቱ። በአሁኑ ወቅት 17 ድርጅቶችን ያስተዋውቃል። ሥራ ሲጀምር ይከፈለው የነበረው በግለሰቦቹ መልካም ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ነበር። አሁን ግን ድርጅቶቹ እየተበራከቱ ሲመጡ፤ የዋጋ ተመን አውጥቶላቸዋል።
ልዩ ተሰጥኦ
ጌታቸው በልዩ ተሰጥኦ የተሞላ ነው። የበርካታ እንስሳትን ድምፅ ያስመስላል። ከአሞራ፣ ከእርግብ፣ ከወፎች ጋር የሚመሳሰሉ ድምፆች ያወጣል። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በየትምህርት ቤቶቹ እየዞረ ሰንደቅ ዓላማ በሚወጣበትና በሚወርድበት ሰዓት ህፃናትን ያዝናናል። ለዚህም ክፍያ አይጠይቅም። ምክንያቱ ደግሞ ሰው ሁሉ በሚችለው አቅም ህፃናት ላይ እውቀትን መዝራትና ማዝናናት ይጠበቅበታል ይላል። በሐዋሳ ከተማው ውስጥ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሲካሄድ ቀደም ብሎ ወደ ስታዲየም ይገባና 15 ደቂቃ ኳስ እያንቀረቀበ ታዳሚውን ያዝናናል፤ በዚህ ጊዜ ከማዝናናት በተጨማሪ በሚለብሰው ልብስ ድርጅቶችንም የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራበታል።
ተንቀሳቃሹ ማስታወቂያ
የጌታቸው መኖሪያ ሰፈር አየር ማረፊያ መከሪያ ሆቴል በሚባለው አካባቢ ነው። ከዚያ ተነስቶ ከተማዋን ያካልላል። በጠዋቱ ይነሳና ድርጅቶቹን በሚያስተዋውቅበት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለሥራ መውጣቱን ሪፖርት አድርጎ ከተማዋን ለ2ሰዓት ከ30 ኳስ እያንቀረቀበና እያንከባለለ ይዞራል። አንድ ድርጅት በወር አንድ ጊዜ ያስተዋውቃል፤ ለልፋቱም በወር 200 ብር ይቀበላል። «እነዚህ ሰዎች ሞራሌን ለመጠበቅና ሊያግዙኝ ፈልገው እንጂ እኔ በምሠራው ማስታወቂያ በደንበኛ ላንበሸብሻቸው አይደለም።
ይህን የሚያደርጉት ከመልካምነታቸው የተነሳ ነው። ከተፈቀደልኝ በዚህ የህዝብ ሚዲያ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ፤ ፈጣሪ ባላቸው ላይ ይጨምርላቸው» ይላል። ጌታቸው ጋራዦች፣ ትልልቅ ሆቴሎችንና ሬስቶራንቶችን ያስተዋውቃል። በአጠቃላይ ስድስት ሬስቶራንቶችን ያስተዋውቃል። ማስታወቂያ የሚሠራላቸውም ሆቴሎች በተራ ምሳ ይጋብዙታል። በየቀኑ ምሳ እንዲበላ ቢፈቅዱለትም፤ ሳልሠራ ለምን ልብላ ሲል? እራሱን ይገድባል። ጌታቸው ከሚያከናውነው ሥራና ከሚያዘወትረው እንቅስቃሴ አኳያ ለመገጣጠሚያ ሰውነት ክፍሎች ጠጋኝ የሆኑ እንደ ሾርባና ጥብስ ያሉ ምግቦችን ያዘወትራል። ከኪሱ አውጥቶ መሸመት ባይችልም፤ የማስታወቂያ ደንበኞቹ እርሱን ለመጋበዝ ፊታቸውን አያጠቁሩም። አልኮል አይጠጣም፤ የአልኮል ምርቶችንም ለማስተዋወቅ ፈቃደኛ አይደለም። ምክንያቱ ደግሞ ከሱስ የፀዳ ትውልድን ለመቅረፅ ኃላፊነቴን መወጣት አለብኝ ብሎ ስለሚያምን ነው።
ማህበራዊ ኃላፊነት
ጌታቸው መንገድ ላይ ቆሻሻ ከተመለከተ ዝም ብሎ አያልፍም። በተለይ የሙዝ ልጣጭ በርካቶችን እያዳለጠ ለአካል ጉዳት እያዳረገ ስለሆነ ፤ ስስ ፌስታል ደግሞ በገፀ ምድርና ከርሠ ምድር ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖና ምርታማነት ለመቀነስ ትልቅ ጫና እየፈጠረ በመሆኑ ስለሚያውቅ ያሳስበዋል። እየለቀመም ከቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ይጥላል። የተቦረቦረ መንገድ ከተመለከተም ዝም ብሎ ማለፍ አይሆንለትም። በተለይ ለእንስሳት መብት የሚቆረቆር ሰው ባለመኖሩ ከባድ ነገር ተሸክመው በአባጣ ጎርበጣ መንገድ እንዲሄዱ መገደዳቸው ያሳስበዋል። በመሆኑም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የተቦረቦሩ መንገዶችን መደልደል ጀምሯል።
ጥረቱን የወደዱ ጥቂት ሰዎች ለሥራው ይረዳው ዘንድ ጓንት እና አካፋ ሰጥተውታል። እርሱም በማለዳ ከየቦታው ድንጋይ ለቃቅሞ አፈር አልብሶ የተቦረቦረውን መንገድ ይደፍናል። ይህን ሲያደርግ በርካቶች ይሳለቁበታል። «ማዘጋጃ ቤት ገባህ እንዴ?፣ ኳስ እያንከባለሉ ከመዞር ይህ ይሻልሃል» እያሉ ይሳለቁበታል። እርሱ ግን «ጆሮ ዳባ ልበስ» ብሎ ከህሊና ተወቃሽነት ለመዳን የሚቻለውን ሁሉ ይከውናል። ይህን ሁሉ ሲያደርግ አንዳችም ክፍያ አይጠይቅም። ምንም እንኳን ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ቢኖርበትም ማህበራዊ ኃላፊነቱንና አገራዊ አደራውን ለመወጣት በሚያደርገው ጥረት ክፍያ አይፈልግም።
ገጠመኞች
በአንድ የክረምት ወቅት በኃይለኛ ዶፍ ውስጥ ኳስ እያንከባለለ ሲሄድ ሰዎች ቆመው ይመለከቱት ነበር። ኃይለኛ ውሽንፍር ስለነበር በሚገባ አካባቢውን ለመቃኘት አላስቻለውም። በአጋጣሚ ኳሷ ሰዎች ከተጠለሉበት አንድ የልብስ መሸጫ ሱቅ ጥግ ሄዳ ከልብስ መስቀያ አሻንጉሊት ስር ታርፋለች። ታዲያ እርሱ ኳሷ ከዝናብ ከተጠለሉት ግለሰቦች እግር ላይ ያረፈች መስሎት እንዲያቀብሉት ይጠብቃል፤ ዝም አሉት። ደጋግሞ ቢማፀንም ሰሚ ያጣል። «እባክህ ገፋ አድርጋት፤ አንተ ተጠልለህ እኔ እኮ ዝናብ ላይ ነኝ» ቢልም መልስ አጣ። ኋላ ጠጋ ብሎ ሲመለከት ኳሷ በሰው ሳይሆን አሻንጉሊት እግር ላይ ነበረች።
ከዚያም ፈገግ ብሎ ኳሷን እያንከባለለ መሄዱን ያስታውሳል። በአንድ ወቅት አንድ ባልና ሚስትም ሲሄዱ «ይህ ሰው ያሳዝናል፤ በዝናብና ፀሐይ ውስጥ ዝም ብሎ ይንከራተታል። የሚያመው መሰልኝ» ብላ ለባሏ ስታወራ ይሰማል። ለእርሱ ግን እንጀራው ነበርና ምንም ሳይናገር ይሄዳል። ከጊዜ በኋላ እውነታውን ያወቀው ባል ጌታቸውን ፈልጎት ከሚስቱ ጋር ስለ እርሱ ያወሩትን ያጫውተውና 50 ብር ለሻይ ብሎ ሰጥቶት አበረታትቶት እንደተለየው ያስታውሳል። በአንድ ወቅትም በሐዋሳ ከተማ ዳር የሚገኘው አላሙራ ተራራ ላይ ኳስ እያንቀረቀበ ሲወጣ፤ ሦስት ልጆች ‹‹እስኪ ኳሷን እንይልህ ብለው ይዘውበት ተሰውረዋል›› የዚያን ዕለት በቁጭት ፀጉሩን እየነጨ፤ ወዲህ በልጆቹ ብልጠት እየተገረመ ወደ ቤቱ ተመልሷል። ጌታቸው እነዚህን የመሰሉ አስቂኝና አሳዛኝ ገጠመኞችን አሳልፏል፤ አሁንም አብረውት ናቸው።
ምኞት
ባለቤቱ ሥራ የላትም። በአሁኑ ወቅት በአንድ ብሎኬት አምራች ግለሰብ ግቢ ውስጥ ተጠልሎ ይኖራሉ። የሚኖርበትን ግቢ የጥበቃ ሥራ እየሠራ 420 ብር ወርሃዊ ክፍያ ያገኛል። እርሱና ባለቤቱ የሚመረተውን ብሎኬት ጠዋትና ማታ ውሃ የሚያጠጡበት ደግሞ 240 ብር ይከፈላቸዋል። በ2001 ዓ.ም ወንድ ልጅ ወልደዋል። ሰዎች ‹‹ስንት ልጅ ወልደሃል?›› ብለው ሲጠይቁት፤ በጥበብ ከሽኖ ይነግራቸዋል። «ለልጄ መሆን ሲገባኝ አያት፤ ገና እየሆንኩ ነው አባት፤ እርሱ ዕድሜው አስር፤ እኔ ሃምሳ ስምንት» እያለ አንድ ልጅ ብቻ እንዳለው ይነግራቸውና በጊዜ ወልደው በሥርዓት እንዲያሳድጉም ለጠያቂዎቹ ምክር ቢጤ ጣል ያደርጋል። ፈጣሪ ቢፈቅድ ለብቸኛ ልጁ ወንድም አሊያም እህት ይሻል።
ጉልበት እስከቻለ ድረስ በዚህ የጀመረው የማስታወቂያ ሥራ መቀጠል ይፈልጋል። በአገሪቱ ያሉ አንጋፋ የማስታወቂያ ባለሙያዎችም ይህን ጥረቴን የማሳድግበት፤ አብረን የምንሠራበት ዕድል ቢያመቻቹልኝ በማስታ ወቂያው ዓለም የተሻለ ነገር ማሳየት እችላለሁ ይላል። የሚሰድቡትንና የሚያንጓጥጡትን ስቆ ያልፋል፤የሚያደንቁትንም እጅ ይነሳል። ጌታቸው በተቻለ መጠን ደስታ ካለበት አነፍንፎ ይሄዳል፤ እርሱ እንዲከፋ ሰዎችም እንዲከፉ አይፈልግም። በአሁን ወቅት በአገሪቱ የሚያያቸው ነገሮች ያበሳጩታል። ለውጡን መቃወም ‹‹ወርቅ ሲነጠፍ ፋንድያ›› እንደመመኘት ነው ሲል ቀደም ካሉት ሥርዓት ጋር እያነፃፀረ ይናገራል። በአየር ወለድ ቤት ማዕረግ ዕድገት በጣም ውድ በመሆኑ፤ ለበርካታ ዓመታት በወታደር ቤት ቢያገለግልም ማዕረግ ሳይሰጠው ነበር ከውትድርና የተለያየው። ኑሮው አስተማማኝ ስላልሆነ አንድ ቀን ኑሮ ከብዶት ጎዳና ላይ እንዳይወድቅ ይፈራል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 30/2011
በክፍለዮሐንስ አንበርብር