ፈጣሪ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር ካሳየባቸው ታሪኮች አንዱ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ሦስት አስደናቂ ነገሮችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተግባር አሳይቶናል። ፍቅሩን፣ ትኅትናውንና ክብሩን።
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ሰው ሆኖ በመመላለስ ልክ የሌለውን ፍቅሩን ገልጦልናል። የክርስቶስ ፍቅር የሚነገር፣ የሚተረክና የሚወራ አይደለም። የሚገለጥና የሚታይ እንጂ። ለዚህም ነው ይህ ወቅት የመገለጥ ወቅት የሚባለው። ሰው ፍቅሩን መናገር ሳይሆን ማሳየት ነው ያለበት። የሚገለጥን ፍቅር የሚያግደው የለም። ፍቅር የአፍቃሪውን እንጂ የተፈቃሪውን ባህሪይ አይፈልግም። ኢየሱስ ክርስቶስ የወደደን ለመወደድ የሚያበቃ ነገር ስላለን ሳይሆን፣ እንዲሁ ነው። ፍቅሩ በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን ፍጹም ፍቅር ነው።
የክርስቶስ ፍቅር በእኛ ምላሽ ላይ የተመሠረተም አይደለም። ብንወደውም፣ ባንወደውም፤ ብናመሰግነውም፣ ባናመሰግነውም፤ ብናደንቀውም፣ ባናደንቀውም፤ ስሙን ብንጠራውም፣ ባንጠራውም፤ እርሱ እኛን ከመውደድ አይለወጥም። ሌሎቻችን ሁሉ አፍቃሪዎች ነን። ክርስቶስ ግን አፍቃሪ ሳይሆን ራሱ ፍቅር ነው። ይሄንን ፍቅር ነው ተገልጦ ያየነው። ኢትዮጵያ ዛሬ የሚገለጥ ፍቅር ያስፈልጋታል። ኢትዮጵያ የምትፈልገው ፍቅር በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ አይደለም። ኢትዮጵያ የምትፈልገው ጊዜና ሁኔታ የማይቀይሩት ዓይነት ፍቅር ነው። አገራችንን በእውነት የምንወድ ከሆነ ምንም ዓይነት ምላሽ ሊለውጠን አይገባም። ስማችን በክብር ቢነሣም ባይነሣም፤ ሥራችንን ሰው ቢያውቀውም ባያውቀውም፤ ሰዎች ቢያደንቁንም ባያደንቁንም፤ ብንመሰገንም ባንመሰገንም፤ የሚያስደስተን ነገር ቢኖርም ባይኖርም፤ ለአገራችን ያለን ፍቅር ሊለወጥ አይገባውም።
ሌላው ክርስቶስ ያስተማረን ትኅትና ነው፡፡ እኛን ለማዳን የወረደው ከሰማየ ሰማያት ነው፤ ማንም አይቶትና ደርሶበት ከማያውቀው መንበሩ። በዕለተ ጥምቀቱ የተገኘው ግን በውኆች መካከል ነው። ፍጡሩ ዮሐንስ እንዲያጠምቀው ፈቅዶ፣ በሰዎች መካከል ለመሆን ወድዶ ነው የታየው። ያሳየን ከሃሊነቱን ሳይሆን ትኅትናውን ነው። የገለጠልን ከፍታውን ሳይሆን ተዋርዶውን ነው። ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላእክት ትቶ ዓሣዎች በሚገኙበት ውኃ ውስጥ ተገኘ። እንዲህ ያለ ትኅትና እንደ ምን ያለ ትኅትና ነው። ለቀደሙ ሰዎች ከሃሊነቱን ገልጦ አስደንግጧቸው ነበር። ለእኛ ግን ትኅትናውን ገልጦ አስደነቀን። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ዓለምን ሲፈጥር ከሃሊነቱን፣ ዓለምን ሲያድን ደግሞ ትኅትናውን ገለጠ። እኛም ችሎታችንን ብቻ ሳይሆን ትኅናችንንም መግለጥ እንዳለብን አስተማረን።
ትኅትናን የድክመት ምልክት አድርገው የሚያስቡ፣ ትዕግሥትን እንደ ፍራቻ የሚቆጥሩ ሰዎች እንደተሳሳቱ ምስክራችን ክርስቶስ ነው። የኃያልነት ምልክቱ ከዕብሪት ይልቅ ትኅትና፣ ከበቀል ይልቅ ይቅርታ እንደሆነ ክርስቶስ አስተምሮናል። ጥላቻን በፍቅር መለወጥ፣ በቀልን በይቅርታ ማክሸፍ፣ ግጭትን በዕርቅ መዝጋት ተገቢ ስለመሆኑ በጥምቀቱ በማመናችን ያወቅነው ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን “ኢትዮጵያ” አድርጎ ያቆያት ዕሴት ይሄው ነው።
አገራችንን የምናከብራት የማይደረገውን በማድረግ ነው። በሕግና በኑሮ ተለምዷችን ውስጥ ሊደረጉ የሚችሉትን የዘወትር ነገሮችን ማድረግ፣ ለአገር ያለንን ክብር አይገልጥም። ክብር ዝቅ ማለትን ይፈልጋል። ማክበር በተጠየቃዊ ኅሊና የማይደረገውን ማድረግን ይጠይቃል። አዳም አጥፍቷል። በጥፋቱ ሞት ተፈርዶበታል። ይሄንን የአዳም መከራ ለማስተሥረይ አያሌ ላሞችና በጎች መሥዋዕት ሆነዋል። አያሌ አባቶች መሥዋዕት አቅርበዋል።
ግን አልሆነም። ተለምዷዊውና በሕግ የተፈቀደው የሚጓዘው እዚህ ድረስ ነበር። ክርስቶስ ግን የማይደረገውን አድርጎ፣ እርሱ በመዋረድ አዳምን አክብሮ አዳነው።
ክርስቶስ እኛን ለማዳን ከመወለዱ በፊት በኃጢአት የተሸፈነውን አዳም የኃጢአት ልብሱን ከላዩ ላይ ሊገፍለት የሞከረ አልነበረም። ክርስቶስ ያለ ቅድመ ሁኔታ የአዳምን የኃጢአት ቀንበር ተሸክሞ ከመከራ አዳነው፤ የሚነትበውን ልብሱን ጥሎ በማይነትብ ዘላለማዊ ልብስ ተካለት። ኢትዮጵያ ዛሬ መከራዋን ወስዶ የሚሸከምላት፣ ስቃይዋን ተቀብሎ የሚሰቃይላት፣ እሱ አቀርቅሮ ቀና የሚያደርጋት ሰው ትፈልጋለች። እኛ መከራዋን ሳንቀበል ለኢትዮጵያችን ምቾት፣ ዝቅታውን ሳናይ ለአገራችን ከፍታ፣ ጨለማውን ሳንጎበኝ ለልጅ ልጆቻችን ብርሃን እንደማይመጣ ማወቅ አለብን። ይሄን ስናደርግ እንዳሰብነው ሽልማትና ውዳሴ፣ አንቱታና ክብር ላናገኝ እንችላለን። ያ ማለት ግን ሥራችን ተደብቆ ይቀራል ማለት አይደለም። በመልካም ተግባራችን ዛሬ ባንወደስም ነገ መነሳቱ አይቀርም፤ እኛ ባንናገረውም ሌሎች ይናገሩለታል።
ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ሊጠመቅ ሲመጣ እየተናገረ አልመጣም። በአካባቢው ያሉ ሰዎች ማን ከእነርሱ ጋር ሊጠመቅ እንደቆመ አላወቁም። እርሱ ዝም ሲል ሦስት ምስክሮች ተሰምተዋል። ዮሐንስ መሰከረ፤ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ መሰከረ፤ አብ በደመና ተናግሮ መሰከረ። ‹እኔ› ከሚለው ሥነ ልቡናዊ በሽታ የሚያወጣን ትኅትና ነው። ከድል ሽሚያና ከባለውለታነት ትዕቢት የሚያወጣን ትኅትና ነው።
ኑ ለኢትዮጵያ ስንል ዝቅ እንበል፤ ኑ ለድኻው ወገናችን ስንል ዝቅ እንበል፤ ኑ ለተበደለው ሕዝብ ስንል ዝቅ እንበል፤ ኑ በድህነት ውስጥ ላለው ሕዝብ ስንል ዝቅ እንበል። ሥራችንን አገር በማዳናችን እንጂ በጠላታችን ትዕቢት አንለካው። ከከፍታችን እንውረድ፤ የሚቻለውን በቀለኝነት ትተን የማይቻለውን ይቅርታ እንዘምር፤ ስሜታችንን እናርቅ፤ በደልን ይቅር እንበል፤ ጉዳታችንን እንሸከም፤ አመላችንን እንግራ፤ አገር ለማክበር ስንል ክብራችንን እንሠዋ። ፍቅራችንን፣ ትኅትናችንንና ክብራችንን ለአገራችንና ለወገናችን እናሳይ። ለኢትዮጵያ ስንል የማይታየውን እናሳይ፤ የማይደረገውን እናድርግ። በተለመደው መንገድ ብቻ ሄደን አገራችንን እንደማናድናት እንገንዘብ።
ሌላው በዓለ ጥምቀቱን የምናከብርበት መንገድ አገራችን በዓለም ላይ ለየት ብላ እንድትታይ የሚያስችላት መሆኑን ልብ እንበል። ጥምቀት ሲመጣ ኢትዮጵያ ታሸበርቃለች። በዓሉን ለመታደም ከመላው ዓለም የሚጎርፉ አማኞችና ጎብኝዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። በቅርቡ ወደ አገራችን የገቡት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አንድም ናፍቀው የመጡት በክብረ በዓላት ላይ የሚታየውን ማኅበራዊ መሰባሰብ ነው። ኢትዮጵያ የብዙ ባህሎች፣ ሃይማኖታዊ ትውፊቶችና ታሪካዊ ቅርሶች አገር ናት። ከሃይማኖታዊ ፋይዳነቱ ባለፈ ጥምቀት አንዱ የምንኮራበት የማይዳሰስ ቅርሳችን ነው። ይሄንን ከግምት ወስደን የቱሪዝም ሥራዎችን ጎን ለጎን ብንሠራ ክብረ በዓሉ የአገራችንን መስሕብነት የሚጨምርና ኢኮኖሚያዊ አበርክቶው እጅግ የጎላ እንደሚሆን አያጠራጥርም።
በድጋሚ፣ መልካም የከተራና የጥምቀት በዓል እንዲሆን እመኛለሁ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
አዲስ ዘመን ጥር 11 ቀን 2014 ዓ.ም