ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ‹‹ለብሔራዊ መግባባትና አገራዊ አንድነት ለማጠናከር›› በሚል በእስር ላይ የነበሩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ላይ የተመሰረተው ክስ በመቋረጡ እንዲፈቱ መደረጉ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ በተለያዩ አቅጣጫዎች አሉታዊ እና አዎንታዊ አስተያየቶች በመሰጠት ላይ ናቸው:: ይህ እንዳለ ሆኖ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም አሸባሪው ሕወሓት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በከፈተው ጦርነት በርካታ አገራት ከኢትዮጵያ ተፃራሪ ሆነው መቆየታቸው ይታወቃል::
ለአብነትም አሜሪካ ኢትዮጵያን የአፍሪካ አገራት ወደ አሜሪካ ከቀረጥና ከታክስ ነፃ ምርታቸውን እንዲያስገቡ ከሚፈቅደው የአፍሪካ የዕድገትና የዕድል ድንጋጌ-አጎዋ ተጠቃሚነት እንድትታገድ የሚያደርግ ውሳኔን ፕሬዚዳንት ባይደን ፈርመው ተግባራዊ ሆኗል።
በእርግጥ አሜሪካ ይህንና ሌሎች ጫናዎችን ስታደርግ የነበረው ከግብጽ የምታገኘውን ጥቅም ለማስጠበቅ በማሰብ ነው:: ይህም በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ጫና ቀይ መስመር ያለፈ ስለመሆኑ ምሁራን ይናገራሉ::
ለማዕቀቡ እንደመነሻ ያደረገችው ሕግ ማስከበር ዘመቻውን ይሁን እንጂ፤ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በነበረው ድርድር የጀመረችው ጣልቃ ገብነት ባለመሳካቱ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ::
ማሳያዎች
አሜሪካ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ 17 ጊዜ ዜጎቹ አዲስ አበባ ለቀው እንዲወጡ መግለጫና ማስፈራሪያ መሰል መረጃዎችን ማውጣቷ የሚታወስ ነው:: ኤምባሲው በተደጋጋሚ የፀጥታ ስጋት መልዕክት በማውጣት ዜጎቻቸው በአስቸኳይ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ሲወተውት ነበር:: መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ተቋማትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ግፊት ሲያደርግ እንደነበር ይታወሳል::
አንዳንድ ምሁራንና የመገናኘ ብዙኃን ባለሙያዎች ይህ ለምን አስፈለገ? ለሚለው የራሳቸውን ትንታኔ ይሰጣሉ:: ቀዳሚው ዓላማ የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት ዓመታዊ የመሪዎች ስብሰባ በፀጥታ ስጋት ምክንያት በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ ማድረግ እንደነበር የሪፖርተር ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅና የፖለቲካ ጉዳዮች ጸሐፊው አቶ ዮሐንስ ይናገራሉ::
እንደ ጋዜጠኛው ሃሳብ፤ የዘንድሮው የመሪዎቹ ስብሰባ ከአዲስ አበባ ውጪ እንዲካሄድ በማድረግ በሂደት ደግሞ የእዚህን ሴራ ቀጣይና ዋና ክፍል መለኮስ ነበር። ዋናው ሴራ የአፍሪካ ህብረት ዋና ጽሕፈት ቤት ከኢትዮጵያ (አዲስ አበባ) ወደ ኬንያ እንዲዛወር ማድረግ ነው።
ኬንያ የሴራው አካል መሆኗ በግልጽ ባይታወቅም ጥያቄውን ለማንሳት ግን ኬንያ አስፈላጊ አልነበረችም ባይ ናቸው። ጥያቄውን በማንሳት ይህንን የአሜሪካ ፍላጎት እንዲያስፈጽሙ የታጩ አፍሪካዊ አገራት አሉ::
ከነዚህም መካከል አንዷ ተጠርጣሪ ዛምቢያ ነች። ዛምቢያ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ጥቂት ዜጎቿ እንዲወጡ ያደረገች የአፍሪካ አገር ነች። ጥያቄውን ለማንሳት ግን በመጀመሪያ የዘንድሮ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ በፀጥታ ምክንያት ከአዲስ አበባ ውጪ መካሄድ አለበት። ይህንን ማድረግ ያስፈለገው ዋናው ጥያቄ ዱብ ዕዳ እንዳይሆንና ድንጋጤ እንዳይፈጥር ነው የሚል ትንታኔ ይሰጣሉ።
ቀጣዩ ጥያቄ በኢትዮጵያ መረጋጋት እስኪሰፍን የአፍሪካ ህብረት ዋና ጽሕፈት ቤት በጊዜያዊነት ወደ ሌላ አገር ይዛወር የሚል ሆኖ እንዲቀርብ ታቅዶ ነበር የሚለው የፖለቲካ ጉዳዮች ጸሐፊው ጋዜጠኛ ዮሐንስ፤ ይህንን ለማስፈጸም ብዙ ጥረቶችና እንቅስቃሴዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ ሳለ አንድ ያልታሰበ ክስተት የአሜሪካ ፍላጎት ላይ ውሃ ቸለሰበት ይላል። ይህ ክስተት የሕወሓት ባልታሰበ ፍጥነት ወደ ትግራይ መመለስ ነበር። ነገር ግን የተጀመረውን ጥረት ሙሉ
በሙሉ እንዲቆም አላደረገውም። ቢያንስ የዘንድሮ ስብሰባ ከአዲስ አበባ ውጪ እንዲካሄድ የተጣለውን ግብ ለማሳካት ጥረቶች ውስጥ ውስጡን ቀጥለው ነበር። በዚህ ወቅት ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት በተለይም የውጭ ጉዳይ ኃላፊዎች ነገሩን ተረድተው ደርሰውበታል።
በመሆኑም ሴራውን የማምከን እንቅስቃሴ ተጀመረ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ገጻቸው ያስተላለፉት መልዕከትም ይህ ድራማ መጨናገፉን ምክንያት ያደረገ ነው::
አሜሪካ ይህንን ለማድረግ የፈለገችው ኢትዮጵያን ገሸሽ አድርጋ የአፍሪካ ቀንድ የውጭ ፖሊሲዋን በኬንያ በኩል ለመፈጸም ስለወሰነች ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ በአፍሪካ አገራት ዘንድ ያላትን ተደማጭነትንም ለማፈራረስ ያለመ ነበር።
ይህንን ማለት ባዶ ውዳሴ አይደለም። ኢትዮጵያ በአፍሪካውያን ዘንድ ያላትን ተደማጭነት ከእኛ በላይ የሚያውቁት ሌሎች ናቸው። የ ‹‹No More›› ዘመቻ አህጉሪቱን ያንቀሳቀሰው በአጋጣሚ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ስለተነሳ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል ይላል -ጋዜጠኛ ዮሐንስ።
የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ይዘዋወር የሚለው ጥያቄ ቢነሳ እንደቀድሞው ጥያቄውን ተከራክሮ ማሸነፍ ቀላል አይሆንም። ምክንያቱም ፉክክሩ እንደቀድሞው በኢትዮጵያና በሊቢያ መካከል አይደለም።
የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ለህብረቱ መመስረት የተጫወቱትን ሚና በምክንያትነት በማቅረብ የህብረቱ መቀመጫ ከአዲስ አበባ ውጪ አይታሰብም ብሎ መከራከርም እንደቀድሞው ውጤት አያስገኝም። ምክንያቱም የህብረቱ መቀመጫ እንዲዛወር የሚጠየቀው ለህብረቱ መመስረት ከንጉሱ ዕኩል (ምን አልባትም በበለጠ ሁኔታ) ሚና ወደ ተጫወቱት ጆሞ ኬንያታ አገር ናይሮቢ ነው። አሜሪካ የሰነዘረችው ይህ ከባድ ጥቃት በአጋጣሚ መክኗል:: ነገር ግን ዳግም እንዳይሞከር ተደርጎ ተመልሷል ማለት አይደለም።
በመሆኑም የዘንድሮ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ ሲካሄድ አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን ቆመው ላሳዩት ወዳጅነት የሚመሰገኑበት እና የኢትዮጵያ አፍሪካዊነት ጎልቶ የሚታይበት ይሁን ሲል ሃሳቡን ያጠቃልላል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከዚህ ቀደም፣ የኢትዮጵያንና የአፍሪካ ቀንድን ጉዳይ በተመለከተ ከጎረቤት አገር ከኬንያ ፕሬዚዳንት ጋር በተደጋጋሚ መወያየታቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትም በዚህ ሁኔታ ደስተኛ አለመሆናቸውን ሲገልጹ መቆየታቸውም የሚታወቅ ነው።
ከጫና የመውጣት ጅምር
ዐቢይ አሕመድ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ምክክር በኢትዮጵያ እና በቀጣናው ላይ ሃሳብ ስለመለዋወጣቸው መረጃዎች በስፋት ተለቀዋል:: ለእዚህ ማረጋገጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት እና ዋይት ሐውስ ባወጡት መግለጫ ላይ ተገልጾ ነበር::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉት፤ ከፕሬዚዳንት ባይደን ጋር በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ወቅታዊ ጉዳዮች፣ በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ግልጽ ውይይት አድርገው ነበር::
ሁለቱ መሪዎች ኢትዮጵያና አሜሪካ በጋራ መከባበር ላይ መሠረት በማድረግ ገንቢ ግንኙነት በማድረግ ትብብራቸውን ለማጠናከር ስለመስማማታቸው ያትታትል:: ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ዋይት ሐውስ የወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው፤ በሁለቱ መሪዎች መካከል በአገሪቱ እየተካሄደ ስላለው ጦርነት እንዲሁም ሠላምና እርቅ ለማውረድ ስላሉ ዕድሎች የስልክ ውይይት ማድጋቸውን መጠቆማቸው ይታወሳል::
ፕሬዚዳንት ባይደን በቅርቡ ስለተፈቱት የፖለቲካ አስረኞች በተመለከተ ያላቸውን በጎ አስተያየት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መግለፃቸውና መሪዎቹ በድርድር ላይ የተመሠረተ ተኩስ አቁም ማድረግን በተመለከተ ስለመነጋራቸው ተወስቷል::
በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አኒከን ሁትፊልድት ጋር የስልክ ውይይት ባካሄዱበት ወቅት በኢትዮጵያ የተከናወኑ አዎንታዊ ለውጦችን በተመለከተ ለሚኒስትሯ ገልፀዋል።
ኖርዌይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እ.ኤአ የጃንዋሪ ወር ፕሬዚዳንት ሆና የተመረጠች ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ለወሰዳቸው አበረታች አዎንታዊ ርምጃዎች ያላቸውን አድናቆት ገልጸው፤ አገራቸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በሚኖራት ቆይታ ኢትዮጵያ በአጀንዳ እንድትያዝ የማድረግ ፍላጎት የሌላቸው መሆኑንም ማረጋገጣቸው ጫና የማድረግ ፍላጎታቸው መለሳለሱን ያሳያል::
1965 ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን የጀመረችው ካናዳም ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጀስቲን ትሩዶ ሰሞኑን ከዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይትም ሁለቱ አገራት ወዳጅነታቸውን የበለጠ ለማሻሻል መወሰናቸውንና ኢትዮጵያ ለሠላም ረጅም ርቀት ሄዳ እጇን መዘርጋቷ የሚያስመሰግናት ስለመሆኑም ተናግረዋል::
ሰሞኑን ከአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት ምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ አማን ሁን ረዳም በሰጡት ሃሳብ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭቱን አስቁሞ ወደ መልሶ ልማት ሲገባ አሸባሪ ሕወሓት ጸብ አጫሪነቱን ያቆማል ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው:: ሆኖም አሁን ኳሷ በሕወሓት እጅ ላይ ናት::
መንግሥት ከልክ በላይ ርቀት ሄዶ ለሠላም እጁን ዘርግቷል:: መንግሥት አቦ ስብሃትን ጨምሮ እስረኞችን ሲፈታ ተቃውሞ እንደሚገጠመው የሚገመት ቢሆንም አሁን መንግሥት ኳሷን በሕወሓት ሜዳ ስለመሆኑ በመጠቆም ከአሁን በኋላ ምዕራባውያን ፊታቸውን ማዞራቸው አይቀጥልም ብለዋል::
ሲጠቃለል…
አሜሪካ ከግብፅ የምታገኘውን ጥቅም ለማስጠበቅ የህዳሴን ግድብ እንደ ቀብድ ለመጠቀም መሞከሯ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ሁለተኛው የዓድዋ ድል ነው:: በተጨማሪ ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን የድህነት አረንቋ መውጫ መሰላል አድርጋ ማሰብ አለባት::
የውጭ አገራትን ጫና መቋቋም የሚቻለው ከድህነት በመውጣት መሆኑንና የኢትዮጵያ አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በማስጠበቅ ነው:: ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሠላም በማድረግ ያበረከተችውን አስተዋጽዖ በሚገባ ማጉላትና ኢትዮጵያ በማናቸውም መልኩ ስትራቴጂክ አገር መሆኗን ማሳየት ያስፈልጋል::
በተለይ ሶማሊያ የተረጋጋች አገር ሆና እንደ አገር እንድትቀጥል ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር በጥምረት የሠራችው ሥራ ሠላምን አጥብቃ የምትሻ አገር መሆኗን ማሳያ ነው::
ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያንም ብሎም ለዓለም የነጻነት ተምሳሌት የሆነች አገር በመሆኗም የጥቁር ሕዝቦችን ከጎኗ ለማሳለፍ አሁንም ብርቱ ሥራ ይጠይቃታል የሚለው የበርካቶች ሃሳብ ነው::
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ጥር 10/2014