በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ጦርነት ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳቶችን ደርሰዋል። በተለይም ደግሞ የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ክፉኛ ታሟል። የኑሮ ግሽበቱም ለዚህ አንዱ ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎችን ከማቀዛቀዝና በርካቶችም ከሥራ ገበታቸው እንዲፈናቀሉና በሌሎች ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደረገ ክስተት ሆኗል። በዚህ ጦርነት ለዘመናት የተከማቹ በርካታ ንብረቶች ወደ ዶግ አመድ የተቀየሩ ሲሆን፤ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራውን በቃላት ለመግለፅ አስቸጋሪ የሆነበት ደረጃ ተደርሷል።
በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በተለይ ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያለው ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ከመገታትና ከመቆምም በላይ ሊያንሰራራ የሚችልባቸውን መሰረተ ልማቶች ጭምር በብዛት ማጣቱ ይታወቃል። ለዘመናት በልፋት የተገነቡት ከተሞች፤ የጤና ተቋማትን፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት፤ የግለሰብ ቤቶች፣ ሆስፒታሎችን አካቶ እጅግ ከፍተኛ የሆኑ እና ትልቅ ሃብት የወሰዱ ዘማናትን ያስቆጠሩ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል።
ምንም እንኳ አሸባሪው ሕወሓት የፈጠራቸው ጫናዎች በርካታ ቢሆኑም መንግስት ሲወስዳቸው የነበሩ እርምጃዎች የሚበረታቱ ስለመሆናቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለአብነት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን በማቃለል ረገድ፣ ከፍተኛ የአገሪቱን የውጭ ዕዳ ክፍያ ጫናን ለማቃለል የመክፈያ ጊዜን ከአበዳሪዎች ጋር ተደራድሮ ከማራዘም እና ዲያስፖራውን በማስተባበር በአገሪቷ ልማት ውስጥ አሻራ እንዲኖራቸው ከማድረግ አንጻር፣ በቆላማው የአገሪቱ ክፍል በመስኖ የሚለሙ የግብርና ምርቶች ማምረት ከማስቻል አኳያ፤ የወጪ ንግድ እንዲያድግ በማድረግ የንግድ ሚዛን ጉድለቱን ለማጥበብ የተሄደባቸው ርቀቶች፣ የብር ኖቶችን በአዲስ በመቀየር እና የአሥር ዓመት መሪ ዕቅዶችን በማውጣት አገሪቱ የመለወጥ ርዕይ እንዲኖራት የተሄደባቸው ርቀቶች ከሚጠቀሱት አዎንታዊ ጥቂቶቹ ስለመሆናቸው ባለሙያዎች ያብራራሉ።
ይህ ሁሉ ጥረት የሚደነቅ ቢሆንም በጦርነቱ ሳቢያ ኢትዮጵያ ውጥንቅጦች ውስጥ ገብታለች። ከበርካታ ሀገራት ጋርም ዲፕሎማሲያዊ መሻከሮችና እሰጣገባዎች ውስጥ የነከራት ሲሆን ከአንዳንዶች ጋር ቀደም ሲሉ የነበሩ የንግድ ግንኙነቶች እስከመቋረጥ ደርሰዋል። ለአብትም ‹‹አጎኣ›› ማንሳት ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ በርካታ የአውሮፓ አገራት እርምጃ ለመውሰድ ሲንደረደሩ አንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
አቶ አማንይኹን ረዳ የንግድ፤ ምጣኔ ሃብት እና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ የማማከር አገልግሎት ይሰጣሉ። በኢኮኖሚው ዘርፍም ለመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ሙያዊ ትንታኔዎችንና ሃሳቦችን ይሰጣሉ፤ ይሳተፋሉ። በዛሬው ዕትማችን የኢትዮጵያ ወቅታዊ የኢኮኖሚ ፈተናዎች፣ መልሶ ግንባታና ማቋቋም፣ የአገሪቱ ቀጣይ ዕድሎችና መደረግ ስለሚገባቸው ጥረቶች መፍትሄዎችን ማዕከል በማድረግ ሙያዊ ትንታኔ እንዲሰጡን እንግዳ አድርገናቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- በጦርነት የተጎዳን ኢኮኖሚ ጫና እንዴት መታደግ ይቻላል?
አቶ አማን ይኹን፡- የመጀመሪያው ሥራ ጦርነትን ባለበት ቦታ ማስቆም ነው። ጦርነት በአንድ ቀን ብቻ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያስወጣል። እንደ ጦርነት በጣም አውዳሚ እና የከፋ ነገር የለም። በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያን የመሰሉ እና በልማት ቀደውሞውኑ ወደኋላ የቀሩ ሃገራት ለዘመናት የተከማቹ ችግሮችን ተሸክመዋል። ከፍተኛ የካፒታል እና እውቀት እጥረት አለባቸው። ያላቸውን መሰረተ ልማት በብድር እና እርዳታ የሚገነቡ ናቸው። ይህ መልሶ መገንባቱ ፈታኝ ነው የሚሆነው። ስለዚህ የውድመት ሁኔታው ለመታደግ ባለበት ጦርነት ማስቆም ይገባል።
ጦርነትን በፍጥነት ማስቆም ከዚህ በላይ ውድመት እንዳይመጣ ያደርጋል። የሚቀጥል ከሆነ በየቀኑ በመቶ ሚሊዮኖች ወጪ ልናደርግ ልንገደድ ነው። ከፍተኛ መሰረተ ልማት ይወድማል። በአንድ ቀን ጦርነት የሚወድመው በርካታ መሰረተ ልማትን ለመገንባት ያግዛል። በመሆኑም ጦርነቱን በማስቆም የደረሰውን ውድመት በባለሙያ ትክክለኛ መረጃ ማወቅና ማስጠናት ይገባል። መንግስትም የወደመው ውድመትና የደረሰው አደጋ መታወቅ አለበት። ይህንን ወደነበረበት መመለስ ሳይሆን ከነበረበት በተሻለ ደረጃ መገንባት አለበት። ወቅቱ እና ዘመኑ የፈጠራቸው ቴክኖሎጂዎች አሉ። የአገሪቱን ቀጣይ ኢኮኖሚ ተስፋ ከግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ ነው። ነገሮችን ቀደሞ ከነበሩበት ሰፋ አድርጎ እና አሻሽሎ መስራት ይገባል። ለዚህ ሁሉ ግን የወደመው በሚገባ ማወቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡-ይህን ለመገንባት ሃብት ከየት ይመጣል?
አቶ አማን ይኹን፡- መንግስት ተጨማሪ በጀት በማፅደቅ፣ እርዳታ ድርጅቶችን በማስተባበር፣ ብድር በማፈላለግ፣ የአገር ውስጥ የገንዘብ ምንጮችን በመጠቀም፣ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚን በማነቃነቅ፣ ባንኮች፣ ኢንሹራንሶች፣ ሆቴሎች፣ ህዝብ የሚሳተፍበትን ቴሌቶኖችን በማዘጋጀት፣ አስመጪዎችን፣ ላኪዎችና እና ባለሃብቶችን በማሳተፍ ገቢ ማግኘት ይገባል። ከአገር ውጭ ያሉ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋሮችን በማሳተፍ ሃብት ማንቀሳቀስ ይቻላል። የሁለትዮሽ እና የብዙሃን ግንኙነት በመጠቀምም ከአገራት እና ለጋሽ ተቋማት ሃብት ማግኘት ይቻላል። በውጭ አገር የሚኖረውን ዳያስፖራም በዚህ ላይ ሚና ሊኖረው ይችላል። አደጋ በደረሰባቸው አማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልል ስለሆኑ ሌሎች ክልሎች ድጋፍ ሊያደርጉ ይችላሉ።
ሂደቱ መሰረተ ልማትን መገንባት ብቻ ሳይሆን የተደፈሩ እናቶችና ህጻናትን መልሶ ማቋቋምና ማህበረሰብ ድጋፍ በማድረግ ማረጋጋት ይገባል። የሥነ ልቦና ጥገና አብሮ መሠራት አለበት። ማህረሰባዊ ድጋፍ እስከታች ወርዶ መሰራት አለበት። ሃብት ንብረታቸው የወደመባቸው በርካታ ዜጎችና አርሶ አደሮች አሉ። እነዚህን መልሶ ማቋቋም በሚለው ውስጥ ታሳቢ መደረግ አለበት። እነዚህ በመልሶ ማልማት ውስጥ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው። ወለድ የሌለው ብድር በማመቻቻት እና ማቋቋሚያ ገንዘብ ማመቻቻት ይገባል። የኢትዮጵያ ሃብቷ ዜጎቿ ናቸው። የሕወሓት ክፋት ደግሞ ዜጎች እንዲደኸዩ የኢኮኖሚ ሃብት ምንጭ የሆነውን ሁሉ አውድሟል። ለዚህም ማሳያው እንስሳትን ሲገድል እና የደረሰ ሰብል ሲያወድምና ሲያቃጥል ነበር። ክፋት የተሞላው አካሄድ ሲከተል ነበር። መንግስት ይህን በሚገባ በመረዳት ዜጎቹን መልሶ ማቋቋም አለበት።
ዜጎች በድህነት ውስጥ እንዲኖሩ ፍላጎት አለው። በመልሶ ማልማትና በመገንባት ረገድ ማዕከል መሆን ያለባቸው ዜጎች ናቸው። በተለይ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ላይ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኙ እና ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በተለይ ደሴ እና ኮምቦልቻ ኮሪደር ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ወድሟል፤ ተዘርፏል። በመሆኑም መንግስት በዚህ አካባቢ በጣም ዝቅተኛ በሆነ ወለድ የባንክ ብድር ሊያመቻች ይገባል። የሚከፍሉት ግብር ቅጣትና ወለድ ሳይኖረው ሊራዘምይገባል። ለተወሰነ ጊዜ የግብር እፎይታ መስጠትም ያስፈልጋል። መሰረተ ልማቶችን ማሟላት ብቻ ለባለሃብቱ በቂ ባለመሆኑ መንግስት እነዚህ ወደ ሥራቸው እንዲገቡ በስፋት መስራትና ማሰብ ይጠበቅበታል። እነርሱ ካልሰሩ መንግስት ምንም አያገኝም።
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ባለሃብቶችም ንብረታቸውና ፋብሪካቸው ወድሟል። ይህ በመልሶ ግንባታው ላይ ጫና አይፈጥርም?
አቶ አማን ይኹን፡- እነዚህን የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሥራቸው ለመመለስ በጣም ጊዜ ይወስዳል። ሥራ ላይ ሆነው ሃብት ንብረታቸው የወደመባቸው ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ሥራቸው ውስጥ እንዲመለሱ ትልቅ ሥራ ይፈልጋል። ተጽዕኖው ቀላል አይደለም። ብድር ማመቻቸት ያስፈልጋል። ቀላል ነገር ሊመስል ይችላል። ለአብነት ኮምቦልቻ ውስጥ ቆርኪ ፋብሪካ አለ። ይህ ወደ ሥራ ካልተመለሰ አገር ውስጥ ያሉ ቢራ እና ለስላሳ ፋብሪካዎች ላይ በሙሉ ችግር ይፈጥራል። እነዚህ ፋብሪካዎች ስንዴ እና ገብስ የሚገዙት ከአርሶ አደሩ ነው። ስለዚህ ነገሮች ተመጋግበው የሚሄዱ ናቸው።
በመሆኑም ሁሉም ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማስቻል የሚመለከታቸው አካላት በስፋት ተናበው መስራት አለባቸው። የአደጋ መጠን በሚገባ መታወቅ አለበት የሚባለው የፋብሪካዎችን ብቻ ሳይሆን ከተራ አርሶ አደር ጀምሮ ያለውን ነው። ከመንግስት ጋር የተያያዙ ችግሮችን የንግድና ገቢዎች ቢሮዎች ከንግዱ ምክር ቤት ጋር በመሆን የአደጋው መጠን ማወቅ አለባቸው። ነጋዴው ዘንድም የደረሰው ችግር ሊታወቅ ይገባል።
በሀገሪቱ አንድ ቦታ ሚከሰተው ከሌላው ጋር የተያያዘና ተዛመደ ነው። በተለይም ፋብሪካ ውስጥ ብዙ ግብዓት የሚፈልግ ነው። የተወሰነ ነገር ቢጓደል ድርጅቶች ከሥራ ውጪ ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት እንደ አገር የደረሰው አደጋ ከፍተኛ በመሆኑ በዝርዝር ጥናት ተለይቶ መታወቅ አለበት። የግል ባለሃብት ዘንድም የደረሰው አደጋ መታወቅ አለበት። በግለሰብ ደረጃም የደረሰው ጉዳት መታወቅ ያለበት መንግስት ለሚወስደው መልሶ ግንባታ ሁኔታዎችን ለማየትና ለመገምገም ያግዛል። በመሆኑም አንዱ ከሌላው ጋር የተያያዘ ነው የሚለው ሃሳብ ትልቅ ግምት ሊሰጠውና ሊሰራበት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- የፋይናንስ ተቋማት ያለወለድ ብድር ያቅርቡ ብለውኛል። ይህ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ይሳካል?
አቶ አማን ይኹን፡- ብዙ አንፃራዊ የገንዘብ ተቋማት ሲባል ከወለድ ነፃ እስከማቅረብ ድረስ መሄድ አለበት። ይህ ሲባል እጅግ ዝቅተኛ ወለድ ድረስ መሄድ አለባቸው። ይህንን መንግስት ማቋቋም ይችላል። ብዙ ቀዳዳ ያለበት አገር ነው። በመሆኑም ሁሉም ጉዳዩን በሚገባ ማወቅና ችግሮችን መጋራት ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ ግን ለእነዚህ ዓይነት ዓላማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብድር የሚሰጡ ተቋማት አሉ። ከወለድ ነፃ ገንዘብ የሚያቀርቡ አካላት አሉ። ለአብነት የአፍሪካ ልማት ባንክ፤ የዓለም ባንክ፣ ደቡብ ምስራቅ አፍሪካ ላይ የሚሰራ ባንክ አለ። ከእነዚህም በተጨማሪ በርካታ አበዳሪዎች አሉ።
ወዳጅ የምንላቸው አገራት አሉ። በሰብዓዊነት ላይ፣ የፕራይቬት ሴክተር ለማጠናከር፣ ሴቶችና ወጣቶችን ለማገዝ በጀት አላቸው። በዚህም ላይ በሚገባ ችግሩን ለይቶ ማወቅ ይገባል። በአሁኑ ወቅት ይህንን እያስተባበረ ያለው ገንዘብ ሚኒስቴር ነው። ነገር ግን ይህን ጉዳይ ለብቻ የሚመራ አካልም የሚያስፈልግ ከሆነ ሊታሰብበት ይገባል። ገንዘብ ሚኒስቴር ለራሱ ፋታ ማይሰጡ ብዙ ሥራዎች አሉበት። ግን ሁሉንም ሴክተር መስሪያቤቶች፣ ክልሎልችን እና ሌሎችን አደረጃጀቶች የሚያስተባብር አካል ያስፈልጋል። ለዚህም በሚገባ ቢታሰብበት መልካም ይመስለኛል።
በአሁኑ ወቅት ብዙ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ይታመናል። በደንብ ከታሰበበት በአገሪቱ ውስጥ ብዙ ሃብት አለ። ይህን እንዴት ማንቀሳቀስ እንደሚቻል በሚገባ ማሰብ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ወቅት የአገር ኢኮኖሚ በፍጥነት እንዲያገግም መተኮር ያለበት ማክሮ ወይስ ማይክሮ ኢኮኖሚው?
አቶ አማን ይኹን፡- የተያያዙ ናቸው። ሁለቱም መናበብ አለባቸው። አንዱ ሌላውን ነው ይዞ የሚሄደው። አንዱ ላይ ብቻ ካተኮርን ሌላው ወደ ኋላ ይቀራል። የእኛ ሀገር ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚፈልገው መቀናጀትና መናበብ ነው። ግብርናው ከኢንዱስትሪ መቀናጀትና መናበብ አለበት። ኢንዱስትሪው ከግብርና፣ ግብርናው ደግሞ ከሥራ ዕድል ፈጠራ እና ሌሎች ክህሎቶችና ተቋማት ጋር በሚገባ መናበብ አለበት።
አንዱ ያለ ሌላኛው መሄድ አይችልም። በመሆኑም በተቀናጀ እና በተናበበ መንገድ መሄድ አለበት። በመሰረተ ልማት መልሶ ግንባታ በርካታ ድርጅቶች ጥሬ ዕቃ ያቀርባሉ። ሌሎች ደግሞ የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል። በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ደግሞ ከፍተኛ ግብር ለመሰብሰብ ያግዛል። በርካቶች የሥራ ዕድል ሲፈጠርላቸው ቁጠባ ይጀምራሉ። በዚህ ውስጥ መገንዘብ የሚቻለው ማክሮ ሆነ ማይክሮ ኢኮኖሚው ለብቻው መንቀሳቀስ አይችልም። አንደኛው ሌላኛውን ይዞ የሚሄድ ነው። በአጠቃላይ አንደኛው ከሌላኛው ጋር መናበብ ግድ ይለዋል።
አዲስ ዘመን፡- በርካታ የውጭ ለጋሽ አገራት በጦርነቱ ሳቢያ ከኢትዮጵያ ተቃራኒ የቆሙ በመሆናቸው ከውጭ ዕርዳታ ማግኘቱን ፈታኝ አያደርገውም?
አቶ አማን ይኹን፡- ጦርቱን ማስቆም ያስፈልጋል። አንዳንዶቹ ጦርነቱን አቁሙናና በሠላምና በድርድር ፍቱት እያሉ ነው። በርካቶችም ለሠላማዊ ምክክር ተብሎ ከእስር እየተፈቱ ነው። ይህም በተወሰነ ደረጃ ከምዕራባውያን ጋር ያለውን መካረርና ፍጥጫ የሚያቃልል ይመስለኛል። ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጋር በስልክ መወያየታቸው የሚያሳየው አንዱ ነገር ይህንን ነው።
በተወሰነ ደረጃ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር እየተቋቋመ ያለ ኮሚሽን ውስጥ ብዙ ሰዎች እየተጦቆሙ ነው። ይህም መንግስት ረጅም ርቀት እየሄደ ነው። አገር ውስጥ ያለው ፖለቲካ ሲረጋጋ ከምዕራባውያን ጋር የሻከረው ሁኔታ የሚለዝብና የሚረጋጋ ይመስለኛል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ አገር ውስጥ ያለው ጦርነት ከረገበ ለጋሾች ድጋፍ ለማድረግ ፊታቸውን ያዞራሉ የሚል ዕምነት የለኝም። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም በቅርቡ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር መወያየታቸው የሚታወስ ሲሆን ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።
ትልቁ ነገር የኢትዮጵያ መንግስት ግጭቱን አስቁሞ ወደ መልሶ ልማት ሲገባ አሸባሪ ሕወሓት ጸብ አጫሪነቱን ያቆማል ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው። አሁን ኳሷ በሕወሓት እጅ ላይ ናት። መንግስት ከልክ በላይ ርቀት ሄዶ ለሠላም እጁን ዘርግቷል። በዚህ ሁኔታ ተመሳሳይ ሁኔታ ከሕወሓት በኩል ካልተፈጠረ የታሰበው ሁሉ ላይሳካ ይችላል። መንግስት አቶ ስብሃትን ጨምሮ እስረኞችን ሲፈታ ተቃውሞ እንደሚገጥመው ሳይጠብቅ ቀርቶ አይመስለኝም። በመንግስት ትኩረት ልክ ሕወሓት ምላሽ ይሰጣል የሚለው ጉዳይ ያጠራጥረኛል። አሁን መንግስት ኳሷን በሕወሓት ሜዳ ያደርጋል። ከአሁን በኋላ ምዕራባውያን ፊታቸውን ያዞሩትን በዚያው ይቀጥላሉ ብየ አላስብም። በመሆኑም ለመልሶ ግንባታ እጃችንን አንዘረጋም የሚሉ አይመስለኝም።
ከዚህም በተጨማሪ በመልሶ ግንባታው ‹‹ኢኖቬቲቭ›› የሆኑ አዳዲስ ሃብት የማሰባሰቢያ መንገዶች መከተል ይገባል። የግድ ለጋሾን መጠበቅና እነርሱን ብቻ አግዙን ብሎ የግድ አይልም። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በራሳችን እየገነባን በራሳችን እውቀት እየመራን ያለን ሰዎች በመሆናችን ሌላ አርበኝነት መፍጠር አለብን። ወኔያዎችን በጦርነት ብቻ ሳይሆን በሁሉም መስክ መጠንከር አለብን። ለውጭ ጫና የዳረገንን ድህነት ሰባብረን እና አሽቀንጥረን መጣል አለብን።
ለድህነት የተዳረግነው ማንም ከእኛ በልጦ ሳይሆን በብልሃት ባለመመራታችን ነው። ከዚህ በተረፈ በብልሃትና በመደማማጥ መስራት ግድ ይለናል። በአጠቃላይ መንግስት በአገር ውስጥና ውጭ ያሉትን በሙሉ ማስተባበር አለበት። አገር መልሶ በማቋቋም ለራሳችን እኛ አለን በሚል ወኔ መነሳት ይጠበቅብናል። የውጭ ዕርዳታ ከተገኘ መልካም ነው፤ ነገር ግን በማንኛውም ሁኔታ አገር መልሶ በመገንባት ረገድ ቀዳሚ መሆን ያለበትና በተሳትፎው ወደር የሌለው የአገሪቱ ዜጋ መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ማዕድን ጨምሮ ያልተነኩ ዘርፎች ላይ ማተኮርና የተለየ ስትራቴጂ መከተል አለበት የሚሉ አካላት አሉ። የእርሶ እይታ ምንድን ነው?
አቶ አማን ይኹን፡- መንግስት እዚህ ላይ ያተኩር ይህን ይተው ብሎ መደምደም አይቻልም። በእኔ እይታ ሁሉም አስፈላጊ ነው። ጦርነቱን በፍጥነት መቋጨት ቱሪዝም እንዲፋጠን ያግዛል። አርሶ አደሩ በፍጥነት ግብዓት ካገኘ በፍጥነት ወደ ምርት ይገባል ግብርና ካደገ ወደ ውጭ የምንልከው ያድጋል፤ የፋብሪካ ግብዓቶችም በሰፊ ይገኛሉ ማለት ነው። ያለንን የኢኮኖሚ አማራጭና ዕድል በሙሉ አሟጦ መጠቀም ይገባል። የሚባክን ጊዜ፣ ዕድልና ሃብት መኖር የለበትም። ማግኘት የምንፈልገውን ከፍተኛውን ጥቅም ለማግኘት ሁሉንም አማራጭ መከተል አስፈላጊ ነው።
ማዕድን ዛሬ ተሰርቶ ዛሬ ሃብት አይገኝበትም። ሃብት ሊገኝ የሚችለው ከአምስት እና ስድስት ዓመት በኋላ ነው። በአቋራጭ የሚመጣ ነገር የለም። መሄድ ያለብንን ያክል መሄድ አለብን። በተናበበ፣ በተቀናጀ እና በተጠና መንገድ ሲሠራ ነው ውጤት የሚመጣው። ሥር ነቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረግ ይገባል። ሁሉም ዘርፍ ለአገር ማበርከት በሚገባው ልክ ዝግጁ መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፡- አገር መሰል ፈተና ሲገጥማት አገርን ከሚመራ መንግስት ፖለቲካዊ ውሳኔ ተጨማሪ በየዘርፉ ያሉ የባለሙያዎች ሚና ምን መሆን አለበት?
አቶ አማን ይኹን፡- መንግስት የምንሰጣቸውን ምክረሃሳቦች እየተቀበለ ነው። ለአብነት ኢኮኖሚው እንዲያገግም አማራጭ የገንዘብ ምንጮችንና በተጨማሪ በጀት መመደብ እንዳለበት ጠቁመን ነበር። ይህን እየተገበረው ነው። ነገር ግን ከዚህ በላይ ብዙ አመአራጮችን መጠቀም አስፈላጊ ነው። የባለሙያዎችን ቡድን ማዋቀርና በኢኮኖሚ ዘርፍ የመጣው አደጋ ማጥናትና ማወቅ ይገባል። ይህም ይፋ መደረግ አለበት። ይህን ዋና ስራ አድርጎ እና መደበኛ ሥራ አድርጎም የሚንቀሳቀስ አካል ያስፈልጋል። ይህ ብሄራዊ ፕላን ኮምሽን የ10 ዓመት እቅድ ጋር ተናቦ መሰራት አለበት። ከቀበሌ እስከ ፌደራል ድረስ ተቀናጅቶ መሥራት አለባቸው።
መልሶ ግንባታው ላይ የሚያስፈልገውን ሃብት በተለያየ ማሰባሰብ ግድ ይላል። እውቀትና ሃብት በአግባቡ ሥራ ላይ መዋል አለበት። ባለሙያዎች ያላቸውን ሚና እና እውቀት በዚህ ወቅት በተግባር ላይ ማዋል አለባቸው። በየዘርፉ ያሉ እውቀቶችን በማዛመድ ችግሮችን መፍታት ይቻላል። እቅዶችና ግቦች በተናበበ እና በጋራ ውሳኔ ላይ የተመሰረቱ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ይህን አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ እንደ ዕድልም ሊታይ ይችላል። በአጠቃላይ የተማከለ መልሶ ማቋቋምና መልሶ ግንባታ ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት ማቋቋም ተገቢ ነው።
በዚህ ውስጥ ሁሉም የፌደራል ተቋማትና ክልሎች ድርሻቸውን በአግባቡ ሊወጡና ሁለንተናዊ መልሶ ማቋቋም ይጠበቅባቸዋል። ዜጎችም ክብር ያለው ህይወት መኖር በሚችሉበት ደረጃ ላይ መልሶ መቋቋም አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ማስተባበሩ ትልቅ ድርሻ አለው። ጉዳት ከደረሰባቸው ክልሎች ውጭ ያሉ ክልሎች፣ ባለሀብቱ፣ የልማት አጋሮች፣ ግብረሠናይ ድርጅቶች፣ ለጋሽ አገራት፣ ወዳጅ አገራት፣ ዳያስፖራው በሙሉ ለዚህ መልሶ ግንባታ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው በማመን በሰፊው ማስተባበር ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- የዝግጅት ክፍላችን እንግዳ ሆነው ሙያዊ ትንታኔና ማብራሪያ ስለሰጡን አመሰግናለሁ።
አቶ አማን ይኹን፡- እኔም ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ጥር 9/2014