እማይታመም የለምና መታመም አዲስ ክስተት አይደለም። ታሞ መዳንም የነበረ፣ ያለና የሚኖር ነውና ይህም አዲስ አይደለም። አዲስ ነገር፣ አዲስ ክስተት የሚሆነው ታሞ መቅረት፤ መዳን፣ መፈወስ ሳይቻል ነው፡፡ አንድ ፊቱ መሞትም አለመቻል ያሳስባል። በአገራችን ከላይ ያልነውን አይነት ችግር የገጠመው ማህበራዊ ዘርፍ ቢፈለግ ትምህርትን ያህል የሚሆን ያለ አይመስልም። ይኸውም በተለይ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ለ27 ዓመታት “አዲሱ” ሲባል የኖረው የትምህርት ፖሊሲ እስካሁንም ድረስ እንዳወዛገበ ያለ ሲሆን፤ በእሱ ሰበብ የተተከሉ ችግሮች እስካሁንም ድረስ ሊነቀሉ አልተነቃነቁም።
የትምህርት ፖሊሲው ያመጣብንን ጣጣ በተመለከተ ያልተባለ ነገር ያለ አይመስልም። ከሊቅ እስከ ደቂቅ አስተያየቱን ሰጥቶበታል። ይሁን እንጂ የተሰጡ አስተያየቶች እምጥ ይግቡ ስምጥ የሚታወቅ ነገር የለም። የተደረጉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ለመደርደሪያ እንኳን ስለመብቃታቸው ማረጋገጫ የለም። ወደ ዝርዝሩ እንግባ፤ መነሻና ምንጫችንንም፣ ከፈረሱ አፍ እንዲሉ፣ ትምህርት ሚኒስቴር አድርገን አንዳንድ ሀሳቦችን እንለዋወጥ።
ባለፈው ታህሳስ ወር መገባደጃ ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዳስታወቀው፤ የትምህርቱን ዘርፍ ቀስፈው የያዙት ችግሮች እንዲህ በቀላሉ ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም። በእለቱ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ እንዳሉት፤ የእነዚህ ሁሉ ችግሮች ድምር ውጤት ነው “ለገጠመን ፈተና መንስኤው የትምህርት ሥርዓታችን ውድቀት ነው። ባለፉት 40 እና 45 ዓመታት የዘለቀው የትምህርት ሥርዓት ውድቀት በኢትዮጵያ ለተፈጠረው አጠቃላይ ውጥንቅጥ አንዱ ምክንያት”።
እነዚህን፣ ዘርፉን ቀስፈው የያዙትን ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ የመፍትሄ ርምጃዎችን ለመውሰድ አስፈላጊው ሁሉ እየተደረገ ሲሆን፤ አንዱም በመላ አገሪቱ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ነው። ለዚህም ፕሮፌሰሩ እንዳሉት በመላ ኢትዮጵያ 50 ዘመናዊ ደረጃቸውን የጠበቁ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለማስገንባት የሚያስችል ፕሮጀክት ተዘጋጅቷል። በዲዛይን ዝግጅቱ ላይም ከኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኀበር ጋር ውይይት የተካሄደ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኀበርም በበጎ ፈቃደኝነት የትምህርት ቤቶቹን ግንባታ ዲዛይን ለማዘጋጀት ፍቃደኛ ሆኗል። ይህ ከላይ ያልነው አጠቃላይ ነው። ዘርዘር እያደረግነው ስንሄድ ደግሞ ሌሎችንም እናገኛለን።
እንደምናውቀው፣ በሁሉም የትምህርት እርከኖች ችግሮች አሉ። በአንደኛ ደረጃ ችግሮች አሉ፤ በመለስተኛውም እንዲሁ ችግሮች አሉ፤ በከፍተኛውም ችግሮች አልጠፉም፡፡ ሰርተፊኬት ከሚሰጡት ጀምሮ እስከ ትላልቆቹ ዩኒቨርሲቲዎች ድረስ ተቆጥረው የማያልቁ ችግሮች አሉ። የችግሩ ድምር ውጤትም የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (በኢንተርኔት አማራጭ የቪዲዮ መልዕክታቸው) አማካኝነት ይፋ እንዳደረጉት “በኢትዮጵያ 48 ሺህ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም ደረጃቸውን የጠበቁት 0 ነጥብ 01 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው። በአጠቃላይም ስድስት ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው ደረጃ አራት ላይ የሚገኙት። እነሱም ቢሆኑ የሚያስተምሯቸው ልጆች 12ኛ ክፍልን ሳይፈተኑ ነው ወደ ውጭ አገራት ለመሄድ ልባቸው የሚነሳሳው። ስለዚህም ኢትዮጵያ ደረጃቸውን የጠበቁ የአካልና የአዕምሮ ማበልጸጊያ ትምህርት ቤቶች ያስፈልጓታል።”
“99 በመቶዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች የሚማሩት ከደረጃቸው በታች በሆኑና በምንም አይነት መስፈርት ትምህርት ቤት ሊያሰኛቸው የሚችል ደረጃ በሌላቸው ተቋማት ውስጥ ነው።” የሚሉት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፤ ‹‹ በእንደዚህ አይነት ተቋማት ውስጥ የተማሩ ወጣቶች መጨረሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም›› ሲሉም ተናግረዋል።
ስለዚህም ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች እንዲኖሩንና ሕጻናት አስፈላጊውን የአካልና የአዕምሮ ማዳበሪያ እንዲያገኙ ማድረግ ከእኛ ይጠበቃል። ለዚህም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን እንደ አዲስ መገንባት” አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ትምህርት ቤቶቹ ለይስሙላ ብቻ ለማስተማሪያነት የሚገነቡ ሳይሆን አስፈላጊው የላብራቶሪ፣ የንጽህና፣ የቴክኖሎጂ እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟሉ እንደሚሆኑ ፕሮፌሰሩ አንስተዋልም፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ምርምር ተቋም አባል የሆኑትና በትምህርት ጉዳይ ላይ ገፋ አድርገው የሄዱት ዶክተር ዋና ሊቃ በአንድ ወቅት ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ “ለቅድመ መደበኛ ትምህርት መንግሥት ትኩረት ከሰጠው በየወረዳውና በየገጠሩ ለምንድነው የመስፋፋት ሁኔታ የማይታይበት?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ “በየወረዳውና በየገጠሩ የማስፋፋት ሙከራዎች አሉ፡፡ ግን ደረጃውን የጠበቀ ላይሆን ይችላል፡፡” በማለት መመለሳቸውም ሆነ ሌሎች ምሁራን ከዚሁ ባልራቀ፤ ምናልባትም ተመሳሳይ የሆነ አስተያየትን መስጠታቸውን እዚህ ላይ አስታውሶ ማለፍ ተገቢ ይሆናል።
ወደ ትምህርት ሚኒስቴር እንመለስ። ሚኒስትር ብርሃኑ እንደሚሉት ከሆነ፤ የሚገነቡት የትምህርት ተቋማት ለትምህርት ጥራት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ፣ ተማሪዎችን ደሀና ሀብታም ብለው ለያይተው የማይመለከቱ ወዘተ ሆነው ነው። ከዚህ አኳያ ደግሞ የኢትዮጵያ አርክቴክቸሮች ማህበር እና አባላቱ ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ተስፋ ይደረጋል።
የትምህርት ሚኒስቴሩ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌም ይህንኑ ሀሳብ ያጠናከሩ ሲሆን፤ በአገሪቱ በርካታ ተቋማት ወድመዋል። ትግራይ ነፃ ወጥቶ እዛ የወደመውን ወደፊት እናውቃለን። ሌሎቹ ጋር የወደሙት ግን በመልሶ ግንባታው የሚገነቡ ሲሆን፤ በመልሶ ግንባታው ወቅት በድሮ መልኩ አይደለም የሚገነቡት። የድሮዎቹ አስቀድሞም ከደረጃ በታችና መስፈርቱን ያሟሉ ስላልሆኑ አሁን ሲገነቡ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ መደረግ አለበት። በመሆኑም ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የመልሶ ማልማትና ግንባታ ሥራው ይከናወናል” በማለት የመስሪያ ቤታቸውን እቅድና አቋም ተናግረዋል።
ሙያዊ ትብብር በማድረግ አገራዊ ሀላፊነቱን እንዲወጣ በትምህርት ሚኒስቴር የተጋበዘው የኢትዮጵያ አርክቴክቸሮች ማህበርም በፕሬዘዳንቱ አማካኝነት በትምህርት ቤቶቹ ዘመናዊ ሕንፃ ግንባታ ሂደት ላይ የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ሙያዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል፤ የተሻለ ሥራም እንደሚያከናውን ተስፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኀበር ፕሬዚዳንት አርክቴክት አማኑኤል ተሾመ እንደገለጹት፤ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ዝግጅት በተመለከተ ከትምህርት ሚኒስቴር አመራሮች ጋር ውይይት ተደርጓል። የተደረገውን የሙያዊ ተሳትፎ ግብዣ መሰረት በማድረግም ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ የሚሆን ዲዛይን ለማዘጋጀት እስካሁን 20 የሚደርሱ አርክቴክቶች ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ ነው። በቀጣይም በርካታ አርክቴክቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው የኢንተርኔት አማራጭ የቪዲዮ ውይይት ላይ ከተሳተፉት አንዱ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ሲሆን፣ በሰጠው አስተያየትም ትምህርት ቤት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን፣ ሲገነባ በርካታ ጉዳዮችን፣ ለምሳሌ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት፣ ብክነትን መከላከል፣ በአካባቢው ያለን ሀብት (ሪሶርስ)፣ ጥራት ወዘተ ያገናዘበ መሆን እንዳለበት አመልክቷል። በእስከ ዛሬው የሀገሪቱ የትምህርት ተቋማት ግንባታ ሂደትም እነዚህን ሳያገናዝቡ በመሰራታቸው ለከፍተኛ ብክነት የተጋለጡ ተቋማት መኖራቸውን የተቋማቱን ሥም እየጠራ አስረድቷል።
ባለፈው ሳምንት በዚሁ አምድና ገፅ ላይ እንዳሰፈርነው በሙያና ቴክኒክ ተቋማት ያለው ችግር ለራስ ምታት ይዳርጋል። የጠቀስናቸው ጥናቶች እንዳመለከቱት በእነዚህ ተቋማት ያሉት ችግሮች ብዙ ሲሆኑ እነሱ በየጊዜው ሲደማመሩ የኖሩና ከሀይ ባይ ማጣት የመጡ ናቸው። ይህ ደግሞ ዞሮ ዞሮ ሰለባ ያደረገው ወጣቶችን ሲሆን ይህም የሚያነጣጥረው ትውልድ ላይ ነውና የወደፊቷ ኢትዮጵያ የሚገጥማት ፈተና ከወዲሁ እየታየ ነው ማለት ይቻላል።
በአዲስ አበባ መስተዳድር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን “በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት፣ የሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን የ2013 በጀት ዓመት የግልና የመያድ (መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት) ኮሌጆች የውጭ ኢንስፔክሽን ትንተና ማጠቃለያ ሪፖርት” በሚል ርእስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠናው ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በከተማው በሚገኙ የሙያና ቴክኒክ ተቋማት ያለው ችግር በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ምንም እንኳን እስከ መታገድ የደረሱ ተቋማት ቢኖሩም ችግሮቹ አሁንም አስቸኳይ መፍትሄን የሚፈልጉ ናቸው።
የትኩረት መስኮቹን ግብዓት /Input/፤ ሂደት / Process/፤ እንዲሁም ውጤት /Outcome/ ያደረገውና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት የተደረገበት ይህ ጥናት ብዙ ችግሮችን የለየና የመፍትሄ አቅጣጫን የጠቆመም ነበር፡፡
ዛሬ የሌለው የከፍተኛ ትምህርትና ሳይንስ ሚኒስቴር እንደፈተሸው ከሆነ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለው ችግር ከቁጥር በላይ ሲሆን ይህንንም “ልየታ” (ዲፈረንሺዬሽን) ሲል ባስቀመጠው የአመዳደብ ዘዴ ዩኒቨርሲቲዎቹን እንደገና በማዋቀር ችግሮቹን መፍታት እንደሚቻል፤ ይህም በአስቸኳይ መደረግ እንዳለበትና በፍጥነትም ወደ ሥራው መገባት እንደሚያስፈልግ አስቀምጦ ነበር። ይህ ዛሬ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ይሠራል ተብሎ ይጠበቃልና ለለውጡ ተስፋ አለ።
ዶክተር ዋና ሊቃ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ በረቂቁ ሥራ ላይ በኃላፊነት የሚሠሩና ችሎታ ያላቸው፣ በየሙያውና በየዘርፉ ለብዙ ዓመታት ያገለገሉ፣ የኢትዮጵያን የውስጥ ሁኔታ በደንብ የሚያውቁ፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያላቸው፣ የተመራመሩና ብዙ የጻፉ ምሁራን ተሳትፈዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱን ወክለው ከተሳተፉት ምሁራን መካከልም አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ተሳትፎ በመነሳት መቶ በመቶ እንኳን ለማለት ባይቻልም የትምህርቱን ጥራትና ደረጃውን የሚያስጠብቅ ፍኖተ ካርታ ይወጣዋል የሚል እምነት አለኝ እንዳሉት እኛም ፍኖተ ካርታውና በፕሮፌሰር ብርሀኑ የሚመራው አዲሱ የትምህርት ሚኒስቴር አመራርና እየወሰዳቸው ባሉ የመፍትሄ እርምጃዎች ችግሮች ተፈትተው መልካም ትውልድ (ዜጋ) የመፍጠሩ ህልም ይሳካል የሚል እምነት አለን።
በማጠቃለያችንም ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ እንዳሉት፣ ዘመኑን የሚመጥን ስብዕናና ትምህርት ሲሰጥ አልነበረም። ይህም አሁን ለተፈጠረው አገራዊ ችግር አንዱ ምክንያት ሆኗል። ይሁንና እነዚህን አይነት ፕሮጀክቶችን (50 አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ማለታችን ነው) በማስፋፋት እና ተጨማሪ የትምህርት ጥራት ሥራዎችን በማከናወን እንደገና የትምህርት ሥርዓት ከወደቀበት እንዲነሳ ማድረግ ይቻላል።
እንደ ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ ማብራሪያ፤ የትምህርት ሥርዓቱ እንደገና እንዲያንሰራራ የሚያስችሉ ጅምር ክንውኖች አሉ። እነዚህን አጠናክሮ በመቀጠል እንደ አገር ውጤት ማምጣት ይቻላል። ለዚህም ለትምህርት ቤቶች ጥራት፣ ግንባታ እና ተመሳሳይ ሥራዎች ከተለያዩ የሙያ ማኀበራትና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በትብብር ይሠራል። መልካም ሳምንት።
አዲስ ዘመን ጥር 9/2014
ግርማ መንግሥቴ