ኢትዮጵያን መከተል ደስታው ምን ያክል ነው? በህዝብ እውነት ላይ መቆም፣ በትውልድ ሀቅ ላይ መገኘት ክብሩ እስከየት ድረስ ነው? መልሱን አላውቀውም የክብር ሁሉ ጥግ እንደሆነ ግን ይሰማኛል። ሁላችንም ስም አለን..ኢትዮጵያ የሚለው ስም ግን የሁላችንም የጋራ መጠሪያ ስም ነው። ለዘመናት በዚህ ስም ስንጠራ መጥተናል። እሷን እየተከተልን ብዙ ድሎችን አስመዝግበናል። አገር የዜጎች መጠሪያ ናት፣ በአገር መጠራት በባህልና በታሪክ ውስጥ መብቀል ነው። በአገር መጠራት እኔነትን መሻር ነው።
አባቶቻችን በአለም አደባባይ አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ የሚያደርግ ገናና ስም አውርሰውናል። ማናችሁ ስንባል ኢትዮጵያዊ ነን እያልን በኩራት ተናግረናል። አለምም ከሌላው አገርና ህዝብ በበለጠ ኢትዮጵያዊነትን ያውቀዋል። የነጻነት ስፍራው ኢትዮጵያ ናት። የጀግንነትና የአትንኩኝ ባይነት መነፅር ኢትዮጵያዊነት ነው። እንደአለመታደል ሆኖ ግን ካለን ነገር ይልቅ የሌለንን የምንቆጥር ሆነናል።
አለም ትላንትና ኢትዮጵያዊነትን ፈልጎት ነበር ዛሬም እየፈለገው ይገኛል ምናልባትም ነገም ይቀጥላል። ለምን ካላችሁኝ..አሁናዊውም ሆነ ትላንትናዊው የኢትዮጵያ ስነ ልቦና ከነጮቹ የራቀ ስለሆነ በእኛነታችን ይደመማሉ። የእኛና የእነሱ የማሸነፍ ታሪክ የተለያየ ነው..እነሱ ለጠላቶቻቸው ሚሳኤልና ኒውክሌር ሲያዘጋጁ እኛ ለጠላቶቻችን አንድነትና ህብረትን ነው የምናዋጣው። እነሱ ነጻነትን በገንዘብና በንዋይ ሲመነዝሩት እኛ በአገር ፍቅር ነው የምንተረጉመው።
የነሱ አገር የቆመው በወታደርና በጦር መሳሪያ ብዛትና ጥራት ነው የእኛ አገር የቆመችው በህዝቦች አንድነትና መደጋገፍ ነው። ይሄ ከአለምና ከሰው ልጅ ልዩ የሆነ ማንነታችን ጥያቄ ስለሚፈጥርባቸው ሁሌም ይፈልጉናል። የቀደሙት አባቶቻችን ከአለም ብዙ ፈልገው አያውቁም፤ አለም ግን በብዙ ጥያቄዎች ውስጥ ሆኖ ፈልጓቸል። አለም ዛሬም ቢሆን ከኢትዮጵያ ብዙ የሚፈልገው ነገር አለ።
አለም የኢትዮጵያን ገናና መልክ፣ የኢትዮጵያን ጸዐዳ ውበት ለማበላሸት የማይፈነቅለው የለም፡ ታሪካችን ከታሪካቸው ስለሚበልጥ፣ ነጻነታችን ከነጻነታቸው ስለሚልቅ። ማንነታችን ከማንነታቸው ስለሚደንቅ፣ ስነ ልቦናችን ከስነ ልቦናቸው ስለሚበረታ አይተኙልንም።
ከትላንት እስከዛሬ ብዙ ጠላቶች ተነስተውብናል። ሁሉም ግን ነካክተውን የሚያፈገፍጉ ናቸው። ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንደሚባለው ዛሬ ላይ የአሸባሪው ሕወሓት ውሾች በከፈቱት ቀዳዳ የገቡት የምዕራባውያን ጅቦች በእርዳታ ስም ክብራችንን ለማዋረድ ነው። ሌላ ለምንም ሊሆን አይችልም። ከትላንት እስከዛሬ የኢትዮጵያ ውርደት በዚህ ከሀዲ ቡድን የመጣ ነው።
አሸባሪው ሕወሓት የኢትዮጵያ ገበና ከታች ሆኖ አያውቅም። አጥር እየቀደደ፣ ሉአላዊነት እየደፈረ ጅቦችን ሲያስገባ ነበር። ዛሬም የምናየው ይሄንን ነው.. እየሆነብን ያለው መከራም ይሄው ቡድን በቀደደው የሉአላዊነት ክፍተት የተፈጠረ ነው። ነጭ የተዋረደው በኢትዮጵያዊነት ነው። የዘመናት የነጮች የበላይነት ማብቂያ ያገኘው አድዋ ላይ ነው። ይህ ውርደት የመጣው ደግሞ በኢትዮጵያውያን የጋራ ሀይል ነው።
በነጮች ታሪክ ውስጥ በጥያቄ ምልክት ውስጥ የተቀመጠ አንድ አሳሳቢ ስም አለ..ኢትዮጵያ የሚል። የተዋረዱት፣ ከክብራቸው ዝቅ ያሉት በዚህ ስም ነው። ዛሬም በዚህ ስም እናዋርዳቸዋለን። ዛሬም በዚህ ስም እናሸንፋቸዋለን። ዛሬም በዚህ ስም በጠላቶቻችን ላይ ከፍ ከፍ እንላለን። ይሄ ስም የጥቁሮችን አንገት ቀና ያደረገ ባለውለታ ስም ነው። ከራሱ አልፎ መላውን አለም ለነፃነት አነሳስቷል።
ነጮቹ ኢትዮጵያዊነት ስላልፈቀደላቸው እንጂ ውርደታቸውን ለማሸሽ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን እያስገቡ ሲዳክሩ ኖረዋል። ዛሬም ለሕወሓት ስንቅ እያቀበሉ፣ የሳተላይት መረጃ እየሰጡ፣ ታረቁ ተስማሙ እያሉ በቻሉት ሁሉ ወንበዴውን ቡድን እያገዙ ሀገራችንን ለማፈራረስ ሲዳክሩ ተስተውለዋል። መልካሙ ነገር ግን ዛሬም እየተሳካላቸው አለመሆኑ ነው።
አለም ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟ እውን እየሆነ ነው። መላ ጥቁር ኢትዮጵያን አትንኩ ሲል እየተቃወማቸው ነው። አሁን ላይ ምእራቡ አለም ኢትዮጵያዊነትን ለብዙ ነገር ይፈልጉታል። ከሁሉም በላይ ግን በአድዋ ላይ የደረሰባቸውን ውርደት አስታውሰው ኢትዮጵያዊነትን ዝቅ የሚያደርግ ተግባር መፈጸም ይፈልጋሉ። ለዚህም ቀን ከሌት የሚለፉ ናቸው።
ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር አብረው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆኑብን በዚህ ምክንያት ነው። የኢትዮጵያ ጠላቶች ሁሉ ወዳጆቻቸው ናቸው። ከግብጽና ሱዳን ጋር አሲረው በአባይ ጉዳይ ጫና ሲያሳድሩብን ነበር። በሆነው ባልሆነው እንቅፋት እያስቀመጡ ሲያደናቅፉን ነበር አሁንም የአሸባሪው ሕወሓት ሀሳብ አራማጅ ሆነው መጥተዋል፤ ግን አላሸነፉንም። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያዊ ነንና።
በጣሊያንን ሽንፈት እጃቸውን አፋቸው ላይ የጫኑ አገራት ብዙ ናቸው። አንዲት ጥቁር አገር እንዴት አንድን ሀያል አገር በጦርነት ልታሸንፍ ቻለች? የሚለው ጥያቄ ዛሬም ድረስ ያልተመለሰላቸው አሉ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ለዳግም ውርደት መሰናዳታቸው የሚገርም ነው። ከሀይልና ከብርታቷ የተነሳ ኢትዮጵያን እንደ አንድ መለኮታዊ አገር የሚቆጥሩ አገራት እየተነሱ ነው።
ከሚስጢራዊነቷ የተነሳ እንደ ፔርሙዳ የሚያዩዋት አገራት እየተፈጠሩ ነው። አዎ ኢትዮጵያ በእውነትና በፍትህ የቆመች አገር ናት። አዎ ለጠላቶቿ ፔርሙዳ ናት። የነኳትን ሁሉ ውጣ የምታስቀር፣ በሀሰትና ባልተገባ ውንብድና የሚያውኳትን የማያዳግም እርምጃ ወስዳ ክብሯን የምታስጠብቅ አገር ናት።
የኢትዮጵያ ሀይሏ ህዝቦቿ ናቸው። ኢትዮጵያ ያለህዝቦቿ ምንም ናት። ከጥንት እስከዛሬ በህዝቦቿ ውስጥ አገርን፣ በአገር ውስጥ ህዝብን አውቅላ ይሄን ሀያል እውነት ከትውልድ ትውልድ ስታስተላልፍ ኖራለች። ነጮቹ ያልደረሱበት ሀቅ ይሄ ነው። እኛ በአገር ጉዳይ ስም የለንም ስማችን ኢትዮጵያ ናት።
ክብራችን፣ ነጻነታችን በእሷ መኖር ውስጥ ነው። እኛ በህዝብ ጉዳይ ስም የለንም ስማችን ህዝባችን ነው። ለአሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያ ስሙ አልነበረችም። በኔነቱ ውስጥ ያበቀላት አንዲት ተቀጽላ እንጂ። ቡድኑ በራስ ወዳድነት የቀመረው የማስመሰል ቀመሩ እንጂ ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር አልነበረም። በኢትዮጵያ ገጽ ላይ የጻፈው አንዳች መልካም ታሪክ የለም።
የአባቶቻችንን እውነት አጥፍቶ የራሱን እውነት ጽፏል። የአንድነታችንን ቀለም አደብዝዞ የራሱን ደብዛዛ ቀለም አስፍሯል። እያጠፋ የጻፈው እንጂ እየሰራ የጻፈው የህዝብ ታሪክ የለም። አገሪቱን በአገዛዝ ዘመኑ አባቶቻችን ያለበሷትን የክብር ሸማ አውልቆ በራሱ የተሰፋ የነውር ሸማ አልብሷታል።
ሰውነት የአእምሮና የልብ ውቅር ነው። አእምሮ ማሰብ ሲጀምር ልብ ማፍቀር ይጀምራል፣ ልብ ማፍቀር ሲጀምር አእምሮ ርህራሄን ይማራል። ሰውነት ይሄ ነው…ሰውነት እንደዚህ ነው። ፍትህ ያለው በአእምሮና ልብ ውስጥ ነው። በአእምሮ ወይም በልብ ውስጥ ብቻ ያለ ፍትህና እውነት የለም። ፍትህ ስፍራው አእምሮና ልብ ነው። እውነት መገኛው አእምሮና ልብ ላይ ነው።
አንዳንዶች በአእምሯቸው ብቻ ይኖራሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ በልባቸው ብቻ ወጥተው ይገባሉ..እንዲህ ስንሆን ሙሉ አንሆንም። ሙላት ያለው አእምሮና ልብ ውስጥ ነው። የእስካሁኑ ጉድለታችን ካለ አእምሮ በልብ፣ ካለ ልብ በአእምሮ መኖራችን ነው። በአእምሮ ብቻ መኖር የልብን ሀቅ መግደፍ ነው። በልብ ብቻ መቆም የአእምሮን ሀይል ሜዳ መጣል ነው።
ሰውነት ፈትል ነው..የአእምሮና የልብ ፈትል። ፈትሉ ጋቢ እንዲሆን የሀሳብና የጽሞና ድውር ያስፈልጋል። ሰውነት የልብና የአእምሮ ውህደት ነው ይሄ እውነት መገኛው ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ውስጥ ነው። ለዚህም ነው በአለም ላይ የእውነትና የፍትህ ጸሀይ የወጣልን። ለዚህ ነው ኢትዮጵያዊነት ማሸነፍ የሆነው።
ኢትዮጵያዊነት ሚዛናዊነት ነው። ለአለም ፍትህን ያስተማረ ማንነት ነው። በነጮችና በጥቁሮች መካከል ያለውን ድንበር የሰበረ፣ እኩልነትን ለመላው የሰው ልጅ የነገረ ድንቅ ብርቅ ማንነት ነው። ኢትዮጵያዊነት ለጥቁሮቹ ኩራት ለነጮቹ ደግሞ ውርደት ሆኖ ዛሬም ድረስ አለ። ነገም ይኖራል። ኢትዮጵያዊነት በዚህ ልክ የገዘፈው ለምን ይመስላችኋል? ሌላው አለም ለምንም ነገር ከኔ በፊት አገሬን የሚል ነው ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን ከአገሬ በፊት እኔን የሚል ነው። በነዚህ ሁለት ሀሳቦች መካከል እጅግ ሰፊ ልዩነት አለ።
ከአገሬ በፊት እኔን የሚለው ኢትዮጵያዊ ስነ ልቦና ዝም ብሎ የመጣ አይደለም..በብዙ ደምና በብዙ ሞት የመጣ የአገር ፍቅር ማህተም ነው። ከአገሬ በፊት እኔን በእውነትና በጽናት የተዋጀ ማንነት ነው። አሁን ላይ አገር እየታደገ ያለው ይሄ ማንነት ነው።
በረከሰ ስብዕናና ሴይጣናዊ በሆነ ራስ ወዳድነት ከኔ በፊት አገሬን ብለው ኢትዮጵያን ለማውደም የተነሱት እነ ሕወሓት አሁን ላይ እየወደሙ ያሉት በዚህ ከአገሬ በፊት እኔን ባለው ትውልድ ነው። ከአገሬ በፊት እኔን አድዋን የፈጠረ ማንነት ነው። ከአገሬ በፊት እኔን ኢትዮጵያን ያቆመ ህብረት ነው።
ሁሉም ዜጋ አገሩን ሊወድ ይችላል እስከ ሞት ድረስ በሚያደርስ መስዋዕት አገሩን የሚወድ ዜጋ ያለው ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። ለዚህ ነው የምናሸንፈው። ለዚህ ነው እየነኩን የሚቃጠሉት። ለዚህ ነው ባስቀመጡልን እንቅፋት እየተደናቀፉ የሚወድቁት። ኢትዮጵያዊነት ከአገርና ከህዝብ ልዕልና የተቀዳ ስለሆነ ደብዝዞ አያውቅም።
ማንነታችንን ድህነት አቆሽሾት አያውቅም። በድህነት ክብርና ነጻነትን አሳልፎ መስጠትን አባቶቻችን አላስለመዱንም። ብዙ ነገር እየነጠቁን፣ ብዙ ነገር እያደረጉን፣ እገዳና ማዕቀብ እየጣሉብን በጽናት የቆምንው ጉዳያችንን አገርና ህዝብን ስላደረግን ነው። አሁንም በኢትዮጵያ መጠራት ክብራችን ነው። ኢትዮጵያን አስቀድመን እኛ እንከተል..ኢትዮጵያ ስትቀድም ሁሌም ድል አለ።
ከእኔነት እኛነት ሲቀድም ጠላት አቅም ያጣል። ከግለሰብ ህዝብ ሲቀድም አገር ዋጋ ታወጣለች። አገር ቀድማ ትውልድ ሲከተል አለም ከነማጣታችንም ይፈልገናል። ይሄ ሁሉ መፈለግ፣ ይሄ ሁሉ አጀብ የሚፈጠረው ደግሞ ነጻነታችንን አስጠብቀን ስንጓዝ ነው። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያለው የአንድነት መንፈስ ኢትዮጵያን ነጻ እንደሚያወጣት እናምናለን።
በዚህ የአንድነት መንፈስ ኢትዮጵያ ቀድማ እኛ ተከትለን ሩቅ እንደምንሄድ እምነቴ ነው። ለሰው ልጅ በነጻነትና በመቻል አብራክ ውስጥ እንደመብቀል ልዕልና አለው አልልም። ገንዘብ የሚገዛው ነጻነትና በትግል የሚመጣ ነጻነት አንድ አይደለም። የአለም ነጻነት በገንዘብ የመጣ ነው የእኛ ነጻነት ግን በሞት የተፈጠረ ነው።
በገንዘብና በሞት የተፈጠሩ አገርና ህዝቦች አንድ ላይ አይቆሙም። ደም ከቧልት፣ ላብ ከፌሽታ ሁሌም አሸናፊ ነው። በአሁኑ ሰዐት አለም ላይ ገንዘብ ኖሯቸው ነጻነት ባጡ ህዝቦች ስር ናት። ምክንያቱም በሞት አልተፈጠሩምና።
ኢትዮጵያ ትቅደም..እኛ እንከተል። አገር የሰውነት ማረፊያ ናት..እናርፍባት ዘንድ እናስቀድማት፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 9/2014