የሕወሓት የሽብር ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ላይ ታሪካዊ ክህደት ከፈፀመ በኋላ የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲል የሆነችውና በልጆቿ ታፍራና ተከብራ የኖረችው ኢትዮጵያ ከራሷ አብራክ በወጣ ባንዳ የተጋረጠባትን የሉአላዊነት አደጋ ለመቀልበስ በቁጣ ተነሳች። አይደለም ለቅርብ ለውጪ ጠላት የማይነበረከከው የአገር ኩራት መከላከያ ሰራዊትም ከሀዲውን ሃይል በአስራ ሰባት ቀናት ውስጥ አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶት ወደ ቆላ ተምቤን ሸኘው።
ሰራዊቱ በትግራይ ቆይታው ህዝቡን ከቀንደኛ ጠላቶቹ በመለየት አረጋግቶ ወደቀድሞ ሁኔታው እንዲመለስ ተደጋጋሚ ጥረቶችን አድርጓል። እንደተጠበቀው ግን ህዝቡ ለሰራዊቱ ደጀን ሊሆን አልቻለም። ሲጠብቀውና ሲያረጋጋው የነበረውን ሰራዊት ከአሸባሪ ቡድኑ ጋር አብሮ ከጀርባው ለመውጋት ተንቀሳቅሷል።
‹‹ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ›› እንደሚባለው መቀሌ የአሸባሪ ቡድኑ የስበት ማእከል እንደመሆኗ በቅድሚያ ሰራዊቱ ቡድኑ ሲጠቀምባቸው የነበሩና ሊጠቀምባቸው ያሰባቸውን ከባድ መሳሪያዎችን ከክልሉ አስወጥቷል። አርሶ አደሩ ወደ እርሻው ተመልሶ እንዲያርስ ከዚያም በላይ ህዝቡ የጥሞና ግዜ እንዲያገኝ በሚል መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም አድርጎ ሰራዊቱ ከትግራይ ክልል ለቆ እንዲወጣ አድርጓል።
ይህን የመንግስት ውሳኔ እንደመልካም አጋጣሚ የወሰደው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን መከላከያ ሰራዊቱ ከትግራይ ክልል ገና እግሩ ከመውጣቱ በአማራና አፋር አጎራባች በሚገኙ አካባቢዎች ላይ ወረራ በመፈፀም ከፍ ያለ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመቶችን አድርሷል።
በወረራውም በርካታ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል። የህዝብ የመንግስትና የዜጎችን ንብረት ስራዬ ብሎ አውድሟል። በአፋር ጋሊኮማና በአማራ ቆቦ፣ አጋምሳና ጭና፣ ንፋስ መውጫና አንፆኪያ ገምዛ ላይ ንፁሃንን በግፍ በመጨፍጨፍ የጭካኔውን ጥግ አሳይቷል።
ቡድኑ ‹‹ሂሳብ አወራርዳለው›› በሚል የአርሶ አደሮችን ማሳ በማውደም፣ ከብቶችን በማረድና በጥይት በመግደል ብሎም ሌሎችንም ንብረቶች በማጥፋት የቻለውንም በመዝረፍ ሽፍትነቱ በአደባባይ አሳይቷል።
አሸባሪ ቡድኑ ለዚሁ እኩይ አላማው ከህፃናት እስከ ሽማግሌ በማሰለፍ ወረራውን አጠናክሮ አብዛኛዎቹን የሰሜንና ደቡብ ወሎ አካባቢዎችን፣ በአፋር በኩልም እስከጭፍራ፣ ደሴን ተሻግሮ ወደ ከሚሴና ሸዋሮቢት ድረስ ብዙ የትግራይ ወጣቶችን ገብሮ የያዘበት ክስተትም ተፈጥሮ ነበር።
ቡድኑ ለምእራባውያኑ በተለይ ደግሞ ለአሜሪካን ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት አሻንጉሊት መንግስት ሆኖ ሲያገለግል የቆየ በመሆኑ ደብረሲና ከተማ ሲደርስ አዲስ አበባ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት እንደሚገባ እርግጠኛ ሆነው በሚዲያዎቻቸው ድጋፋቸውን ሲገልፁለት ተስተውሏል። አዲስ አበባ አለቀላት ብለው ዜጎቻቸው በአስቸኳይ ከተማዋን ለቀው እንዲወጡም አዘዋል።
በክቡር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ መሪነት በተጀመረ የተጠናከረና ሁሉን አቀፍ ዘመቻ ታዲያ በሁለትና ሶስት ቀናት ውስጥ በጀግናው የአገር መከላከያ፣ በአማራ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ፣ በአፋር ልዩ ሃይልና ሚሊሻ በተባበረ ክንድ አሸባሪ ቡድኑ አከርካሪው ተመቶ ከባድ ኪሳራ ደርሶበታል። በሺዎች የሚቆጠሩ ያሰለፋቸው ተዋጊዎቹም ሙትና ቁስለኛ ሆነዋል። የቀሩትም እግሬ አውጪኝ ብለው ፈርጥጠዋል።
ይህንም ተከትሎ ገና ሁለት ሳምንት እንኳን ባልሞላ ግዜ ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው የህብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻ በጠላት እጅ ተይዘው የነበሩ ቦታዎች ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆነዋል።
እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን እንዲህ ከትግራይ አልፎ ሰፋፊ የአማራና የአፋር ቦታዎችን በመያዝ እንዳሻው ሊፈነጭ የቻለው ለምድን ነው? የሚለው ነው። እርግጥ መንግስት ባለው አቅም ወራሪውን ሀይል ባለበት ለማቆም የአቅሙን ጥሯል። ነገር ግን በበቂ ሁኔታ ራሱን ባለማደራጀቱ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ አሸባሪ ቡድኑ ከሊቅ እስከደቂቅ ህዝቡን ወደ ጦር ግንባር አሰልፎ በመምጣቱ ለወራትም ቢሆን በርካታ ቦታዎችን ሊቆጣጠር ችሏል።
በሌላ በኩል ደግሞ አሸባሪ ቡድኑ ጦርነቱን ህዝባዊ በማድረጉና ከህፃን አስከ አዋቂ አሰልፎ ለጦርነት በማሰማራቱ ለተወሰነ ግዜም ቢሆን የሃይል የበላይነት አግኝቷል። ቡድኑ ካሰለፈው የህዝብ ማእበል ጋር የሚመጣጠን ሃይል ከወገን በኩል አለመኖሩም ትልቅ ዋጋ አስከፍሏል። የአካባቢው ሚሊሻንና ነዋሪው በሚፈለገው ልክ አለመታጠቅና አለመደራጀትም ጠላት በቀላሉ ወደፊት እንዲገሰግስ አግዞታል።
ከሁሉ በላይ ደግሞ በውሸት ተፈጥሮ በውሸት ያደገው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በየግዜው የሚነዛቸው የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎች ሰዎች የሚኖሩባቸውን ከተሞችና አካባቢያቸውን በቀላሉ እንዲለቁ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል። ቡድኑ ጥይት እንኳን ሳይተኩስ የገባባቸው ከተሞች ቁጥርም ቀላል የሚባል አልነበረም።
በርግጥ አንዳንድ አካባቢዎች በአሸባሪው የሕወሓት ፕሮፓጋንዳ ሳይታለሉ አካባቢያቸውን በንቃት በመጠበቅና እስከ ግንባር ድረስ ዘምተው በመፋለም የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። ሆኖም በጉያቸው ለረጅም አመታት አብሯቸው ሲኖር የነበረ ባንዳ ለጠላት አሳልፎ ሰጥቷቸዋል። በዚህም ታሪካዊቷ የደሴ ከተማ በአሸባሪው እጅ የወደቀችበትን ክስተት ማስታወስ ተገቢ ነው።
በዚህ ሁሉ ሂደት ታዲያ የመከላከያ ሰራዊቱ፣ ልዩ ሃይሉና ሚሊሻው የአሸባሪ ቡድኑን ግስጋሴ ለማስቆም በርካታ መስዋዕትነትን ከፍለዋል። በተለይ ደግሞ አሸባሪ ቡድኑ በአማራ ክልል ወልቃይት በኩል የከፈተውን ተደጋጋሚ ጥቃት በመመከት ረገድ የነዚህ ጥምር ሃይሎች ሚና ጉልህ ነበር። በተመሳሳይ በአፋር ክልል ሚሌን ለመቁረጥና የሀገሪቱ የገቢና የወጪ ምርቶች የሚተላለፍበትን መንገድ ለመያዝ ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረትም በመከላከያ፣ አፋር ልዩ ሃይልና በሚሊሻው ከሽፏል።
መንግስትም በበኩሉ የሀገሪቱን የመከላከያ ሃይል በልዩ ልዩ መልኩ ለማጠናከር በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። ክልልሎችም በተለያየ ግዜ የክተት ዘመቻዎችን በመጥራት ህዝቡ ሰራዊቱን፣ ልዩ ሀይሉንና ሚሊሻውን እንዲቀላቀል አድርገዋል፡ በዚህም በርካታ ቁጥር ያለው ወጣት ሰራዊቱን በፍቃደኝነት ተቀላቅሏል።
አሁን ሁሉም ነገር ተቀይሮ ጠላት ክፉኛ ተደምስሶና የተረፈውም እግሬ አውጪኝ ብሎ ወደመጣበት ተሸኝቷል። ከዚህ በኋላ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ አሸባሪ ሃይል ዳግም መሰቃየትና መከራ ማየት አይፈልግም። በህፃናትና ሴቶች ላይ የደረሰው አስገድዶ መደፈር፣ በሌሎች ዜጎች ላይም የደረሰው ሞትና መፈናቀል ዳግም እንዲመጣ ማንም አይሻም።
ስለሆነም ህዝቡ የሰላም አየር እንዲተነፍስ ከተፈለገ ይህ ሃይል እንዳይነሳ ተደርጎ መቀበር አለበት። ለዚህ ቡድን ግዜም ፋታም መስጠት አይገባም። የወገንም ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ሁሉም በየሞያውና በአቅሙ ሰራዊቱን ከመደገፍ ባለፈ ለሰራዊቱ የሰው ሀይል አቅም ሊሆን ይገባል።
የህልውና ዘመቻው ምዕራባውያንን ጨምሮ ከሌሎች የውጪ ጠላቶች ጋር የሚደረግ በመሆኑና የኢትዮጵያ ህልውና የሁሉም አፍሪካውያን ህልውና በመሆኑ ይህ ከሃዲ ቡድን በፍጥነትና በማያዳግም መልኩ መደምሰስ ይኖርበታል። የውክልና ጦርነት የሚያደርጉና ዙሪያችንን የከበቡ ሃይሎች በመኖራቸው ኢትዮጵያን ከቶም የማይደፍሯት ብቻ ሳይሆን በህልማቸው እንኳን የማያስቧት እንድትሆን የዚህ አሸባሪ ቡድን መክሰም ወሳኝ ነው።
ይህ ብቻ ሳይሆን በዘር ፖለቲካ ለታወሩና ኢትዮጵያን በዘር ከፋፍለው ካልመራናት ለሚሉ የሀገር ውስጥ ባንዳዎችና ሸኔን ለመሰሉ የሕወሓት ጀሌዎች እንደ መቀጣጫ ስለሚሆን የዚህ ቡድን መወገድ ለነገ የማይባል በመሆኑ ዘመቻው አሁንም ቢሆን ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
ዘመቻው ንፁሃን የትግራይ ህዝቦችንም ጭምር ከመከራና ከጭቆና ነፃ የሚያወጣና መጪ ተስፋቸውን የሚወስን ከመሆኑ አኳያ ሕወሓትን ከአማራና ከአፋር ክልል ማፅዳት ብቻ ሳይሆን ራሱ ከበቀለበት ከትግራይ ክልልም ጭምር ማጥፋት ያስፈልጋል። ቡድኑ ከጦርነት ሁሌም ማትረፍ ይቻላል ብሎ ስለሚያምን ተመልሶ የኢትዮጵያ ህዝቦች ራስ ምታትና መከራ መሆኑ አይቀርም። ለዚህ ሲባል የህልውና ዘመቻው የማያዳግምና የሕወሓት ቡድን ዳግም መቃብር ፈንቅሎ እንዲወጣ የሚፈቅድ ሊሆን አይገባም። ድል ለኢትዮጵያ !
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 9/2014