አ ገርና ሕዝብን እንደሚወዱ አካላቸውን ጭምር ሰጥተው ያሳዩ ናቸው። ዛሬ ድረስ በአገር ጉዳይ ላይ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እየሠሩ ያሉትም ምንም እንኳን የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ቢሆኑም ቢሯቸው ውስጥ ፍራሽ ዘርግተው እየተኙ ነው።
በተጨማሪ ወላጆቻቸው በደብረ ታቦር ከተማ ቢኖሩም ቤተሰቦቼ ተማሪዎቼና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም ጭምር ነው ብለው ስለሚያስቡ ከተማሪዎቻቸው ጎን ለደቂቃም መለየትን አልፈለጉም።
በዚህም በቅርብ ሆነው ችግራቸውን መጋራትና መፍታት ልዩ ደስታን ይፈጥርላቸዋል። በእርሳቸው እምነት ለአገር የሚሰሰት ነገር የለም። በዚህም ለአገራቸው ክብር ዝቅ ብሎ መሥራትን ያውቁበታል። ማሳያውም ለመከላከያ ሰራዊት ለሚደረገው ድጋፍ ከተማሪዎቻቸው ጋር በመሆን ጫማ መጥረጋቸው ነው።
በቀጣይም ለአገር ፍቅርና ለሕዝባቸው ክብር የማይከፍሉት መሰዋዕትነት እንደሌለ፤ ሁልጊዜም ውግንናታቸውን ከሕዝብና ከአገር ጋር እንጂ ከራስ ጋር እንዳልሆነ ይናገራሉ ዶክተር ክንዴ ገበየሁ።
በማንኛውም ጊዜ የሰላምና የልማት ዋልታ ሆኖ መገኘት የሚያስደስታቸው ዶክተር ክንዴ የአማራ ልማት ማህበር የሰላም አምባሳደር ናቸው። የታማኝነታቸውና የበጎነትም ምሳሌ ናቸው። በዚህም በጸረ ሙስና ኮሚሽንና በበጎሰው ሽልማት አግኝተዋል።
በአሁኑ ወቅት ብዙዎች ያጡትን የመቻቻል እና የአብሮነት ባህል በደማቸውና በአጥንታቸው ውስጥ አዋህደው ለሌሎች ጥሩ አርአያ የሆኑትም ለዚህ ነው። እኛም ብንሆን ለዛሬ ‹‹የሕይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳ ያደረግናቸው ይህ ተሞክሯቸው አስተማሪ በመሆኑ ነውና አንብቧቸው አልን።
እናት አገልጋዩ ልጅ
ተወልደው ያደጉት በደብረታቦር ከተማ ሲሆን፤ አስተዳደጋቸው ግን እንደማንኛውም ልጅ አልነበረም። ጨዋታ ጭምር የሚናፍቃቸው ልጅ ነበሩ። ምክንያቱም እርሳቸው የመጀመሪያ ልጅ ከመሆናቸውም ባሸገር አባታቸው በቅርባቸው ስላልነበሩ ብዙ ኃላፊነቶችም ነበሩባቸው።
ምንም እንኳን ልዩ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ከአያታቸው ጋር እንዲያድጉ ቢደረጉም እናታቸውን መተው ግን አልሆነላቸውም። ስለዚህም በቻሉት ሁሉ እናታቸውን ለመደገፍ ይሞክራሉ። ከሚያግዟቸው ሥራዎች መካከል ልጆችን የማዘሉና የመንከባከቡ ኃላፊነት አንዱ ነው።
የእናታቸው ጉዳት ያሳስባቸዋልና ከአያታቸው ተደብቀው በመሄድ ባልጠነከረ ጉልበታቸው ጭምር የቀን ሥራ እየሠሩ ያግዟቸዋል። በአካባቢው ዘንድ የቀን ሥራ የሚባለው ብዙ ጊዜ የአጨዳ ሥራ ነውና ያንን ለማድረግ ረጅም መንገድ ይሄዳሉ።
በትንሽ ገንዘብ ሠርተውም ይመጣሉ፤ ድንጋይ በትከሻቸው ተሸክመውም፣ መሰል ሥራዎችን ተግብረውም ያገኙዋትን ገንዘብ ለእናታቸው ይሰጣሉ። እናታቸው በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ በመሆናቸው ርቀት መንገድ ብቻቸውን እንዳይሄዱ ያደርጋሉ።
ሲመለሱም ከተማው ላይ ሊሸጡ የሚችሉ እንደ ዶሮ አይነት ነገሮች ይዘው በመምጣት አትርፈው የገቢ ምንጭ ይሆኗቸዋል። አያታቸው እንዳይቆጧቸውና ከፊታቸው እንዳያጧቸውም በማሰብ ይህ ስራ ይሰሩት የነበረው ከትምህርት ቤት በመቅረትም ጭምር ነበር። በዚያ ላይ አያታቸውንም ማገዝ ስላለባቸው ደከመኝ ሳይሉ አያታቸውን ያግዛሉ።
ስለዚህም ልጅነታቸው ያለፈው ከሥራና ከሥራ ጋር ብቻ እንደነበር ያስታውሳሉ። ዶክተር ክንዴ በልጅነታቸው አደራ የሚቀበሉ፣ ታማኝና ሰውን በማገዝ የሚደሰቱ ሲሆኑ፤ በጣም አስተዋይና ብልህም ናቸው።
ሁሉን ነገር በበጎ ጎኑ መመልከት የሚቀናቸውም አይነት ልጅ ነበሩ። በዚህም በልጅነታቸው መሆን የሚፈልጉት ኢንጅነርና መርማሪ ፖሊስ ነው። ኢንጅነር መሆን የፈለጉት መሰረቱ የሂሳብ ትምህርት አቅማቸው ነው። ነገር ግን በአጠቋቆር ችግር ምክንያት ትምህርቱ ‹‹ዲ›› ስለመጣ አልተሳካም።
መርማሪ ፖሊስን የተመኙት ደግሞ ሕጉን ተገን አድርጎ ወንጀለኛን ማስቀጣትና ከስህተቱ መመለስ ስለሚፈልጉ ነው። ይህ ደግሞ ዛሬ ድረስ ከሰራዊቱ ጋር ልዩ ቁርኝት እንዲኖራቸው እድል ሰጥቷቸዋል።
ትናንት በኦጋዴን፣ ዛሬ ደግሞ በሰሜኑ ክፍል ተቀራርበው እንዲሰሩም ያደረጋቸው ይህ ሙያውን መውደዳቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ሁለቱም ሊሳካላቸው አልቻለም። ነገር ግን የሁሉም መሰረት የሆነው ላይ ደርሰዋል።
ይህም መምህርነት ሲሆን፤ በሙያው ዛሬ ድረስ ማለትም 34 ዓመታትን ሲያሳልፉም አንድም ቀን ተቆጭተውበት አያውቁም። እንዲያውም የሁሉም አባት ስለሆኑ ደስተኛ ናቸው።
ፈተና ያልበገረው ትምህርት
ከትምህርት ጋር የተዋወቁት እንደማንኛውም ልጅ በአብነት ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ብዙም ግን አልገፉበትም። ምክንያቱም በቅርባቸው ዘመናዊው ትምህርት ተጀምሮ ስለነበር በቀጥታ ወደዚያ አመሩ።
ስለዚህም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ደብረ ታቦር ከተማ ላይ በሚገኘው ዳግማዊ ቴዎድሮስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታተሉ።
ሁለተኛ ደረጃንም ቢሆን በዚያው ነው የተማሩት። እነዚህን ክፍሎች ሲማሩ በጣም ጎበዝ ተማሪ ስለነበሩ በተለይ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ባሉ ክፍሎች ላይ ብዙ የቆዩበት ሁኔታ የለም። «ደብል እየመቱ» ክፍሎቹን እንዳጠናቀቁ ያስታውሳሉ። አስራ አንደኛ እና አስራ ሁለተኛ ክፍልን ግን እናታቸውን በማገዙ ሥራ ላይ ተጠምደው ስለነበር ለፈተናው መዘጋጀት አልቻሉም። ስለዚህም የ12ኛ ክፍል ውጤታቸው የሚጠብቁትን ያህል አልሆነላቸውም። በዚህም ለዲግሪ ያሰቡት ዲፕሎማ ሆነ።
በዚህ ውጤትም ባህርዳር መምህራን ኮሌጅን ተቀላቅለዋል። በኮሌጁ በጆኦግራፊ የትምህርት መስክ ዲፕሎማቸውን የያዙ ሲሆን፤ ከዓመታት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላም ትምህርታቸውን መቀጠል ችለዋል።
ይህ የሆነውም በሐረመያ ዩኒቨርሲቲ ነው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢንቫይሮመንታል ጆግራፊ የትምህርት መስክ በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቀዋልም። ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረዋል።
የትምህርት መስኩ የተለያየ ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኢንቫይሮመንታል ጂኦግራፊ፤ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኢንቫይሮመንትና ዴቨሎፕመንት ትምህርት መስክ ተከታትለዋል።
ከዚያ በኋላ ያለው የትምህርት ሁኔታቸው በተለያዩ ስልጠናዎች የዳበረ ሲሆን፤ በተለይ በአመራር ሥራ ስልጠና ላይ ብዙ ጊዜ ተሳትፈዋል። አሁንም ማስተማሩ በራሱ መማር ስለሆነ ከትምህርት እንዳልራቁ አጫውተውናል።
ጎልማሳው ሙያ በሥራ
የሥራን «ሀሁ» የጀመሩት በ20 ዓመታቸው በጅግጅጋ ጭናግሰን በምትባል ቦታ ሲሆን፤ በጂኦግራፊ መምህርነት ተመድበው የሠሩበትም ነው። ጎበዝ ሠራተኛ በመሆናቸውም ስድስት ወር ሲሆናቸው ምክትል ርዕሰ መምህር ሆነው እንዲያገለግሉ ተመረጡ። ሁለት ዓመት ተኩልም በቦታው ላይ አገለገሉ። ሥራ ስኬትና እድልን ይሰጣልና ውጤታማነታቸው ወደ ከተማ እንዲገቡ አደረጋቸው። በ1983 ዓ.ም ጅግጅጋ ከተማ ውስጥ መምህርነታቸውን ቀጠሉ።
እዚህም ብቃታቸውን ማሳየታቸውን አላቋረጡም ነበር። በዚህም ለሌላ ሥራ ታጩ። ይህም በከተማው ትልቅ ሕዝብ የሚያቅፈውን ቀበሌ 06 ተብሎ የሚጠራውን ስፍራ በሊቀመንበርነት እንዲመሩ የተመረጡበት ነው። በአሁኑ ወቅት የቀበሌው ብዛት ወደ አምስት ከፍ ሊል ችሏል።
በሊቀመንበርነት 12 ዓመት ከሰባት ወር ሲሠሩም ቢሆን ማህበረሰቡን በብዙ መንገድ አገልግለዋል። በአካባቢው ይንቀሳቀሱ ከነበሩ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ሁሉ ተፋልመው የሕዝብን ፍላጎት የሞሉ ናቸው።
ከባለድርሻ አካላት፤ ክልል መስተዳደር፤ ከጸጥታ ሀይሎች፣ ከጥምር ኮሚቴ በጋራ ሆነው የሕዝብ የሰላም ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥም ሳይተኙ ሠርተዋል። ይህንን ሲያደርጉ ደግሞ የብሔር ልዩነትን አቻችለው በመምራት ነበር። በተለይም አብዛኛው አመራር ለመሀል አገር ተወላጆች ያለው አመለካከት የተዛባ በመሆኑ በወቅቱ የነበረውን ውጥረት በጥበብ በመቀነስ፤ አልፎ አልፎም ስሜትን በሚፈትንበት ጊዜ ፊት ለፊት በመጋፈጥ ብዙዎችን ከጥቃት ሰለባነት ታድገዋል።
በአንድ ወቅት የክልሉ አመራር በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት የሚሰጡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመዝጋት በተጀመረው ዘመቻም ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን የከተማውን የሀገር ሽማግሌ፤ ታዋቂ ግለሰቦች እና የሃይማኖት አባቶችን በማስተባበር የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አማርኛ የሆኑና አማርኛ ተናጋሪዎችን ለመታደግ እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ በጅግጅጋ ከተማና በክልሉ ትምህርት ቤቶች ጭምር ውሳኔው እንዲቀለበስ አድርገዋል። ዶክተር ክንዴ ሊቀመንበርነቱን በተረከቡበት ወቅት ሌላ የሚሰሩት ሥራም ነበራቸው። የማስተማር ሥራቸውንም አልተውም። ሁሴን ግሬን በሚባል ትምህርት ቤት ላይ ምክትል ዳይሬክተርና መምህር ሆነው ለዓመታት ሠርተዋል። ከዚያ ባሻገር የአማራ ልማት ማህበር ሊቀመንበርም በመሆን አገልግለዋል።
ይህንን ሁሉ ሥራ ሲሠሩ ደከመኝን አያውቁም። በተለይ ጊዜው የሱማሌው መስተዳደር ያልተጠናከረበትና በየአቅጣጫው ፈተና የበዛበት ስለነበር ብዙ መሥራትን ይጠይቃል። በዚህም አይበገሬነታቸውን እያሳዩ ነበር ፈተናውን ያለፉት። ‹‹ሰው አንጻራዊ ቢሆንም አዕምሮው ንጹህ ሲሆን፤ ፍላጎት ሲኖረውና አገልጋይነትን ሲወድ ምንም ሥራ ቢበዛ ይጠነክራል እንጂ አይደክምም።
›› የሚሉት እንግዳችን፤ አዕምሮ መልካም ጎኖችን ብቻ ከተሰጠው ብዙ ነገሮችን ያሳካል፤ ይሠራልም። እንደ አንድ መምህር ነጭ ጠመኔ ይዘው፤ እንደ አንድ ርዕሰ መምህር በአሳታፊ የአመራር ጥበብ መርተው፤ እንደ ወላጅ ተማሪዎችን መክረው እና ዘክረው በሊቀ መንበርነታቸውም ኃላፊነታቸውን ተወጥተው የመቀጠላቸው ምስጢር በጎ ህሊና ስላላቸው መሆኑን ይናገራሉ። በቅንነትና ብዙን ባሳተፈ መልኩ ነገሮችን መከወን መቻል ሥራዎች በብዙ ሰዎች እንዲሰሩና ውጤት እንዲመጣም ማስቻል ነው።
ብዙ ተከታይ እንዲኖርም ማድረግ እንደሆነ የሚያምኑት ዶክተር ክንዴ፤ ማንም ሰው እኔ ከሌለሁ ሥራዎች አይከወኑም ብሎ ማሰብ የለበትም። ከዚያ ይልቅ ሥራን ማስለመድ፣ ለሌሎች ማጋራትና ኃላፊነትን መስጠት እንደሚገባ በጽኑ ያምናሉ። ሰዎችም በተለይ መሪዎች ይህንን መርሃቸው እንዲያደርጉ
ይመክራሉ። ዶክተር ክንዴ ከምንም በላይ የኃላፊነት ጉዳይ የሚያስጨንቃቸው ናቸው። ሳላደርገው የሚል ቁጭት ራሳቸው ላይ መፍጠር አይፈልጉም። በዚህም ቀደመው መታከም ሲኖርባቸው ይህንን ሥራ ልጨርስ በሚል በቀላሉ የጀመራቸው ሕመማቸው ወደ ካንሰር ለመቀየር ተቃርቦ ነበር። ሆስፒታል የገቡትም ሁኔታው ሲብስባቸውም ነበር። ይህ ደግሞ በአካላቸው ጭምር ለአገራቸውና ለክልሉ ሕዝብ ዋጋ እንዲከፍሉ ሆነዋል። ከሁለት ዓመት በላይ ሆስፒታል ሲቆዩ አገጫቸውና የታችኛው አካላቸው በአርቴፊሻል አካል ተተክቶ ሥራ እንዲገቡ ሆኑ። በእርግጥ የአርቴፊሻል አካላቸው አሰራሩ ምንም ስለማያሳውቅ ማንም ምንም አይላቸውም።
ደከመኝ ሰለቸኝን የማያውቁት ዶክተር ክንዴ በጉልህ በሚታይ ስራቸው የተጎዳ አካላቸውን ከሰዎች ይደብቁታል። ከማንም ያነሰ ሥራ ሰርተውም አያውቁም። እንዲያውም በዚያ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ከሚጠበቅባቸው በላይ መሥራት ያስደስታቸዋል፤ ያኮራቸዋልም። ብዙ አርያነታቸውን ያሳዩበትን እድልም ሰጥቷቸዋል። ለዚህ ደግሞ ብርታታቸው የሱማሌ መንግስትና ሕዝብ እንደሆነ ያነሳሉ። ምክንያቱም በሆስፒታል ቆይታቸውም ሆነ ከወጡ በኋላ ድጋፋቸው አልተለያቸውም።
ደመወዛቸውም አልተቋረጠም። ከዳኑ በኋላም ቢሆን መናገር አይችሉምና ለተወሰኑ ጊዜያት ታግሰዋቸዋል። ይህ ደግሞ ‹‹ሕዝብ ለከፈለልኝ ዋጋ የማልከፍለው ነገር የለኝም። ዳግም መነሳትና መሥራት የቻልኩት በእነርሱ ስለሆነም ወደ አፈር እስክገባ ድረስ ሳልሰስት አገለግላቸዋለሁ። ›› እንዲሉ አድርጓቸዋል። ‹‹ሰው አገርም ሆነ ሕዝብ ስለሰጠው ዋጋና ዳግመኛ እድል ማሰብ አለበት። ለእርሱ የሚሰስተው ነገር ሊኖርም አይገባም። ›› የሚሉት እንግዳችን፤ ተመልሰው በመምህርነት ማህበረሰቡን ሲያገለግሉ በኢኮኖሚ ምክንያት ትምህርት ያቋረጡ ተማሪዎችን አድራሻቸውን በማፈላለግ ጭምር ችግራቸውን አቅም በፈቀደ እየደገፉ ነው።
የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ከተመሰረተ ጀምሮ ጠንክሮ እስኪወጣ ድረስ በመምህርነት፣ የተቋማዊ ለውጥና የትምህርት ጥራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የማኔጅመንት አባል ሆነው ከአቆሙት መካከልም አንዱ ነበሩ። እንግዳችን በሱማሌ ክልል የአማራ ልማት ማህበርን /አልማን/ በማጠናከር ሂደትም መጠነ ሰፊ ሥራዎችን ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን አከናውነዋል። ለዚህም ማሳያው ሰፊውን የሶማሌ ክልል ሕዝብ በማስተባበር የድጋፍ ተግባራትን እንዲጠናከር በማድረግ በጅግጅጋ እና አካባቢው ነዋሪዎች ስም ትምህርት ቤት ማስገንባታቸው ሲሆን፤ የክልሉ ነዋሪ ስለ አማራ ያለውን እሳቤ ያስቀሩበት ነበርም። ረጅም ሕይወታቸውን ያሳለፉት የምስራቁ የአገሪቱን ክፍል ሲሆን፤ ሕዝቡን ከማገልገላቸው በተጨማሪ ከሶማልኛ ቋንቋ ተናጋሪ ውጪ የሆኑ ዜጎችን መብት በማስጠበቅ ነው።
ለዚህም አንዱ በ2002 ዓ.ም በሶማሌ ክልል በተለይ በአማራ ተወላጆች ላይ ከክልሉ ሴክተር ቢሮዎች ውስጥ የሚሠሩ ከ1000 በላይ ሰራተኞች ላይ የተፈጸመው መቀነስ በሌሎችም ላይ እንዳይተገበር ያደረጉበት ነው። በሕዝቦች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን በጥልቀት በመገምገም መፍትሄ ለመስጠት እና በተከሰቱ ችግሮች የእርቅ ስርአት በመዘርጋት ወደ ቀደመው ሁኔታ ለመመለስ ብዙ የሠሩም ናቸው። የአገሪቱን ለውጥ ተከትሎ የጥፋት ኃይሎች በዘረጉት ሴራ በጅግጅጋ ከተማ በ2010 ዓ.ም መጨረሻ ከተማዋን ወደ ሰላም ለመመለስ በተደረገው ትግል በአካል በመገኘት እና የሥራ ባህሪያቸው ሆኖ ደግሞ ካሉበት ደብረ ታቦር በርቀት ሆነው ጉዳዩን በመከታተል የሕዝቡን እንባ ማበስ የቻሉም ናቸው።
ቅድሚያ የሚሰጡት የመቻቻልና የመተሳሰብ ህብረ ብሄራዊነት ላይ በመሆኑም ለሰዎች ሁሉ እኩል ወገንተኝነት ያላቸው፤ አብሮነት፤ መተሳሰብና ሕዝባዊ ባህሪያትን በማጠናከር የአገርን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ የቻሉም ናቸው። ለዶክተር ክንዴ የእረፍት ጊዜ ማለት የእንቅልፍ ጊዜ ብቻ እና ብቻ ነው። ከዚያ ውጭ ያለው ሰዓት የአገራቸውና የሕዝባቸው ነው። በዚህም ለራሳቸው የተሻለ ኑሮ ሳይኖራቸው ጭምር ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ብዙ ተግባራትን በመፈጸም ያሳልፉታል።
ሕዝብና አገራቸውን በጽናትና በታማኝነት በማገልገላቸው ደግሞ ከበርካታ አካላት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ጸረሙስና ኮሚሽንና የበጎ ሰው ተሸላሚም መሆናቸው ነው። በተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲዎችና የሠሩባቸው መስሪያ ቤቶችም ቢሆኑ የወርቅና መሰል በርካታ ሽልማቶችን አበርክተውላቸዋል።
በየጊዜው የምስጋና ወረቅትም የሚጎርፍላቸው ናቸው። ይህ ሲሆን ግን ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን ያነሳሉ። የመጀመሪያው ‹‹በእኔ ሥራ ሳይሆን በእናንተ ዓይን የተደረገ ነው›› የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው‹‹ ሌላ የቤት ሥራ እየሰጣችሁኝ ነው የሚል ነው። በአሁኑ ወቅት በአገራችን በተለይም በአማራ ክልል ላይ በተከፈተው ጦርነት የቀጠናውን ሰላም ለማረጋገጥ ሳይታክቱና ሳይተኙ የሚሠሩት ዶክተር ክንዴ፤ በተግባሩ ሲሳተፉ ደጋፊ፣ ኃላፊነትን ተግባሪና ከአስፈለገም በሚል ስልጠና ወስደው ውትድርናን ለመቀላቀል በመወሰን ነው። ሕዝቡ ራሱን ከመጠበቁ ባለፈ ፈጥኖ ወደ ልማት እንዲገባም በማድረግ ነው።
ዶክተር ክንዴ የተጣላን አስታራቂ፤ ሰውን በሰውነቱ ተገቢውን አክብሮት የሚሰጡ፤ በሥራቸው ታታሪ፤ ከማንም በፊት ቀድመው በመገኘት ተግባራትን የሚከውኑ የአገር ፈርጥ ሲሆኑ፤ ይህ ባህሪያቸው በአንዳንድ ጥቅመኞች ዘንድ አልተወደደላቸውምና ብዙ ስቃይ እንዲያሳልፉ የሆኑም ናቸው። በተለይ ጅግጅጋ ላይ የገጠማቸው ችግር ዛሬ ድረስ አይረሳቸውም። ምክንያቱም ቤታቸው ጋይቷል፤ ሀብት ንብረታቸው ጠፍቷል፤ ቤተሰባቸውም ተንገላቷል።
ይሁን እንጂ በሕዝብ የተደረገ ስላልሆነ አይከፉበትም። እንደእርሳቸው እሳቤ ‹‹ሕዝብ በምንም መልኩ በታማኝነት ያገለገለውን ሰው አይጎዳም፤ አያንገላታም፤ አገርንና ሕዝብንም የማይወዱ ሰዎች ካልሆኑ በስተቀር።
ተግባሩ የተፈጸመው ለምን ሕዝብ ወደደህ በሚል ጥላቻና የአገር ንብረትን አትነኩም በመባላቸው ቂም ስለያዙ ነው። ለዚህም ማሳያው ሕዝብ አድርጎት ቢሆን ኖሮ ራሱ የሰራልኝን አያወድመውም፤ መልሶም ሊጠግነው አይፈልግም። የደረሰውን ጉዳትም ሊመልሰው አይችልም። ዛሬ ድረስ የቤተሰቤ ጠባቂም አይሆንም። ስለዚህም ስላደረጉልኝ እንጂ ስለሆነብኝ አላነሳም። እንደውም አመሰግናቸዋለሁ›› ይላሉ። አሁን በሚሠሩት ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የገቡት በፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር አስበው ሲሆን፤ ሁለተኛ በመውጣታቸው የተነሳ የትምህርት ክፍሉ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።
ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋርም ሆነ ከአመራሩ ጋር እንዲሁም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ጥሩ ግንኙነት ስላላቸው ሥራዎቻቸው ስኬታማ ናቸው። በተለይም በዚህ አገር ችግር ላይ ባለችበት ወቅት ግዴታቸውንና ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሳይታክቱ መሥራታቸው ከምንም በላይ የሚደሰቱበት ነው። ቤቴ የሚሉት ነገር ሳይኖራቸው መጀመሪያ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሚያነሷቸው የብሔር ግጭቶች ምክንያት አደጋ እንዳይፈጠር ለማድረግ ዩኒቨርሲቲውን ቤታቸው አድርገው ሲሰሩ ቆይተዋል። አሁንም አካባቢው የጦርነት ቀጠና በመሆኑ ከዚህ ችግር የመታደግ ኃላፊነት የእርሳቸውና መሰሎቻቸው እንደሆነ ስለሚያምኑ ከዩኒቨርሲቲው ሳይወጡ ሥራዎችን ያከናውናሉ።
ወጡ ከተባለም ግንባር ድረስ በመሄድ መደገፍና የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ ነው። በዚህም ደስተኛ ናቸው። ‹‹ጦርነቱ እኛ ጋር ደርሶ ቢሆንስ ብለን ነው እያሰብን የሠራነው። ደርሶም ነበር። ሆኖም በጥምር ጦሩ አይበገሬነት እኛ ድነናል። በእርግጥ እኛም ብንሆን ተዘጋጅተን እየጠበቅን ነበር። በብዙ መልኩ ስልጠና ወስደንም የመጣውን ለመመከት በተጠንቀቅ ነን። ጠላት ሲመለስና ሲመከት ደግሞ ጠላትን ለመከተው፣ አካልና ሕይወቱን ለሰዋልን ወታደርና ማህበረሰብ የበኩላችንን አለማድረጋችን ራስ ወዳድነት ብቻ ሳይሆን አገርንም ከመክዳት አይተናነስም ብለን በማሰብ እንደ ተቋምና እንደግለሰብ ለወገን ጥምር ጦር የበኩላችንን ብዙ አድርገናል።
ከእነርሱ መሰዋዕትነት አንጻር ግን ገና መክፈል ያለብን ዋጋ አለ›› ይላሉም። ከዚህ በላይ ቀድመው ቢያደርጉ ኖሮ ሌሎች ከተሞችና ሕዝብን ማዳን ይቻል እንደነበር የሚያስረዱት ዶክተር ክንዴ፤ አሁንም ቢሆን በሥራ ላይ ያሉ ኃላፊዎች ሞዴል በመሆን፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለአገር በሚመጥን መልኩ መከወንና በምንም የማይደራደሩና ለሕዝብ የሚሞግቱ መሆን እንዳለባቸው ይናገራሉ።
የሕይወት ፍልስፍና
በረከትን ይሰጣል ብለው ማመናቸው ነው። ሰው ከረባት አስሮ፣ በቤት መኪና እየሄደ፣ በተደላደለ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሕዝብን የሚሰርቅ ከሆነ ተዋርዷል የሚል መርህ አላቸው። በዚህም ጉቦ መቀበልና መለመን ራስን ከማዋረድና ከማቅለል አይተናነስም ባይ ናቸው። በተለይም ሕዝብ በሰጠ ኃላፊነት ተጠቅሞ በእጅህ ና! ማለት እጅግ መዝቀጥ ነው ይላሉ። በአገር ላይ መቀለድም ነው ብለው ያምናሉ። በመሆኑም ሰው ሲስገበገብና ሊያግበሰብስ ሲሞክር መምከር ያስፈልጋል።
ካልተመለሰ ጊዜ ይመልሰዋልና ለድርጊቱ ተባባሪ አለመሆን ያስፈልጋል ብለውም ያስባሉ። የሰው ልጅ በሕይወት ሲኖር መልካምም ሆነ ክፉ ነገር ይገጥመዋል። እነዚህን በበጎ ነገራቸው እየተጠቀመባቸው ከመጣ ሁልጊዜ አሸናፊ ይሆናል፤ ሌላው የሕይወት መመሪያቸው ነው። ምክንያታቸውም በጎነት ይቅርባይነት፤ አርአያነት፤ በረከትን ማፈሻና መመስገኛ ከሚያገለግሉት ማህበረሰብ ሳይነጠሉ መኖርና ያሰቡትን ማድረግ ነው ብለው ያምናሉ።
መልዕክት
መደመጥ በጸሎትና በተዓምር አይመጣም። ቡድን በመመስረት አለያም ተከታይ በማብዛት አይፈጠርም። በሥራና አምኖ በሚከተል እንጂ። ስለዚህም መሪዎች በቻሉት ሁሉ የሚደመጡና የተናገሩት የሚተገበርላቸው መሆን ላይ ሊሰሩ ይገባል። ከስነ ምግባር እስከ ሥራ ድረስ አስተማሪ መሆንም አለባቸው። እሺ እንዲላቸውና እንዲረዳቸው ማድረግ ላይም ሊታትሩ ይገባል። አብሮ ሊያኖረውና ሊያሠራው የሚችለውን ስነልቦና መገንባትም ያስፈልጋል።
ከዚያ ሕዝብ ተከታይ በመሆኑ ችግሮች በቀላሉ ይፈታሉ፤ በቀጣይም እንዲህ አይነት አገራዊ ችግሮች አይፈጠሩም የመጀመሪያው መልእክታቸው ነው። ሌላው ያነሱት ነገር ጦርነት ጥሩ ባይሆንም አሻራን ማሳረፍ ላይ ያለውን ደስታ ነው። በአሁኑ አገራዊ ችግር ላይ ብዙዎች መሳተፋቸው የታሪክ አካል የመሆናቸው ምልክት እንደሆነ ያወሳሉ። በደስታ ጊዜና በሀዘን ጊዜ የመገኘቱ ዋጋ ከታሪክ አንጻር ልዩ ልዩ ነውና አሁን በሕልውና ዘመቻው ጊዜ የተገኘ ሁሉ ታሪክ ሰሪ እንደሆነ ሊያስብ ይገባል ባይ ናቸው።
የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውንም ሊያምኑበት ይገባል ይላሉ። በዚያው ልክ ያላለቀ ብዙ ነገር ስላለ መሳተፋቸውን ማቆም የለባቸውም። ታሪክ ሰሪነታቸውን እስከ መጨረሻው ሊያስቀጥሉ ይገባልም ሲሉ መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ። ለአርሶ አደሩ ከ150 ሄክታር መሬት ያላነሰ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ሲያጭድ፤ ወታደራዊ ስልጠናዎችን ሲወስድና በግቢው ውስጥ አስፈላጊውን ተግባራት ሲፈጽምና እንዲፈጸም ሲፈቅድ እንዲሁም ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር እንዲያግዙ ሲጠይቅ በብዙ መልኩ እንደተሳተፈና ማህበረሰቡን እንዳገዘ ያስበዋል።
ከምንም በላይ ለሌሎችም ምሳሌ እንደሚሆን ያምንበታል፤ ሆኖበታልም። በቀጣይም ቢሆን ዩኒቨርሲቲው ብቻ ሳይሆን ሁሉም የታሪኩ አካል የነበሩ ዜጎች በልማቱም ሆነ በሌሎች እገዛዎች መሳተፋቸውን ማጠንከር አለባቸው የሚለው መልእክታቸው ነው።
አሁን ሕዝብ የሚጠነክርበት እንጂ በመጣው ነገር ሁሉ የሚረበሽበት፤ የሚጨነቅበትና አንድነቱን የሚንድበት ጊዜ ላይ አይደለም። ምክንያቱም የጠፋውን አንድነት ያገኘንበት ጊዜ ይህ ወቅት ነው። ስለዚህም በጦርነቱ አንድነታችን ኃይል ሆኖን በርካታ ድሎችን እንዳስመዘገብን ሁሉ፤ በቀጣይም የጀመርነውን ሕብረት አጠናክረን ታላቂቷን፣ የማትደፈረዋን ኢትዮጵያን መገንባት አለብን። በድንገተኛ ነገሮች መፈርጠጥና አንድነትን መበተን አይገባም። ጉዳዩ የስነልቦና ጨዋታ መሆኑን ተረድተን ነቅተን አገራችንን መጠበቁ ያስፈልገናል።
ማንም አንድነታችንን እንዲሰብረው መፍቀድ የለብንም። እርሱ ከተመታ አገር ይጠፋል። ሌላው ደግሞ መንግስት ጆሮው ሰፊ ነው። ለእኛ የተሳሳቱ የመሰሉን አስተሳሰቦች፣ ስህተት ላይሆኑ ይችላሉ። ምክንያቱም መንግስት አገርን የሚንድና ሕዝብን የሚያስጠቃ ተግባር በምንም መልኩ አይፈጸምም። በተለይም አንድነታችንን በሚያፈርስ መልኩ ይሠራል ተብሎ መታመን የለበትም። የአንድነትን ጥቅም ስለሚረዳው። በመሆኑም ትችታችንን በልክ ማድረግ ይገባናል።
እገዛ የሚያስፈልግበት ሊሆን ይችላልና፤ በተለይ ምሁራኑ አገርን በመታደጉ ዙሪያ መሥራት ይኖርባቸዋል። መመካከር ላይ ትኩረት ማድረግ ተገቢ ነው። ከዚያ ያለፈው ለጠላቶቻችን በር መክፈት ነውና ጥንቃቄ ያስፈልገናል። ደካሞች ሆነን መታየት የለብንም፤ ድክመቶቻችንን ለጠላቶቻችን መፈንጠዢያ ልናደርጋቸው አይገባም የሚለው የመጨረሻ መልዕክታቸው ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥር 8/2014