የይቅር ባይነት ትሩፋቶች ዘርፈ ብዙ ናቸው። ወዴትም ሳንሄድና ከየትም ነገር ጋር ሳናያይዘው ወደ ራሳችን ውስጥ ጠልቀን ብናየው እንኳ ይቅር ባይነት ትልቅ የህሊና እርካታ ይሰጠናል። የበደለንን ይቅር ስንል ህሊናችን እረፍት ያገኛል። ሁለንተናችን ሰላም ይጎናፀፋል። ሲያቆስሉን፣ ሲያሳስቡን፣ ሲያበሳጩንና ሲያውኩን የነበሩ ከበደሉን ሰዎች ጋር የተያያዙ ሃሳቦች ሁሉ እንደ ጢስ ብን ብለው ይተኑና ይጠፋሉ። በፍፁም እንረሳቸዋለን። በተፈጥሯችን ተበቃይ ባንሆንም እንኳን ምንም ያህል ትንሽ ቢሆንም የቁጭትና የቅሬታ ስሜት ሳይሰማን አይቀርምና ይቅር ባይ ስንሆን ይሄ ሁሉ ቅሬታ ሳይተው ከውስጣችን ይተናል። ውስጣችን ንፁህ ይሆናል።
የይቅር ባይነት ትሩፋቶች እንደ ግለሰብ ከሌሎች ጋር ላሉን ግንኙነቶች ያለው አስተዋጽዖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ትናንት በጠላትነት ሲያየን የነበረ ሰው ይቅር ስንለው ለእኛ የነበረው አመለካከት ይለወጣል። ምንም ያህል የበደለን በደል እንደተራራ ቢገዝፍና እንደ ውቂያኖስ የሰፋ ቢሆን እኛ ይቅር በማለት ምህረት ያደረግንለት መሆኑን ለማመን ቢከብደውም ሁለተኛ እኛን ወደ መጉዳት አይመለስም። እኛን ፈጥኖ ወዳጅ ማድረጉ ቀድሞ የበደለን የራሱ ሥራ እያጠራጠረ በመፈታተን ቢያስቸግረውም ምን አልባት እንዲርቀንና ከሕይወታችን እንዲወጣ ያስገድደው ይሆናል እንጂ በፍፁም ዳግም ፈተና እንዲሆንብን እንዲሁም እጁን እንዲያነሳብን አያደርገውም።
ጊዜ ቢወስድበትም ከእኛ ይቅር ባይነታችን ግለሰቡን ወይም ግለሰቧን እየቀየረው ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሰዎች ያለውን ጭምር ጎጂ የሆነ አመለካከት ቀስ በቀስ እየሸረሸረው፣እያሻሻለውና እየለወጠው ይመጣል።
እዚህ ጋር ሰሞኑን መንግሥት በይቅርታ እንዲፈቱና ክሳቸው እንዲቋረጥላቸው ያደረጋቸውን የፖለቲካ መሪዎች ለአብነት እናንሳ ፤ መሪዎቹ በግልም በቡድንም እንደ አገርም ሆነ እንደ ሕዝብ የፈፀሙብን በደል ቀላል እንዳልሆነ ሁላችንም እናውቀዋለን።
በብዙ መልኩ አገርና ሕዝብን በድለዋል ፣ የአገርን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከቱ ተግባራትን ፈጽመዋል፤ አንዳንዶቹ ቀድሞ የፈፀሙት ድርጊት ከሰይጣን በላይ ሊመስለን ይችላል። ምህረታችን ከድርጊታቸው የሚመልሳቸው ስለማይመስለንም እንሰጋም ይሆናል። ግን ደግሞ ይቅርታ የተደረገላቸው ሰዎች እድሉ ቢሰጣቸው ያልተገመተ ነገር ሊሆን ይቻላል ። እድሉን ተረድቶ በአግባቡ መጠቀም የነሱ ፋንታ ነው ።
ግለሰቦቹ በሰው አምሳል የተፈጠሩ ሰው እስከሆኑ ድረስ አይለውጣቸውም የሚል ሥነ ልቦናዊም ሆነ ማሕበራዊ ሳይንስን መሰረት ያደረገ ማስረጃ ማቅረብ አንችልም። አይሆንም እንጂ ከእኛ ይቅር ባይነታችን ካልተማሩና ዳግም ወደ ጥፋታቸው የሚመለሱም ቢሆን የተቋረጠውን ክስ መዝገብ ከፋይል መልሶ መምዘዝ ዋስትና ሊሆነን እንደሚገባም መዘንጋት አይገባንም።
እንደ ማሕበረሰብና እንደ ሕዝብ ሲታሰብም ቢሆን ከእኛ ይቅር ባይነት ያሉት ትሩፋቶች ብዙ ናቸው። ለአብነት ባለፈው ጥቅምት ሰሜን እዝ በነበረው የጀግናው መከላከያ ሠራዊት ላይ የሽብር ቡድኑ ጥቃት ካደረሰና እንደ አገር ወደ ጦርነት ከተገባ ጀምሮ የአማራና የአፋር ማሕበረሰብና ሕዝቦች ተጎራባች ከሆነው ከትግራይ ክልል ማሕበረሰብና ሕዝብ ጋር ጦርነት የገቡበት ግልፅ ሁኔታ ባይኖርም አገራቸውን ኢትጵያን ለመበተን ከተመኘውና ምኞቱን ኢትዮጵያን በመውረር ጭምር ካሳየው ከአሸባሪው ቡድን ጋር ግልፅ ጦርነት መግባታቸው ይታወሳል።
ይሄ ሁኔታ ደግሞ ‹‹አፍንጫ ሲነካ ዓይን ያለቅሳል›› እንዲሉት ተረት በክልሎቹና በማሕበረሰቡ መካከል ቀጥተኛ ቅሬታ ፈጥሯል ተብሎ ባይታሰብም የሽብር ቡድኑ ወገኖች በሆኑ የተወሰኑ የትግራይ ክልል የሕብረተሰብ ክፍሎችና በአማራና በአፋር በአጠቃላይም በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ቅሬታ አልፈጠረም ማለት አይቻልም። በመሆኑም ከመንግሥት የመጣው የእኛ ይቅር ባይነት ይህን ቅሬታ በመፍታት በኩል ዓይነተኛ መፍትሄ የሚሆን ቱሩፋት ይኖረዋል።
እነዚህ ወገኖች ቅሬታቸውን አንስተው ቀድሞ ወደነበሩበት የእርስ በእርስ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ መስተጋብራቸው እንዲመለሱ በማገዝ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጾ ያደርጋል። የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን ያጠናክራል። የእርስ በእርስ መተማመን እንዲኖራቸው ያስችላል። የእኔ የሚሏቸው ባህላዊም ሆኑ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ እሴቶቻቸው ሳይነኩና ሳይበረዙ ለአንድ አገር አንድ ሆነው በጋራ እንዲሰሩ በማድረጉም ረገድ የሚኖረው አስተዋጾ በቃላት ብቻ ሊነገር የሚችል አይሆንም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በምህረት የተፈቱትንና ክሳቸው እንዲቋረጥላቸው የተደረገውን የሕብረተሰብ ክፍሎች አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር “ይቅር ባይነቱ ለልጅ ልጆቻችን ቱሩፋት አለው ። የትኛውም ዓይነት ቅሬታና ቂሞች ወደ ትውልድ እንዳይሻገርና ሌላ ተጨማሪ ቂም በቀል እንዳይፈጠር ያደርጋል። ለሌሎች ቀጣይ ግጭቶች መነሻ ሆነው ትውልዱን እንዳያምሱ ያስችላል” ነበር ያሉት ።
‹የውሾን ልጅ ውሾ በላው›› እንዲሉት ተረት የትኞቹም ዓይነት መጥፎ ነገሮች የቅሬታና የግጭት ምንጭ በማይሆኑበት ደረጃ ለዘለዓለም ተቀብረውና ተዳፍነው እንዲቀሩ በማድረጉ ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍ ያለ ነው። ከእኛ ይቅር ባይነት ሰላምና ስምምነት ያወርድልን።
ከእኛ ይቅር ባይነት እንደ አገር የሚኖረውም ፋይዳ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ። በተለይ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ እዛም እዚህም ያሉ ግጭቶችን በማስቆምም ሆነ ምንጮቻቸውን በመዝጋቱ ዓይነተኛ መፍትሄ ይሆናል። የምንጋጭባቸው ነገሮች ብዙ ቢሆኑም ቢያንስ እንዲቀነሱ በማድረግ በኩል አበርክቶ አለው። እንዲታጠቡ በማድረግ በኩልም የራሱን ሚና ይጫወታል። ችግሮቻችን በጠበቡ ቁጥር እንቀራረባለን። በተቀራረብን ቁጥር አንድ እንሆናለን። አንድ በሆንን ቁጥር ደግሞ የውጭ ኃይሎችን መግቢያ ቀዳዳ በር እንዘጋለን። በር ስንዘጋ በአንድ በኩል ሙሉ በሙሉ ወደ ራሳችን እንመለሳለን። ስንመለስ ራሳችንንም ሆነ ሀገራችንን ከዕውቀት ጀምሮ በሁሉም መስክ እናሳድጋለን። በግልም በጋራም የሰራነውን የጥረታችን ያህል እናድግና ድህነትን እናሸንፋለን። በዋናነት የሚያናቁረን ድህነት በመሆኑ ከእኛ ይቅር ባይነት ቱሩፋት እኛንም ከግጭት ሀገራችንንም ከመበተን እንታደጋለን። እንደ መንግሥትም ከውስጥም ከውጭም ኃይሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ይኖረናል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥር 8 ቀን 2013 ዓ.ም