እኔ ምለው ወገን! ይሄ ዲያስፖራዎችን የተቀበልንበት፣ ተቀባብለን ያዜምነው ማጀቢያ ሙዚቃ ማለቴ ሳል/ማሳል ማለቴ ነው/ እንዴት ነው ተገታ ወይስ ዲያስፖራዎቹ እስኪሄዱ ይቀጥላል።
አቤት ኡሁ… ኡሁን ዘንድሮ ኖርነው፤ ሰማነው። እንደ ጉድ ተቀባበልነው። ጉንፋን ነው እያልን ተዘናግተን ኮሮና ሆኖ ወይ ጉድ ያሰኘን ብዙ ነን፤ አንዳንዶች ደግሞ ግብሩ አንድ ሆኖ ስሙን ለማቅለል “ምን ጉንፋን እኮ ነው፤ አትፍሩ” እያሉ ተዳፍረውት ቆይተዋል፤ ወረርሽኙ መቼም ያልገባበት ቤት፣ ሰፈር፣ወዘተ የለም፤ ለመሆኑ እንዴት አደርጓችሁ ይሆን? አቤት ቆረጣጠመኝ፣ እንቅልፍ አሳጣኝ፤ ሳሉ እረፍት ነሳኝ ያላለ ማን ነው? በጋራ ኡሁ… ኡሁ ያላሰኘው ቤተሰብ አለወይ? ድምፁን ያላጎራናውስ ኧረ ማን ነው?። እንኳን አቀለለልን እንጂ እንደ ስርጭቱ ስፋትማ ቢሆን ጎበዝ አልቀን ነበር።
ደሞ ግጥምጥሞሹ፤ ሆይ ጉድ፤ ለስንት አመት ተለይተናቸው የቆየናቸው ከውጭ የመጡ ዘመዶቻችንን አቅፍን እንዳንስም አደረገን እኮ። ይሁና ! አቅለው እንጂ አታምጣው አይባልም አይደል? ለማንኛውም እንኳን አቀለለልን።
በበዛ የጦርነት ማጥ ውስጥ ገብተን፣ በአገራዊ ጉዳዮች እረፍት አጥተን ፋታ ሳናገኝ የጉንፋኑ ማለቴ የኮሮናው ደሞ ምን የሚሉት ነው። ዘንድሮ ጠላት በዝቷል፤ ማር እንጂ ለምን አሳመምክ አይባልም፤ ዋናው ቆፍጠን ማለቱ ላይ መበርታት ነው እንግዲህ። አሁንም መጠንቀቅ አይከፋም።
ምን አልባት ብዙዎቻችንን ሳይጠናብን ቆረጣጥሞ ቢለቀንም፣ በዚሁ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ጥቂት አለመሆናቸውን ማወቁ መልካም ነው። አሁንም ተጓዳኝ ህመም ያለባቸውና ደካሞች ዘንድ ሲደርስ የሚያስከትለው መዘዝ ከባድ ሊሆን ይችላልና ጠንቀቅ ማለት ያስፈልጋል። ትንሽ ጉንፋን ይዞኝ ነው፤ ሌላ አይደለም ብሎ ሊጨብጠን አልያም አስጠግቶ ሰላም ሊለን የሚፈልግ ሰው ሊያጋጥመን ስለሚችል ርቀትን መጠበቁ ላይ እንበርታ። ዲያስፖራዎቻችን ሳላችንን ሰምተውና ሁኔታችንን
አይተው ምን ብለው ይሆን? የሚገርመው እነሱ ሊመጡ ሲሉ በሽታው ማገርሸቱ ነው። ሳሉ እንግዶቹን ልንቀበልበት ያዘጋጀነው ማጀቢያ ሙዚቃ ይመስል ነበር።
መቼም መዲናችን አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን አገራችን አገራዊ ጥሪ ተቀብለው በመጡ ዲያስፖራዎች ተሞልተዋል። እናም አገራዊ ናፍቆታቸውን እየተወጡ ካሉት ዲያስፖራዎች ጋር ባንድም በሌላ መልክ ተገናኝተናል።
መገናኛ ብዙሃኑም ውሏቸውን አመላክተውናል። ዲያስፖራዎቹ የአሁኑ የአገር ቤት ጉዟቸው ዘና የሚሉበት እንዳልሆነ ሲናገሩ ሰምተናል፤ ይህ ወቅት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተጎዱ አካባቢዎችን በመጎብኘትና የሚረዱ ወገኖቻቸውን በመደገፍ በጎ ተግባር ላይ የተሰማሩ የቁርጥ ቀን ልጆችን አሳይቶናል።
በወረራው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የአልባሳት፣ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም ለተዘረፉና ለወደሙ የጤና ተቋማት መድሐኒትና የህክምና መሳሪያዎችን ይዘው መጥተዋል። ዲያስፖራዎች በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት ለአመታት ያፈሩትን ጥሪት ይዘው በመምጣት አገሬ፣ ቤቴ ብለው ሀላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
ሰፊ ሀሳብ ይዘው የመጡም አሉ። ለአገር ጠቃሚ የሆኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ነድፈው ተግባር ላይ ሊያውሉ የመጡና ያላቸውን ሀብት በኢንቨስትመንት መልክ በማዋል ለአገራቸው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋፅኦም ለማድረግ እየታተሩ ይገኛሉ።
እነዚህ የቁርጥ ቀን ልጆች አገራቸው ልጆቼ ስትል “አቤት” ያሉና አለኝታነታቸውን ያረጋገጡ ጀግኖች ናቸውና ደጋግመን ማመስገን ይገባናል። ከዚህ በተፃራሪ የቆሙም ገጥመውናል። ብሄራዊ አካባቢ ከጓደኛዬ ጋር ሻይ ቡና እያልን በመጫወት ላይ ሳለን ከ6 ዓመት በፊት ዲቪ ሎተሪ ደርሶት አሜሪካ የሄደ አንድ ጓደኛችንን ፊት ለፊት አየሁና ተጠራጥሬ ጠራሁት። “ ኦ ማይ ጋድ …ማይ ፍሬንድ ..አይዶንት ብሊቭ… ”እያለ መጥቶ ሊጠመጠምብኝ ሲል ወዳጄ ኮሮና ኮሮና ብዬ ክርኔን ደገንኩለት። ቁጭ ብለን ብዙ ተጨዋወትን።
በፊት እዚህ እያለ እናደርጋቸው ስለነበሩ ነገሮች፣ ስለ ሸገር ለውጥና የሰው ሁኔታ፣ እዚያ አሜሪካ ስላለው ህይወት … ብቻ ብዙ አነሳን ጣልን። ‹‹እንዴት እዚህ ሰፈር ተገኘህ›› አልኩት፤ ሰፈራችን ሩቅ ነበር።
ለምንዛሬ መምጣቱን ነገረኝ። እዚያ ያለህበት ሰፈር ባንክ የለም እንዴ? ስለው “ብላክ ነው፤ ይሄኛው አሪፍ ይጨምራል አሉ”ብሎኝ አረፈው። ይሄኔ ትከሻውን መታ መታ እያደረኩ እንደ ጨዋታ አድርጌ ለአገራችን መጣንልሽ ብላችሁ መጣችሁባታ አልኩት፤ ህገ ወጥነት ማበረታታት ላይ መገኘቱ አብሽቆኝ።
ባንክ ቢዘረዝር አገሪቱ ተጠቃሚ እንደምትሆን በማሰብ ለአገርህ ቢያንስ የያዝከውን ምንዛሬ በህጋዊ መንገድ በመመንዘር ውለታ ብትውል አሪፍ ነው ብዬ ልመክረው ስቃጣ ‹‹ግን እኮ ያው ነው፤ አልሸሹም ዞር አሉ ነው፤ ገንዘቡ አገር ውስጥ እስከ አመጣ ድረስ እዚያም እጅ ገባ እዚያ ያው አይደለም ወይ ሲል በጥያቄ መልክ ሀሳቡን ሰነዘረ። ለየት ባለ መንገድ ሊሞግተኝ ሞከረ።
በጨዋታ በጨዋታ እያረግሁ ማስረዳቴን ቀጠልኩ። የውጭ ምንዛሬ ጥቁር ገበያ ሲሄድ ለህገወጥ ተግባር እንደሚውል፣ በአሁኑ ወቅት ትህነግ እያካሄደ ያለው ወረራም የገንዘብ ምንጩ አንድም የጥቁር ገበያው መሆኑን አስረዳሁት።
በባንክ ሲመነዘር ለአገራዊ ጉዳይ አንደሚውል፣ አናንተ ያመጣችሁትን የውጭ ምንዛሬ ሀገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንደምትፈልገው፣ ለደህንነትም ቢሆን የሚሻለው ባንኩ መሆኑን አስረዳሁት። ትንሽ ዝምታ ውስጥ ገባን።
ዝምታውን ለመስበር እስቲ ወደ ሰፈር እንሂድ ስለው በሀሳቤ ተስማማ። ጉዞ ወደ ሰፈር ተጀመረ። ቆይቶ ቆይቶ በሀሳቤ ተስማማ። እሱ የውጭ ምንዛሬው አገር መግባቱ ብቻ የሚበቃ መስሎት ነበር። ከዚህ በሁዋላ ባንክ እንደሚመነዝርም አረጋገጠልኝ። እዚህ ላይ ጥጃ ጠባ ሆድ ገባ ብሎ ነገር የለም። ሁለቱ መንገዶች ፍጹም የተለያዩ ናቸው።
የሚገርመው አብረውት የመጡ ዲያስፖራ ጓደኞቹ በተመሳሳይ መንገድ የውጪ ምንዛሬ በጥቁር ገበያው እንደሚቀይሩ ሲነግረኝ ገረመኝ። ለካስ እሱ ብቻ አይደለም፤ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ዲያስፖራዎች ጥቁር ገበያው አካባቢ ሲርመጠመጡ ይታያሉ።
ውድ ልጆቼ እንኳን ደህና መጣችሁ ብላ በተቀበለቻችሁ አገራችሁ ላይ ይህን አይነት ህገወጥ ተግባር መፈጸማችሁ ተገቢ አይደለም፤ ኧረ ደስ አይልም ።
አገሪቱ የውጪ ምንዛሬ ችግርዋን ለመቅረፍ የዲያስፖራዎች መምጣት አንድ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮላታል ብለን ስንጠብቅ አገሬ ብለው ከመጡት ጋር ተቀላቅለው የመጡት የአንዳንድ ዲያስፖራዎች ህገወጥ ተግባር አስገርሞናል።
በየስርቻው እየገቡ የጥቁር ገበያውን የሚያነፈንፉና የያዙትን የውጪ ምንዛሬ በህገ ወጥ ተግባር የሚመነዝሩ ሃላፊነት የማይሰማቸው ልጆችዋ ለዚያውም በዚህ ወሳኝ ሰዓት ላይ በዚህ ህገወጥ ተግባር ላይ በመታየታቸው አገራቸውና ኢትዮጵያውያን እንዴት ይታዘቧቸው ይሆን! አገራዊ ጥሪውን ተቀብሎ አገሬ ትፈልገኛለች ብሎ የመጣው ዲያስፖራ እንዳለ ሁሉ ከመጡት ጋር ያለ ዓላማ ወይም ለአፍራሽ አላማ የመጣ ስለመኖሩ የውጭ ገንዘብ በጥቁር ገበያ ለመመንዝር ከሚልከሰከሱት ዲያስፖራዎች መረዳት ይቻላል።
እነዚህ ህገወጦች የራስን ትንሽ ትርፍ ከማግኘት ይልቅ ትልቅ የሆነችውን አገራቸውን ማሰብ እንዴት ተሳናቸው ጎበዝ። አገሬን ብለው ከመጡት ጋር ተቀላቅሎ መጥቶ በአገር ላይ በህገወጥ ተግባር መሰማራት ምን ይሉታል ጎበዝ? አንዳንድ በመሰል አሳፋሪ ተግባር ላይ ያገኘናቸውን ዲያስፖራዎች ብንታዘብም፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው አገራቸው መጥተው ታሪክ እየሰሩ ባሉ ዲያስፖራዎች ተደስተናል።
በያሉበት አገር አገራዊ ሀላፊነታቸውን ድምፃቸውን በማሰማት ሲሟገቱ የነበሩት እነዚህ ኢትዮጵያዊያን ዛሬም አገሬ ኑልኝ ስትላቸው መሪ ሲጠራ ይመጣል ብለው በአገራቸው ተገኝተው በወራሪው ሀይል የወደሙ አካባቢዎችን እየጎበኙ ይገኛሉ፤ በወረራው የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ፣ የወደሙና የተዘረፉ ተቋማትን ከህዝብና መንግስት ጋር በመሆን መልሶ ለመገንባት ብቻ ሳይሆን አስበልጦ ለመገንባት እየታተሩ ይገኛሉ።
እነዚህን የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች ኢትዮጵያዬ ታመሰግናቸዋለች። አበቃሁ፤ ቸር ያሰማን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥር 7/2014