አዲስ አበባ፦ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሚገኘው የአርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም መቃብር ቦታ ሃውልት ሳይሰራለት መቀመጡ በታሪክ ተወቃሽ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ። የአርቲስቱ ቤተሰቦች እና ወዳጆች ደረጃውን የጠበቀ ሃውልት ለማሰራት ጨረታ ወጥቶ ስራው ሊጀመር መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ከፍተኛ የጥናት ባለሙያ መምህር መክብብ ገብረማርያም በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ አርቲስት ፈቃዱ ተክለማርያም በኢትዮጵያ የቴአትር እና ኪነጥበብ ስራዎች ላይ የጎላ አሻራ አሳርፏል። ለሌሎቸ ሙያተኞችም አርዓያ በመሆን በስራው አንቱታን ያተረፈ ነው። ነገር ግን መቃብር ቦታው አፈር ለብሶ ያለሃውልት ሲታይ ለተመልካቹም ያሳዝናል በታሪክም ተወቃሽ ያደርጋል። እንደ መምህር መክብብ ገለፃ፣ የአርቲስቱ ሃውልት ልክ እንደነ ጥላሁን ገሰሰ እና ሌሎች የአገር ባለውለታዎች ሀውልቱ ተሰርቶለት ለጉብኝዎች ክፍት መደረግ ነበረበት።
ይህን ማድረግ የሚያስችል አቅም ከሌለ የአርቲስቱን ወዳጆች እና መላው ኢትዮጵያውያንንአስተባብሮ ቋሚ መታሰቢያ ሃውልት በቦታው ማስቀመጥ ይቻላል። አሁን ግን መቃብሩ በላስቲክ የተሸፈነ እና ያልጸዳ በመሆኑ የአርቲስቱን ውለታ የማይገልጽ አሳዛኝ ድባብ እንዳለው ጠቁመዋል። የአርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ቤተሰብ የሆነው ሰዓሊ ዲሜጥሮስ ኪዳኔ፤ በእነ አቶ ኃይሉ ከበደ የሚመራው ኮሚቴ የሃውልት ስራውን ለማከናወን እየሰራ ይገኛል። ለሃውልት ስራ የሚሆን ጨረታ ወጥቶ በሶስት መቶ ሺ ብር ያሸነፈ አርቲስት ተገኝቷል። በመሆኑም ለስራው የሚያስፈልገው ሙሉ ክፍያ በኮሚቴው ስር ካለው እና ለአርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ማሳከሚያ ከተሰበሰበው አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ላይ ወጪ ይደረጋል።
እንደ ሰአሊ ዲሜጥሮስ ገለፃ፤ የአርቲስቱን የኪነጥበብ የአገር ውለታ ሊወክል የሚችል እና ለታሪክ የሚተርፍ ሃውልት ማቆም የቤተሰቡም ፍላጎት ነው። የሃውልት ስራው ንድፍ ተጠናቆ ቀርቧል። በመሆኑም በቀጣይ ጊዜያት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በሚገኘው የቀብር ስፍራው ደረጃውን የጠበቀ ሃውልት እንዲቆም ይደረጋል። እስካሁን ሃውልቱ ያልተገነባው ቀደም ብሎ የተቋቋመው ኮሚቴ በ«ጎ ፈንድ ሚ» አማካኝነት ለአርቲስቱ መታከሚያ ከሰበሰበው ገንዘብ ላይ ለሃውልት ስራ የሚሆን 350 ሺ ብር ለመክፈል ፍላጎት ባለማሳየቱ ነው መሆኑን ተናግሯል። ከአርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ የአርቲስተ ፈቃዱ ተክለማርያም ሥርዓተ ቀብር ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም መፈጸሙ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 30/2011
በጌትነት ተስፋማርያም