የአዲስ አበባ አስተዳደር ጥናቱን አላውቀውም ብሏል
አዲስ አበባ፡- በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት በ2009 ዓ.ም የተሰራውና በአዲስ አበባ ከተማ ምንም አይነት ሰው ሳይፈናቀል፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሳይፈጠር መኖሪያ ቤት መስራት የሚያስችለው ጥናት እስካሁን ተግባራዊ አለመሆኑን ተገለፀ፡፡ በአስተዳደሩ የመሬት ልማትና ከተማ አስተዳደር ኤጀንሲም ጥናቱን አላውቀውም ግን የራሴን አዲስ ጥናት እያጠናሁ ነው ብሏል፡፡
የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የከተማና መሰረተ ልማት ፖሊስ ጥናት ማዕከል መሪ ተመራማሪ ዶክተር ዘመንፈስ ገብረእግዚአብሄር ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ መንግስት አዲስ አበባን ጨምሮ በስድስት ዋና ዋና ከተሞች በመልሶ ማልማት ምክንያት በነዋሪዎች ላይ የሚደርሰውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ በወሳኝ መልኩ መፍታት የሚያስችል ጥናት በ2009 ዓ.ም ተጠንቷል፡፡ ጥናቱም እንደተጠናቀቀም ለሚመለከታቸው አስፈፃሚ አካላት ተግባራዊ እንዲያደርጉት ቢሰጣቸውም እስካሁን በተጨባጭ መሬት ላይ የወረደ ነገር የለም፡፡
እንደ ተመራማሪው ማብራሪያ፤ ጥናቱ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ መሃል አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በመልሶ ማልማት ምክንያት ለዘመናት ከኖሩበት መንደር ሳይፈናቀሉ፤ ማህበራዊ ትስስራቸው ሳይበጠስና የገቢና የስራ ዋስትናቸውን በማይጎዳ መልኩ ለ800ሺ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ማከናወን ያስችላል፡፡ ወጥና ባለድርሻዎችን ማዕከል ያደረገ ዘላቂና ተቀባይነት ያለው የከተማ መልሶ ማልማትን በማረጋገጥ ደረጃውን የጠበቀ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንዲመዘገብም ያደርጋል፡፡ ለዜጎችም የኑሮ ሁኔታ የበኩሉን ድርሻ የሚጫወት፣ ከልማትባሻገር ለአረንጓዴ ስፍራ ቦታን ማግኘት የሚያስችልና ከባቢያዊ ሁኔታ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዝ የፖሊሲ ማዕቀፍና ዝርዝር የአሰራር ስርዓት እንዲዘረጋም ትልቅ አቅም አለው፡፡
በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በመሃል አካባቢዎች እንዲገነባ ለማድረግ ጅምር ስራዎች ቢኖሩም ከዚህ ቀደም በመልሶ ማልማት ምክንያት የተፀዱ አካባቢዎች አሁን ድረስ ለልማት አለማዋላቸውና የተፈናቀለውም ህዝብ በመሰረተ ልማትና በትራንስፖርት እጦት ለእንግልት እየተዳረገ መሆኑን አንስተዋል፡ ፡ ይህም በነዋሪዎች ከፍተኛ ቅሬታ የፈጠረ ከመሆኑንም ባሻገር አገሪቱ ላቀደችው ሁለንተናዊ እድገት ማነቆ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ለታ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በከተማዋ መልሶ ማልማት ስራ ዙሪያ ስላስጠናው ጥናት ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸውና ሰነዱንም ማግኘት አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
ይሁንና በከተማዋ አዳዲስ አመራሮች ወደ ስልጣን መምጣት ጋር ተያይዞ መልሶ ማልማት ስራ ህብረተሰቡን ሳያፈናቅልና በተጨባጭ ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚገባ አዲስ አቅጣጫ መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡ በዚህ መሰረትም ኤጀንሲው ከተለየዩ ተቋማት የተውጣጡ አባላት ያሉበትን ኮሚቴ በማዋቀር አዲስ ጥናት ላለፉት አምስት ወራት እያከናወነ መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ጥናቱ መጠናቀቁንና በቅርቡም ለአስተዳደሩ ካቢኔ ፅህፈት ቤት በማቅረብ እንዲፀድቅ የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል፡ ፡ ጥናቱ ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት ግን ህብረተሰቡ እንዲወያይበት የሚደረግ መሆኑንና ከህብረተሰቡ ተጨማሪ ሃሳብ እንደሚወሰድ አስገንዝበዋል፡፡ እንደዋና ስራ አስኪያጁ ማብራሪያ፤ የአዲሱ ጥናት ዋነኛ ትኩረት መልሶ ማልማት ስራው ህብረተሰቡ በሙሉ ፈቃደኝነትና ተሳታፊ ሆኖ የራሱን ቤት ባለበት ቦታ ላይ ለመገንባት ያስችለዋል፡፡
በተለይም የከተማዋ ፕላን በሚፈቅደው መልኩ ነዋሪዎች ተደራጅተው የመኖሪያ ህንፃቸውን እንዲገነቡ ሰፊ እድል ይሰጣል፡ ፡ ከዚህ ቀደም ይነሳ የነበረውን የምትክ ቦታና የካሳ ክፍያ ውዝግብም በከፍተኛ መጠን ይቀንሰዋል፡፡ ዶክተር ዘመንፈስ በበኩላቸው፤ የጥናቱ ባለቤት ምንም ኢንስቲትዩቱ ቢሆንም የተሰራው ለአገር ጥቅምና በመንግስት አቅጣጫ ተሰጥቶበት እንደመሆኑ የአስተዳደሩ ኃላፊዎች አያውቁትም የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ «እገሌ ያውቀዋል፤ አያውቀውም፤ ወደሚል ክርክር ውስጥ መግባት አልፈልግም፤ ነገር ግን ጥናቱ የተሰራው ከፍተኛ መዋለንዋይ ፈሶበት፣ ጉልበትና ጊዜ ወስዶ እንደመሆኑ በተጨባጭ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ በሰነድም መልክ ተዘጋጅቶ ለሁሉም አካል እንዲሰጥ አድርገናል» ብለዋል፡፡
በመሆኑም አመራሮቹ አዲስ ቢሆኑም እንኳን አሰራርና ስርዓት ተበጅቶለት ቢሆን ኑሮ ክፍተቱ አይፈጠርም የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ አክለውም «ይህ ማለት ግን አስተዳደሩ ለምን አዲስ ጥናት አስጠና በሚል ቅሬታ ኖሮኝ አይደለም፤ ማንኛውም ጥናት ከተጠና በኋላ አዳዲስ ነገሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ እንዲሁም ያልዳሰሳቸው ችግሮችም ሊኖሩ ስለሚችሉ የቀደመውን ጥናት መነሻ አድርጎ ማሻሻሉ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ» ብለዋል፡፡ ይሁንና በአዲስ መልክ ጉልበት ጊዜና ገንዘብ ወስዶ ያንኑ የሚደግም ጥናት መስራት ለአገርም ትልቅ ኪሰራ የሚያስከትል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ጥናቱ ተግባራዊ ሊደረግበት የሚችልበትን ጊዜ በመውሰድ ህብረተሰቡን ወደ ባሰ ምሬት ይከታል የሚል ስጋት እንዳላቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 30/2011
በማህሌት አብዱል