ሰላም ውድ የአዲስ ዘመን ቤተሰቦች፤ እንደምን ከረማችሁ፤ መቼም በአገራችን የሰላም እንጂ የግጭት አጀንዳ አጥተን አናውቅም፤ ሰሞኑን የከረምንበት አጀንዳም የዚሁ አካል ነውና እኔም የበኩሌን ጥቂት ሃሳብ እንዳነሳ መነሻ ሆነኝ።
ስለምን እንደማወራ ገብቷችኋል ብዬ ለመገመት ብዙ መመራመር የሚያስፈልገኝ አይመስለኝም፤ እንደው ለነገሩ ግን ግልጽ ለማድረግ ሰሞኑን አንዴ በእስረኞች መፈታት ሌላ ጊዜ ደግሞ በመስቀል አደባባይ፤ ከዚያም በጄኔራሎች ሹመት ምን ያህል ጊዜአችንን እንዳባከንን ሁላችንም ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን። እኔም የዚሁ አካል ነኝና የታዘብኩትን ለማለት ፈልጌ ነው “ኪቦርድ” ማንሳቴ።
ታዲያ ይህንን ሳስብ ከዚህ በፊት ያነበብኩት አንድ ታሪክ ትዝ አለኝ። ታሪኩ አመታትን ተሻግሯል። በሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የቀረበ ተረትን ያስቀደመ ፅሁፍ ነው። ውሾቹን “ተዉ” በሏቸው ይላል ርዕሱ። እኔም ተረቱን ለዛሬው ጉዳዬ ወስጄ ላወጋችሁ ወደድኩ። የሽማግሌ ምክር ! በማለት ጀመርኩ። ተረቱ እንዲህ ነው።
በአንድ መንደር ውስጥ ሮቤል መግራ የሚባሉ ጥበበኛ ሽማግሌ ነበሩ። አንድ ቀን የሁለት ጎረቤታሞች ንብረት የሆኑ ሁለት ውሾች ሲጣሉ ያያሉ። እኒህ ጥበበኛ ሽማግሌም «እነዚህን ውሾች እንገላግላቸው፤ ያለበለዚያ ችግራቸው ለሁላችንም ይተርፋል፣ በዓለም ላይ ችግር የሚነሣው ከአጥንት በላይ ማሰብ በማይችሉ ውሾች የተነሣ ነው» ይላሉ። በአካባቢው የነበሩ ሽማግሌዎች እና መንገደኞችም በሽማግሌው አባባል ተገርመው «ሁለት ውሾች ተጣልተው ምን ሊያመጡ ነው» እያሉ ሳቁባቸው።
በዚህ መካከል ከሁለቱ ጎረቤታሞች መካከል አንድ ልጅ ወጣና የውሾቹን ጠብ ተመለከተ። የእርሱ ውሻ የተበደለ ስለመሰለው ፍልጥ አምጥቶ ያኛውን ውሻ ደበደበው። ወዲያውም ከሌላኛው ቤት ሌላ ልጅ ወጣና ያኛውን ውሻ መደብደብ ጀመረ። ነገሩ ወደ ሁለቱ ልጆች ተዛመተና በውሾቹ ምትክ ልጆቹ ይደባደቡ ጀመር። ሽማግሌውም «እባካችሁ እነዚህን ልጆች አስታርቁ» አሉ። በሥፍራው የነበሩትም «ተዋቸው ይዋጣላቸው» ብለው እንደ ቀልድ አለፉት።
ልጆቹ እየተደባደቡ እያለ የአንዱ እናት ብቅ አለች። ወዲያውም ያኛውን ልጅ በፍልጥ ታንቆራጥጠው ጀመር። የልጇን ጩኸት የሰማችው ሌላዋ እናትም መጣች። የልጆቹ ጠብ ቀረና ድበድቡ በሁለቱ እናቶች መካከል ሆነ። ሮቤል መግራም «እባካችሁ ይህ ጠብ ተዛምቶ ሁላችንንም ከማካተቱ በፊት ገላግለን እናስማማቸው» አለ። ተመልካቾቹ ግን የሁለቱን ጠብ እንደ ነጻ ትግል እያዩ ይዝናኑ ነበር። አንዳንድ ሽማግሌዎችም «ሁለት ሴቶች ተጣልተው የት ይደርሳሉ» እያሉ ንቀው ተውት።
በግርግሩ የከበቡትን ሰዎች እየጣሰ አንድ ሰው ወደ መካከል ገባ። ያንደኛዋ ባል ነበር። እንዴት ሚስቴን ትመቻታለሽ ብሎ ያቺኛይቱን ሴት መደብደብ ያዘ። ይኼኔ ነገሩን የሰማው ሌላኛው ባልም ሲሮጥ መጥቶ ድብድቡን ተቀላቀለ። ሮቤል መግራ አሁንም «እባካችሁ ገላግሏቸው፤ ይህ ጠብ ለሀገር ይተርፋል» ሲሉ ተናገሩ። ሰሚ ግን አላገኙም።
ሁሉም የራሱን ልጅ፣ ሚስት እና ቤት ብቻ ይጠብቅ ነበር። ወንዶቹም ልጆቻቸው እና ሚስቶቻቸው እንዳይገቡ ይቆጡ ነበር። የሁለቱ ባሎች ጠብ ተባባሰ። ሕዝቡም ከብቦ ያይ ጀመር።
በዚህ መካከል የሰውዬው ወገኖች ነን ያሉ ያንደኛዋን ባል መደብደብ ያዙ። ተመልካች ሆነው ከቆሙት መካከል የዛኛው ወገን ነን የሚሉ ደግሞ ያኛውን ይዘው ይደበድቡ ጀመር። እንዳጋጣሚ የሁለቱ ሰዎች ጎሳቸው የተለያየ ስለነበሩ ጠቡ ወደ ጎሳ አደገ። ዱላ እና እጅ ብቻም ሳይሆን የጦር መሣሪያም ተጨመረበት። ቤት ንብረት መዝረፍ፣ ማቃጠል እና መግደል እየተባባሰ መጣ። መንደሩም የጦርነት አውድማ ሆነ። ከሁለቱም ወገን ስምንት ስምንት ሰዎች ሞቱ። በስንት መከራ ጠቡ ቆመ። ሮቤል መግራም አዘኑ። «ውሾቹ ሲጣሉ ብናስቆማቸው ኖሮ ጎሳዎቹ አይጣሉም ነበር» አሉ።
ሽማግሌዎቹ ጉማ ተቀመጡ። በባህሉ መሠረት ለእያንዳንዱ ለሞተው ነፍስ ከሌላው ወገን ሰው ይገደላል ወይንም መቶ መቶ ከብት ይሰጣል። ይህ ከሆነ ደግሞ ከሁለቱም ወገን ስምንት ስምንት መቶ ከብት ያስፈልጋል ማለት ነው። በሞቱት ምትክ ከሌላው ወገን ሰው ይገደልም ከተባለ በተጨማሪ አስራ ስድስት ሰዎች ሊገደሉ ነው። የሟቾቹም ቁጥር ወደ ሠላሳ ሁለት ከፍ ሊል ነው። ይህ ነገር ሽማግሌዎቹን አስጨነቀ።
ይኼኔ ሮቤል መግራ ተነሡ። «ቀድሞ እኔን ሰምታችሁኝ ቢሆን ኖሮ መልካም ነበር። እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን እንጂ ስለ ሌላችን ግድ ስለሌለን ዕዳው በመጨረሻ እኛው ላይ መጣ። ውሾቹን ተው ማለት አቅቶን እዚህ ደረጃ ደረስን። ምን ጊዜም ጦርነቶች የሚነሡት ውሾቹን ተው የሚል እየጠፋ ነው። ጎረቤት እና ጎረቤት፣ ጎሳ እና ጎሳ፣ ንጉሥ እና ንጉሥ፣ ሀገር እና ሀገር፣ ሙስሊም እና ክርስቲያን፣ መንደር እና መንደር፣ የሚጣላው ውሾቹን ተው የሚል እየጠፋ ነው። ውሾቹ በአጥንት የጀመሩት ጠብ ሕይወት አስከፈለን።
«እነዚያን ውሾች ለያዩዋቸው ስላችሁ ሁላችሁም የእናንተ ውሾች አለመሆናቸውን ብቻ ነበር የምታዩት። ሌሎች ተበጥብጠው እኛ እንዴት ሰላም እንሆናለን? ሌሎች እየተዋጉ እንዴት እኛ በደኅና እናድራለን? ሌሎች ተርበው እንዴት እኛ እንጠግባለን? የማይሆን ነገር ነው።
በሉ አሁንም ሌላ ሕይወት ማጣት የለብንም፣ ከብቶቻችንንም ማጣት የለብንም፤ ከሁለቱም ወገን የየአንገታችሁን የብር ማተብ አምጡ፤ ያንንም ሰብስባችሁ ወንዝ ውስጥ ጣሉ፣ ሁሉም ጦሱን ይውሰድ፤ እናንተ ግን ይቅር ተባባሉ» ብለው አስታረቋቸው ይባላል።
አዎ ዛሬ ይህ ተረት በተግባር እየታየ ነው። ዛሬ ላይ ጥቂት ውሾች ሲጣሉ ውሾቹን ከጥላቸው ከሚገላግለው ይልቅ ዳር ቆሞ የሚያይ ከዚያም በውሾቹ ፀብ ሌላ ግጭት እና ሁከት ለመፍጠር የሚሯሯጥ ትውልድ በስፋት እያየን ነው። እነዚህ የግጭት ነጋዴዎች በተለያየ መስክ የተሰማሩ ናቸው። ዛሬ ለዚህ ሁሉ ብጥብጥ መነሻ የሆኑት ጥቂት የአሸባሪው ሕወሓት መሪዎች ናቸው። በእርግጥ እነዚህ የሕወሓት መሪዎች ከዚህ ተረት ይለያሉ። እነሱ ተው ሲባሉ የሚሰሙ፤ ሽማግሌም የሚያከብሩ አይደሉም። ሆኖም በነሱ የተጀመረው ፀብ ዛሬ አገር ብዙ ጥፋት አስከትሏል።
እንደሚታወቀው አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ግማሽ ምዕተአመት የቆየ ድርጅት ነው። ነገር ግን በነዚህ አመታት አገርን በጠንካራ መሠረት ላይ ከማቆም ይልቅ ከስር ሲገዘግዝ የኖረ እና በመጨረሻም ከስሯ ለመጣል ሲሰራ የኖረ አሸባሪ ቡድን ነው። ቡድኑ ቀደም ሲል የነበረውን አገራዊ አንድነት ለመናድ ከመነሻው ጀምሮ ሲሰራ ኖሯል። በዚህ ከፋፋይ አስተሳሰቡም አገሪቱን በብሄር፣ በሃይማኖት በአካባቢ ወዘተ በመከፋፈል እና በውስጡም መርዝ በማስቀመጥ የተለያዩ ደባዎችን ሲሰራ የኖረ ነው።
ለዚህ ደግሞ በቅድሚያ የእንዲያመቸው የራሱን ካርታ አዘጋጀ። ቀደም ሲል የነበረውን የክፍለሀገር አደረጃጀት ቀልብሶ ለራሱ በሚመቸው መንገድ ክልሎችን መሠረተ። በዚህም የሚፈልጋቸውን አካባቢዎች ጭምር እንደሚፈልገው አድርጎ አደራጀ።
ከዚህ በኋላ በ27 አመታት የስልጣን ዘመኑም አንዱን ብሄር ከሌላው ጋር ለማጋጨት እና ታሪካዊ ጠላትነትን ለማኖር ሃውልት ጭምር እያኖረ ሕዝብን ለመከፋፈል ሞከረ። ከዚያም በብሄር ብሄረሰቦች እና በፌዴራሊዝም ስም ዜጎች እርስ በእርሳቸው ተስማምተው የጋራ አገር እንዳይገነቡ፤ የጋራ ሰንደቅ ዓላማ እንዳይኖራቸው እያረገ አገርን በመከፋፈል ኖረ።
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የራሱን የኢኮኖሚ ኤምፓየር በመፍጠር በኤፈርት ስም የአገሪቱን ኢኮኖሚ በጥቂት የቡድኑ አባላት ኮማንድ ፖስት ስር በማኖር አገሪቷን ለድህነት ለመዳረግ ባለ በሌለ አቅሙ ሁሉ ጥረት አደረገ። ይህ ሁሉ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ወደ ፀቡ አልገቡም። ነገር ግን በጊዜ ከዚህ ችግር እንዲወጡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይነግራቸው ነበር። ከዚያ በኋላ በመጨረሻ ችግሩ ተባብሶ ግጭቱ ሲፋፋም የለውጡ መምጣት ግድ ሆነ።
የሚገርመው ነገር ለውጡ ከመጣ በኋላም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለነዚህ ሃይሎች ያለፈውን ሁሉ ረስቶ ይቅርታ አድርጎ ነበር። ምንም እንኳ የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም የሚል አባባል ቢኖርም እነሱ ግን በተቃራኒው በመሆን የበላይነታችንን ዝም ብለን አንሰጥም በሚል ዳግም ወደሌላ ጥፋት ሄዱ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ሰሞኑን እንደተናገሩት ስድስት ዋና ዋና በደሎችንም ፈፀሙ።
ከለውጡ በተቃራኒ በመቆም ወደሌላ ጥፋት ገቡ፣ በዚህም መሠረት ከብልጽግና አፈንግጠው መውጣት፣ በራሳቸው ያዘጋጁትን ሕገ-መንግሥት በሚቃረን መንገድ ወደምርጫ መግባት፣ ሰሜን እዝን ማጥቃት፣ መንግሥት ለጥሞና ጊዜ ሰጥቶ መቀሌን ለቆ ሲወጣ ወደክልሎች ዳግም መዝመት፣ ከዚያም መንገዱ ተመቸኝ ብሎ ቁልቁል ወደደሴ መንደርደር ከፀብ ራሳቸውን ለመገላገል ፈጽሞ የማይፈልጉ ስለመሆናቸው ማሳያ ነው።
ነገር ግን እነዚህ ጥፋቶች ሁሉ በጊዜ ሊቀጩ የሚችልበት እድል ሰፊ ነበር። በነዚህ ሁሉ ጉዞዎች መካከል በአገራችን ባህል ሽምግልናን እንዲቀበሉ ያልተላከ የአገር ሽማግሌና የመንግሥት ባለስልጣን አልነበረም። ይሁን እንጂ ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም እንደሚባለው ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው በሚል ያካሄዱ ናቸውና ከያዙት የፀብ መንገድ ሊመልሳቸው የሚችል አንዳችም ኃይል አልተገኘም። እነዚያ ሁሉ የትግራይ ወጣቶች እስከሚያልቁ ድረስም ከዚያም አልፎ ዛሬም ድረስ ከፀብ መንገድ ወደሰላሙ የሚመልሳቸው ኃይል አልተገኘም። ገና በእንጭጩ ይህንን የፀብ መንገድ ማስቀረት ቢችሉ ኖሩ ያ ሁሉ ጥፋት ባልተከሰተ። ያ ሁሉ ንብረት ባልወደመ። እነሱም ዳግም ለብዙ አመት ወደኖሩበት የሰቆቃ ኑሮ ባልተመለሱ ነበር።
ሌላው ግንባር ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት የሚከፈቱት ፀቦች ናቸው። ይህ የፀብ መንገድ ብዙ ተዋንያን ያሉበት ነው። በአንድ በኩል ጭር ሲል የማይወዱ የጦርነት ነጋዴዎች አማካኝነት የሚከፈቱ የፀብ ጥሪዎች ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሽንጣቸውን ገትረው በሚሰሩ የውጭ ጠላቶች አማካኝነት የሚፈፀሙ ናቸው።
ከዚህ አንጻር ሰሞኑን የከረምንበትን ውዝግብ ማንሳቱ አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል።ሰሞኑን መንግሥት ጥቂት እስረኞችን ክስ በማቋረጥ ከእስር እንዲለቀቁ ባደረገበት ወቅት ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የውሻ ፀብ ለማስነሳት የሚሞክሩ በርካታ ተዋንያንን ተመልክተናል። በዚህ ውስጥ በእርግጥ ብዙ ተዋንያን እንዳሉ ጠቅላዩ ራሳቸው ተናግረው ነበር። በአንድ በኩል ሆን ብለው የማህበራዊ ሚዲያ አካውንት ከፍተው አንዱን ብሄር ከሌላው ለማጋጨት የሚሰሩ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳዩን በሰከነ አእምሮ ባለማየት ወይም አሸባሪው ሕወሓት ያደረሰውን ጉዳት ብቻ በመመልከት እንዴት መንግሥት ምህረት ያደርጋል በሚል በስሜት የሚነዱ አሉ። በአጠቃላይ በዚህም ሆነ በዚያ ግን እነዚህ ሁሉ የፀብ ምክንያቶች ናቸው።
ከዚህም አልፎ ሰሞኑን በመስቀል አደባባይ ጉዳይ የከረምንበት የውዝግብ ሌላው መነሻ ነው። እንደው ግን እንደ እምነት ሰው ብቻ ሳይሆን ከዚያ ውጭ ላለውም ቢሆን የተነሳው ውዝግብ ለፀብ የሚጋብዝ ነው ወይ ብለን ካየን ከዚህ በስተጀርባ ዛሬም በፀብ ትርፍ የሚያገኙ ሰዎች መኖራቸውን ከማሳየት ውጭ አንዳችም ፋይዳ ያለው አይመስለኝም።
ከሁሉ በላይ ደግሞ የሚገርመኝ ግጭቶች የሚነሱት ምናልባት ከፍ ያለ የትምህርት፣ የእምነት እንዲሁም የስነልቦና ዝግጅት አላቸው በሚባሉ አካላት ነው። እነዚህ ኃይሎች ደግሞ አሁን አገራችን ከገባቸበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በተቻለ መጠን ማረጋጋት እና ሕዝብ ሰከን ብሎ እንዲያስብ ለማድረግ መስራት የሚገባቸው ናቸው። ነገር ግን በእሳት ላይ ቤንዚን ሲያርከፈክፉ ማየት እንቆቅልሽ ነው።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ ህብረተሰቡም ቢሆን ወደግጭት ከመግባት በፊት ቆም ብሎ ማሰብ፤ ወደፊት እንደአገር ሊያቆመን የሚችለው መንገድ የቱ ነው ብሎ ማሰብን መለማመድ አለበት። ከዚህ በተቃራኒ ሆኖ ሁሉም እየተነሳ ዘራፍ እያለ የሚፎክር ከሆነ ነገአችን የተበላሸ ሊሆን ይችላል።
ለመሆኑ አሁን ባለው ሁኔታ አንዱ በሌላው ጉዳይ ጣልቃ እየገባ የሚያንቦራጭቅበት ምክንያት ምንድነው? የመንግሥት ጉዳይ የመንግሥት ብቻ መሆን ሲገባው ከታችኛው የሕብረተሰብ ክፍል እስከ ምሁሩ ድረስ መንግሥትን እሱ በሚፈልገው መንገድና በራሱ ልክ እንዲያስብ ለማድረግ የሚሞክር አለ፤ አንድ ጉዳይ ሲነሳ ስሙን በትክክል መፃፍ ከሚከብደው ጀምሮ እስከ ፕሮፌሰሩ ድረስ ሲከራከር ይውላል። በዚሀ መልኩስ እንዴት ወደአንድ ሊመጣ ይችላል?
አንዳንድ ጊዜ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰዎች ሰብሰብ ብለው ፖለቲካዊ ትንታኔ ሲሰጡ ሲታይ እኛ አገር ትምህርት ቤቶች ሁሉ የፖለቲካ ትምህርት ቤት ሆነዋል እንዴ የሚል ጥያቄን ያጭራል። በዓሉ ግርማ በኦሮማይ ላይ የስብሰባ ባህል ፈጥረናል እንዳለው አሁን ደግሞ የፖለቲካ ባህል ፈጥረናል እንዴ ያሰኛል። ፖለቲካችን ደግሞ የሚጥመን ሁሌ በውዝግብ የተሞላ ሲሆን ነው። መስማማትን እንደሽንፈት የሚቆጥር ፖለቲከኛ በየመንደሩ ተባዝቷል።
ዛሬ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ተከታይ የሚያገኙት መንግሥትን ሲቃወሙ ብቻ እንደሆነ ማሰብ ከጀመሩ ውለው አድረዋል፤ ደጋፊውም የሚበዛው በምትቃወመው ልክ ከሆነ ውሎ አድሯል። አክቲቪስቶችም በራሳቸው መንገድ መንግሥት ካዘወርን የሚሉበት ዘመን ላይ ነን። ዛሬ አንድ አክቲቪስት ከመንግሥት በተቃራኒ ቆሞ ካልተናገረ ወይም ካልጻፈ ሼር እና ላይክ የማግኘት እድሉ ጠባብ ነው። ይህ ግን በራሱ እንደአገር ወደምንፈልገው ከፍታ የሚያሻግረን ነው የሚል እምነት የለኝም።
ወዳጄ ዛሬ እንደልብህ የምትናገረው እና ለመዘወር የምትፈልገው መንግሥት ከሌለ ማህበራዊ ሚዲው ሆነ ሌሎቹ እድሎች አይገኙም። ዛሬ እንደቀልድ የምትወረውራቸው ቃላት ነገ አገር የሚያሳጡ እንዳይሆኑ ተጠንቀቅ። እናም ዛሬን ቆም ብለህ አስብ፣ ሰከን በል፤ እዚህም እዚያም የሚናከሱ ውሾችን ለመገላገል እንጂ ፀቡን ለማባባስ አትሯሯጥ፤ የመንግሥትን ጉዳይ ለመንግሥት፣ የሃማይኖትን ጉዳይ ለሃይማኖት አባቶች፣ ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ትተህ በተሰማራህበት ሙያ ላይ ብቻ አተኩር፤ ይህ ሲሆን ሁላችንም አገራችንን እናሻግራለን።
ወርቁ ማሩ
አዲስ ዘመን ጥር 6/2014