እንደ አገር ዛሬ ላይ ከፊታችን የተደቀኑ ብዙ የቤት ሥራዎች አሉብን። አሸባሪዎቹ የሕወሓትና የሸኔ ቡድን በከፈቱት ጦርነት ብዙ ዜጎቻችን ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከኖሩበት ካደጉበት ቀያቸውም ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ራሳቸውን ባልጠበቁበት ቦታ ተፈናቀለው እንዲያገኙት አስገድዷቸዋል። ይባስ ብሎም ሴቶች፣ ሕጻናትና አዛውንቶችም የመደፈር አደጋ ደርሶባቸው፤ ልባቸው ተሰብሮ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ስብራትም ገጥሟቸዋል።
ይህን መሠሉ ግፍና መከራ እንዲያበቃ የመከላከያ ሠራዊቱን ጨምሮ ልዩ ኃይሉና ሌሎች የጸጥታ አካላት ከፍተኛ መስዋትነት ከፍለዋል። ሕዝባችንንም እንደ ሕዝብ ለሠራዊቱ ደጀን በመሆን ለአገሩ እና ለነጻነቱ ያለውን ክብር በተግባር አሳይቷል ።
ሕዝባችን እንደ ሕዝብ ባደረገው ተጋድሎ ትናንት ከገባንበት የህልውና አደጋ ወጥተን ዛሬ በተሻለ ተስፋ ላይ እንገኛለን። ይህም ሆኖ ግን አገርን እንደ አገር በጸና መሰረት ላይ ማዋቀር ሆነ፤ ትናንት በአሸባዎቹ በተሰራው ግፍና በደል ችግር ውስጥ ያሉ ዜጎቻችንን ማቋቋም ከፊታችን ከሚጠብቁን ስራዎች ዋንኞቹ ናቸው። ሕዝብ አሁን ባለበት አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ከዚህ በላይ እንዲቆይ ማድረግ አደጋው ብዙ ነው። የተፈናቀሉ ወደ ቤታቸው ሳይገቡ፤ የተደፈሩ ወደ ህክምና ተቋማት ሳይደርሱ፤ የፈረሱ ተቋማት በከፊል እንኳን ስራ ሳይጀምሩ በፊት ሌላ አንድነታችንን እና ጽናታችንን የሚገዳደር አጀንዳ መጨመር የለብንም።
እንደ ሕዝብ በአሸባሪው ሕወሓት ሆነ በሸኔ የደረሰብን ልብ ሰባሪ የሽብር ተግባራት የፈጠሩብን ቁሳዊ ውድመትና ሥነልቦናዊ ሕመም ከፍ ያለ ቢሆንም፤ በድርጊቶቹ ተስፋ ቆርጠን ከማዘንና ከመቆጨት ይልቅ ቀጣይ የቤት ሥራችንን አውቀን በጀመርነው የወገን ደራሽነት ስሜት በቁርጠኝነት ልንንቀሳቀሰ ይገባል። ቁዘማ አማራጭ አይደለም። እንቆዝምም ብንል ጠላቶቻችን ያንን እድል እንኳን የሚሰጡን አይሆኑም።
ትናንት እንደ ሕዝብ ያንገዳገደን የአሸባሪዎቹ ቡድኖች የሽብር ተግባርም ሆነ የውጭ ሃይሎች ጫና ነገ ላይ መልኩንና አይነቱን ቀይሮ ሊመጣ ስለሚችል እንደ አለፉት ጊዜያት ነገሮች ‹‹ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ›› እንዳይሆኑ እንደ መንግሥትም ይሁን እንደ ሕዝብ በጥልቅ አስተውሎትና መረዳት እራሳችንን ማዘጋጀት ይጠበቅብናል።
‹‹ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት›› ብሎ ዘወትር ስለታላቅነቷ ከመናገር በሻገርም፤ ታላቅነቷ ተጠብቆ እንዲኖር ውስብስብ ችግሮቿን በመለየትና በመነጋገር መቅረፍ፤ በተለይም ሕብረተሰቡ ግጭት ነጋዴዎች ከሚነዙት አሉባልታ እራሱን መጠበቅ፣ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ መመልከት ያስፈልጋል።
በቀጣይ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል ውይይት ሊጀመር ከመሆኑ አንጻር የግጭት ነጋዴዎች ይህን ለማደናቀፍ የቻሉትን ያህል እንደሚሞክሩ የታወቀ ነው። በሌላ መልኩ የአገርን ጥቅም ታሳቢ አድርገው ወደ ድርድሩ የሚመጡ ሃይሎችን ማሸማቀቅ፤ ማዋከብ፤ ጽንፈኞችን ማበረታታት ፤ ከፋፋይ አጀንዳዎችን ማራገብ በብዛት ሊታይ ይችላል። ይህን ከአሁኑ ቀድሞ መገንዘብ እና ሳይደናገጡ እንዳመጣጡ ለመመከት እንዲሁም አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት መዘጋጀት ያስፈልጋል።
በአሸባሪዎቹና ከሃዲዎቹ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ተረባርቦ የመገንባቱ የቤት ሥራ በጅምር ደረጃ ላይ ቢሆንም ፤ ከፍ ባለ ሕዝባዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ለዚህም እያንዳንዱ ዜጋ ባለው አቅም ሁሉ ተሳታፊ ሊሆን ይገባል ሆስፒታሎች፤ ትምህርት ቤቶች፤ ፖሊስ ጣቢያዎች ፤ ፍርድ ቤቶች ወዘተ አሁኑኑ ወደስራ እንዲገቡ ከዚያም በሂደት ቀድሞ ከነበራቸው በተሻለ ሁኔታ እንዲገነቡ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ጉዳዩ አገርን መልሶ የመገንባት ሥራ መሆኑም በአግባቡ መረዳት ያስፈልጋል።
በአሁኑ ወቅት የሕክምና ተቋማትን ስንመለከት አንዳንድ የህክምና ተቋማት አንዳንድ ውድመት የደረሰባቸው ተቋማትን በመረከብ ወደ ቀደመው ተግባራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እየሠሩ ይገኛሉ። ይህ መንገድ ተቋማት ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ ያስቻለ ትልቅ ተግባር እየተከናወነ ያለ ነው። ሌሎች ተቋማትም ከዚህ ተሞክሮ በመውሰድ ወደ ስራ ያልገቡ ተቋማት ለመደገፍ ፈጥነው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። በዚህ በኩል የመንግሥት የጤና ተቋማት ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ይህን አርአያነት ያለው በታሪክ ሲወሳ የሚውል ተግባር የግሉ ዘርፍ የጤና ተቋማትም ፈጥነው ሊቀላቀሉት ይገባል።
ይህ ተቋማት ለወደሙ ተቋማት የሚያደርጉት ድጋፍ ይበልጥ እንዲጠናክር መስራትም ያስፈልጋል። አብዛኞቹ የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ዛሬ ላይ በግብአት እጥረት፣ በደረሰባቸው ጉዳትና ውድመት ወደ ቀደም ሥራቸው ያልተመለሱ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ፤ አገር ወዳዱን ዳያስፖራውንና አገር ውስጥ ያሉትን ባለሀብቶችን፣ ግለሰቦችንና የተለያዩ ግብረ ሠናይ ድርጅቶችን በማስተባበር የድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት ብዙ መሥራት ካለብን የቤት ሥራዎቻችን መካከል እንደ አንዱ በመውሰድ በኃላፊነት ስሜት መሥራት የሚገባበት ወቅት ላይ መድረሳችንም ማወቅና ማሳወቅም ያስፈልጋል። ያለብን የቤት ሥራ መጠን መንግሥት ለብቻው ሊሰራው የሚችለው ብቻ አይደለም።
ከፋፋይና አገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሃሳቦች ወደ ጎን በመተው፤ መንግሥትም የትኞቹ ችግር ቅድሚያ መፈታት አለባቸው ብሎ በመለየት በመምከር ችግሮቹን ከሥራቸው ለመፍታት መስራት ይኖርበታል። ይህም ከገባንበት ወስብስብ ችግር መውጫ መንገድ መሆኑን በመረዳት ስለ ኢትዮጵያ ህልውና ብሎ መሥራትንም ያካትታል። ወቅታዊ ባልሆነ አጀንዳ መጠለፍ፣ ብልጣብልጥነት ፤ ስግብግብነት፤ ሥልጣን ሽሚያ ፤ አድርባይነት፤ ግትርነት ወዘተ.. መከራችን ከማርዘም ውጭ ፋይዳ የላቸውም።
እንዲሁም መንግሥት ሕብረተሰቡ የመረጃ ብዥታ ተፈጥሮበታል ብሎ ሲያምን ዝርዝር መረጃዎችን በመስጠት ማስገንዘብና ብዥታዎችን ማጥራት ሌላኛው የቤት ሥራው መሆኑንም አውቆ መሥራት ይኖርበታል። የመረጃ ክፍተት እስካሁን የፈጠረው ክፍተት ካሁን በኋላም እንዲዘልቅ ማድረግ አደጋው ብዙ ነው።
በመሆኑም መንግሥት፣ የማሕበረሰብ አንቂዎች፣ ምሁራንና እያንዳንዱ ዜጋ የእለት ተእለት እንቅስቃሴዎቻቸው ሲያደርጉም ሆነ ሃሳባቸውን ሲገልጹ ጥንቃቄና ብስለት የተሞላበት መንገድን መከተል ይኖርባቸዋል። ይህም አሁን ላይ አገራችን ከገባችበት ውስብስብ ችግር የበለጠ ችግር ውስጥ እንዳትገባ ከማድረግ በተጨማሪም የቤት ሥራዎቻችን እንዳይበዙብን አይነተኛ ሚና ይኖራቸዋል።
ሌላው ከፊታችን ያለው የቤት ሥራ አገራዊ ምክክር ነው። ይህ ምክክር በአገራችን የነበሩትን ችግሮች ለመፍታት ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖረውና ብዙዎችም ተስፋ የሰነቁበት ነው። ይህም በተስፋና በምኞት እንዳይቀር ሁሉም ዜጋ በምክክሩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ድርሻ ያለውን መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ከወዲሁ ለውጤታማነቱ መሥራት ይጠበቅበታል።
መድረኩ አገራዊ ምክክር ነው ተብሎ መንግሥት እና ፓርቲዎች ብቻ እንደፈለጉ የሚያወሩበት፣ ለእነሱ ብቻ የሚተው መሆን የለበትም። ሕዝብ በየደረጃው ተሳታፊ መሆን አለበት። ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም የውይይቱ አካል መሆን አለባቸው።
በአጠቃላይ ጠላት ኢትዮጵያ ቀና እንድትል አይፈልግም። ለዚህ በተለያዩ ጊዜ የተለያዩ አጀንዳዎችን በመፍጠር ሕብረተሰቡን በማሸበር አገር ለማፍረስ የሚሠራውን ሴራ እስከወዲያኛው ማክሸፍም ተጠባቂ የቤት ሥራችን በመሆኑ፤ የጠላት ሴራና እቅድ እንዳይሳካም ከወዲሁም ብርቱ ትግል ይጠብቀናል።
ይህንን ተጨባጭ እውነታ በመረዳት መንግሥት እንደ መንግሥት፤ ሕዝቡም እንደ ሕዝብ፤ የሚጠበቅብንን የቤት ሥራ መሥራት አለበት። ተጽዕኖ ፈጣሪና ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች፣ የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የዳያስፖራው ማሕበረሰብና ሁሉም ዜጋ ለአገር ግንባታ ያለመታከት በመሥራት ኢትዮጵያን ማዳን ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። አሸባሪዎችና ተላላኪዎቻቸው በዜጎች ላይ የሚያደርሱት ሞት፣ መፈናቀል የሴቶች መደፈርና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲያበቁ ተባብሮና አስተባብሮ መሥራት የግድና የግድ በሚልበት ወቅት እንገኛለን።
ለመወቃቀስም ይሁን ለመሞጋስ አገር እንደ አገር ህልውናዋ ተጠብቆ ሊቆይ ይገባል። ይህ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አለመሆኑንም በመረዳት ያሉብን የቤት ሥራዎች ‹ገና ተጀምረዋል እንጂ አልተቋጩም› ብሎ በቁጭት በመነሳት መሥራት ይገባል።
በምስጋና ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ጥር 6 ቀን 2014 ዓ.ም