አዲስ አበባ፦ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የቀረበለትን የሥራ መልቀቂያ መቀበሉን ተከትሎ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዶክተር አምባቸው መኮንን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መረጠ።ዶክተር አምባቸው መኮንን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መርጧል። በአማራ ቴሌቪዥን በቀጥታ በተላለፈው የምክር ቤት 5ኛ ዙር፤ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባዔ ፤ዶክተር አምባቸው መኮንን ባደረጉት ንግግር «የተጣለብኝ ኃላፊነት ከባድ፣ የሚያስጨንቅ እና በውስብስብ ፈተናዎች የተሞላ መሆኑን ባምንም የአማራን ክልል ህዝቦች የመምራት እና የማገልገል ዕድል ማግኘት ደግሞ መብት ሳይሆን መታደል በመሆኑ ለዚህ ዕድል በመመረጤ ከፍ ያለ ኩራትና ደስታ የተሰማኝ መሆኑን ስገልጽላችሁ በታላቅ አክብሮት ነው» ብለዋል።
በመልዕክታቸውም፤ «ወንድም ለሆነው የትግራይ ህዝብ የቆየውን ዘርፈ ብዙ አንድነትና ወንድማማችነት በማደስ ለጋራ ሰላማችን እና ብልጽግናችን ተግባብተንና ተደጋግፈን እንድንሰራ የአማራ ህዝብ ጠንካራ ፍላጎት ነው» ብለዋል። በቀጣዮቹ ጊዜያት ትኩረት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች መካከል ጠንካራ የመንግሥት መዋቅር በየደረጃው መዘርጋቱን ማረጋገጥ፤ ድክመት የታየባቸውን ተቋማት ማጠናከርና ጠንካራ የለውጥ አመራር መገንባት የመጀመሪያው ጉዳይ ነው። በዚህ ላይ ተመስርቶ በመላ የክልሉ አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን ትኩረት ይሰጣል። የህግ የበላይነትን ማክበር እና ማስከበር እንዲሁም የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ሰፊ ጥረት ይደረጋል። በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ተሰናባቹ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ፤ ለአማራ ህዝብ የሚያዋጣው አብሮነት እና ወንድማማችነት በኢትዮጵያ ህዝቦች ሲዳብር ነው። ለዚህም በጠንካራ ድርጅት እየተመራ ለኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግና የእራሱን አዎንታዊ ሚና መጫወት አለበት። ከዚህ አንጻር የአማራ ህዝብ በየጊዜው በሚፈጠር ጥቅሙን በሚነካ የፖለቲካ ውዥንብር ሳይወናበድ አስተውሎ ወደፊት መራመድ እንዳለበት አሳስበዋል። «በርዕሰ መስተዳድርነት በቆየሁባቸው አምስት ዓመታት አቅሜና ሁኔታዎች በፈቀዱልኝ መጠን ለአማራህዝብ መብትና ጥቅም መከበር የበኩሌን አስተዋጽኦ አበርክቻለሁ የሚል እምነት አለኝ። በሥራ ቆይታዬ ዙሪያ መለስ ድጋፍ ላደረገልኝ የአማራ ህዝብ እንዲሁም ከጎናቸው ለነበሩ ሁሉ አመሰግናለሁ።
በስልጣን ዘመኔ በወሰንኳቸው ውሳኔዎች ቅር የተሰኛችሁ፤ ምናልባትም በእኔ ውሳኔና በስልጣን አመራሬ የተጎዳችሁ ወይም ሌላ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ያስከፋኋችሁ ወገኖቼ ሁሉ ይቅርታ ታደርጉልኝ ዘንድ በአክብሮት እጠይቃችኋለሁ» ብለዋል። ለአዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው ምኞታቸውን ገልጸዋል። ዶክተር አምባቸው መኮንን የትምህርት ዝግጅ – የመጀመሪያ ዲግሪ (BA) በኢኮኖሚክስ ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ፣- ሁለተኛ ዲግሪ (MA) በፐብሊክ ፖሊሲና ኢኮኖሚክስ ከደቡብ ኮሪያ KDI School of Public Policy and Management – ማስተርስ ዲግሪ (MSC) በዓለም አቀፍ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ኬንት ዩኒቨርሲቲ፣ – ፒ.ኤች.ዲ (PHD) በኢኮኖሚክስ እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ኬንት ዩኒቨርሲቲ፣ዋና ዋና የሥራ ልምዶች – ከ1983-1987 ዓ.ም ድረስ የወረዳ አመራር፣ – ከ1990-1993 ዓ.ም የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ኃላፊ፣ – ከ1994-1997 ዓ.ም የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅ/ቤት ኃላፊ፣ – ከ1998-1999 ዓ.ም የአማራ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ፣ – ከ2004-2005 ዓ.ም የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) ዋና ዳይሬክተር፣ – ከ2006-2007 ዓ.ም የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ፣ – ከ2008 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር፣የኢንዱስትሩ ሚኒስትር፣የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ እንዲሁም በሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነቶች አገልግ ለዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 30/2011
በጌትነት ተስፋማርያም