አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ የሚያደርግና ተቀባይነትን የሚጨምር ነው

አዲስ አበባ፣ አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ የሚያደርግና ተቀባይነትን እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑን የደን ልማት አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ብክለትና ብክነት የምድራችን ዋነኛ ፈተና መሆን ከጀመረ ዋል አደር ብሏል፡፡ ለዚህ ለዓለም ዋነኛ ስጋት ተጨባጭ፣ ተግባራዊ ምላሽ የሠጠ ሀገር ቀድማ የምትጠራው ኢትዮጵያ ናት፡፡ ከ2010 ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነትና በመላ ሕዝቡ ተሳትፎ ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኘው አረንጓዴ ዐሻራ ለዚህ ማሳያ ነው፡፡

ይህን ጥረት ይበልጥ በሚደግፍ መልኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአረንጓዴ ዐሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1361/17 ማፅደቁን ያስታወሱት አቶ ከበደ፣ የአዋጁ መውጣትም የኢትዮጵያ መንግሥት ለተፈጥሮ ሃብትና አካባቢ እንክብካቤ እንዲሁም የአካባቢ ብክለትና ብክነትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያለውን ሁለንተናዊ ቁርጠኝነት በግልፅ ያሳያል›› ብለዋል፡፡

ትግበራው ከመንግሥት በጀት እንዲመደብ የሚያስችል መሆኑምና ደኖችን ለመንከባከብና ለማልማት አረንጓዴ ዐሻራን ለማስፈጸም አቅም የሚፈጥር መሆኑን ያስገነዘቡት አቶ ከበደ፣ ‹‹ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የሀገር መሪ የእለት እለት አጀንዳ ሲሆንና ለውጤታማ ትግበራውም ሀብት ተመድቦለት ወደ እንቅስቃሴ ሲገባም በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ነው›› ብለዋል፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ተቀባይነቷን ከፍ የሚያደርግ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ኢትዮጵያ በደን ዘርፍ ከልማት አጋሮችና ከሌሎች ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ሰጪ ምንጮች እና ከካርበን ግብይት ሥርዓቶች የምታገኘውን ድጋፍና ጥቅም ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You