– አጠቃላይ ሀብቱም 139 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ደርሷል
አዳማ ፡- ባለፈው በጀት ዓመት ( እ.አ.አ በ2023/24) ያልተጣራ 2 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ማትረፉን እና አጠቃላይ ሀብቱ 139 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር መድረሱን የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ገለጸ::
የባለአክሲዮኖች 11ኛው አስቸኳይ እና 20ኛው ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ከትናንት በስቲያ በአዳማ ከተማ በተካሄደበት ወቅት የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው ፍቅሩ ዴክሲሳ (ዶ/ር) ባቀረቡት ሪፖርት፤ ባንኩ ባለፈው በጀት ዓመት ያልተጣራ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ማትረፉን እና አጠቃላይ ሀብቱ 139 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል::
ባንኩ ካሉት 758 ቅርንጫፎች ከ505 በላይ የሚሆኑት በገጠራማው አካባቢ የሚገኙ መሆኑና በየአካባቢው የሚስተዋለው የፀጥታ ችግር ባንኩ በሙሉ አቅሙ እንዳይሠራ አድርጎታል ብለዋል:: በዚህም የተነሳ ያለፈው ዓመት አፈጻጸም አጥጋቢ አለመሆኑን አስረድተዋል:: ያም ሆኖ በሂሳብ ዓመቱ ከግብር በፊት 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስረድተዋል:: ባንኩ በአሁኑ ሰዓት ባለፈው ዓመት ከነበረበት ሁኔታ ተላቆ ወደ መደበኛ የሥራ ሁኔታው እየተመለሰ ይገኛልም ብለዋል::
አጠቃላይ የባንኩ ተቀማጭ ብር 117 ነጥብ 15 ቢሊዮን እንደሆነና የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ 258 ነጥብ 35 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሆነ ጠቅሰዋል::
የባንኩ ካፒታል 18 ነጥብ እንደሆነና ከዚህም ውስጥ የተከፈለው ካፒታል 11 ነጥብ 18 ቢሊዮን ብር መሆኑን፤ የባንኩ የብድር መጠንም 97 ነጥብ 17 ቢሊዮን መድረሱን ገልጸዋል::
የባንኩ ዓላማ ከከተሞች ርቀው ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የባንክ አገልግሎት መስጠት እንደሆነ የገለጹት ፍቅሩ (ዶ/ር) ቀደም ሲል በነበሩት ላይ 20 ቅርንጫፎችን በመክፈት በበጀት ዓመቱ የቅርንጫፎችን ብዛት 758 ማድረስ ተችሏል ነው ያሉት:: ባንኩ ወረቀት አልባ አገልግሎት የሚሰጡ 200 ስማርት ቅርንጫፎችን ወደ ሥራ ማስገባቱንም አክለዋል::
2 ነጥብ 2 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞችን ማፍራት እንደተቻለና የደንበኞች ቁጥርም ከ11 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወደ 13 ነጥብ 34 ሚሊዮን ማደጉን አስረድተዋል::
ከቴክኖሎጂ አንጻር ባንኩ ምቹ አንድና ምቹ ሁለት የተባሉ መተግበሪያዎችን ሥራ ላይ በማዋል 199ሺ 600 ለሚሆኑ ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች አገልግሎቱን ተደራሽ አድርጓል ብለዋል:: የባንኩ አጠቃላይ የሰው ሃብት ብዛትም 15 ሺህ 467 መደረሱን ገልጸዋል::
የባንኩን ቋሚ ንብረት ከማፍራት አንጻር በፊንፊኔ ከተማ ፍልውሃ አካባቢ ቀድሞ የነበረውን ዲዛይን በመቀየር የባንኩን ዋና መሥሪያ ቤት፣ የንግድ ማዕከል/ሞል፣ እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል ያካተተ አድርጎ ለመገንባት የመጨረሻዎቹ ምዕራፎች ላይ እንደተደረሰ ተናግረዋል:: በሻሸመኔ፣ በሐረርና በአዳማ ከተሞችን ሕንጻ እያስገነባ እንደሚገኝ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው ፍቅሩ (ዶ/ር) በሪፖርቱ አመላክተዋል::
የውጭ ሀገር ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ባንኩ የሚገጥመውን ውድድር አሸንፎ ለመውጣት በቀጣይ ጠንክሮ ለመሥራት እንደተዘጋጀ ተገልጿል::
የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በግብርና ሥራ ለተሠማሩ ዜጎች የፋይናንስ አቅርቦት በማድረግ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና እድገት ላይ የድርሻውን አስተዋፅዖ ለማበርከት ከዛሬ አስራ ዘጠኝ ዓመት በፊት የተቋቋመ መሆኑን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመላክታል::
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም