በአገረ አሜሪካ 35 ዓመት ያህል ኖረዋል:: ሁለት ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ አንደኛው በአቪዬሽን ሳይንስ ላይ ነው:: ሁለተኛው ደግሞ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ በሲስተምስ ኢንጂነሪንግ ላይ የሰሩ ሲሆን፣ ኤም.ቢ.ኤ (ማስተር ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን) በዲጂታል ማኔጅመንት ሰርተዋል – የዛሬው እንግዳችን ኢንጂነር ወንድወሰን ካሳ:: ኢንጂነሩ፣ የመጀመሪያው ስድስት ዓመት በአሜሪካ መንግስት የባህር ኃይል ውስጥ ኢንጂነር ሆነው ሰርተዋል::
በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የ787 ቦይንግ ከፍተኛ ኢንጂነር ናቸው:: ይህም በድሪም ላይነር ውስጥ ማለት ነው:: ኢንጂነር ወንድወሰን፣ ወደአገር ቤት የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በውጭ ለሚኖሩ ለአንድ ሚሊዮን ዲያስፖራ ጥሪ ከማድረጋቸው በፊት ነው:: በአገራቸው ላይ በተለይ ደግሞ በአማራ ክልልና በአፋር ክልል የደረሰውን የጭካኔ በትር ሰምተው መቋቋም ስላልቻሉ ከስራቸው ፈቃድ ጠይቀው ነው እገዛ ሊያደርጉ የመጡት:: አዲስ ዘመንም ኢንጂነር ወንድወሰንን ባገኛቸው በደብረታቦር ከተማ ውስጥ ቃለ ምልልስ አድርጎ እንደሚከተለው አጠናቅሯል:: መልካም ንባብ ይሁንልዎ::
አዲስ ዘመን፡- ብዙዎቹ እየመጡ ያሉት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ጥሪ በኋላ ነው፤ እርስዎ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ጥሪው ከመተላለፉ በፊት ነውና ምን አነሳሳዎት?
ኢንጂነር ወንድወሰን፡- በአሜሪካ ስራ ላይ እያለሁ ወያኔ የአማራንና የአፋር ክልል መውረሩን እሰማ ነበር:: በተለይ ደግሞ በደቡብ ጎንደር ነፋስ መውጫ መውረሩን ሰማሁ:: ይህ በጣም ድንጋጤ ፈጠረብኝ:: ማመን አቃተኝ::
ነፋስ መውጫን በተወሰነ መልኩ አውቀዋለሁ፤ አንድ ዓመትም ቢሆን ተምሬበታለሁ:: ጁንታው በአገራችን ህዝብ ላይ ያደረገው ግፍና መከራ የጀርመን ናዚ ጁሾች ላይ ያላደረገውን ድርጊት ነው:: እጅግ በጣም የሚከብድና በህይወቴ ውስጥም አንብቤ የማላቀውን ታሪክ ነው የሰማሁት::
ይህን አስነዋሪ ተግባራቸውን ከሰማሁ በኋላ ምን ምን ናቸው ውድመት የደረሰባቸው ብዬ ሳስብ የሜዲካል ዕቃዎች ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን ሰማሁ:: ስለዚህ በዚህ ዘርፍ ለመርዳት አሰብኩ:: ነገር ግን ያንን ሁሉ የሚዲካል ዕቃዎች አጠራቅመን በኮንቴነር ለመላክ የራሱ የሆነ ሂደት አለውና ጊዜ ይፈጃል:: በመርከብ እንኳ እናምጣው ቢባል ወደ ስድስት ወራት ያህል የሚወስድ ሆኖ ተሰማኝ:: ስለዚህ በግል ቢያንስ አራትና አምስት ሻንጣ ይዤ መሄድ እንዳለብኝ ብዬ አሰብኩ:: ስለዚህ የማውቃቸው ሜዲካል ዶክተሮች አሉ:: እንዲሁም ነርሶችም አሉ:: ወቅቱ የኮቪድ ጊዜ እንደመሆኑም ለእርሱ የሚያስፈልጉ ዕቃዎችንም ወደ አራት ሻንጣ በራሴ ወጪ ይዤ ወደ አገር ቤት መጣሁ:: በነፋስ መውጫ ላለው ማህበረሰብም አስረክቤያለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ይዘው የመጡት ዕቃ ምን ያህል የሚገመት ነው::
ኢንጂነር ወንድወሰን፡- ዕቃው አንድ አስር ሺህ ዶላር የሚያወጣ ነው:: ነገር ግን ዕቃውን ስናመጣ ጉዳዩ በትክክል በስራ ላይ የሚውሉ ስለመሆናቸው አጥንተን ያመጣናቸው መሆናቸው ነው ለየት የሚያደርገው:: በተለይም የተዘረፉና በአሁኑ ወቅት ወሳኝና አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው በሚል የመጣ ዕቃ በመሆኑ ለነፋስ መውጫ ሆስፒታል ያለውን ችግር ይቀርፋል በሚል የመጣ ነው::
ይዤ የመጣሁት መድኃኒት ደግሞ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ፔን ኪለር 500 ሚሊ ግራሙ ወደ 12 ሺህ ነው:: ወደ ሁለት ሺህ ያህሉን ፔን ኪለር እና ሌላ የህክምና መሳሪያ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲም ይዤ መጥቻለሁ::
በተመሳሳይ ደግሞ ወደማውቃቸው ልጆች ሲያትል ደውዬ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ ስለሚመጡ ቢያንስ እያንዳንዱ 500 ሚሊ ግራም የሆነ መድኃኒት ሁለት ሁለት ሺህ ይዘው እንዲመጡ መልዕክት አስተላልፌያለሁ::
በዚህ አይነት አንድ መቶ ሰው እንኳ ቢመጣ ሁለት መቶ ሺህ ይሆናል:: ዲያስፖራዎቹ ይህን ይዘው በሚመጡበት ጊዜ ተቀባይ ፍለጋ እንዳይቸገሩ በጎንደር ፒያሳ በሚባልበት አካባቢ አንድ አማካይ ቦታ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እዛው ጎንደር ቀበሌ 18 አንድ አማካይ ቦታ ማድረስ ብቻ የሚጠበቅባቸው መሆኑን አስታውቄያቸዋለሁ::
ዕቃውን ይዘው የሚመጡ ሰዎች ዕቃውን በተባለው ወይም በሚቀርባቸው ስፍራ ሲያስረክቡ ተቀባዩ ደግሞ ደረሰኝ ይሰጣቸዋል:: የመጣውን መድኃኒት ደግሞ ተቀብሎ ለሚመለከተው ክፍል እንዲደርስ የሚያደርጉ አካላት ይኖራሉ:: በዚህ መልክ ነው በማስተባበር ላይ ያለሁት::
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ አስቀድመው እንደገለጹልኝ የወገንዎ ጉዳት ፋታ ስላልሰጥዎ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ሳይጠብቁ አስቀድመው አገር ቤት መግባትዎን ተረድተናልና ከመጡ በኋላ ወራሪውን የትግራይ ቡድን የፈጸመውን ግፍ እንዴት አዩት?
ኢንጂነር ወንድወሰን፡– አንድ የግሌ የምለው ዕቃ ቢጠፋብኝ ምንም ሊሰማኝ አይችልም:: ይዤ የመጣሁት እያንዳንዱ ከፋሻ ጀምሮ ብዙ ሰው ሊጠግን የሚችል ነገር እንደሚያስፈልግ ሳውቅ ነው:: እኔ በግሌ ወራሪው ቡድን ያጠፋውን ነገር መረጃውን መሰረት አድርጌ በትንሹም ቢሆን ጥናት ለማድረግ ሞክሬያለሁ::
ኢትዮጵያ እንደገባሁ ወደ ጎንደር አቀናሁ፤ ሰዎችም ተባበሩኝ እና ወደ ነፋስ መውጫም ደርሼ የያዝኩትን ዕቃ በማስረክብበት ጊዜ በሰዎች ላይ የነበረውን ደስታና አቀባበል ሳየው በእውነት ነው የምናገረው እንባዬን መቋቋም አልቻልኩም ነበር::
በሆስፒታሉ ውስጥ ያገኘኋቸው ህሙማንም ሆኑ ቁስለኞች ያሳዩኝን ፍቅር ለመግለጽ እቸገራለሁ:: ዕቃውን በማስረክብበትም ወቅት ደረሰኝ ተቀብያለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ወራሪው ጁንታ በቆየባቸው አካባቢ ተዘዋውረን እንዳየነው ከሆነ በተለይ የጤና ተቋማትንና የትምህርት ተቋማትን በማውደሙ ረገድ ተወዳዳሪ ያልተገኘበት ሆኖ አግኝተንዋል፤ ተቋማቱን በማውደም ብቻ ሳይወሰን በእያንዳንዱ ተቋም ባልተለመደ መልኩ ሲጸዳዳበትም ነበርና እንደ አንድ ምሁር ይህን እንዴት ያዩታል?
ኢንጂነር ወንድወሰን፡- እውነት ለመናገር ያደረጉትን ጸያፍ ተግባር ለመናገር ምንም ቃላት የለኝም:: ድርጊታቸውንና የጭካኔያቸውን ጥግ ለመግለጽ ሌላ አዲስ ቃላት መፍጠር የሚያስፈልግ ይመስለኛል::
እውነት ለመናገር የዓለምን ያለፈ ታሪክ ሁሉ ብናገላብጥ ይህንን ተግባራቸውን በየትኛው ጥግ የምናገኝ አይመስለኝም:: እንዴት የተማሪ ጥቁር ሰሌዳ በጥይት ይመታል፤ እነርሱ ግን ይህን አድርገውታል:: በተለይ በትምህርት ቤትና በጤና ተቋም ላይ በአማራ እና አፋር ክልል ላይ ያደረጉት ተግባር የሚከብድ ነው::
አንድ ሰው ትምህርት ከሌለው የደረቀ ትውልድ ነው የሚሆነው:: ወደጥንታዊው የጋርዮሽ ስርዓት የሚመለስ ነው የሚሆነው:: የጤና ተቋማት የማይኖሩ ከሆነ እናቶች ጤናቸው ተጠብቆ መውለድ አይችሉም::
ወራሪዎቹ በደመነፍስ የሚመራ እንሰሳ እንኳ የማያደርገውን ኢሰብዓዊ ድርጊት ነው የፈጸሙት:: ብዙ ጊዜ ነገሮችን በቁጥርም በጥራትም መለየት ይቀናኛል:: ለአነዚህ ግን የጭካኔያቸውን ጥግ ለመግለጽ ቁጥር እንኳ የለኝም::
አዲስ ዘመን፡- በርካታ ጉዳት መድረሱን ብዘዎች ተገንዝበዋልና በቀጣይ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ኢንጂነር ወንድወሰን፡- አሁን የጠፋው የሰው ህይወትም ሆነ የወደመው ንብረት ወድሟል:: ደግመን ደጋግመን የተፈጸመብንን በደል እያነሳን ብናለቅስ ችግሩን ማስወገድ አንችልም:: ስለዚህም የወደሙ ትምህርት ቤቶች ወደነበሩበት ቦታ መመለስ አለባቸው::
እያንዳንዱ ዲያስፖራ ወገኑን ለመርዳት ፈቃደኛም ደስተኛም ነው:: በዚህ ልክ አሰራሩ ውጤታማ ይሆን ዘንድ የሁሉም ትብብር የግድ ይላል:: ለምሳሌ እኔ ወደአገር ቤት ከመምጣቴ በፊት አንድ ያቀረብኩት ሐሳብ ነበር::
ተማሪው ይማርበት የነበረው ትምህርት ቤት ተጠግኖ ወደ ትምህርቱ መመለስ አለበት:: ይሁንና አንዳንድ ቦታ እየተነገረ ያለው ነገር እንዳለ ሰማለሁ:: ትምህርት ቤቶችና ሌሎች ተቋማት ስለወደሙ እነርሱን ወደስራ ለመመለስ እና ኢኮኖሚውን ለማስተካከል 30 እና 50 ዓመት ይጠይቃል እየተባለ ነው::
እኔ እንዲህ አይነቱን ነገር አልቀበለውም:: ይህ በራሱ ሟርት ነው:: በመጀመሪያ ደረጃ በየትኛው መረጃ ላይ ተመስርተው ነው 30 እና 50 ዓመት ይፈጃል እየተባለ የሚናገሩት:: ለምሳሌ አንድ የደብረ ታቦር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አለ እንበል፤ በድሮ በወያኔ አገዛዝ ለዚህ ወይም መሰል ትምህርት ቤት 150 ሚሊዮን ብር ወጣ ሲሉ ይደመጡ ነበር:: እሱ ዋጋ ግን ራሳቸው የሚነግሩን ዋጋ እንጂ ትክክለኛ ዋጋ አይደለም:: እነርሱ 150 ሚሊዮን ብር ብለው ትምህርት ቤቱ የሚያወጣው ግን 50 ሚሊዮን ብር ነው:: የቀረውን መቶውን ሚሊዮን ብር የእነርሱ ልጆች ናቸው አሜሪካ አገር የሚጫወቱበት::
አሁን እየታየ ያለው ግምት ያንን ዳታ መሰረት በማደረግ ነው:: ስለዚህ ችግራችንን በ30 እና በ50 ዓመት እንኳ መመለስ አይቻልም ከተባለ ኒውክለር ወድቋል ማለት ነው:: ይህን ግን እኔ አልቀበልም::
አዲስ ዘመን፡- ይህን የማይቀበሉ ከሆነ አማራጩ ምንድን ነው ይላሉ?
ኢንጂነር ወንድወሰን፡- ምንድን ነው የምትለው የምትይኝ ከሆነ ሁሌም ቢሆን መፍትሄ መምጣት አለበት ባይ ነኝ:: በእኔ እምነት መፍትሄ ለማምጣት አራት ኃይሎች አንድ ላይ መስራት አለባቸው፤ የፌዴራል መንግስት፣ ክልሉ፣ እዚያው ያለው ማኅበረሰብ እና ዲያስፖራው:: ከዲያስፖራው ምን ይጠበቃል ያልሽኝ እንደሆነ አንድ ያቀረብኩላቸው መነሻ ሐሳብ አለ:: ሶስት አማራጭ ሰጥቻቸዋለሁ:: አንደኛው ለማሳያ ያህል ሲያትልን እንወሰደው:: በሲያትል ውስጥ ለምሳሌ ሁለት ሺህ የአማራ ተወላጆች አሉ እንበል:: በአሜሪካ አኗኗር ዝቅተኛ ደመወዝ ነው የሚባለው በዓመት 30 ሺህ ዶላር ነው እንበል::
ከፍተኛው የሆነው ደግሞ እስከ 250 ሺህ ዶላር በዓመት ሊያገኝ ይችላል:: ከሁለቱም አማካይ ስናወጣ 50 ሺህ ዶላር ይሆናል:: ስለዚህም እያንዳንዱ እዛ ያለው በአማራ ላይ የተካሄደውን ውድመት ወደነበረበት ለመመለስ ከዓመታዊ ደመወዙ ላይ 5 በመቶ ቢያደርግ ከሃምሳ ሺህ ዶላር የሚገኘው 2 ሺህ 500 ዶላር ይሆናል:: ይህን ቁጥር ደግሞ ሲያትል ውስጥ ብቻ ባሉ ሁለት ሺህ አማራዎች ቢባዛ አምስት ሚሊዮን ዶላር ሆነ ማለት ነው:: ያቺን 2 ሺህ 500 ዶላሯን ቢፈልጉ በየወሩ፣ ቢያሻቸው ደግሞ አንድ ጊዜ ይክፈሉት:: እሱ ላይ ችግር አይኖርም፤ የአከፋፈሉን ሁኔታ ማስተካከል ይቻላል:: ሁለተኛው ደግሞ ፕሮጀክትን ስፖንሰር ማድረግ:: ለምሳሌ ንፋስ መውጫ ውስጥ የወደመ የሙያና ቴክኒክ ትምህርት ቤት አለ ከተባለ ዋጋውን እናጥና:: ዝርዝር የሆነ የዋጋ ጥናት ማካሄድ እንጂ ይህን ያህል ወደመ የሚለውን ተከትለን መስራት አይገባንም:: ለምሳሌ አሁን የሚሰማው ነገር ይህ ትምህርት ቤት የደረሰበት ውድመት በጣም ትልቅ ነው ተብሎ ነው:: ይህን አባባል እኔ አልቀበለውም:: በደፈናው ትልቅ ማለት ሳይሆን በጣም ዝርዝር የሆነ መረጃ በመያዝ ምን ያስፈልጋል የሚለው መለየት አለበት:: ለምሳሌ የወደመው የትምህርት ቤቱ ኮምፒውተር ነው? ወይስ መማሪያ ቁሳቁሱ? ይህ ከተለየ በኋላ የዋጋ ጥናት ይሰራል:: ነገር ግን አሁን አንዳንድ ቦታዎች የማያቸው ነገሮች በጥቅሉ ወደመ የሚባል አይነት መረጃ ነው::
እንዲህ አይነቱን ጥቅል የሆነ መረጃ ይዤ እዛ ሄጄ ማስተባበር ይከብደኛል:: ስለዚህ የዋጋ ጥናት ላይ ያየኋቸው ክፍተቶች ትንሽ ስሜት የሚጎዱ ናቸውና ቢስተካከሉ መልካም ናቸው:: ሰው የሚናገረው ብዙ ኮምፒውተሮች ወድመዋልን እንጂ በቁጥር ይህን ያህል ነው የሚለውን የሚናገር ሊኖር የግድ ነው:: ፕሪንተር ከሆነም ስንት ነው? የሚለው መለየት አለበት:: አንድ የማረጋግጠው እና የማምንበት ነገር ቢኖር ትምህርት ቤቱ ወደነበረበት መመለስ አለበት የሚለውን ነው::
በህጻናት ተማሪዎቹ ላይ መቀለድ አይቻልም፤ ምክንያቱም ልጆቹ የወደፊቱ ትውልዶች ናቸው:: ሁሉን ወደነበረበት ለመመለስ 30 እና 50 ዓመት ይፈጃል ብለን ከወዲሁ እጅ ሰጥተን የምንቀመጥ ከሆነ ትውልድን ማምከን ነው የሚሆነው::
ስለዚህ ይህ እንዳይሆን አማራጭ አለ፤ የወደመ ወድሟል፤ ያንን ለማስተካከል መደረግ ያለበትን ነገር እናደርጋለን:: ለምሳሌ ለነፋስ መውጫ ትምህርት ቤት የጎደለው 30 ያህል ኮምፒውተር ነው ተብሎ ከሆነ ያንን ማድረግ ነው:: በመሆኑም ልጆች ያለትምህርት መቀመጥ አይኖርባቸውም::
በዚህ አይነት ሁኔታ በደብረ ታቦር፣ ጎንደርም ሆነ ባህርዳር በመሄድ ሰዎችን አነጋግራለሁ:: በዚህ መልኩ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እናደርጋለን::
አዲስ ዘመን፡- የዲያስፖራውን ተነሳሽነት እንዴት ይገልጹታል?
ኢንጂነር ወንድወሰን፡- በአሁኑ ሰዓት ዲያስፖራው መካከል ቀደም ሲል ያላየሁት አይነት ኢትዮጵያዊነትን ነው እያየሁ ያለሁት:: በአሜሪካ አገር በየቀኑ ‹‹ይብቃ›› የሚለውን መፈክር ይዞ መውጣት በራሱ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ አይነት መስዋዕትነት የጠየቀ ነው::
ይህም ሳይሰለች እየተፈጸመ ያለ የአገር ወዳድነት ስሜትም የሚንጸባረቅበት ነው:: በ‹‹ይብቃ›› ንቅናቄ የተነሳ ብዙ ነገር አለ፤ ይህ የትግል ውጤት ነው:: ዲያስፖራው ያንን ማድረግ ከቻለ እዚህ ያሉት ወገኖቻችን መከላከያው፣ ልዩ ኃይሉና ፋኖው ጠላትን ካንበረከከ እንዲህ አይነቱን ጥንካሬ ደግሞ ወደትምህርት ቤት መልሶ ወደ መጠገን የማንጠቀምበት ምክንያት እኔ አይታየኝም::
የወደሙ ንብረቶችን ለመተካት በመልሶ ግንባታው እንችላለን ብለን መነሳት አለብን እንጂ እያለቃቀስን ጊዜ መፍጀት አይኖርብንም:: በዚህ ረገድ የዲያስፖራው መነሳሳት በጣም ከፍተኛ ነው:: በእርግጠኝነት ደግሞ የመንግስት ባለስልጣናት ይህንን መነቃቃት እንዲጠቀሙበት ነው የምመክረው::
መነሳሳቱ ጥሩ አጋጣሚ ነውና በአግባቡ ይጠቀሙበት:: ከወደሙት ትምህርት ቤቶች ደረጃው ከፍ ባለ ሁኔታ መስራት የምንችለበት ጊዜው አሁን ነው:: ሁሉም ያለምክንያት አልሆነም፤ የሆነውን ወደመልካም መቀየር ይገባናል:: ምክንያቱም ትምህርት ቤቱ የወደቀ ነበር፤ አሁን ግን የተሻለ መስራት እንችላለን:: እንዲያውም የዛሬ ሃያ ዓመት የነበረ ቁሳቁስን ከመጠቀም ይልቅ የተሻለ አድርገን እናደራጀዋለን::
ህጻናቱ ስቀውና ደስተኛ ሆነው መማር አለባቸው:: ይህን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሚያነቡ ወገኖቼ ሁሉ በዚህ ጉዳይ እንዲተባበሩ ጥሪ አቀርባለሁ:: ሁላችንም መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅትና ሌሎቻችንም በቅንጅት ከሰራን ኢትዮጵያ እንድትበለጽግ ማድረግ እንችላለን::
አዲስ ዘመን፡- በጣም አመሰግናለሁ::
ኢንጂነር ወንድወሰን፡- እኔም አመሰግናለሁ::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ጥር 5/2014