አዲስ አበባ፡- የአንድነት ብርታት ያልገባቸውና ከሶማሊያ እንኳን መማር ያልቻሉ ሰዎች ህዝቡን ይዘውት እንዳይጠፉ ሴቶችና አገር ወዳዶች ዝምታውን ሰብረው በመውጣት ለአገር አንድነት በጋራ እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ፡፡ 43ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን «የላቀ ትኩረትና ቁርጠኝነት ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት» በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በድምቀት ተከብሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የበዓሉን መክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የጀግኖች አምባ ብትባልም ዛሬ ከፍተኛ የሆነ የጀግና ችግር አጋጥሟታል፡፡ አሁን ያሉት ጀግኖች የመንጋ ተከታዮች በመሆናቸው የሚሳደቡ፣ የሚገሉ፣ የሚደበድቡ፣የሚሰርቁና የሚገፉ ናቸው፡፡ በመሆኑም የአገሪቱን ህዝብ ግማሽ ያህሉን የሚይዙት ሴቶችና አገር ወዳዶች ይህንን የመንጋ አስተሳሰብተቃውመው በመውጣት አገራቸውን ከጥፋት ኃይሎች መታደግ ይገባቸዋል፡፡
የጀግኖች ባህሪ በችግርና በተቃርኖ ውስጥ እውነትን ይዞ መቆም መሆኑን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ «የሴቶችን ቀን ከማክበር በዘለለ ጀግና ሴቶች ከትግራይ ባህርዳር በመሄድ እንዴት ወንድም ወንድሙን ይገድላል? ነውር ነው በሉ፤ እንዲሁም ከባህርዳር መቀሌ በመሄድ መገዳደል ጀግንነት ሳይሆን ነውር መሆኑን አስተምሩ» ብለዋል፡፡
አክለውም «የተጠናወተን ነውር እንዲቆም ከተፈለገ ምንም እንኳን የሚጮህና የሚደግፋችሁ ሰው ቢያንስም በጀግንነት በመጋፈጥ አገራችንን ትክክለኛዋ የጀግኖች አምባ ልታደርጓት ይገባል» ሲሉ አሳስበዋል፡፡ በተለይም ደግሞ ሴቶች የቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የአገርም ተሸካሚ ምሰሶ እንደመሆናቸው አገርና ህዝብ ሲጠፋ ዝም ብሎ መመልከት የማይቻላቸው መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር አብይ ፣ ሌሎች ኃላፊነታቸውን እንዲያስታውሱና የአገራቸውን ክብርና ጀግንነት እንዲያወሱ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡ «ሴቶች፣ የኢትዮጵያውን ሰላም ወዳዶችና አንድነት የሚፈልጉ ሰዎች ዝምታ ጥቂቶች እንዲጮሁና እንዲደመጡ እያደረጋቸው ነው፡፡
ስለሆነም ድምፃችሁን ከፍ በማድረግ አገሪቱን ከውጭ ወረሪ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም አጥፊ ልትታደጉ ይገባል» ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ዛሬ ሁሉም እንደዋዛ የሚያላግጥባት ኢትዮጵያ ብዙዎች የደሙላት፣ሴቶች የቆሰሉላት ልጆቻቸውን ያጡላት፣በመከራ የተገነባች አገር ነች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣በመሆኑም ሴቶች የተለመደ ጥበባቸውን በመጠቀምህዝቡን የአንድነት ብርታት ያልገባቸው ከሶማሌ እንኳን መማር ያልቻሉ ይዘውት እንዳይጠፉ ድልን ብቻ የመጋራትና ሽንፈትን የመሸሽ አባዜ እንዲወገድ ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ አሳስበዋል፡፡
«እኛ ኢትዮጵያውያን በጋራ የማረም ባህላችንን ተጠቅመን በውስጣችን ያሉትን ስንክ ሳሮች ማስወገድ ይኖርብናል፡፡ለመከፋፈልና ለጦርነት ያለን ጉልበት ለሰላምና አብሮ ለመኖር ልናውለው ይገባል» በማለትም ተናግረዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ተወካይ ሚስተር ሚሼል ሲዲቤ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት የሴቶችን ተጠቃሚነት በተጨባጭ ለማረጋገጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚያስመሰግነው መሆኑን ተናግረዋል፡ ፡ በተለይም አገሪቱን በርዕሰ ብሄርነት ሴት መሪ እንድትኖር ከማድረግ ባለፈ ቁልፍ ቦታዎችን በመስጠት ሴቶች በፖለቲካውም ዘርፍ ያላቸውን ብቃት እንዲያሳዩ ማድረጉ ለሌሎችም በአርአያነት የሚጠቀስ ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሴቶች በተለይም በአሁኑ ወቅት በአገራቸው ብሎም በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እያደረጉ ያሉት ሁለንተናዊ ጥረት በከፍተኛ ደረጃ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም መንግሥት አሁንም ገና ያልወጡትን ሴት ምሁራን በመጠቀም ለአገሪቱም ሆነ ለአህጉሪቱ ብልፅግና እና ዘላቂ ሰላም ሚናቸውን እንዲወጡ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ፀጋይ በበኩላቸው በአገሪቱ በተለይም በአሁኑ ወቅት «ጀግኒት ጀግኒትን ትወልዳለች» በሚል መሪ ሃሳብ እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ሴቶች ለአገራቸው ሰላምና አንድነት ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ይህም የሴቶች አመራርና ውሳኔ ሰጪነት እንዲጎለብት ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም የአገሪቱ መንግሥት ሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲጎለብትና ያላቸውን እውቀትና አቅም ተጠቅመው ለአገር ብልፅግና እንዲሰሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 30/2011
በማህሌት አብዱል