የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ከስምንት አመት በኋላ በ33ኛው የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ መሆኑን ማረጋገጡን ተከትሎ ባለፉት በርካታ ወራት ቡድኑ በውድድሩ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘገብ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። የተደረጉ ጥረቶች ሁሉ በተለይም የወዳጅነት ጨዋታዎችን በተመለከተ ስኬታማ ነበሩ ለማለት ግን አይቻልም። ያም ሆኖ ዋልያዎቹ ከውድድሩ ሁለት ሳምንት ቀደም ብለው በያውንዴ ከትመው አንድ የአቋም መፈተሻ ከሱዳን አቻቸው ጋር አድርገው በቀጥታ ወደ ውድድሩ ገብተዋል።
በውድድሩ ምድብ አንድ ከአስተናጋጇ ካሜሩን፣ ኬፕቨርዴና ቡርኪናፋሶ ጋር የተደለደሉት ዋልያዎቹ የመጀመሪያ የምድቡ ጨዋታቸውን ባለፈው እሁድ ከኬፕቨርዴ ጋር በማድረግ አንድ ለምንም በሆነ ውጤት መሸነፋቸው ይታወሳል። ዋልያዎቹ በምድባቸው በአንጻራዊነት ቀላል ተጋጣሚ የሆነችውን ኬፕቨርዴን መርታት ባይችሉ እንኳን ነጥብ ተጋርተው ይወጣሉ የሚል ተስፋ በብዙዎች ዘንድ አድሮ ነበር፡፡ የታሰበውና የተመዘገበው ውጤት ግን ተቃራኒ ሆነዋል።
በጨዋታው ገና በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ተከላካዩ ያሬድ ባዬ በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱን ተከትሎ ዋልያዎቹ ሙሉ ጨዋታውን በአስር ተጫዋች ለማጠናቀቅ ተገደዋል። አንጎላዊው አርቢትር የመዘዙት ቀይ ካርድም የጨዋታውን ይዘት ቀይሮታል። በፋሲል ከነማ ጥሩ ስምና ብቃት ያለው ተከላካዩ ያሬድ ባዬ ሊቆጠር የሚችልን ግብ ለማስቀረት የወሰደው ውሳኔ ትክክል ነው አይደለም የሚለው ሃሳብ ራሱን የቻለ ክርክር ቢያስነሳም፣ በጨዋታው ግን ዋልያዎቹን ዋጋ እንዳስከፈላቸው መካድ አይቻልም።
ያሬድ ምናልባትም ያንን ጥፋት ሰርቶ በቀይካርድ ባይወጣና ግቡ ቢቆጠር ዋልያዎቹ በቀሪ የጨዋታው ጊዜ በሙሉ ተጫዋች ውጤቱን ሊቀይሩ የሚችሉበት እድል ሊኖር እንደሚችል ይታመናል። ዋልያዎቹ ወሳኙን ተከላካይ በቀይ ካርድ ካጡ በኋላ የተረበሸ ስሜት ውስጥ እንደገቡ ሜዳ ላይ በግልጽ ታይቷል። ይህም በአፍሪካና በአለም ዋንጫ ማጣሪያ በርካታ ጨዋታዎች የነበራቸው ቅንጅትም ሆነ የጨዋታ እቅዳቸውን እንዳበላሸው መካድ አይቻልም።
ዋልያዎቹ በኬፕቨርዴ የተወሰደባቸው የተጫዋቾች ቁጥር ብልጫ ያን ያህል በጨዋታውም ብልጫ አሶስዶባቸዋል ለማለት ቢከብድም፣ ከቀይ ካርዱ መመዘዝ በኋላ በመጀመሪያው የጨዋታ መጠናቀቂያ ላይ ግብ የተቆጠረባቸው መሆኑ የበለጠ በራስ መተማመናቸው እንዲወርድ አድርጎታል። በሁለተኛው አጋማሽም ዋልያዎቹ የአሸናፊነት ስነልቦናቸውን ገንብተው ወደ ሜዳ አልተመለሱም። አሰልጣኝ ውበቱ አባተም በጨዋታው ውጤት ሊለውጥና ቡድኑን ሊያነቃቃ የሚችል ትርጉም ያለው የተጫዋች ቅያሬ ሲያደርጉ አልታዩም።
በጨዋታው ላይ ከተከሰቱ እውነታዎች ባሻገር ውጪያዊ ተጽእኖዎችም ዋልያዎቹ በኬፕቨርዴው ጨዋታ ያሰቡትን ውጤት እንዲያጡ አስተዋጽኦ አልነበረውም ማለት አይቻልም። ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫውና የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በአንጻራዊነት የተሻለ ቅንጅትና እንቅስቃሴን በማሳየት ጋናና ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉ አገራትን መፈተን እንደቻሉ ይታወቃል። ይህም በራሳቸው በተጫዋቾቹም ይሁን በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃንና እግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ አፍሪካ ዋንጫው ላይ ቢያንስ ከምድባቸው የሚያልፉበት እድል ይኖራል ብለው ተስፋ እንዲያሳድሩ አድርጓል።
ይህ ትልቅ ተስፋ እንዲለመልም በኬፕቨርዴው ጨዋታ ላይ ቢያንስ ነጥብ መጋራት ለዋልያዎቹ ወሳኝ ነበር። በጨዋታው ላይ ነገሮች ከታሰበው በተቃራኒው የሚሆኑበት ክስተት ገና በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ሲከሰቱ በውድድሩ መድረክ ልምድ ለሌላቸው የዋልያዎቹ ስብስብ ድንጋጤ ፈጥሮ ጨዋታቸው ሁሉ እንዲበላሽ ቢያደርግ የሚያስገርም አይደለም። በዚህ ላይ ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ የተሻለ ልምድ ያለውን ብቻ ሳይሆን ጨዋታ አቀጣጣዩን ወሳኝ ተጫዋች ሽመልስ በቀለን በጉዳት ምክንያት ማካተት አለመቻላቸው መሃል ሜዳ ላይ ያላቸውን እንቅስቃሴ በተገቢው ሁኔታ የሚመራና ለአጥቂዎቹ ጌታነህ ከበደና አቡበከር ናስር የተሳካ የግብ እድል እንዳይፈጠር አድርጓል። ይህም በጨዋታው አንድ ለግብ የቀረበ ሙከራ ብቻ አድርገው እንዲወጡ አስገድዷቸዋል።
ዋልያዎቹ ከዘጠኝ አመት በፊት በደቡብ አፍሪካው ዋንጫ ሲሳተፉም ገና በመጀመሪያው ጨዋታ ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ቢወጣም በጎዶሎ ቁጥር እጅግ አስደናቂ እንቅስቃሴ አድርገው ቻምፒዮን ከነበረችው ዛምቢያ ጋር በአዳነ ግርማ ብቸኛ ግብ ነጥብ ተጋርተው መውጣታቸው አይዘነጋም። ዋልያዎቹ በዚህ ታላቅ መድረክ አላስፈላጊ ወይም ቡድኑን የማይጠቅም ስህተት ሰርተው የቀይ ካርድ ሰለባ የሚሆኑበት ጉዳይ ልምድ ከማጣት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።
ይህን ስህተት ማረም ግን ተጫዋቾቹ ዛሬ ምሽት አንድ ሰአት ከካሜሩን ጋር ከሚያደርጉት ሁለተኛ የምድብ ጨዋታ ጀምሮ ተግባራዊ መሆን አለበት። በኬፕቨርዴው ጨዋታ የተጠበቀው ውጤት ስላልተመዘገበ በዛሬው ጨዋታም ጥሩ ውጤት አይመዘገብም ተብሎ መታሰብ የለበትም። በእርግጥ የመጀመሪያውን ጨዋታ ቀላል ተብላ በታሰበችው ኬፕቨርዴ ሽንፈት አስተናግዶ ሁለተኛውን ጨዋታ ቡርኪናፋሶን አሸንፋ ከመጣችው እንዲሁም የውድድሩ አስተናጋጅ ሆና በሜዳዋና በደጋፊዋ ፊት ከምትጫወተው ካሜሩን ጋር ማድረግ የራሱ የሆነ የስነ ልቦና ጫና እንደሚያሳድር ግልጽ ነው።
ያም ሆኖ ይህ እግር ኳስ ነው፤ የታሰበው ቀርቶ ያልታሰበው የሚሆንበት፣ ያሸንፋል የተባለው ቀርቶ የተናቀው የሚያሸንፍበት አለም። ስለዚህም ዋልያዎቹ ይህን የስነልቦና ጫና ወደ ጎን ትተው ታላላቅ የሆኑትን እንደ ኮትዲቯር አይነት ቡድኖች ማሸነፍ መቻላቸውን እንዲሁም ጋናና ደቡብ አፍሪካን በተግባር እንደፈተኑ በማስታወስ ለዛሬው ፈተና የአሸናፊነት ስነልቦናቸውን መገንባት ያስፈልጋል።
ወሳኙ አማካኝ ሽመልስ በቀለም ከጉዳቱ አገግሞ ትናንት ከቡድኑ ጋር ልምምድ ሰርቷል። በዛሬው ጨዋታ ሊሰለፍ እንደሚችልም ይጠበቃል። ይህም ለዋልያዎቹ መልካም አጋጣሚ ሲሆን ካሜሩንም እንደታሰበው ከባድ እንዳልሆነች ከቡርኪናፋሶ ጋር ያደረገችው የመጀመሪያ ጨዋታ ምስክር ነው። ስለዚህ ዋልያዎቹም ይሁኑ ደጋፊዎቻቸው ተስፋ የተጣለበትን ውጤት አጥተው ተስፋ ያልተደረገበትን ለማሳካት ጥረት ማድረግ እንጂ ተስፋ መቁረጥ አይጠበቅባቸውም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 5 ቀን 2014 ዓ.ም