በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1970 ዓ.ም የወጡ የጋዜጣችን ሕትመቶች ለመቃኘት ሞክረናል። እነሆ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ለሶማልያ የጦር መሣሪያ የጫነ አይሮፕላን ተገዶ ኬንያ አረፈ ባለፈው ረቡዕ ልዩ ልዩ የጦር ማሣሪያዎችን ጭኖ ወደ ሶማሊያ ይበር የነበረ አንድ የግብፅ አይሮፕላን በኬንያ ተዋጊ ኤሮፕላን ተገዶ ናይሮቢ እንዲያርፍ መደረጉን የኬንያ ዜና አገልግሎት ገልጧል።
ከጦር መሣሪያዎች መካከል 244 ቦንቦችና ፈንጂዎች ይገኙባቸዋል። የግብፅ አየር መንገድ አኤሮፕላን ሊታገድ የቻለው በሱዳን በኩል አልፎ ቱርካና ሐይቅ አካባቢ ወደ ኬንያ አየር ክልል ውስጥ እንደገባ መሆኑ ታውቋል።
በኬንያ ተዋጊ አኤሮፕላኖች ተገዶ እንዲያርፍ የተደረገው የግብፅ አኤሮፕላን ናይሮቢ እንደደረሰ የጦር መሣሪያዎች ወዲያው እንዲራገፉ ተደርገዋል።
የኬንያ መከላከያ ሚኒስትር ጀምስ ኪቹሩ መሣሪያዎችን ለማየት ወደ ቦታው ሔደው እንደነበር ቃል አቀባዩ ጠቅሶ እነዚህም የጦር መሣሪያዎች ግብፅ ለሶማሊያ ስለምታደርገው የጦር መሣሪያ እርዳታ የመጀመሪያው ማስረጃ ሊሆን ይችላል ብሏል።
እነዚህም መሣሪዎች በሶቪየት የተሠሩ ሳይሆኑ እንደማይቀሩና ሲቪየት ለግብፅ እስካለፈው ዓመት ድረስ ትሰጣት ከነበሩት መሣሪያዎች ውስጥ ለሶማሊያ እርዳታ የተላኩ መሆናቸውን ቃል አቀባዩ በተጨማሪ አረጋግጧል።
ግብፅ ለሶማያ ስለምታደርገው ያልተቆጠበ እርዳታ የተደጋገመ ክስ አሰምታ እንደነበረ ሲታወቅ ባለፈው ማክሰኞም በኢትዮጵያ ግዛት በሆነው በኦጋዴን ጦርነት ላይ የሚሳተፉ ፭ ሺ የግብፅ ወታደሮች በዝግጅት ላይ እንደነበሩ መገለጡ ይታወሳል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የግብፅ የጭነት ማጓጓዣ አኤሮፕላኖች በኬንያ በኩል ወደ ሶማሊያ እንዲያልፉ ግብፅ ኬንያን ጠይቃ እንደነበርና በግብፅ የኬንያ አምባሳደር አህመድ ማርቡክም የሚጓጓዙት ዕቃዎች መድኃኒት ልብስና ምግብ የመሳሰሉት ብቻ ናቸው በማለት አስታውቀው እንደነበር ቃል አቀባዩ ጠቅሷል።ይሁን እንጂ ኬንያ በነገሩ ስለተጠራጠረች ፈቃድ መከልከሏ ታውቋል።
ባለፉት ሰኞና ማክሰኞም ሦስት ቦይንግ ፯፻፯ የሆኑና የግብፅ አውሮፕላኖች የኬንያን የአየር ክልል አቋርጠው ወደ ሶማሊያ ሄደዋል። ያጓጓዙትም የጦር መሣሪያ ሳይሆን እንደማይቀር ፤ከትናንት በስቲያው የግብፅ አይሮፕላኖች የኬንያን የአየር ክልል ሲጥሱ ፬ኛ ጊዜያቸው መሆኑን ቃል አቀባዩ አስታውቋል።
ቃል አቀባዩ ከ፲፱፻፷፬ እስከ ፲፱፻፷፯ ድረስ ሶማሊያ የኔ ነው በምትለው በሰሜን ምሥራቅ የኬንያ ግዛት ሲያካሂዱት የነበረውን ጦርነት አስታውሶ በዚያ ጊዜም ግብፅ የኬንያን ወታደሮች ለማስወጋት ለሶማሊያ የጦር መሣሪያ እርዳታ ትሰጣት እንደነበር ጠቅሷል።
በሌላ በኩል የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ሙንያ ዋያኪ ማናቸውም ሶማሊያን በጦር መሣሪያ የሚረዱት ሀገሮች ሀገራቸው በጥብቅ እንደምታወግዝና በነዚህም ሀገሮች ላይ ቅሬታ መንፈስ እንደሚኖራት መግለጣቸው ታውቋል።
ዶክተር ዋያኪ በቴሌቪዥን ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ አንዳንድ የምዕራብ ሀገሮች በአቀባባይ ሀገሮች አማካኝነት ለሶማሊያ እርዳታ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አረጋግጧል። ሶማሊያ «ታላቋ ሶማሊያ» የሚለው ከንቱ ምኞቷ ኬንያንም እንደሚጨምር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠቁመው ይህን ከንቱ ምኞቷን ከግብ ለማድረስ ሶማሊያ ወደ ኋላ እንደማትል አስገንዝበዋል።
(የካቲት 10 ቀን 1970 የወጣው አዲስ ዘመን)
ገበሬዎች በወረራው የፈራረሱባቸውን ሱቆች አቋቋሙ
ድሬዳዋ/ ኢ-ዜ-አ-/ በድሬዳዋ ዙሪያ አውራጃ የሚገኙት አርሶአደሮች ከአሻጥረኛ ነጋዴዎች ብዝበዛ ለመዳን ቀድሞ ከፍተዋቸው ይገለገሉባቸው የነበሩት የኅብረት ሱቆች በእብሪተኛው ዚያድ ባሬ ወራሪ ጦር በመፍረሳቸው ለ ፮ ቀበሌ ገበሬ ማኅበራት በ፴፪ ሺህ ብር በሁለት አማካኝ ቦታዎች እንደገና በመክፈት ይገለገሉባቸው ጀምረዋል።
የ፮ ቀበሌ ገበሬ ማኅበራት አርሶ አደሮች ባደረጉት የጋራ መዋጮ አዲስ በተቋቋሙት በነዚህ ሁለት የኅብረት ሱቆች ውስጥ በአሁኑ ወቅት ጨው ስኳር አቡጀዲ የላስቲክ ጫማ የባትሪ ድንጋይና ሌሎችም የአካባቢውን ሕዝብ ኑሮ የሚመስሉ ቁሳቁሶች ለኅብረተሰቡ በተመጣጠነ ዋጋ በመሸጥ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
(የካቲት 2 ቀን 1970 የወጣው
አዲስ ዘመን)
የሶማሊያ ጦር ከጅጅጋ ሲባረር 64 መኰንኖቹን ረሸነ
የሞቃዲሾ አድኃሪ የገዥ መደብ ወራሪ ወታደሮች በጀግናው አብዮታዊ የኢትዮጵያ መደበኛ ፤የወዝአደርና የአርሶ አደር ሚሊሺያ ሠራዊት ከጅጅጋ ከመባረራቸው አስቀድሞ ፷፬ የራሳቸውን መኰንኖች ረሽነዋል።
የኢትዮጵያ ጀግና ሠራዊት በድል አድራጊነት ጅጅጋ በገባበት ወቅት ፷፬ ቱም መኰንኖች ተረሽነው መገኘታቸው ታውቋል። ስለተገደሉት ወታደሮች በተገኘው መረጃ መሠረት ፤ በጅጅጋ ውስጥ ሠፍረው በነበሩት አምስት የወራሪው ብርጌዶች መካከል በተፈጠረው የሞራል ውድቀት ምክንያት የተረሸኑት ወታደሮች አብዛኛዎቹ ወጣቶችና የሰሜን ሶማሊያ ተወላጆች መሆናቸው ታውቋል።
በተለይ እነዚህ የሶማሊያ መኰንኖች ጭፍጨፋ በይበልጥ ተጋኖ ሊወጣና ሊሰማ የቻለው፤ ወራሪው ኃይል በኢትዮጵያ ሠራዊት እየተባረረና መላቅጡ ጠፍቶት በሚወጣበት ጊዜ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ አብዮታዊ ሠራዊት በጠላት የተጠናከሩትን ምሽጎች እየሰበረ በሚገፋበት ጊዜ በጠላት ሠፈር ሽብር ከመፍጠሩም በላይ ፤ ጠላትም ፊቱን እያዞረ እግሬ አውጪኝ እያለ መሸሹን በዚህም ሽሽት ወቅት የጠላት ወታደሮች በሕዝብ ንብረት ላይ ብዙ ጉዳት ሊያደርሱ መቻላቸው ታውቋል።
(መጋቢት 7 ቀን 1970 ከወጣው አዲስ ዘመን )
አዲስ ዘመን ጥር 3/2014