ካሳለፍነው ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ዕርዳታ በማሰባሰብ አለሁ ለወገኔ በሚል በቦታው በመገኘት ተለጎጂዎች ድጋፉን አስረክቧል። በድጋፍ ማሰባሰቡ ወቅት ያጋጠማትን ያወጋችን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጇ ጽጌሬዳ ጫንያለው እንዲህ ብላናለች።
በችግር ተጎሳቁላለች። በጀርባዋ ልጅ አዝላለች። በእጅዋ ደግሞ በርከት ያለ መድሃኒት ይዛለች። “ድጋፍ የምታሰባስቡት ለማን ነው?” ብላ ጠየቀች። ‹‹ለተፈናቀሉ ወገኖች ነው’ ስንላት ከማሀረቧ ፈትታ 50 ብር ሰጠችን። የተረፋትን ሳይሆን ያላትን ሁሉ አበረከተች።”
በማከልም ‹‹ይህ ሴቶች የራሳቸውን ችግር ሳያዳምጡ በአሸባሪው ቡድን የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ ምን ያህል ተነሳሽ፣ ዝግጁና ቅን እንደነበሩ ያሳያል›› ትላለች ፅገሬዳ ጫንያለው። ከራሳቸው አስቀድመው ለወገናቸው ደራሽ መሆናቸውን ጠቋሚ መሆኑንም ትገልፃለች። ለዚህም ለሕይወታቸው የማይሳሱ እንዳልሆኑና በአውደ ውጊያ ግንባሮች ተሳትፈው የጽሑፍና የፎቶ ግራፍ መረጃዎችን ለመሰነድ የበቁ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሴት ጋዜጠኞች ምስክር መሆናቸውንም ትጠቁማለች።
ድጋፉን የማሰባሰብ ሃሳብ ካመነጩት የድርጅቱ ሴት ሠራተኞች ውስጥ አንዷ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጅ አስቴር ኤሊያስ እንደምትለው ሴቶች ስሜታቸው ስስ በመሆኑ ከባድ ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ቀጠና ውስጥ እንኳን ሆነው እርዳታ ለሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ያደርጋሉ። በጦርነቱ ለሞተ ለየትኛውም ሰው ደረታቸውን እየደቁ ያለቅሳሉ፤ ይቀብራሉ። በየግንባሩ ነጠላቸውን እያወለቁ የወደቀ አስክሬን የሚያለብሱም ነበሩ። ነጠላና ትርፍ ልብስ የሌላቸው በውስጥ ልብሶቻቸው ብቻ በመሆን ከላይ የለበሱትን አውልቀው ለታረዙት እስከ መስጠትና፤ ከረጅም ቀሚሳቸው ላይ ቀደው ህፃናት ሲያለብሱም ተስተውለዋል።
የሰሜን እዝ በሽብር ቡድኑ ከተጠቃ በኋላ ሠላም አለመኖሩንና መሀል አገር ያለው ሁኔታ ምን አልባት ትኩረት የተሰጠው ባይመስልም በአማራና አፋር ክልል ብዙ ሮሮ ሲሰማ መቆየቱን የምትጠቅሰው ጋዜጠኛዋ፤ ነገሮች እየከረሩ ሲመጡ እርሷ ግንባር ባትሄድም ለረጅም ጊዜ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ዘገባ ስትሰራ መቆየቷን ታወሳለች። ጦርነቱ በተፋፋመበት ጊዜ ደግሞ በጦር ግምባር በመዝመት የአውደ ውጊያ ውሎዎችን መዘገብ እንደምትፈልግ የጠየቀችው ራሷ እንደነበረችም ታወሳለች።
ዘመቻውን በተመለከተ ከድርጅቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ጋር ከተመካከረች በኋላ ከራሷና ከቤተሰቦቿ ያሰባሰበቻቸውን አልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶች በግንባር ቀጠና ለሚገኙ ተጎጂ ሴቶችና ቤተሰቦቻቸው ለመስጠት በሻንጣዎቿ ሞልታ እንደሄደችም ትናገራለች። አብረዋት የሄዱት ሹፌርና የፎቶ ግራፍ ባለሙያዎች የየራሳቸውን ድጋፍ ይዘው እንደሄዱም ትገልፃለች።
በግንባር ቆይታዋ ጋዜጠኛዋ በአሸባሪ ቡድኑ ተደፍረውና መራመድ አቅቷቸው በሕብረተሰቡ ታዝለውና ታቅፈው የሚንቀሳቀሱ ታዳጊ ሴቶች፣ ወጣት ሴቶች፣ እናቶች፣ ምን አልባትም ለደፋሪዎቹ ቅድመ አያት የሚሆኑ ዓለም በቃኝ ብለው በመቁረብ ቆብ የደፉ አዛውንት ሴቶችን ተመልክታለች። አልባሳትና ለብዙዎቹም ከወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ ሞዴስ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎች የሚያስፈልጋቸው እንደነበሩም ታዝባለች።
በተለይ ሰቆጣ ግንባር እስከ አበርገሌ የሽብር ቡድኑ ባደረሰው ጥቃት በርካታ ሴቶች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን፤ የሚለብሱት እንኳን እንዳልነበራቸውና በጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ተጋድሎ በሕይወት መትረፋቸውን ማየቷንም ትናገራለች። ይህ ትልቅ ዕድል ቢሆንም ታዲያ በመፈናቀል የሸሹት በለበሷት አንዲት ልብስ ግማሾቹም በውስጥ ልብስ ብቻ በመሆኑ በእነርሱ አቅም የተደረገላቸው የአልባሳት ድጋፍ ታሪክ ለመሰነድ ከሚያስችል የአውደ ግንባር ዘገባቸው ባሻገር ከፍተኛ ፋይዳ እንደነበረው ትመሰክራለች።
በሙያቸው አገራቸውን ለማገልገል ወደ ግንባር የዘመቱት እርሷና የስራ ባለደረቦቿ ከህፃናት ልጆቻቸው ጋር ሽሽት አልመች ብሏቸው በጦርነቱ ለተጎዱ ቤተሰቦችና ለማሕበረሰቡ ድጋፍ ማድረግን ማስቀደማቸውንና በጦርነቱ ይበልጥ የተጎዱትም ሴቶች መሆናቸውን እንዳስተዋለችም ትገልፃለች።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ወሎና ደቡብ ወሎ እስከ ወገል ጤናና ደላንታ አውደ ግንባሮች በመዝመት የህልውና ዘመቻውን ሂደት በፎቶ ግራፍ ያስቀረችው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የፎቶግራፍ ባለሙያዋ ፀሐይ ንጉሴ በበኩሏ በግንባር በነበራት ቆይታ ጦርነቱ ያስከተለው ቀውስ ይበልጥ ሴቶች ላይ መበርታቱንና ለነዚሁ የሕብረተሰብ ክፍሎች የበለጠ ድጋፍ የሚስፈልጋቸው መሆኑን ትናገራለች። በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንና የሚለበስ፣ የሚላስም ሆነ የሚቀመስ እንዳልነበራቸውም ታስታውሳለች።
በነዚሁ አካባቢዎች አይገኝም እንጂ ጦርነቱ ሲረጋጋ ከተገኘ ቁራሽ አንባሻ 40 ብር፣ አንዲት ትንሽ ብርጭቆ ሻይ ደግሞ እስከ 35 ብር ይሸጥ እንደነበርም ትገልፃለች። አብዛኞቹ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ሴቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት ድንገት በመሆኑና ገንዘብ ይዘው ባለመውጣቸው የመግዛት አቅም እንዳልበራቸውም ታስረዳለች። በየመንገዱ ላይ ወድቆ ከሚታየው አስከሬን የሴቶች አስከሬን የማይገኝበት አንድም ቦታ እንዳልነበርም ትናገራለች።
ልጆቻቸው ተገድለውና መላው ቤተሰባቸው አልቆ ብቻቸውን በመቅረታቸውና ደጋፊ በማጣታቸው ሌትና ቀን የሚያለቅሱ ሴቶች ቁጥርም ቀላል እንዳልሆነ ማየቷንም ትጠቁማለች። በንምባር እነርሱ ካደረጉት ድጋፍ ባለፈ የድርጅቱ ሴት ሰራተኞችም የአልባሳትና የቁሳቁስ ድጋፍ በማስባሰብ ለተረጂዎች እንዲቀርብ ማድረጋቸውንም የፎቶግራፍ ባለሙያዋ ትናገራለች።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሄለን እስክንድር በበኩላቸው እንደሚሉት እንደ ድርጅት ሠራተኛው ተሰባስቦ ከአመራሩ ጋር በመወያየት የሽብር ቡድኑ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ጥቃት ላደረሰባቸው ወገኖች ከወር ደሞዙ ጀምሮ በሚችለው አቅም ድጋፍ አድርጓል። በተጨማሪም ‹‹አለሁ ለወገኔ›› በሚል መሪ ቃል ታላቅ ንቅናቄ በመፍጠር ሕብረተሰቡን አስተባብሮ ባካሄደውና ለ15 ቀናት በዘለቀው ድጋፍ የማሰባሰብ ሂደት ከድርጅቱ ጋር አብረው የሚሰሩ አጋሮቹና ተቋማት እንዲሁም ሕብረተሰቡ ተሳታፊ ሆነዋል።
ድርጅቱ ለመከላከያ ሠራዊት ያደረገው ድጋፍ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን ከአፋርና ከአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖችም ለእያንዳንዳቸው ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የምግብ፣ የአልባሳትና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል። ጋዜጠኞቹን ወደ ሁሉም ግንባር በመላክ የዕለት ከዕለት ጦርነቱን ውሎ እንዲዘግቡም አድርጓል። ሠራዊቱ ያደረገው ተጋድሎ፣በጦርነቱ የተጎዱ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም ለእነሱ የሚደረገው ድጋፍ ድርጅቱ በሚያሳትማቸው አምስት ጋዜጦች ሽፋን እንዲያገኝና ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆንም ተደርጓል።
ድርጅቱ አምስተኛ ግንባር ተብሎ በሚጠራው በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ቀዳሚ በመሆን ለሕብረተሰቡ መረጃዎችን ሲያደርስ ቆይቷል። የዚህን ጦርነት ምዕራፍ የታሪክ አሻራ ለማስቀረት ከታህሳስ 25 እስከ ጥር 15፣ 2014 ዓ.ም የሚቆይ የፎቶ ግራፍ ኢግዚቢሽን በመክፈት ለመጀመሪያ ጊዜና በብቸኝነት አዘጋጅቷል።
ከዚህ ባሻገር ድርጅቱ የህልውና ዘመቻ ሂደቱን ታሪክ ሆኖ በሚሰነድ ምስል ጭምር ሕዝቡ እንዲያየው እያደረገ ይገኛል። ለዕይታ ከቀረቡት ፎቶግራፎች ውስጥ ሴት የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ያነሷቸው አሉ። የድጋፍ ሃሳቡን በዋነኛነት ያመነጩት የድርጅቱ ሴት ሠራተኞች ሲሆኑ የአካባቢው ነዋሪና አላፊ አግዳሚው ድጋፍ እንዲያደርግ ድንኳን ጥለው ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
‹‹ድርጅቱ የድጋፍ ዕቅዱን ይዞ የተንቀሳቀሰው የሴቶች ለችግር ተጋላጭነት የከፋ መሆኑን ታሳቢ አድርጎ ነው›› ያለችው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጇ ጽጌሬዳ ጫንያለው ነች። እንኳን በጦርነት፣ በሠላሙም ጊዜ ከቤታችን ወደ ሌላ ቦታ ስንሄድ ብዙ ነገር ያስፈልገናል ትላለች። አሸባሪው ባደረሰው ጥቃት በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከአማራና ከአፋር ክልሎች ሀብት ንብረታቸውን ሙሉ በሙሉ ትተው ነፍሳቸውን ለማዳን ወደ ሌሎች አካባቢዎች መሸሻቸውንም ትጠቁማለች።
ሁኔታው የሚበሉበት፣ የሚተኙበትና የሚለብሱት እንዳሳጣቸውም ጠቅሳ፤ ሴቶች እንደሴትነታችን ችግሩን በጥልቀት እንገነዘበዋለን ስትል ትገልፃለች። የተሰበሰበው የአልባሳትና ቁሳቁስ ድጋፍም ከቡና ስኒና ከማራገቢያ ጀምሮ ለሴቶች የሚያስፈልግ መሆኑንና የሁሉንም ሕብረተሰብ ልብ በመንካት እጅ ማዘርጋቱን በምትሰበስብበት ወቅት እንደገጠማት ትጠቁማለች።
እንደርሷ ገለፃ የተሰበሰቡት አልባሳት በአፋር ክልል ባህል ለሴቶች ስለማይሆኑ ወደ አማራ ክልል እንዲላኩ ተደርገዋል። የሴቶች ንጽሕና መጠበቂያ ሞዴስ ጨምሮ ፍራሽ፣ የፅዳት ዕቃዎች፣ ማኮሮኒ፣ ፓስታ፣ ዱቄትና ሌሎች ምግቦችና የምግብ ማብሰያ ቁሳቁሶች ለአፋርም ለአማራም ክልል ተልከዋል። በተጨማሪም ፕሬስ ድርጅት ለተቋማትም አገልግሎት የሚውል ድጋፍ አበርክቷል። ለፈረሰባቸው መገናኛ ብዙሃን፣ ለከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ለሆስፒታሎች ያደረገው ድጋፍም የዚሁ አንዱ ማሳያ ነው። በዚህም የመጀመርያው ዙር ድጋፍ ስኬታማ በመሆኑ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
ሌላዋ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጅ የሆነችው ምህረት ሞገስ “በማንኛውም ቀውስ ወቅት ተጎጂ የሚሆኑት ከወንዶች ይልቅ ሴቶች መሆናቸውን” ትጠቁማለች። በችግር ወቅት ለራሳቸው ሳይሆን የሚያስቡት ለልጆቻቸውና ለመላው ቤተሰባቸው መሆኑንም ትጠቅሳለች። በቀውስ ወቅት ደግሞ ይህ ሁኔታ ተጎጂነታቸውን ይበልጥ እንደሚያባብስው ትናገራለች።
ሴቶች በቀውስ ወቅት በአካባቢያቸው ችግር ሲፈጠር እንደ ወንዶች ማቄን ጨርቄን ሳይሉ የሚሸሹበትና ራሳቸውን የሚያድኑበት ሁኔታም እጅግ ጠባብ መሆኑን ገልፃ፤ ጉልበታቸው ልጅ ወልዶ በማሳደግና በተደራራቢ ኃላፊነት እንደሚደግም ታስረዳለች። ትንሽ የተሰባሰበች ጉልበት ቢኖራቸውም ህፃን ልጆች ሊኖራቸው ስለሚችል አንዱን አዝለው ሌሎቹን እየጎተቱ መሸሽ የማይታሰብ እንደሚሆንባቸውም ትጠቁማለች። ልጆቻቸውን ትተው መሸሽ ባለመቻላቸው በጦርነቱ ጾታዊና ሰብአዊ ጥቃቶች ሲደርሱባቸው እንደነበርም ትጠቅሳለች።
እንደ ምሕረት ሞገስ ገለፃ ድጋፉን ማሰባሰብ ያስፈለገበት ዋና ዓላማ በዋናነት አሸባሪው ቡድን ጦርነት በከፈተባቸው በአማራና በአፋር ክልል ያሉ ተፈናቃዮችን በተለይ ደግሞ ሴቶችን ለመደገፍ ነው። በጉዳዩ ላይም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሴት አመራሮችና ሠራተኞች የሴቶች ጉዳይ ተወካይ በተገኙበት ከድርጅቱ አመራሮች ጋር ተወያይቷል። ሠራተኛውም ለመከላከያ ሠራዊት የወር ደሞዙን ሰጥቷል።
ለተፈናቃይ ሴቶችስ ምን እናድርግ በሚል ጥያቄ ተነስቷል። በሕብረተሰቡ እና በማሕበረሰብ ውስጥ ሴቶች ጾታ ሳይለይ ልጅና ባሎቻቸውን፣ ወንድሞቻቸውን፣ አባቶቻቸውን የመንከባከብ ድርብ ኃላፊነቶች ስላሉባቸው ይሄንኑ ታሳቢ ያደረገ ድጋፍ ማሰባሰብ ለማካሄድ ተወስኗል። በዚሁ መሰረትም ድጋፉ ተሰባስቦ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተልኳል። በድጋፉ አሰባሰብ ወቅትም የሴቶቹ ተሳትፎ የነቃ በመሆኑ በተመሳሳይ በቀጣይም የድጋፍ ማሰባሰቡ ተገባር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥር 3/2014