ለኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ እናት እና የህልውናቸው መሰረት ናት። እሷ ወድቃ እነርሱ አይቆሙም። እሷ እያዘነች እነሱ አይደሰቱም። እሷን ረስተው እነርሱ አይታወሱም። እሷ ከሌለች የእነርሱ በሕይወት መቆየት ትርጉም አልባ ነው።
ለኢትዮጵያውያን አገራቸው የነፃነታቸው ምንጭ ናት። የሚኖሩት በእሷ ተከብሮ መቆየት ውስጥ ነው። እርሷ ሰላሟን አጥታ ሕሊናቸው አትረጋጋም። ኢትዮጵያ ጎድሎባት እነርሱ አይሞላላቸውም። እርሷ ዝቅ ብላ እነርሱ አይገዝፉም። የሚኖራቸው አገራቸው ሲኖራት ነው። ያለ ኢትዮጵያ የሚበሉት አይጣፍጣቸውም። የሚጠጡት አያረካቸውም።
ኢትዮጵያውያን መቼም ቢሆን ለአገራቸው ያላቸው ፍቅርና አክብሮት የሚለወጥ አይደለም። ልባቸውን እንጂ ጀርባቸውን ለኢትዮጵያ የሚሰጡም አይደሉም። እድገቷን እንጂ ዝቅታዋን፣ ደስታዋን እንጂ ሃዘኗን፣ ክብራን እንጂ ውርደቷን ፈፅሞ አይመኙም።
አገር ውስጥ እንዳሉት ሁሉ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም የዚህ እሳቤ አንጸባራቂዎች ናቸው። ከምንም በላይ የአገራቸውን ፍቅር በልባቸው ይዘው የሚኳትኑና በአካል ቢርቁም በመንፈስ ሁሌም ከኢትዮጵያ ጎን የሚገኙ ናቸው። አብዛኞቹም አገራቸውን የሚወዱ፣ አገራቸው ተሻሽላና አድጋ ማየት የሚፈልጉና አንድ ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትኖር ከልብ የሚመኙ፤ ለዚያም የሚታገሉ ናቸው።
ኢትዮጵያዊውን በአካል ከኢትዮጵያ ታወጣው እንደሆነ እንጂ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊው ውስጥ ማውጣት አይቻልም። እንዲሁም ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን አይተውም እንደሚባለው፣ እውነተኛ ኢትዮጵያውያንም መቼም ቢሆን ለአገራቸው ያላቸው ፍቅርና አክብሮት የሚለወጥ አይደለም። ልባቸውን እንጂ ጀርባቸውን ለኢትዮጵያ የሚሰጡም አይደሉም። እድገቷን እንጂ ዝቅታዋን፣ ደስታዋን እንጂ ሃዘኗን፣ ክብራን እንጂ ውርደቷን ፈፅሞ አይመኙም።
ይህ ስሜታቸውም በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በግልፅ አደባባይ የታየ ነው። በዶክተር ዐቢይ አመራር በተመዘገቡ ለውጦች ምክንያት በኢትዮጵያና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል የነበረው ርቀት በአስደናቂ ፍጥነት ጠቧል። በሁሉ ረገድ የሚያስተሳስር ድልድይ ተገንብቷል። በፖለቲካ ቅራኔ እና በተለያዩ ምክንያቶች ከአገሩ ጋር ተኳርፎ የነበረው የአገር ልጅ ኩርፊያው ሽሯል። ዳግም ከእናት አገሩ ጋር ያለው ትስስር ታድሷል።
በአሁኑ ወቅትም በመላ ዓለም የሚገኙ ዳያስፖራዎች ለእናት አገራችን ለኢትዮጵያ አናንስም፣ ባለን ሁሉ እንቆምላታለን ብለው ተነስተዋል። በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻም በተለያየ መልኩ እየተሳተፈ ይገኛል።
በተለይ ኢትዮጵያ ላይ የተከፈቱ ወቅታዊ ሴራዎችን ለመቀልበስ ዓለም እውነቱን እንዲረዳ ድምጻቸውን በማሰማት ታላቅ ገድልን እየፈጸሙ ናቸው። ለዚህ ሕዝባዊ ተነሳሽነት ሰሞኑን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚደረጉ ‹‹no more ወይንም ‹‹በቃ” በተሰኘ ሃሳብ የተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች በቂ ምስክሮች ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም ከቀናት በፊት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት በመግባት በዓላትን እንዲያከብሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎም፣ በርካቶች የአገራቸውን አፈር እየረገጡ፣ በጋራ ቤታቸው መሰባሰብ ጀምረዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም የዳያስፖራው አገር ቤት መግባት ለአገሪቱ ወቅታዊ ፈተና ምን ምላሽ ይኖረዋል? ለኢኮኖሚው የሚኖረው ትርጉምስ? የዳያስፖራውን አቅም ወቅታዊ ተነሳሽነት ለመጠቀምስ ቀጣይ ተግባራት ምንድ ናቸው? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ምሁራን፣ ዳያስፖራዎችና አመራሮችን አነጋግሯል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡን የምጣኔ ሀብት ምሁራን መካከል በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ሞላ አለማየሁ አንዱ ናቸው። ዶክተር ሞላ፣ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ለአገሩ ማበርከት የሚችለው የገንዘብም ሆነ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እጅጉን ከፍተኛ ስለመሆኑ ያስረዳሉ። አንዳንድ አገራትም ከወጭ ንግድ ከሚያገኙት ገቢ ባልተናነሰ መልኩ ከዳያስፖራው እንደሚያገኙም ያነሳሉ። ለአብነትትም ቻይና በትንሹ እስከ 20 ቢሊየን ዶላር ከዳያስፖራው ማሕበረሰብ እንደምታገኝ ያጣቅሳሉ።
‹‹ኢትዮጵያ በአንጻሩ ባላት ልክ የዳያስፖራዎችን አቅም ተጠቅማበታለች ለማለት እጅግ አስቸጋሪ ነው›› የሚሉት ዶክተር ሞላ፣ ችግሩ ዳያስፖራውን በአንድነት አስተባብሮ በአገሩ ጉዳይ እንዲተባበር በማድረግ ረገድ በቂ የሆነ ስራ መስራት ያለመቻል ስለመሆኑም ያስገነዝባሉ።
በአሁኑ ወቅት የዳያስፖራው ወደ አገር ቤት መግባት ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ስለመሆኑ የሚያስረዱት ዶክተሩ፣ በተለይም ምእራባውያኑ ከተለያየ አቅጣጫ በተቀነባበረ መልኩ የሃሰት ዘገባን በማራገብ ዓለም ኢትዮጵያን በተሳሳተ መንገድ እንዲገነዘብ የማስጨነቅ፣ የመክሰስ፣ የመወንጀል ዘመቻን በተያያዙበት በዚህ ወቅት መሆኑ ትርጉሙን የላቀ እንደሚያደርገው ያሰምሩበታል። ‹‹ከሁሉ በላይ በገፅታ ግንባታ ኢትዮጵያ እንደሚባለው እንዳልሆነች ግልጽ መልእክት ያስተላልፋልም›› ይላሉ።
የምጣኔ ሀብት ምሁራኑ እንደሚያስረዱት ከሆነም፣ ዳያስፖራው ወደ አገር ውስጥ መግባት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በተለይ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማሳደግና ለማዘመን የራሱን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። በተለይም በጦርነቱ የወደሙትንም የቱሪስት መዳረሻዎችን መልሶ ለመገንባት በቱሪስት ፍሰት ገቢ ያገኝ የነበረውን ዜጋ ለማገዝና በጦርነቱ ምክንያት የተመሰቃቀለው ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲያገግም ለማድረግ አስተዋፅኦ የጎላ ነው።
የአገልግሎት ዘርፉን ከገባበት ድብርት በማነቃቃት በአንድ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገውና በተለይ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለባትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማቃለል ረገድ አስተዋጽኦው ቀላል የሚባል እንዳልሆነም አፅእኖት ይሰጡታል።
‹‹የዳያስፖራው መግባት በኢኮኖሚ ረገድም በተለይ ለአገልግሎት ዘርፉና ለተዋናዮቹ ከፍተኛ እድል ይፈጥራል›› የሚሉት ዶክተር ሞላ አለማየሁ፣የእንግዶቹ ቆይታም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሰላማዊ ሁኔታ ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ያለውን ምቹነት ለማሳየት እንደሚያስችል ያሰምሩበታል።
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ተሾመ ዱላም፣ የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መምጣት ኢትዮጵያ ሰላማዊ አገር መሆኗን ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ከማስገነዘብ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን ለማፋጠንና ለማንሰራራት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ይላሉ።
ዳያስፖራው ከወትሮው በተለየ መልኩ ወደ አገር ቤት በብዛት መምጣት በተለይም አሸባሪው ሕወሓት በከፈተው ጦርነትና በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ምክንያት የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ያሰምሩበታል።
አሸባሪው ሕወሓት ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉት ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ፣የወደሙትን ተቋማትን መልሶ በመገንባት የዳያስፖራው ጉብኝት ወሳኝ ድርሻና ተሳትፎ እንዲኖረው ያደርጋል የሚሉት መምህሩ፤ የዳያስፖራውን ዕውቀትና ሀብትን ወደ አገር በማምጣት ስደትን በመቀነስ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠርና ኢኮኖሚውን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አፅእኖት ይሰጡታል።
አገራቸውን በኢንቨስትመንት በመሰማራት፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የአገራቸውን የቱሪዝም መስህቦች እና ምርቶች ለዓለም በማስተዋወቅና የአገራቸውን መልካም ገጽታ ለመገንባት ጉልህ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መንግሥት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚኖርበት ምክረ ሃሳባቸው ይሰጣሉ።
የቀድሞ የአየር ኃይል አባል፣.ካፒቴን ክንዴ ዳምጤም፣ ዳያስፖራው ከመቼው ጊዜ በላይ ወደ አገሩ ለመግባትም ሆነ ለመደገፍ በከፍተኛ መነሳሳት ውስጥ ነው፣ በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ባለው ግፍና በደል ውስጡ ተቆጥቶም፣ በየቀኑ የተቃውሞ ሰልፎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ በየትኛውም የአገሩ ጉዳይ ላይ ዘብ ቆሞ እየተሟገተ ነው›› ይላሉ።
ይህንን ከፍተኛ ተነሳሽነት ወደ ጥሩ አጋጣሚ መቀየር እንደሚያስፈልግ አፅእኖት የሚሰጡት ካፒቴኑ፣ በተለይም በጦርነቱ የተጎዱ ክልሎች ለማቋቋምም ሆነ የአግዋን ተፅእኖ ለመቋቋም የውጭ ድጋፍ ሳያሻ የኢትዮጵያውያን መረዳዳትና መደጋገፍ ብቻውን በቂ ስለመሆኑም ያስገነዝባሉ።
ዳያስፖራው በአመዛኙ ለአገሩ ምን ማድረግ እንዳለበትና እንዴት ሊያደርግ እንደሚችል እውቀቱ እንደሌለው የሚጠቁሙት ካፒቴኑ፣ይህን አይነት ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ደግሞ መንግሥት የዜግነት ግዴታ መጣልን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን ያስገነዝባሉ።
ካፒቴኑ እንደሚያስረዱት፣ የዳያስፖራውን አቅም ለመጠቀም መንግሥትም ለዚህ እሳቤ ተገቢውን ትኩረት መስጠትና ጉዳዩን የሚከታተል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መክፈት ይኖርበታል። በመንግሥታዊም ሆነ በግል ተቋማት ለሚጠይቁት አገልግሎትም የተቀላጠፈ ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል።
‹‹ዳያስፖራውም ከያለበት አገር ሆኖ አንድ ቀን ለኢትዮጵያ ብቻ ብሎ ቢሰራ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። በወር 4 ሰዓት እንኳን ብንሰራ ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል። ይህንን ግን የሚያስተባብር አካል ያስፈልጋል። ለዚህም የፌዴራል መንግሥቱና የክልል መንግሥታት ተናበውና ተጠናክረው መስራት ይገባቸዋል›› ነው ያሉት።
በተለይም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት ይዘውት የሚመጡትን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ የሚለውጡት ከሆነ የአገሪቱን ትልቅ የውጭ ምንዛሬ ሸክም ለጊዜውም ቢሆን ሊያቃልል ይችላል የሚለውም ከምሁራን አስተያየት መካከል ጎልቶ ይነሳል።
ባለፉት አስራ ሰባት ዓመታት ነዋሪነታቸውን በእንግሊዝ አገር ለንደን ከተማ አድርገው የቆዩት አቶ በቀለ ወዬቻም በዚህ እሳቤ ይስማሙበታል። አቶ በቀለ ‹‹ከአገር ውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአግዋ ክልከላን ጨምሮ ወቅታዊውን የምእራባውያን አሻጥር የማክሸፍና በተለይም የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሬ ጥያቄ በመመለስ ረገድ ከፍተኛ አቅም አላቸው›› ይላሉ።
በተለይ፣ በአሸባሪው ቡድን እኩይ ስራ የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለማስተካከል እየተሰራ ያለው ስራ በውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳይጎዳ ዳያስፖራው የበኩሉን መወጣት እንዳለበት የሚያመላካቱት ዳያስፖራው፣አገራዊ ጥሪ ተቀብሎ የመጣ ሁሉ ለጥቂት ሽርፍራፊ ትርፍ ብሎ የውጭ ምንዛሬን በጥቁር ገበያ መቀየር እንደሌለበት አፅእኖት ይሰጡታል። ማንኛውንም ልውውጥና ግብይት በህጋዊ መንገድ በባንክ መልኩ ቢፈፅም ኢኮኖሚውን በመደገፍ ረገድ ሁነኛ አቅም እንደሚፈጥም ነው የገለፁት።
ወደ አገር ቤት ከሚገባው ዳያስፖራው ተጠቃሚ ለመሆን እነሱን ማስተናገድ የሚያስችል አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግም ይታመናል። አንድ ሚሊዮን የሚሆን ዳያስፖራ ወደ አገር ከመጠራት ባሻገር እነርሱን ማስተናግድ የሚያስችል አቅም ስለመኖሩም ታሳቢ ማድረግ የግድ ነው።
ዳያስፖራዎቹ በኢትዮጵያ የሚኖራቸው ቆይታ ያማረ እንዲሆን አገልግሎት ሰጪና አቅራቢዎች ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚያመልክቱት ዶክተር ሞላ አለማየሁ በበኩላቸው፣ ምክንያታዊ ባልሆነ መልኩ ያልተገባ ጥቅም ፍለጋና ደረጃውን ያልጠበቀ አገልግሎትም የእንግዶችን ቆይታ ከማሳጠር ባለፈ በቀጣይም ወደ አገራቸው እንዳይመጡ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ሳያስገዝቡ አላለፉም።
መንግሥት ከአንድ ሰሞን ባለፈ በውጭ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር ወዳጅነቱን አጠናክሮ መቀጠልና አቅማቸውን አስተባብሮ ወደ ፊት መራመድ የሚችል ከሆነም የአገሪቱ ችግር በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የማይቃለልበት ምንም አይነት ችግር አይኖርም።
በተለይ በጉብኝት ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ወደ አገራቸው እንዲመጡ ማድረግ ላይ ተግቶ መስራትና ለዚህም ምቹ ከባቢን መፍጠር ከተቻለ ውጤቱ አመርቂ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።
ከዚህ ቀደም ዳያስፖራውን በአገሩ ለማሳተፍ የፖለቲካ ተቃዋሚና ደጋፊ የሚል ልየታ እንደነበር የሚያስታውሱት ዶክተር ሞላ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ሆነ ኤምባሲዎች ሁሉም ኢትዮጵያዊ አገሩን ለመጥቀም እስከፈለገ አሁን ላይ ሁሉንም በእኩል አይን ተመልክተው አቅማቸው መጠቀም እንዳለባቸውም ነው አፅእኖት የሰጡት።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የኮሚኒኬሽን ዳይሬከተር አቶ ወንድወሰን ግርማም፣ በአሁኑ ወቅት ዳያስፖራውን እጅግ አስደናቂ በተባለ መልኩ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለእናት አገሩ እያደረገ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ኤጀንሲው በተለይም ዳያስፖራው መብትና እና ጥያቄ በማስከበር ረገድ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ለማከናወን በተለይም ኢንቨስት ለማድረግ በሚፈልግበት ጊዜ እንቅፋቶች ሳይገጥሙት፣በተቀላጠፈ መልኩ አገልግሎት እንዲያገኝ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑንም ይገልፃሉ።ይሁንና ‹‹ዳያስፖራው ገንዘቡን፣ ዕውቀቱንና ልምዱን አቀናጅቶ አገሩን የሚደግፍበት መደላድል እንዲፈጠር፣ ጥረቶቻቸውን ይበልጥ ማስተባበር ይጠይቃልም›› ይላሉ።
በተለይ ጥቁር ገበያ ምንዛሬን ለማስቆም ዳያስፖራው ገንዘብ በሚልክበት ወቅት የመላኪያው ወጪ ባንኮች የሚጋሩበት ሁኔታ መፍጠርና መደበኛ መልኩ የሚልኩ ዳያስፖራዎችን ይበልጥ ማበረታታት፣ ሽልማት መስጠትና የእውቅና መርሃ ግብሮችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ሳይጠቁሙ አላለፉም።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ግርማ ሰይፉ፣ ‹‹ዳያስፖራው የአገሩን መሪ ጥሪ ተቀብሎ ወደአገር ቤት ለመምጣት መወሰኑ በራሱ ትልቁን ሚና ተወጥቷል የሚያስብል ነው፣ እነዚህ ዜጎች በመምጣታቸውም በአገራቸው ላይ ተሟርቶ የነበረውን ትልቅ ሟርት አክሽፈዋል፣ የጠላትን ቅስም ሰብረዋል›› ይላሉ።
በተሳትፏቸውም በጦርነት ምክንያት የተዳከመው ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና እንዳለው የሚያስረዱት አቶ ግርማ፣ እንደ ኢንቨስትመንት ቢሮ እነዚህ ዳያስፖራዎች ሀብታቸውን እዚሁ ኢንቨስት አድርገው እንዲሄዱ አንዳንድ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ስለመሆኑ ነው ያስገነዘቡት።
ተሳትፋቸውን ወደ ሀብት ለመቀየርም በተቻለ ሁኔታ ሳቢና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የሚያስገነዝቡት ኮሚሽነሩ፣ በተቻለ መጠን ከቢሮክራሲ የጸዳ አገልግሎት እንዲያገኙ ጉዳዮቻቸው በፍጥነት ሕግና ደንብን በተከተለ ሁኔታ እንዲፈጸሙ ያላሰለሰ ጥረት እናደርጋለን›› ነው ያሉት።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 3/2014