ዘመኑ ጦርነት በጦር መሣሪያና በሰብዓዊ ኃይል ብቻ የሚካሄድበት አይደለም፡፡ ፕሮፖጋንዳ ያስፈልጋል፡፡ ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው እንደሚባለው፡፡ ወሬ ማለት ለዚህ ዘመን ፕሮፖጋንዳ ነው፡፡ እናም ይህ ፕሮፖጋንዳ በጦርነት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
ፕሮፖጋንዳ እኔ እንደሚገባኝ አንድ አጀንዳ በተለያየ መንገድ ወደ ሕዝብ እንዲደርስ የሚደረግበት የማሳመኛ መሣሪያ ነው፡፡ ይህ ተግባሩ ግን በአንዳንድ ወገኖች ተጠልፎ ይታያል፡፡
ቡድኖች በኩል ሲታይ የሐሰተኛ መረጃ ማሰራጫ ሆኗል፡፡ ምዕራባውያኑና ትህነግ በኛ አገር ላይ እያደረጉ ያሉትም ይህንኑ ነው፡፡ የኢራቁ ሳዳም ሁሴን የስልጣን ጀንበር እየጠለቀችባቸው በነበረበት ወቅት የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር አሜሪካ መራሹ ጦር ባግዳድን ሙሉ ለሙሉ እስከሚቆጣጠር ድረስ የኢራቅ ጦር በድል ጎዳና ላይ ነው ሲሉ ይገልጹ ነበር፤ ለእዚያውም በሙሉ መተማመን ላይ ተመሥርተው፡፡ የባግዳድ አውሮፕላን ማረፊያ በከባድ መሣሪያ አመድ እየተደረገ ባለበት ወቅትም በእዚሁ ቀጥለዋል፡፡ አንድ ጋዜጠኛ በስልክ ይህን የአየር ማረፊያውን ድብደባ አስመልክተው ምን ይላሉ ስትል ትጠይቃቸዋለች፡፡ እሳቸው ግን የምትይው ሁሉ ከእውነት የራቀ ነው፤ ከፈለግሽ ነይና ላስጎብኝሽ እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡
በቅርቡ በወረራ ይዘዋቸው ከነበሩ የአማራና አፋር አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ ተደምስሰው ወሬ ነጋሪያቸውን ብቻ ይዘው ያመለጡት የኛዎቹ ትህነጎችም እንደዚያው ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ልንገባ ነው ብለው ሕዝባቸውን ዋሹ፡፡ የተፈጠሩበትን ቀን እስከሚረግሙ ድረስ ተቀጥቅጠው ወደ ትግራይ ተመለሱ፡፡ ልብ በሉልኝ ወሬ ነጋሪ እንጂ የተመለሰ ሠራዊትም፣ የረባ መሣሪያም አልነበራቸውም፡፡ ተሸንፈው ተሸንፈን ብለው አያውቁም፤ ተሸነፍኩን ይፈሩታል፡፡
ከውሸት ግብአቶች የተሰሩት እነዚህ ጉዶች ግን መጀመሪያ ላይ ከአማራና አፋር ክልል የወጣነው በስልታዊ ማፈግፈግ ነው ሲሉ ተናገሩ፤ አምስት መቶ ሜትር ምን የሚሉት ማፈግፈግ ነው፡፡ ጦርነቱን ትተነዋል ቢሉ ይሻላል፡፡ ሌሎች አመራሮቻቸው ደግሞ ቆይተው ለሰላም ብለን ነው አሉ፡፡ ውሸታሞች! ቡድኑ ራሱ የጦርነት ጀማሪ ሆኖ ፣ ይህንንም ራሱ አምኖ እያለ ሌላ ጊዜ መንግሥትን ጠብ ጫሪ አርጎ ከሷል፤ የእርዳታ አቅርቦትን ራሱ እያስተጓጎለ አሁንም በትግራይ ውስጥ አስከፊ ረሃብ ሊከሰት ይችላል ብሎ መንግሥትን የከሰሰ ነው ፤ ሁሉም በሐሰተኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ የሚፈጸም ክስ ነው፡፡
ትህነግ ሲፈጠርም በሐሰተኛ መረጃ ላይ የሚሠራ ነው፡፡ እውነት ቢናገር ውሎ የሚያደር የማይስል ቡድን፡፡ በእውነተኛ መንገድ ታላቋ ትግራይ የሚላትን አገር ተብዬ እውን እንደማያደርግ እንዲሁም ዘረፋውን አንደማይቀጥል በማመኑ ሐሰተኛ መንገዶችን ሲቀይስ፣ ሲገነባና ሲደለድል ኖሯል፡ ፡ የመንግሥትን ስልጣን ይዞ በነበረበት ወቅት ደግሞ ይህን በሚገባ ተጠቅሞበታል፡፡ በእዚህ መንገድ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲያታልል ኖሯል፡፡
ያልሠራውን ሠርቻለሁ ሲል፤ የማይሠራውን እየለጠጠ ማቅረብ ሥራው ነበር፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ያልደረሰበትን ደረጃ ደርሷል ሲለን ኖሯል፡፡ የስኳር ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ ያሰራጫቸው የነበሩ መረጃዎች ውሸት መሆናቸውን ዛሬም ድረስ ያልተፈታው የአገራችን የስኳር ችግር ያመለክታል፡፡
ሜቴክ የሌለውን አቅም አለው እያለ በከፍተኛ ጥንቃቄ መገንባት ያለበትን ይህን ግድብ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራ ለለማጅ ድርጅት ሰጥቶ መጫወቻ ማድረጉ አንሶ ድርጅቱ ምንም ባልሰራበት ሁኔታ ከፍተኛ መቶኛ አፈጻጸም ደርሷል፤ ለእዚህ ደካማ ተቋም ያገር ልጅ የማር እጅ እያለ እያንቆለጳጰሰ ያሰራጭ በነበረው መረጃ በሕዝብ ተስፋ ላይ ሲጫወት ኖሯል፡፡ አንዳንድ ምሳሌ ለማንሳት እንጂ ትህነግ የሠራው ሁሉም ነገር በውሸት የተለወሰ ነው፡፡ በእውነት ተጀምሮ በእውነት ያለቀ የለውም፡፡ ሥራው እስከሚያልቅ ገንዘብ ሲሰርቅ፤ ጊዜ
ሲሰርቅ ፣ የትውልድ ተስፋ ሲሰርቅ ነው የኖረው፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ቀስ እያለ እየገነባ ብዙ ዶላር ሊያገኝበት ቢያስብም አገራዊው ለውጥ ከአፉ ላይ ነጠቀው፡፡ ይህ ሀሳቡ ሳይሳካለት ቢቀር ትግራይ ላይ መሸጎ በግድቡ ላይ መዶለቱን ቀጥሏል፡፡
የለውጡ መንግሥት ግድቡን ከነበረበት ውስብስብ ችግር በማውጣት በትክክለኛው መንገድ እንዲጓዝ እያደረገ ባለበት ወቅት ደግሞ ሌባ እናት ልጇን አታምንም እንዲሉ ነገር ሆነ፡፡ መንግሥት በትኩረት እየሠራበት ባለው የህዳሴ ግድብ ላይ ነጭ ውሸት መንዛታቸውን ቀጠሉ፡፡ ጌታቸው ረዳ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ግድቡን ለአረቦች ሸጦታል ሲል መግለጹን እዚህ ላይ ማስታወስ ይገባል፡፡
ትህነግ ወደ ደቡብ ወሎና ሰሜን ሸዋ በዘለቀበት ወቅትም ሌሎች የውሸት ናዳዎችን አወርዷል፡፡ የቡድኑ መሪ ደብረ ጽዮን ጦርነቱ ተጠናቅቋል፤ እጃችሁን ስጡ ፣የምታድኑት ከተማም ሆነ ሕዝብ የለም፤ ሲሉ መግለጫ ሰጡ፡፡
በዚያው ሰሞን አንድ የታጣቂዎቹ መሪ ድርድር የሚባል ነገር የለም፤ ጦርነቱ አልቋል፤ ከማን ጋር ነው የምንደራደረው ብለው ነበር፡፡ አሁን ትግራይ ላይ ተሰብስበዋል፡፡ የውሸታቸውን ልክ አንድም ከዚህ መረዳት ይቻላል፡ ውሸታም የሚለው ቃል ይህን ቡድን ባይገልጸውም ፣ ውሸቱ ግን ልክ እንደሌለው ከሚምታታው መረጃቸውም መረዳት አያዳግትም፡፡ ጋሸናን መልቀቅ መቀሌን መልቀቅ ነው ይሉ የነበሩት ትህነጎች በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ደርሶባቸው ጋሻናን ለቀው ከወጡ በኋላ እንደገና መልሰን ይዘነዋል ብለው ነበር፡፡
በዚህ ወቅትም 80 ሺ የአቢይን ጦር ከሥራ ውጪ አርገናል አሉን፡፡ ይህን ማድረግ ከቻሉ ምን የቀራቸው ጦር አለ? ውሸታቸው ልክ የለውም፡፡ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ደምሰሰናል ማለትማ ልማዳቸው ነው፡፡ ይሄ በሐሰት መረጃ ያበጠ፣ ቀላማጅ ቡድን ነው እንግዲህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ድርድር የሚጠይቀው፡፡
አንዴ ለአሜሪካ፣ ሌላ ጊዜ ለአውሮፓ ኅብረት እንዲሁም ለተመድ ሳይቀር ደብዳቤዎችን እየላከ ለሰላም ዝግጁ መሆኑን እየገለጸ አደራድሩኝ የሚለው፤ የኢትዮጵያ መንግሥትን ባልዋለበት እያዋለ ሰብዓዊ መብት እየጣሰ ነው እያለ በመክሰስ እኔ እመኑኝ
የሚለው ይህ ቡድን ነው ድርድር እየጠየቀ ያለው ፡፡ ድርድርን ሲጠይቅ ምክንያት ብሎ ያቀረበው ራሱ እኮ ውሸት ነው፡፡ ተሸንፌ ነው ትግራይ የተመለስኩት መች አለ? በመጀመሪያ ደረጃ ለድርድር ዝግጁ የሆነ አካል ቀላማጅ መሆን ይለበትም፡፡ ቡድኑ በከፍተኛ ደረጃ ይቀላምዳል፡፡
በአገራችን ከአነጋገር ይፈረዳል ፤ ከአያያዝ ይቀደዳል ይባላል፡፡ ቡድኑ በእኩይ ድርጊቱ ብቻ ሳይሆን በእኩይ አነጋገሩ የወደቀ ነው፡፡ ከእዚህ ቡድን ጋር ድርድር እንዲደረግ የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ ይታወቃል፡፡
አነዚህ አካላት /አሜሪካ ፣አውሮፓዎችና የተባበሩት መንግሥታት የተለያዩ ተቋማት/ በቅድሚያ የቡድኑ ተባባሪዎች ናቸው፡፡ ቡድኑ እዚህ ደረጃ ያደረሱት ፣ በክፋቱ እንዲቀጥል ያደረጉት እነሱ ናቸው፡፡ በመቀላመዱ እንዲቀጥል ያበረታቱት ወይም እንዲቀላምድ የሚያደርጉትም እነሱው ይመስሉኛል፡፡ ከዚህ ቡድን ጋር መደራደር ያበቃለት ጉዳይ፤ መደራደር አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝ እንኳ፣ በቅድሚያ መሠራት ያለበት አንድ ትልቅ ሥራ አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ ግዴላችሁም ተደራደሩ፤ ይቅር ለእግዚአብሔር ብላቸው ተነጋገሩ፤ ለዘላቂ ሰላም ብላችሁ እባካችሁን ዋጋ ክፈሉ ብለው ጉምቱ ጉምቱ አባቶች ቢጠይቁ / ልብ በሉልኝ መደራደሩ ይጠቅማል ከተባለ ነው/ እንዳልኩት ትህነግ አንድ ነገር ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ከሁሉም በፊት ውሸቱን፣ ቀላማጅነቱን ማቆም ይኖርበታል፡፡ ሐሰተኛ መረጃ መፈብረክና ማሰራጨቱን ማቆም አለበት፡፡ ቡድኑ ውሸታምነቱን እተዋለሁ ብሎ የሚምል የሚገዘት ሌላም ሌላም ማረጋገጫ የሚሰጥ ከሆነም መሐላው ግዝቱ ሌላውም ሌላውም ማረጋገጫው በትክክል መሬት ላይ የሚወርድ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ እንዲቻል የጽሞና ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡
ለእዚያውም የዓመታት፡፡ እናንተ በቅድሚያ መሣሪያ ማስቀመጥ እና ወንጀለኞችን አሳልፎ ነው መስጠት ያለበት ትሉኝ ይሆናል፡፡ እኔ ከእነዚህ ቅደመ ሁኔታዎች ባልተናነሰ መልኩ የትህነግ ትልቁ መሳሪያው ውሸት ነውና መዋሸቱን ማቆም አለበት እላለሁ፡፡ ቡድኑ ሊተመን የሚችለው ውሸት ሲያቆም፣ ውሸት ሲጦም ብቻ ነው፡፡ ይህን እንዲያደርግ የጥሞና ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡
ዘካርያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ጥር 2/2014