በመሠረታዊነት የኢትዮጵያን ቀውስ ሊፈቱ ከሚችሉ መንገዶች መካከል ተደጋግሞ የሚጠቀሰው ብሔራዊ መግባባት ነው፡፡ በአገራዊ አንኳር ጉዳዮች ላይ በመወያየት ብሔራዊ መግባባት ላይ ይደረስ የሚሉ ጥያቄዎች ዘመናትን ያስቆጠሩ ሲሆን፤ ከሰሞኑ ወደ ተግባር ለመግባት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ፀድቋል፡፡
አገራዊ የምክክር ዓላማ እና ግብ እንዲሁም የተሳታፊዎቹን ማንነት በሚመለከት የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር እና በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ጋር ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአገራችን ብሔራዊ መግባባት ጉዳይ ሲነሳ የሚግባባው ማን ከማን ጋር ነው? ማን ከማን ተጣላ ? የሚል ጥያቄ ይነሳል፤ ለመሆኑ የዚህ ምክክር ዓላማና ግብ ምንድነው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ቢቂላ፡- በአጠቃላይ በሌሎችም አገሮች እንደሚደረገው በተለይ በአገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ከሚባለው ውስጥ አገራዊ መግባባት መፍጠር ዋነኛው ነው:: አገራዊ መግባባት ደግሞ የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድኖች ወይም ልሒቃን በር ዘግተው ወረቀት ወይም ሰነድ ወይም ሕገመንግሥትን መሠረት በማድረግ የተግባቡበት ብቻ አይደለም::
ሰፋ ያለ ውይይት እና ምክክር በማድረግ የሚደረስበት ጉዳይ ነው:: ይህ ሲሆን አገራዊ መግባባቱ ዘላቂነት ይኖረዋል ማለት ነው:: ኢትዮጵያ እጅግ ብዙ ማለትም ከሦሥት ሺህ በላይ ዘመናትን አስቆጥራለች የምትባል አገር ብትሆንም እነዚህ ዘመናት የራሳቸው ውጣ ውረድ መልካም ጎን እና ትርክት ያላቸው ናቸው::
ከዚህ በፊት የተሠራ ስህተት ካለ እርሱን ማረም ከዚህ በፊት በነበርንባቸው ዘመኖች ያካበትነው መልካም ልምድን በሚገባ መውሰድ እና ኢትዮጵያ እንዴት አድርጋ ወደ ፊት ትቀጥል የሚለው ላይ ሁሉም ዜጋ በስፋት ተስማምቶበት በተስማማንባቸው ነገሮች ላይ መሠረት አድርገን አገርን ማስቀጠል አለብን:: አገራዊ መግባባት ሰው ስለተጣላ የሚደረግ አይደለም::
እንዲህ ዝቅ ተደርጎ የሚታይ ሳይሆን ፅንሰ ሃሳቡም እጅግ በጣም ከፍ ያለ ዴሞክራሲን ለመገንባት እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነ ከምንም በላይ ዘላቂ አገረ መንግሥትን እና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት በጣም አስፈላጊ የሆነ ሃሳብ ነው::
በአገራችን ውስጥ እስከ አሁን በጣም መሠረታዊ መግባባት ላይ ያልደረስንባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ:: ለግጭት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ፤ ላለመግባባት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ የአገረ መንግሥቱን ቀጣይነት ፈተና ውስጥ ሊጥሉ የሚችሉ እና እንዲሁ በየጊዜው ሰዎች እየተነሱ ለኩርፊያ ለግጭት የሚዳርጉ ነገሮች አገር ውስጥ አሉ:: እነዚህ ነገሮች ኢትዮጵያውያን ሰፊ ጊዜ ወስደው ቢወያዩባቸው መስማማት ላይ የሚደረሱባቸው ናቸው::
ስለዚህ ለውይይት በሚገባ በቂ ዕድል አልሰጠንም ማለት ነው:: ስለዚህ ሰዎች እንዲሁ ላልተገባ ግጭት እና ላለመግባባት እንዲሁም እስከ ጦርነት ለሚደርስ ችግር እንዳረጋለን ማለት ነው:: በአገራችን በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ጭምር ተቃርኖ፣ ልዩነት ፣ የአረዳድ እና የግንዛቤ እንዲሁም የአስተሳሰብም ጭምር ችግር አለ:: እነዛ ነገሮች ያለምንም ችግር ወደ ፊት መጥተው በጠረጴዛ ዙሪያ አጀንዳ ሆነው ለውይይት ቀርበው ኢትዮጵያውያን ሰፊ ጊዜ ወስደው ሊወያዩባቸው ይገባል::
አብዛኞቹ የአገራችን ጉዳይ ላይ በውይይት መግባባት ላይ ይደረሳል ተብሎ ስለሚታሰብ ዕድል መስጠት እና ኢትዮጵያውያን ያለምንም የውጪ ጣልቃ ገብነት ቁጭ ብለው እንዲወያዩ ዕድል መፍጠር አስፈላጊ ነው:: ጉዳዩ እከሌ የሚባል ፓርቲ እከሌ ከሚባል ፓርቲ ጋር ስለተጋጨ ወይም የእነእከሌ ብሔር ከእነእከሌ ብሔር ጋር ተቃርኖ ስላለው የእነከሌ ፍላጎት እና የነእከሌ ፍላጎት ስለማይገናኝ የሚል ነገር አይደለውም:: በአገራችን ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያውያን ቁጭ ብለው እንዲወያዩ የታሰበበት በጣም ሩቅ አሳቢ ፕሮጀክት ነው::
አዲስ ዘመን፡- በአገራዊ መግባባቱ ላይ የሚሳተፉ አካላትን በሚመለከት በብዙዎች ዘንድ የጠራ ግንዛቤ የለም:: እነማንናቸው? በሽብርተኝነት የተሳተፉ አካላትስ ጉዳይ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚታየው እንዴት ነው?
ዶክተር ቢቂላ፡- ሃሳቡ ላይ ኢትዮጵያውያን እጅግ በጣም በጥንቃቄ እንድንረዳው የሚያስፈልገን የአገራዊ ምክክር ፕሮግራሙ ያስፈልገናል ብለን ካመንበት አገራዊ ምክክር እናድርግ::
“ኢትዮጵያውያን ቁጭ ብለን በጠረጴዛ ዙሪያ በሰለጠነ መንገድ ውይይት አድርገን በታሪክ ውስጥም አሁንም ወደ ፊትም ሊያጋጥሙ የሚችሉ አገራዊ ጉዳዮችን አጀንዳ ቀርፀን እንወያይባቸው” የሚለው ጉዳይ ላይ ከተግባባን እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ እስከማውጣት ካደረሰን የሚሳተፈው ማን ነው? የሚለውን እኛ አሁን ላይ ቁጭ ብለን የምንናገረው ሳይሆን የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ወደ ፊት በሚገባ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ሲገባ የተሳታፊ ጉዳይን የሚመለከት አሠራር፣ ደንብ እና ሒደትን ይቀርጽልናል:: የሚሳተፉት የትኞቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው? እንዴት ይሳተፋሉ? በፓርቲ ደረጃ በልሒቃን ደረጃ የተሳትፎ ሁኔታ ምን ይመስላል? መሳተፍ የሚፈቀድላቸው ምንን የሚያሟሉ ናቸው? የሚለውን ዝርዝር ጉዳይ ሠርቶ ሕግ እና ሥርዓት ጠብቆ የሚያቀርበው በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ነው::
አሁን ግን እነዛ ነገሮች እየተለዩ እና እየተጣሩ ወደ ውይይቱ የሚመጡበት እና የሚሳተፉበት በአገራቸው ግንባታ የራሳቸውን ሚና እና አስተዋፅኦ የሚያበረክቱበት ሁኔታ በኮሚሽኑ የሚወሰን ይሆናል:: ነገር ግን በጣም ብዙ ሰዎች አንዳንዶቹ ሆነ ብለው የሚሠሩ በሚመስል ሁኔታ ሕዝብን ለማደናገር እና ይህን እጅግ መልካም ለሕዝብ የሚበጅ አጀንዳን እንዳይሳካ የሚሠሩ አካላት ስላሉ ዜጎቻችን ከዚህ መጠንቀቅ አለባቸው ብለን እናምናለን:: አሁን አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በደረሰበት ደረጃ ስለሚሳተፉ እና ስለማይሳተፉ አካላት ምንም የተለየ ነገር የለም::
ኢትዮጵያውያን በሠለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን ስለጉዳያችን እንነጋገር፤ ሊያግባቡን የማይችሉ እና ለወደ ፊቱ ዘላቂ ሰላም እና ለአገራችን ፈታኝ ሊሆኑ የሚችሉትን በውይይት መፍታት እንችላለን የሚል ነው::
ጉዳዩ የእከሌ ፓርቲ ይሳተፋል፤ የእከሌ ፓርቲ አይሳተፍም፤ ይህኛው የልሒቃን ቡድን ይሳተፋል፤ የእከሌ የልሒቃን ቡድን አይሳተፍም የሚል ነገር ለኮሚሽኑ የተተወ ነው:: በኮሚሽኑ ስልጣን እና ተግባር ውስጥ የተቀመጠ፤ በአግባቡ ኮሚሽኑ ወደ ፊት ዝርዝር አሠራሮችን እየቀረፀ እና ለሕዝብ እያቀረበ እያፀደቀ በውስጥ አሰራሩ እየተገበረ የሚሔድበት ጉዳይ እንጂ አሁን ላይ ቆመን የፓርቲ፣ የተወሰኑ አመራሮች ወይም የተወሰነ ቡድን ጉዳይ እንዳናደርገው አደራ ለማለት እፈልጋለሁ:: ይህንን ወደ ፊት ኮሚሽኑ እያሳወቀ እያጠራ የሚሄደው ጉዳይ ነው::
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪ ተብሎ በምክር ቤት የተቀመጠ ቡድን ተይዞ ለሕግ ከማቅረብ ውጪ በምክክር ሃሳብ ውስጥ መግባት የለበትም የሚሉ ሃሳቦች ተደጋግመው ይነሳሉ:: በሽብርተኝነት የተሳተፉ አካላትስ ጉዳይ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚታየው እንዴት መሆን አለበት ይላሉ?
ዶክተር ቢቂላ፡- አሁን ባለንበት ሁኔታ በአገራችን ላይ ባደረሱት የሽብር ተግባር ምክንያት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ብሎ የለያቸው ቡድኖች አሉ:: እነዚህ ቡድኖች በአሸባሪ ቡድን ዝርዝር ውስጥ ያሉ ናቸው:: ስለዚህ አሁን እጃችን ላይ ባለው መረጃ አሸባሪ ተብለው የተበየኑ ቢሆንም እነዚህ ይሳተፋሉ ወይም አይሳተፉም ማለትም ባልተገባ መንገድ አገራዊ የምክክር ሥራውን ማበላሸት ነው::
አሁን ላይ ቆሜ የአገራዊ የምክክር ፕሮጀክቱን ኮሚሽኑ የሚመራው እንዴት ነው? ሥራ ላይ የሚቆየው ሦሥት ዓመት ነው:: በእነዚህ ሦሥት ዓመታት ውስጥ በአሸባሪነት ተፈርጀው ያሉ ቡድኖችን በተመለከተ ኮሚሽኑ እንዴት ያያቸዋል? ምን ሃሳብ አለው? ስለተሳትፏቸው ምን ይላል? በሽብር ውስጥ ያሉ አካላት በአገራዊ ምክክሩ ማካተትን አስመልክቶ ኮሚሽኑ ምን ሃሳብ ያቀርባል? ምን ይወስናል? እንዴት ይኬድበታል? የሚሉ ጉዳዮችንም ኮሚሽኑ ያመጣል ብዬ አስባለሁ:: ምክንያቱም አገራዊ ምክክሩን በሚመለከት አጠቃላይ ግንዛቤ ያስፈልጋል::
ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ፤ ኢትዮጵያ እንደአገረ መንግስት እንዳትቀጥል የሚያደርጉ ነገሮች በምክክር እንዲፈቱ ሲባል ለዚህ የሚመቸውን መንገድ ኮሚሽኑ ያጠናል፤ ይለያል:: ኮሚሽኑ ለአሁንም ሆነ ለወደፊት ለኢትዮጵያ በሚበጅ ሁኔታ ሊሳተፉ የሚገባቸው አካላትን ወደ ተሳትፎ የማመጣቸው እንዴት አድርጌ ነው? የሚለውን ምክረሃሳብ እና የውሳኔ ሃሳብ እያጠና ያመጣል::
ስለዚህ የሽብር ቡድኖችን በሚመለከት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ያቀረበው ነገር የለም፤ አዋጁ ላይ ስለዚህ ጉዳይ የተነገረ ነገር የለም:: አሁን እኛ የምናውቀው ሁለት ቡድኖች አሸባሪ ተብለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለዩ መሆናቸውን ብቻ ነው:: ኮሚሽኑ እነዚህን በተመለከተ የራሱ አሠራር፣ ታክቲክ እና ምክረ ሃሳብ አምጥቶ በውስጡ ወስኖ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ችግሩ ሊፈታ የሚችልበትን ሁኔታ ራሱ ሊቀይስ ይችላል የሚል እምነት አለኝ:: እስከ አሁን ባለው ብቻ እዚህ ላይ ቆመን ምንም ነገር ማለት አንችልም::
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው ልዩነት እና አስተሳሰብ የተራራቀ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ለማቀራረብ ከባድ አይሆንም? ከዚህ ጋር ተያይዞ ለማቀራረብስ በመሃከል ሊሆኑ የሚችሉት የሚለዩት እንዴት ነው?
ዶክተር ቢቂላ፡- በአጠቃላይ አንድ እውነታ አለ:: እውነታ ብቻ ሳይሆን ባለፉት በርካታ ዓመታትም የተገለፀ እና በተለይ ባለፉት ሦሥት ዓመታት ተኩል የእዚህ የለውጥ ሂደቱ ከመጣ በኋላም በአግባቡ ለሕዝቡም ቃል የተገባ ነገር ቢኖር አገራችንን እኛ ኢትዮጵያውያን ቁጭ ብለን በጠረጴዛ ዙሪያ በመመካከር ሊያግባቡን በሚችሉ በርካታ ጉዳዮች ላይ በውይይት ወደ መግባባት እንዲመጣ ማድረግ እንችላለን የሚል እምነት አለን::
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያውያን ችግራቸውን ለመፍታት የሚያስችል አቅም ፣ ብቃት ፣ ስነ ልቦና የቆየ ባህል እሴት አላቸው:: ይህ በሁሉም ብሔሮች ውስጥ በሁሉም ሃይማኖት ውስጥ ያለ መልካም ሀብት ነው::
ኢትዮጵያውያን ከተወያዩ ችግራቸውን መፍታት ይችላሉ:: ከውጪ ጣልቃ ገብነት በፀዳ መንገድ በራችንን ዘግተን በጠረጴዛ ዙሪያ አጀንዳዎችን እየቀረፅን ውይይት ብናደርግ ችግሮቻችንን መፍታት እንችላለን:: ሌላው ተቃርኖ ያለባቸው መስማማት ሳይኖርባቸው ለዘመናት የቆዩ ባንዲራን እና ሌሎችም የአገሪቱን አጀንዳዎችን ጨምሮ እየተነጠሩ እየተለዩ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ የሚመጡበት አሠራር መዘርጋት አለበት::
አገራዊ አጀንዳዎቹ ምንም ቢከብዱ ምን ውስብስብ ቢሆኑ በውይይት አብዛኛዎቹ ላይ መግባባት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ:: በዛ ምክንያት ኢትዮጵያውያን የሰማይ እና የምድር ያህል የተራራቀ አጀንዳ የላቸውም ብዬ አስባለሁ:: ቢያንስ ቢያንስ የሁላችንም እናት በሆነችው በኢትዮጵያ አገራችን ላይ መስማማት እንችላለን ብዬ አስባለሁ::
ስለዚህ ይህች የሁላችንም እናት የሆነችውን ኢትዮጵያን እንዴት እናስቀጥላት የሚለው ላይ ውይይቱ ክፍት መሆን አለበት:: ስለዚህ በብሔርም ሆነ በሃይማኖት እንዲሁም በርዕዮተ ዓለም ብንለያይም ስለኢትዮጵያ መስማማት አያቅተንም::
ይህችን ኢትዮጵያን እንዴት እናስቀጥል በሚለው ላይ አጀንዳ እየቀረፅን በልበ ሙሉነት፣ በማስተዋል፣ በምክንያታዊነት ኢትዮጵያን በማስቀደም ቁጭ ብለን በሰከነ አዕምሮ እና ልቦና ከተወያየን ምንም ሃሳባችን ቢራራቅም በአገራዊ ዋና ዋና ጉዳዮች እና ለእናታችን ለኢትዮጵያ በሚያስፈልጉ አጀንዳዎች ላይ መስማማት እንችላለን የሚል እምነት አለኝ::
አዲስ ዘመን፡- ከብሔራዊ መግባባት አንጻር ከዚህ ቀደም በሌሎች አገራት ተሞክሮ ውጤታማ የሆነ አሠራር አለ? በተለይ በአፍሪካ ካለ ይጠቅሱልኛል?
ዶክተር ቢቂላ፡- አዎ! በጣም ብዙ አገሮች ሞክረዋል:: ሲጀምሩ መልካም መስሎ በየመሐሉ ውጣ ውረድ የገጠማቸው አሉ:: ማኔጅ በሚደረግበት ጊዜ በአግባቡ አሳታፊ ከመሆን አንፃር፤ ልሒቃንን እና ሕዝብን በአግባቡ ባለማሳተፍ ምክንያት በመወለካከፋቸው የሚጠበቅባቸውን ፍሬ ሳያፈሩ መሐል ላይ ደርሰው የተጨናገፈባቸው አሉ:: በስኬት አጠናቀው የሰከነ አገር ለመመስረት የቻሉ አሉ:: ለምሳሌ የሩዋንዳን መጥቀስ ይቻላል::
የደቡብ አፍሪካ እና ሌሎችም የአፍሪካ አገራት ቁጭ ብለው ጊዜ በመውሰድ ገለልተኛ ተቋም አበጅተው ልሂቃንን እና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን አሳትፈው ‹‹እንደአገር እንድንቀጥል የማያደርገን እና ውስጣዊ ሰላማችንን እያናጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ የጦርነት አዙሪት ውስጥ እንድንሆን ያደረገን ችግር ምንድን ነው? ስለዚህ ይህንን ችግር እንዴት እንፍታ?›› ብለው ተወያይተው የተወያዩበትን እያንዳንዷን የተስማሙበትን ነገር ተፈራርመው ወደ ስምምነት ቀይረው፤ ከወረቀት ባለፈ በተግባር ዓላማቸውን የተጎናፀፉ አገራት አሉ:: ከእነዚህ መካከል ሩዋንዳን መጥቀስ ይቻላል::
ሌሎችም አሉ:: እንዲህ ያለ አገራዊ ምክክር መድኃኒት ነው:: እዚሁ ጎረቤት አገር አብረን የምንኖረው አፍሪካ አገራት ውስጥ የተተገበረ የአገራት ዘላቂ ሰላም እና ብልፅግናን አስተዋፅዖ ያደረገ የምክክር ቆንጆ ልምድ አለ::
ይህንን ልምድ ደግሞ ኮሚሽኑ በሚገባ ያየዋል፤ ይወስደዋል:: ይህ የተለመደ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮችም የሚፈፀም ነው:: በኢትዮጵያም በተደጋጋሚ ሲሞከር ወደ ኋላ ሲመለስ የነበረ ነገር ነው:: በተለይ ደግሞ ኢህአዴግ በነበረው የተሳሳተ ግንዛቤ የተነሳ ማን ከማን ጋር ተጣልቶ ነው? ምክክር የምናደርገው እና የምናስታርቀው በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ በመኖሩ ምክንያት እንጂ፤ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ጭምር በተለያዩ የአገራችን ልሒቃን እና ለአገር በሚያስቡ ዜጎች ሲነሳ የነበረ ነው:: ባለፉት ሦሥት ዓመታት እና ከዚያም በፊት ሙከራዎች ነበሩ::
ነገር ግን ሙከራዎቹ ፍሬ ሳያፈሩ ቀርተው አሁን በአዲስ መልክ ተጀምሯል:: እንጂ ከጎረቤት ሀገሮች ከሩዋንዳ እና ከደቡብ አፍሪካ እና ከሌሎችም ከሩቅ አገራት ወስደን ይህንን ነገር በሚገባ ከመራን ውጤታማ ልናደርገው እንችላለን የሚል እምነት አለን::
ሰው ከተወያየ እንደሚስማማ፤ ከተስማማ ደግሞ ሰላምን እንደሚጎናፀፍ የሚያሳዩ በርካታ ዓለምአቀፍ ተሞክሮዎች አሉ::
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የተራራቀ እና ውስብስብ ፍላጎት ቢኖርም ይሳካል የሚል እምነት አለዎት ማለት ነው?
ዶክተር ቢቂላ፡- እንደውም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ውስብስብ ነው ብዬ አላስብም:: ምክንያቱም ከላይ እንደገለፅኩት ኢትዮጵያውያን በዘመናት መካከል የተጎናፀፍነው መልካም እሴት አለ:: የፖለቲካ እና የአገረ መንግሥት ልዩነቶች ምንም እንኳ ውስብስብነት ቢኖራቸውም ኢትዮጵያውያን ያንን ውስብስብነት ሊፈታ የሚችል የቆየ ባህል፣ ልምድ እና እሴት አለን:: ለምሳሌ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በየቤቱ በየጥላው ሥር ቁጭ ብሎ የመወያየት ድምፁን ዝቅ አድርጎ ምስጢር የተባሉትን ነገሮች በሙሉ ተወያይቶ የመፍታት፤ የተፈታውን ለሌላው የማሳወቅ በጣም ቆንጆ ቆንጆ ልምዶች አሉ::
ስለዚህ ይህ አገራዊ ምክክሩ በአገራዊ እሴት የሚመራ በመሆኑ ፈጣሪ አድሎን የመወያየት ችግሮችን የመፍታት የቆየ ልምድ ያለን በመሆኑ ምንም ችግር እና ያልተግባባንባቸው ነገሮች ቢኖሩም ያለውን ባህላችን እና እሴታችን ችግሮቻችንን ለመፍታት እንደዋነኛ ስንቅ ሆኖ ያገለግላል የሚል እምነት አለኝ:: አዲስ ዘመን፡- የምክክር መድረኩ የመጨረሻ ግብ ምንድን ነው? በዚህ አገራዊ መግባባት አገራችን ምን ታተርፋለች ተብሎ ይታሰባል? ዶክተር ቢቂላ፡- የአገራዊ ምክክር ውጤቱ ለኢትዮጵያ አገራዊ ብልፅግና እንደዋነኛ ምሰሶ ሊያገለግል የሚችል አገራዊ መግባባት መፍጠር ነው::
አገራዊ መግባባት መፍጠር ለሁሉም ነገር ዋነኛ ምሰሶ ነው:: እኛ እንደ አንድ አገር ሕዝብ በአገራችን ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከተግባባን ኢትዮጵያ አገራችንን በጋራ ለማበልፀግ የሚሆን ስሜት እና የአብሮነት ቁርጠኝነት ስለሚኖረን አገራዊ ምክክሩ ውጤቱ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አገራዊ መግባባትን ይፈጥራል:: ይህ ከተፈጠረ በየጊዜው ብቅ ጥልቅ እያሉ ሰላም የሚነሱ ግጭቶች ጦርነቶች እና ተቃርኖዎች ያልተገባ የሰላም ማጣት ይቀርና አገራችንን ማበልፀግ ላይ ማልማት እና ችግሮቿ መፍታት ላይ ከድህነት መውጣት ላይ ትኩረት አድርገን አገራችንን እንገነባለን ማለት ነው:: ስለዚህ ፈጣሪ ፈቅዶልን ከተሳካልን ቀጣይነት ያለው አገረ መንግሥት ለመገንባት የሚያስችል አገራዊ መግባባት ላይ እንደርሳለን::
አገራዊ መግባባት ላይ ከደረስን ደግሞ ሰላማችንን ያመጣል፤ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚ ስብራቶቻችንን በሙሉ ይጠገናል:: ሁለንተናዊ ብልፅግናዋ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራ አገራዊ መግባባትን እንድንፈጥር እንችላለን ማለት ነው::
አዲስ ዘመን፡- በአገራዊ መግባባቱ ላይ ልዩነትን የሚያሰፉና ለመቀራረብ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማደናቀፍ የሚሰሩ ኃይሎችን ለመከላከል ምን ይሠራ?
ዶክተር ቢቂላ፡- አዎ! አገራዊ መግባባቱ በቅን ልቦና እና በበጎ ፈቃድ የተጀመረ የሁሉም ልብ ውስጥ ሲመላለስ የነበረ ነው:: ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሲፈልገው የነበረ እና በተለያየ አጋጣሚ ሳንጀምረው የዘገየብን ነገር ግን በጣም ወሳኝ በሆነ ወቅት የተጀመረ በጣም አስፈላጊ ሥራ ነው:: ይህንን እጅግ በጣም ብዙ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለ ኢትዮጵያዊ በበጎ መልኩ ይመለከተዋል:: ለተግባራዊነቱም አስፈላጊውን ሚና ይጫወታል::
ይሁን እንጂ አገራዊ መግባባቱ እንዲጨናገፍ የሚሠሩ የውጪም ሆነ የውስጥ ኃይላት ደግሞ ከእነዚህ ኃይላት መጠንቀቅ ያስፈልጋል:: እኛ ኢትዮጵያውያን በጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጣችን እና መወያየታችን ሰላም የሚነሳቸው አካላት በትንሹ እና በትልቅ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚሞክሩ በመሆኑ በምንም ዓይነት መንገድ እንዳይደናቀፍ እኛ ቅን ኢትዮጵያውያን እንጠንቀቅ::
ይህ ጉዳይ በተለያየ መንገድ በየሚዲያው አጀንዳ በመቅረፅ ጣልቃ በመግባት ሊሠሩ የሚችሉ ስለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጭ ብለው እንዳይወያዩ የሚያደርጉ ማናቸውም አካላት የኢትዮጵያ ጠላቶች ናቸው:: ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ ጠንካራ አገር እንዳትሆን ችግሮቿን እንዳትፈታ የሚፈልጉ ሊኖሩ ስለሚችሉ በመጀመሪያ፣ በመካከል ወይም መጨረሻ ላይ ሊያደናቅፉ ከሚችሉ ኃይሎች ኢትዮጵያውያን እንጠንቀቅ::
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እጅግ አመሰግናለሁ::
ዶክተር ቢቂላ፡– እኔም አመሰግናለሁ::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥር 2/2014