እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችሁ? ትምህርት እንዴት ይዟችኋል? መቼም ጥሩ ነው እንደምትሉኝ አልጠራጠርም። ምክንያቱም ጎበዝ ያልሆነ ተማሪ ምን እንደሚገጥመው በደንብ ታውቃላችሁ። መልካም ዛሬ ስለ ገና በዓል /ስለጌታችን አምላካችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት/ እንነግራችኋለን። ስለ በዓሉ ስንነግራችሁ በሁለት መልኩ ነው። የመጀመሪያው ኢትዮጵያውያን ከእምነታቸውን አንጻር እንዴት ያከብሩታል የሚለው ሲሆን፤. ሁለተኛው በባህል ዘንድ እንዴት ይከበራል የሚለው ነው። ይህንንም ቢሆን በከተማና በገጠር ለያይተን እንነግራችኋለን። በደንብ ተከታተሉን።
ከላይ እንዳልናችሁ በመጀመሪያ የምንነግራችሁ ከእምነት አንጻር ይሆናል። ለምሳሌ የክርስትና እምነት ተከታዮች የገና በዓልን የልደት በዓል በማለት ያከብሩታል። የመከበሩ መንስኤው ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ በከብቶች በረት መወለድ ነው። አውግስጦስ ቄሳር የተባለ ንጉሥ ሰው ሁሉ ይቆጠር ዘንድ በአዘዘበት ጊዜ ሰው ሁሉ ሊቆጠር ወደ የትውልድ ከተማው ሄደ። ዮሴፍና የኢየሱስ እናት ማርያም ሊቆጠሩ ከናዝሬት ወደ ቤተልሔም ጉዟቸውን አደረጉ። በቤተልሔም ሳሉም ማርያም የምትወልድበት ቀን ደረሰ። በዚያ ሥፍራም ብዙ እንግዳ ስለነበር የሚያርፉበት ቦታ አጡ። ስለዚህም ማደሪያም ስላልነበራቸው በከብቶች ማደሪያ በበረት ውስጥ ልጅዋን ወለደችው።
በጨርቅ ጠቅልላ እዛው በበረት ውስጥ አስተኛችው፤ በዚያ አገር ይኖሩ የነበሩ እረኞችም ሌሊት ከብቶቻቸውን ይጠብቁ ነበርና ሕፃን በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ አገኙት። በአዩትም ጊዜ በጣም ተደነቁ። በመደሰታቸውም ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር
ይሁን በምድርም ለሰው ልጆች በጎፈቃድ ሆነ›› ብለው አመሰገኑ። አያችሁ ልጆች እነዚህ እረኞች በአዩት ነገር ደስተኛ ነበሩ፤ ደስታ ሲሆን ደግሞ መጨፈር፣ መጫወትና መቦረቅ አስፈላጊ ነው። ስለዚህም እነርሱም በመዝሙር ደስታቸውን ገልጸዋል። ይህ የሚያስተምረን ደግሞ ልደቱን ስናከብር ደስተኛ መሆን እንዳለብን ነው።
ወደ ሁለተኛ ጉዳያችን ስንገባ ባህላችንን እናነሳለን። ልጆች የገና በዓል የወንዶች ገና እንደሚባል ታውቃላችሁ? ምክንያቱ ምን ይመስላችኋል? ወንዶች በቡድን ሆነው በገና ጨዋታ ስለሚያከብሩት ነው ካላችሁ ልክ ናችሁ። በባህላችን ዘንድ የገና በዓል የሚከበረው በገና ጨዋታ ነው። በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በስፋት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይከበራል። ጨዋታው ልዩ ነው። በቡድን ተሆኖ ሩር እየመቱ ጨዋታውን ያደምቁታል። አሸናፊና ተሸናፊ እየተዛዘለ ይቀጣል። ጨዋታው ፍቅር የሞላበት ስለሆነ መቀያየም የለበትም። በየዓመቱ የሚናፈቅም ነው።
ልጆች በገና ጨዋታ ልጆች ብቻ አይደሉም የሚሳተፉት። አዋቂዎችም አድማቂና ታዛቢ ናቸው።
በተለይ ግን በቡድኑ ውስጥ ገብተው የሚጫወቱት ወንድ ልጆች የጨዋታው ተዋናይ ሲሆኑ፤ በዓሉን በዓል ያሰኙታል። ብዙ ልጆች የዕረፍት ጊዜያቸውን የሚያጣጥሙትም በዚህ ነው። ማንም ክልከላ የማይጥልበትም በዓል ነው። እንዲያውም ከእነዘፈኑ ‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› ይባላል። ስለዚህም ይህ ጊዜ የልጆች የደስታና የመቦረቂያ በዓል ነው።
የገና በዓል ብዙ የዕረፍት ምሽቶችን የሚሰጥም ነው። ለምን ቢባል በባህላችን ዘንድ የገና ጀንበር ይባላል። ይህ ማለት ቀኑ አጭር ሲሆን፤ ሌሊቱ ደግሞ ረጅም ነው። ስለዚህም የእንቅልፍ ጊዜው ከሥራና ትምህርት ጊዜው ይረዝማል። በዚህም ረጅም የዕረፍት ጊዜ ስለሚኖራቸው ልጆች ደስተኛ ይሆኑበታል።
የገና በዓል በከተማም ቢሆን ልዩ ድባብ አለው። ያው ባህሉን በረዝ ያደረጉት የምዕራባውያን አከባበሮች ቢኖሩትም። ነገር ግን እንደ በዓልነቱ ብዙዎች ስጦታ የሚሰጣጡበት ነው። ምርጥ ቦታዎች እና የቤተሰብ መዝናኛዎች የሚፈጠሩበትም ነው። በዚህም የሽርሽር ቦታቸውን መርጠው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይደሰታሉ። ቤቱ ውብና አስደሳች እንዲሆንም የማይደረጉ ነገሮች የሉም። ይህ ሲሆን ደግሞ የማይረሳ የዕረፍት ጊዜ እንድታሳልፉ ትሆናላችሁ።
በበዓሉ ወቅት ብሩህ እና ማራኪነት ባለው የገበያ ማእከልም በመዘዋወር የምንፈልገውን እንሸምታለን። ስለዚህ ልጆች ገና ለልጆችም ሆነ ለአዋቂዎች በጣም የሚያነቃቃ በዓል ነው። ምክንያቱም ልጆች ተዓምርን እየጠበቁ የሚቆዩበት፣ ጠዋት ላይ ስጦታቸውን የሚያገኙበት ገጠሪቱ ክፍል ላይ ያሉ ከሆኑ ደግሞ ተወዳጁን ጨዋታቸውን ከመረጧቸው ጓደኞቻቸው ጋር የሚጨዋቱበት ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥር 1 / 2014