ትኩረት ለሙያ ትምህርቶች

የመስከረም ወር የትምህርት መጀመሪያ ወር ነውና ትምህርታዊ አጀንዳዎች ይበዛሉ፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የተለመደው የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ እንዲሁም የቅድመ ምረቃ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ብቻ አይደለም አጀንዳ የሆነው፡፡ የድህረ ምረቃ ትምህርትም የመስከረም ወር አጀንዳ መሆን ጀምሯል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው የትምህርት መመሪያ መሰረት የድህረ ምረቃ ትምህርት በብሔራዊ ፈተና መልክ መሰጠት መጀመሩ ነው። ከዚህ በፊት ዩኒቨርሲቲዎች በራሳቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየፈተኑ ያስተምሩ የነበረበት አሰራር ቀርቶ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ሆኗል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰሞኑን የዚህን ፈተና የጊዜ ሰሌዳ የያዘ ሰነድ ሲያሰራጭ ተመልክተናል፡፡ በአጠቃላይ መስከረም ወር የትምህርት አጀንዳ ነው።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አንድ ልብ ያልተባለ ነገር አለ፡፡ ይሄውም የሙያ ትምህርት ነው፡፡ የሙያ ስል የተለመዱትን የሕክምና፣ የምሕንድስና…. አይነት ትልቅ ትኩረት የተሰጣቸውን ማለቴ አይደለም። የእጅ ሙያ ትምህርት የሆኑት ናቸው ትኩረት ያልተሰጣቸው፡፡ በተለምዶ ቴክኒክና ሙያ እየተባሉ የሚጠሩት ማለት ነው፡፡ ቴክኒክና ሙያ ውስጥ አሉ የሚባሉት ራሱ አገር በቀል የሆኑ የእጅ ሙያ ትምህርቶች ትኩረት የተሰጡበት አይመስልም። ምክንያቱም የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ክፍሎች ውስጥ የሸክላ ሥራ፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ ሥራ፣ የባሕላዊ መሳሪያዎች አሰራር የመሳሰሉት ሲወራባቸው አይሰማም፡፡

የአንዲት አገር የሥልጣኔ እና የዕድገት መገለጫ ኢንዱስትሪ ሆኗል፡፡ የትልልቅ ኢንዱስትሪዎች መነሻ ደግሞ የጎጆ ኢንዱስትሪዎች ናቸው፡፡ የጎጆ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ እነዚህ አገር በቀል የሆኑ የማሕበረሰቡ የእጅ ሥራዎች ናቸው፡፡ እነዚህ አገር በቀል የጥበብ ሥራዎች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደረጃ ትኩረት ቢሰጣቸው ወደ ዘመናዊነት ያድጋሉ። ፈጠራ ፈጠራን እየወለደ ዘመናዊ ኢንዱስትሪ ይሆናሉ።

ሰዎች ለሥራ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ሲሄዱ፤ ከሄዱበት አካባቢ ያለ ባሕላዊ የመገልገያ ዕቃ ይገዛሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከዘመናዊ የፋብሪካ ዕቃዎች በተሻለ የሚወደዱ እና የሚፈለጉ ባሕላዊ ዕቃዎች አሉ። እነዚህ ዕቃዎች የተሰሩት ከዋናው ጥሬ ዕቃ በባሕላዊ መንገድ ነው፡፡ እነዚያን ዕቃዎች የሰሩ ሰዎች ዘመናዊ ትምህርት የተማሩ አይደሉም። በልማዳዊ መንገድ ነው የሰሩት፡፡ የሰሩት ሰዎችም እንደ ባለሙያ ሳይሆን የሚታዩት እንደ ኋላቀር ነው፡፡ ከእነዚያ ባለሙያዎች ይልቅ ለአገር ምንም ጠብ ያላደረገ ዲግሪ የደራረበ ሰው ይከበራል፡፡

እውነታው ግን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ‹‹የተማረ›› ከሚባለው ዜጋ ይልቅ ዘመናዊ ትምህርት ያልተማረው ለኢንዱስትሪ ግብዓቶች ይቀርባል። ለምሳሌ፤ የግብርና መገልገያ ዕቃዎች አሁንም በባሕላዊ መንገድ የሚዘጋጁ ናቸው፡፡ የተማረ የሚባለው ግን ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን መገጣጠም አልቻለም። እነዚያው ጥቂቶችም ቢሆን ከውጭ የሚመጡ ናቸው፤ ለዚያውም በብዛት የሉም፡፡

ለመስክ ሥራ በምንሄድባቸው የገጠር አካባቢዎች ብዙ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ይገኛሉ። የተማረ የሚባለው የሕብረተሰብ ክፍል እነዚህን ዕቃዎች ይገዛል፤ እሱ ግን የመገልገያ ዕቃዎችን በዘመናዊ መንገድ ማምረት የሚያስችል ክሕሎት የለውም፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃ ብቻ ሳይሆን የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ

 

ከውጭ የሚመጡ ናቸው፡፡ መዘመን እና መሰልጠን የተባለው እነዚህን የፈረንጅ ምርቶች መግዛት ነው። በአንፃሩ በአገር በቀል ጥበብ የተሰሩት ዕቃዎች የኋላቀርነት መገለጫ ተደርገው ይታያሉ፡፡

እርግጥ ነው አንዳንድ ባሕላዊ ዕቃዎች በጥንካሬም ሆነ በአገልግሎት ፍጥነት ከፈረንጅ ምርቶች ያነሱ ናቸው፡፡ ዳሩ ግን በሥርዓተ ትምህርታችን ውስጥ ተካተው ትኩረት ቢሰጣቸው የመዘመን ዕድል ይኖራቸዋል፡፡ የእጅ ሙያ ትኩረት ቢሰጠው በራሱ እየዳበረ ይሄድ ነበር፡፡ ባሕላዊ ዕቃዎችን የሚሰሩት ሰዎች ራሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻሉት ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና ትኩረት የሚሰጠው ቢሆን ይዳብር ነበር ማለት ነው፡፡

ቀደም ሲል በነበሩት ጊዜያት ‹‹የእጅ ሥራ›› የሚባል የትምህርት አይነት ነበር፡፡ ቢሆንም ግን በቂ ትኩረት የተሰጠው አልነበረም፤ የንድፈ ሀሳብ ትምህርት የለውም፡፡ ተማሪዎች የሚችሉትን የእጅ ሥራ ይዘው እንዲመጡ ይደረጋል፡፡ አንዳንዱ የግብርና መሳሪያዎችን ይሰራል፣ አንዳንዱ የጦር መሳሪያ ይሰራል፣ አንዳንዱ የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎችን ይሰራል፡፡ የመጨረሻ ግቡ ግን የቁጥር ነጥብ ለማግኘት ብቻ ነው፡፡ ተማሪው በዚያ ሙያ የመቀጠል ፍላጎት የለውም፤ ምክንያቱም ያ ሙያ እንደ ትልቅ ሙያ የሚቆጠር አልነበረም፡፡ ይህ ችግር እነሆ አሁን ድረስ ስለዘለቀ አሁንም የእጅ ሙያ በትምህርት ውስጥ ትኩረት ሲሰጠው አይታይም፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት ይመስለኛል የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በቡራዩ አካባቢ የእጅ ሙያ ትምህርት ቤት አስገንብቶ ሲያስመርቅ አጀንዳ ሆኖ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በወቅቱ ብዙ ሰዎች አድንቀዋል፡፡ ምክንያቱም የዘመናዊ ኢንዱስትሪ መነሻው የአካባቢ የእጅ ሙያዎችን ማዳበር ነው፡፡ ይህ የኦሮሚያ ክልል ጅማሮ ግን በአገር አቀፍ ደረጃ አጀንዳ ሲሆን አላየንም። አሁንም ትምህርት ሲባል ያው የተለመደው የአውሮፓ ሳይንቲስቶችን ስም እና ንድፈ ሀሳብ መሸምደድ ነው ትኩረት የሚሰጠው። ጎበዝ ተማሪ የሚባለውም ያንን ሸምድዶ ከፍተኛ ቁጥር ሲያስመዘግብ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ከሚታዩ የጎበዝ ልጆች የፈጠራ ሥራዎች በስተቀር ተግባር ተኮር ውጤት አልታየም፡፡

ይባስ ብሎ እንዲያውም የእጅ ሙያ ያላቸው ልጆች እንደ ሰነፍ የሚታዩበት አጋጣሚም አለ፡፡ የተለመደው ጎበዝ ተማሪ ማለት ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ፣ ባዮሎጂ፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ…. ሸምድዶ ከፍተኛ ቁጥር የሚያመጣ ነው፡፡ የፊዚክስ ውጤት የሆነውን አንድ ቀላል ማሽን ከመሥራት ይልቅ የፊዚክስ ንድፈ ሀሳብ ሸምድዶ ከፍተኛ ቁጥር ማምጣት የተሻለ ጎበዝ ተማሪ ያሰኛል፡፡ ከዚህ ልማድ መላቀቅ አለብን፡፡

ይህ ይሆን ዘንድ ለእጅ ሙያ ጥበቦች ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ እንደ ትምህርት ሊታዩ ይገባል፤ እንደ ሳይንሳዊ ፈጠራ ሊታዩ ይገባል፡፡ ቀላል ማሽኖች እንደ ኢንዱስትሪ መነሻ መታየት አለባቸው። በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ መካተት አለባቸው፡፡ በልማዳዊ መንገድ የሚሰሩ የአካባቢ ሰዎች ልክ እንደ ፊዚክስ መምህር መማሪያ ክፍል ውስጥ ገብተው ልምዳቸው ማካፈል አለባቸው፡፡ የመማሪያ መጻሕፍት ላይ ምሳሌ የሚሰጠው በአካባቢ ያሉ ነገሮችን ነው፡፡ ስለዚህ እነዚያን ነገሮች በተግባር የሚሰሩ ሰዎች ልምድ ቢያካፍሉ፣ ትምህርት ቢሰጡ ምን ችግር አለው?

የእጅ ሙያ ያላቸው ተማሪዎች ልክ ከፍተኛ ቁጥር አምጥቶ እንደሚሸለመው ተማሪ መሸለምና መበረታታት አለባቸው፡፡ ያኔ ሙያውም ክብር ያገኛል፤ ሥራውን የሚለማመዱ ተማሪዎችም ይፈጠራሉ፡፡ ፊዚክስ ከ100/100 ካመጣ ተማሪ ይልቅ አንድ ቀላል ማሽን የሰራ ተማሪ ለፊዚክስ ትምህርት ይቀርባል ማለት ነው፡፡ የእጅ ሙያ ውጤቶች የሳይንስ መነሻ ናቸውና ትኩረት ይሰጣቸው!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You