ኢትዮጵያዊው የፋሽን ሳምንት

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ እና በፋሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ባሉ ተሳታፊዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቁ የፋሽን ሳምንት ትርኢቶችና ፕሮግራሞች ይካሄዳሉ፡፡ የኒውዮርክ ፋሽን ሳምንት፣ የበርሊን እንዲሁም ለንደን የፋሽን ሳምንቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁት የፋሽን መድረኮች ይጠቀሳሉ። በሀገራችንም ዲዛይነሮች የራሳቸውን ስራዎች ለማስተዋወቅ፣ የፋሽን ዲዛይን ማሰልጠኛ ተቋማትም ተማሪዎቻቸውን ሲያስመርቁ የፋሽን ዲዛይን ትርኢቶችን ሲያዘጋጁ ይስተዋላል፡፡

ማህሌት ተክለማርያም ትባላለች፡፡ ከሀገር ውጭ ለረጅም ጊዜ ቆይታለች፡፡ የሀብ ኦፍ አፍሪካ ፋሽን ሳምንት (HUB Of Africa Fashion week) መስራች እና አዘጋጅ ናት፡፡ እሷ እንዳለችው፤ የፋሽን ሳምንቱ የተመሰረተው ከ15 ዓመት በፊት እ.አ.አ በ2010 ነው፤ የተመሰረተበት ዓላማም ለፋሽን ዲዛይነሮች መድረክ መስጠት እና ኢንዱስትሪውን ማሳደግ እና ይበልጥ ማስተዋወቅ ነው፡፡

የፋሽን ሳምንቱን ለመጀመር ስታስብ ከሀሳቧ ተጋሪ ኬንያዊት ጋር መምከሯን ማህሌት ጠቅሳ፣ ሀሳቡም በሌላው ዓለም የሚታወቁት የፋሽን ሳምንት ትርኢቶች ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ አፍሪካ ውስጥ እንዲካሄዱ መፈለግ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

የመጀመሪያው የሀብ ኦፍ አፍሪካ ፋሽን ሳምንት 12 ዲዛይነሮችን ማሳተፉን ትገልጻለች፡፡ እነዚህም ስድስት ከኢትዮጵያ ሌሎች ስድስቱ ደግሞ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ እንደነበሩም አስታውሳለች፡፡

ለፋሽን ሳምንቱ ‹‹ሀብ ኦፍ አፍሪካ›› የሚል ስያሜ የተሰጠውም የአፍሪካ መዲና የሚል ስያሜ ባላት አዲስ አበባ አህጉረ አፍሪካን በሚመለከቱ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች የሚደረጉና ውሳኔዎች የሚተላለፉ በመሆናቸው ነው ብላለች፡፡

አብዛኛውን ጊዜዋን በኒውዮርክ እና ቨርጂኒያ ያሳለፈችው ማህሌት፣ በማርኬቲንግ እና ቢዝነስ ላይ ትምህርት መከታተሏንም ገልጻለች፡፡ ‹‹ስንጀምረው የነበረው ዝግጅት ለሁለትና ሶስት ቀና የሚካሄድ ነበር፤ ከዚያም እያደገ ሄደ፡፡ አሁን የፋሽን ትምህርት ቤቶችም ስለበዙ ያለው እንቅስቃሴ በፊት ከነበረው አድጓል ማለት እችላለሁ፡፡›› በማለት ትገልጻለች፡፡

‹‹የፋሽን ኢንዱስትሪው በአፍሪካም ጭምር አድጓል›› የምትለው ማህሌት፣ በናይጄሪያ የሚዘጋጀውን ሌጎስ ፋሽን ሳምንትን፣ የደቡብ አፍሪካው ፋሽን ትርኢትን /ከ20 ዓመት በላይ ያስቆጠረ / እና በሴኔጋል የሚካሄደው ዳካር ፋሽን ሳምንትን ለእዚህ እንደ አብነት ይጠቀሳሉ። ‹‹እኛ በይበልጥ ዘርፉ ላይ ለተሰማሩ ዲዛይነሮች እድል መፍጠር ላይ እንሰራለን›› ብላለች፡፡

የፋሽን ኢንዱስትሪ ከፍተኛ አቅም እና ፈጠራ የሚገኙበት መሆኑን ጠቅሳ፣ ‹‹ አቅም እና ችሎታ እያላቸው ገበያው ላይ መቆየት ባለመቻላቸው ከገበያው የሚወጡ እንዳሉም ጠቅሳ፣ ስለዚህ በመንግስት ደረጃም ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባም አስገንዝባለች። ይህንን ዘርፍ ለመደገፍ የተቋቋመ የፋሽን ዲዛይን ማህበር ከባሕልና ቱሪዝም እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር እየሰራ እንደሚገኝም ገልፃለች።

በሀብ ኦፍ አፍሪካ የፋሽን ሳምንት ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚመጡ ዲዛይነሮች ተሳታፊ ይሆናሉ። ‹‹ያለፈው ሀብ ኦፍ አፍሪካ ላይ ከ25 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊ ዲዛይነሮች እና ከናይጄሪያ፣ ጋናም እንዲሁም ሌሎች ዲዛይነሮች ይሳተፋሉ›› ብላለች፡፡

እሷ እንዳለችው፤ የፋሽን ሳምንቱ ቀደም ሲል በጥቅምት ወር ይካሄድ ነበር፣ የብዙ ዲያስፖራዎች እንቅስቃሴ በጥር ወር መሆኑ ታይቶ ዝግጅቱ የሚካሄድበት ወቅት ወደ ጥር ወር ተዛውሯል። በፋሽን ሳምንቱ ላለፉት 15 ዓመታትም ወደ 200 የሚጠጉ ዲዛይነሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ‹‹ ፋሽን ኤግዚቢሽን ብለን ጀማሪ ዲዛይነሮችን እናሳትፋለን፤ ኢንዱስትሪው ላይ የቆዩ ዲዛነሮች ደግሞ በፋሽን ትርኢቱ ላይ ይሳተፋሉ›› ብላለች፡፡

ሀብ ኦፍ አፍሪካ ፋሽን ሳምንት በውስን ሙያ ዎች የተገደበ እንዳልሆነም ጠቅሳ፣ የጸጉር ሙያ ባለሙያዎች፣ የሜካፕ አርቲስቶች፣ የፋሽን ዲዛይነሮችና የፋሽን ፎቶግራፍ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት መሆኑን አመልክታለች፡፡

በመድረኩ ስራቸውን ለሚያቀርቡ ፋሽን ዲዛነሮች በተቀመጠው መመዘኛ መሰረት ምዝገባ መጀመሩንም ጠቁማለች፡፡ ሀብ ኦፍ አፍሪካ የራሱ የቦርድ አባሎች አሉት፤ እነሱም ዲዛይነሮች የሰሯቸውን ስራዎች በመመዝገቢያ ቅጹ ላይ በፎቶ አድርገው ይልኩልናል፤ በአካል ማየት የምንፈልገው ስራ ከሆነ ደግሞ እንዲያመጡልን አድርገን እንገመግማለን፤ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የምንጋብዝ ከሆነ ደግሞ ከገጾቻቸው ላይ ስራቸውን ለማየት እንሞክራለን ፡፡ ›› ብላለች፡፡

ስለፋሽን ሳምንቱ እንዳብራራችውም፤ በአሁኑ ወቅት በዚህ ዘርፍ የሚሳተፉ ዲዛነሮችም ሆኑ ሞዴሎች በርከት እያሉ መጥተዋል፤ እንደ አንድ መድረክ ለዲዛይነሮች ራሳቸውን ማስተዋወቂያ መንገድ ነው፤ በቦታው ለሚገኙ ታዳሚዎች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ መገናኛ ብዙሀኖች ፋሽን ላይ ብቻ ተመርኩዘው የሚሰሩ መጽሄቶች ላይ የሚዲያ ሽፋኖችን ስለሚያገኙ የመታየት እድል አላቸው፡፡ በተጨማሪም በፋሽን ሳምንቱ ደግሞ በቀጥታ ከደንበኞች ጋር ስራቸውን ከወደዱ ሰዎች ጋር እንዲገናኙ እናደርጋለን ብላለች፡፡

በፋሽን ሳምንቱ ላይ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተጋባዥ እንግዶች ጋር በመሆን ውይይቶች ይደረጋሉ፤ ይህም ለዲዛነሮች ተጨማሪ ግብዓት ይሆናል፤ በስራቸው እንዲያድጉ የሚረዳቸው ነው ፡፡

የዘንድሮውን የሀብ ኦፍ አፍሪካ ፋሽን ሳምንትን ለማዘጋጀት ዲዛይነሮችን በመቀበል ላይ መሆኗን ጠቅሳ፣ የወደፊት እቅዱ ከዚህ የበለጠ እንደሚሆን ገልጻለች፡፡ ‹‹ የፋሽን ሳምንት ብሎ ማዘጋጀት የራሱ የሆነ ውጣ ውረድ አለው፤ አቅምና ዝግጅትን ይጠይቃል፡፡ እኔም ከዚህ በላይ አቅም ያለው እንዲሆን አፈልጋለሁ›› ብላለች፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You