የብስክሌት ጎዳናዎች ለስፖርት ምን ይፈይዳሉ? የብስክሌት ጎዳናዎች ለስፖርት ምን ይፈይዳሉ?

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ዳር ፕሮጀክቶችን (ኮሪደር ልማትን) በመስራት ከተማዋን ውብና ምቹ የማድረግ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ይህም መንገዶች ለእግረኞችና ተሽከርካሪዎች ምቹ እና ተስማሚ፤ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ማድረግ ችሏል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የብስክሌት መጋለቢያ ጎዳናዎች ትኩረት መሳብ የቻሉና የብስክሌት ስፖርት የልምምድና መወዳደሪያ ስፍራ እጥረትን ይቀርፋሉ ተብሎ ታምኖባቸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ካለው ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ ፍሰት እና የሰዎች እንቅስቃሴ የብስክሌት ስፖርትንም ሆነ ሌሎች ጎዳና ላይ የሚካሄዱ ስፖርቶችን ለማዘውተር አመቺ ሁኔታ አልነበረም። የብስክሌት ስፖርትን ብቻ ታሳቢ ያደረገ መጋለቢያ ጎዳና ታሳቢ ባደረገ መልኩ አለመሰራቱ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የብስክሌት መጋለቢያ ስፍራን አካቶ እየተሰራ መሆኑ ችግሩን ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የብስክሌት ስፖርትን ያማከለ የመጋለቢያ ጎዳና መሰራቱ በልምምድና ውድድር ቦታ የሚታየውን ተግዳሮት እንደሚቀርፍ የአዲስ አበባ ከተማ ብስክሌት ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡ ፌዴሬሽኑ አዲስ በተሰሩ የከተማዋ ብስክሌት ጎዳናዎች በተለያዩ እድሜ ክልል የሚገኙ ብስክሌተኞችን ጨምሮ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ ሳምንታዊው የብስክሌት ሽርሽር እያካሄደ ይገኛል፡፡ ይሄ ዘወትር እሁድ የሚያዘጋጀው “ሽርሽር በሳይክል” መርሃግብር የሕብረተሰቡን የብስክሌት እና መንገድ አጠቃቀም ግንዛቤን እንደሚያሳድግም ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ብስክሌት ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ ተረፈ፣ እንደ ፌዴሬሽን ውድድሮች እና ስልጠናዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ገልጸው፤ ከ2015 ዓ.ም በፊት በነበሩት ወቅቶች የልምምድና ውድድር ቦታዎች ችግር መሆኑን ያስታውሳሉ።

አሁን ግን በኮሪዳር ልማት ውስጥ ተካተው የተሰሩት የብስክሌት ጎዳናዎች ለፌዴሬሽኑ ትልቅ ግብዓት ይሆናሉ ብለዋል። ለልምምድና ውድድሮች ረጅም ርቀት መጓዝን የሚያስቀሩና ታዳጊዎች፣ ትልልቅ ስፖርተኞችና ኅብረተሰቡ በየ አከባቢው በአመቺ ግዜ ልምምድ ማድረግ፣ ወደ ትምህርት ቤት፣ ወደ ስራ እና ለመዝናኛም ለመጠቀም መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ስፖርተኞች ከመኪና እና እግረኞች ጋር ተጋፍተው ልምምድ ሲያደርጉ የነበረውን ችግር በመቅረፍ እንደዚህ አይነት አገልግሎቶችን በመስጠት ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ብስክሌት ፌዴሬሽን በ2017 ዓ.ም የብስክሌት ጎዳናዎች የመጠበቅና አጠቃቀሙን የማስተማር ግዴታ እንዳለበት ተቋም በሕብረተሰቡ የብስክሌት መንገድ አጠቃቀም ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ይናገራሉ። ለዚህም የተለያዩ ብስክሌተኞችን በተለያዩ ቀናት እና ሰዓታት ልምምድ፣ የብስክሌት ፌስቲቫል እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው። ብስክሌተኞች እንዲሁም ሕብረተሰቡ ለብስክሌት ስፖርት ብቻ የተሰሩ ጎዳናዎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እግረኞች መንገዳቸወን ይዘው እንዲጓዙ የማስተማሩ ስራ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚሰራም ይገልጻሉ፡፡

በዚህም በአምስቱም የኮሪደር ልማት ጎዳናዎች የሚካሄደው የብስክሌት ጉዞ እየተለመደ መምጣቱን እንዲሁም ሽርሽሩ የብስክሌት ስፖርት በሕብረተሰቡ ዘንድ ተዘውታሪ እንዲሆን ከማስቻሉ ባሻገር ጤናማ ትውልድ ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጨምረው ይጠቅሳሉ፡፡ በኮሪደር ልማት ጎዳናዎች በሚካሄዱ የብስክሌት ጉዞዎች ታዳጊዎች፣ ወጣቶች፣ እና የስፖርት ቤተሰቦች እየተሳተፉ ሲሆን ተቀባይነቱ እየሰፋ ሊመጣ ችሏል፡፡ ጎዳናዎቹን በብስክሌት ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚጠቀሙ አካላት በመኖራቸው ፌዴሬሽኑ እነዚህን አገልግሎቶች ማስተማሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡ በቀጣይም ሕብረተሰቡ በአጠቃቀሙ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖረው ፌስቲቫሎችን፣ ስልጠናዎችን እና ውድድሮችን ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር ለማዘጋጀት ይሰራል፡፡

በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ የሚገነቡት እነዚህ፣ የብስክሌት ጎዳናዎች የትራፊክ መጨናነቅን ከመቀነስም በላይ ለብስክሌት ስፖርተኞችና የሕብረተሰብ ክፍሎች የተመቻቸ ሁኔታን እንደሚፈጥሩ ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በአምስቱም የብስክሌት ኮሪደሮች ዘወትር እሁድ ሽርሽር በሳይክል ተጠናክሮ እንደሚካሄድም ያመላክታሉ፡፡ የብስክሌት ጎዳናዎቹ አሁን ባላቸው አቋም ለልምምድ የሚሆኑ ሲሆን በከተማዋ ለስፖርቱ እየተሰጠ በሚገኘው ትኩረት ውድድሮችን ለማካሄድ በቀላሉ የሚመቻችበትን ሁኔታ ይፈጥራል። ሕብረተሰቡም ልጆቹን በታዳጊዎች፣ በጤና ቡድኖች፣ ክለቦች፣ በፌስቲቫል፣ ስልጠና እና ውድድር እንዲያሳትፍ የማድረግ እቅድ መኖሩንም ገልጸው፣ መንገዶችን በሚፈለጉ ሰዓት ከሚመለከተው አካል ጋር ምቹ በማድረግ ውድድሮችን እንደሚካሄዱ አስረድተዋል፡፡

ታዳጊዎች በየአከባቢው በሚገኙ የብስክሌት ኮሪደሮች ላይ ልምምዳቸውን እያደረጉ በመሆኑ ጥሩ ውጤት እየታየ መሆኑን እና ብስክሌተኛ በብስክሌት ጎዳና እንዲሁም እግረኛ በእግረኛ ጎዳና እንዲጠቀሙ የሚደረገው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ተስፋ ሰጪ ነው ይላሉ፡፡ የብስክሌት ተጠቃሚነት መዳበር የአየር ብክለትን ከመቀነስ፣ የትራንስፖርት መጨናነቅን ከማስቀረት እንዲሁም ጤናን መጠበቅን እንዲሁም ጥሩ ስፖርተኞችን ለማፍራት የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡ በብስክሌት ስፖርት የሚታወቁት ከተሞች አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ስፖርቱ የተዳከመ ሲሆን አሁን በስፖርቱ የተሻለ እንቅስቃሴ ከሚደረግባቸው ጋር የልምምድ ልውውጦች እየተደረጉ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ በ2017 ዓ.ም የተመረቁ የኮሪደር ልማትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ”ሽርሽር በሳይክል” የሚለውን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ ውድድሮችን፣ ፌስቲቫሎችን፣ ስልጠናዎችን ከደጋፊ አካላት፣ መገናኛ ብዙሃን ጋር በመቀናጀት ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ማቀዱንም አክለዋል፡፡

ዓለማየህ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You