መልካም መምህር፣ ድንቅ መሪ፣ ተስፋን አብሳሪ፣ በክፉ ቀን የሚያፅናኑና የሚፀኑ አባት ናቸው፡፡ የሚከተሏቸውን ሳይታክቱ ወደ መልካሙ ሥፍራ የመሩ፣ ለምስጋና የበረቱ፣ ደግነት፣ አዛኝነት የማይለያቸው መሆናቸውን በጦርነቱ ጊዜ ጭምር አስመስክረዋል። ሰው በሰውነቱ የተከበረ መሆኑንም አሳይተዋል፡፡ በእርሳቸው ሥራ ውስጥ ሃይማኖት አይመረጥም፤ ዘር አይቆጠርም፤ ቋንቋ አይለይም፤ ሰው የሆነውን ሁሉ በልጅነቱ ተቀብለው አባቴ እንዲሉ አድርገዋል፡፡ የሁሉም ሆነው ሁሉንም በአንድነትና በመረዳዳት ችግርን እንዲያልፉ መሠረት ጥለዋል፡፡ በዚህም በተለይ የሰሜን ወሎ ሕዝብ በፅናት እንዳገለገሏቸው ሁሉ ሳይሰስቱ ይወዷቸዋል። በወልድያ ጎዳናዎች ብቻ ሳይሆን በመገናኛ ብዙኃኑ ጭምር እየተመላለሰ ሰሞነኛ የወግ መጀመሪያና መጨረሻ የሆኑትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ እኛም ይህ ታሪካቸው ላልሰሙት መሰማት አለበት፤ ታሪካቸው ሊሰነድ ይገባል ስንል የብፁዕ አቡነ ኤርሚያስን ሥራ የሕይወት ተሞክሮ በዛሬው ‹‹የሕይወት ገጽታ›› አምዳችን ልናስቃኛችሁ ወደድን፡፡ ብዙ የምትቃርሙት ልምድ አለና ተማሩባቸው ስንልም ጋበዝናችሁ፡፡
መንፈሳዊነት በልጅነት
ፈጣሪ ክብሩን ሊገልጥባቸው፣ ደግነቱን ሊያሳይባቸው፣ መልካምነትን ሊያስተምርባቸው ገና ከእናታቸው ማሕፀን እያሉ የተመረጡት ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ፤ በመልካሙ መንገድ እየተጓዙ እንዲያድጉ በመደረጋቸው ብዙ የመንፈስ ፍሬዎች የሚባሉ ባህሪያትን እንዲላበሱ ሆነዋል። ዛሬ ለተቸገረ ደራሽ፣ ለታረዘ አልባሽ፣ ለተራበ ተበድረው ጭምር መጋቢና በተሰጣቸው ጸጋ አጽናኝ የሆኑትም ይህ ባህሪያቸው ሳይለወጥ መልካም ተክል ሆኖ በማበቡ ነው።
እርሳቸው በንግግራቸው ጭምር መባል ያለበትንና የሌለበትን የሚያርሙ ናቸው። ምክንያቱም አቡኑን የት ተወለዱ፣ አስተዳደግዎት እንዴት ነበር ላልናቸው ጥያቄ ‹‹ልጄ የመነኩሴ አገሩ አይጠየቅም። ምክንያቱም እናቱ ቤተክርስቲያን፣ እህት ወንድሞቹ ገደብ የሌለባቸው ምዕመናን ናቸው። በሁሉም ቦታ ያሉና የሚኖሩ። መቼ ተወለዱ ካልሽኝ ግን በተባረከች ቀን በተባረኩት ሰዎች እግዚአብሔር ወደዚች ምድር ያመጣኝ 1966 ዓ.ም ነው።›› በማለት መልሳቸውን ሰጡን። ይህ ማለት በአካባቢም መወሰን አይፈልጉም። የአንድ ሰፈር ልጅ ነኝ የሚለውም ምቾት አይሰጣቸውም። ምክንያቱም እርሳቸው የዓለም ጭምር ናቸውና።
አስተዳደጋቸው ብዙ ነገር እንደሰጣቸው ግን አልሸሸጉንም። በተለይም የአባታቸው የአመራር ሰጪነት ጥበብ ብዙ ነገራቸውን የቀየረላቸው እንደሆነ ይናገራሉ። የዛሬ ማንነታቸው አናጺ እርሳቸው ናቸው። መልካም ነገር ብቻ ተናጋሪ፣ መልካም ነገር ብቻ አድራጊ፣ የተቸገሩትን ደጋፊ ፣ በመንፈስ የተጨነቁትን በመንፈሳዊ ፀጋቸው አጽናኝ አድርገው ሠርተዋቸዋልና። በሥራ በኩልም ቢሆን የመልካም እረኝነትን ጥበብ በመኖር ጭምር እንዲረዱት አድርገዋቸዋል። እንደማንኛውም የገጠሪቱ አካባቢ ልጅ ከብት በመጠበቅ፣ ውሃ በመቅዳትና እንጨት በመልቀም እንዲሁም እርሻውም ላይ በመሠማራት ቤተሰብን ሲያገለግሉ አገልጋይነትን በፍቅር ወደውት እንደነበርም ያስታውሳሉ።
በአካባቢው ማኅበረሰብና በቤተሰቦቻቸው እገዛ በፈሪሃ እግዚአብሔር ማደጋቸው ደግሞ ለሁሉም መሠረት እንደነበር ያነሳሉ። አገልጋይነትን በሥራው መስክ በልጅነታቸው ጠንቅቀው ቢያውቁትም ከእንስሳት ለበለጡት፣ ከፍጥረታት ሁሉ ለከበሩት እረኝነት አስቀድመው እንደሚመረጡ ግን አያውቁም። ሆኖም ሕልም ነበራቸው። በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ መቆየት። በ50 ዓመቴ እመነኩሳለሁ የሚል። ነገሩ ግን እንዳሰቡት ሳይሆን እግዚአብሔር እንደፈቀደው ሆነ። በ28 ዓመታቸው ቀንበሩን ተሸከሙ። ለዚህ ስኬታቸው መድረስ ያገዛቸው በቅንነት ወላጆቻቸውንና ሌሎች ሰዎችን እየታዘዙ ማደጋቸው ነው። በየቀኑም የሚወርድላቸው ምርቃት ክብርና ሞገስን ሰጥቷቸዋል።
ከአባታቸው በላይ ቤተክርስቲያን የሰጠቻቸው የልጅነት ክብርና ማንነት ወደር እንደማይገኝለት የሚያስረዱት ብፁዕነታቸው፤ ዛሬ በምንኩስናውም ሆነ በሌላው መንፈሳዊ ማንነቴ ላይ እርሷ ምሰሶ ነበረች። ሰውንና አገርን መውደድንም የተማርኩት ከእርሷ ነው። አሁን ማንንም ሳለይ የማገልገሌ ምስጢርም በቤቷ የሰጠችኝ ማንነት ነው ይላሉ።
ትምህርት
ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ትምህርትን የጀመሩት በእግዚአብሔር መለኮታዊ ተአምር እንደሆነ ይናገራሉ። እንደቤተሰቦቻቸው እቅድ ይህ አይሆንም ነበር። ቤተሰብ አገልጋይነታቸው ብቻ ነው የሚቀጥለው። ምክንያቱም ቤት ውስጥ ብዙውን ሥራ የሚያከናውኑት እርሳቸው በመሆናቸው ቤተሰብ ሥራው እንዳይጓደልበት ያስባሉ። ስለዚህም ሌላ ሕይወት ውስጥ ይገቡ ነበር። ነገር ግን ከማህፀን ጀምሮ ተመርጠዋልና መንፈሳዊ ትምህርቱን የሚማሩበት መንገድ ተዘረጋላቸው። እንዴት ከተባለ ነገሩ እንዲህ ነው። አጋጣሚው የደርግ ሥርዓት ያመጣው ነው። ከቤት ውስጥ ቢያንስ አንድ ልጅ በግድ ወደ ትምህርት ቤት መላክ አለበት። እናም ወላጆቻቸው እርሳቸውን ሳይሆን ታናሻቸውን ትምህርት ቤት አስገቡ።
ቤተሰብ ያሰበው ቀርቶ አምላክ የፈቀደው ነገር አለና ታናሽ ወንድማቸው ወደ ትምህርት ቤት መላካቸውን እንዳይወዱት ሆነ። እንዲያውም ከዚህ በኋላ ከላኳቸው ችግር እንደሚፈጥሩ ገለጹ። በዚህም ቤተሰብ ተጨነቀና ቢቀር ይሻላል በማለት ሀሳባቸውን ወደ ብፁዕነታቸው አዞሩ። ትልቅ የሚሆኑት ተማሪ ለመማር ተንደረደሩ፤ ለማስተማር የታደሉት አባት ፊደልን ለመቁጠር ወደ ታላቁ አባት አባ ገብረ እግዚአብሔር ዘንድ አመሩ።
አባ ገብረ እግዚአብሔር በድንግልና የሚኖሩ ደግ አባትና የተናገሩት ሁሉ የሚደመጥላቸው ሰው በመሆናቸው የእንግዳችንን የመማር እድል አጽንተውላቸዋል። እንደውም የፊደል አያያዛቸውን ሲያዩ ‹‹ይህን ተማሪ እንዳታስቀረው፣ ጥሩ ተሰጥዖ አለው፣ ነገ ጥሩ ካህን ይሆናል›› ሲሉ ለአባታቸው አስረድተው ትምህርታቸው ቀና መንገድን እንዲይዝ ከአደረጉላቸው የመጀመሪያው ሰው እንደሆኑ ያነሳሉ። እርሳቸውን ጨምሮ ብዙ አባቶች ለአብነት ትምህርቱ መሠረታቸው እንደነበሩም ይናገራሉ። በዚህም በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ በቆዩባቸው ጊዜያት በተለያዩ አድባራትና ገዳማት እየተዘዋወሩ በአብነት ትምህርቱ ከንባብ ጀምሮ ያሉትን እንደ አቋቋም፣ ዜማ፣ ቅኔ የመሳሰሉ ትምህርቶችን ተምረዋል። ዳዊትም ደግመዋል፤ መጽሐፍትን መርምረዋል።
የዚያን ጊዜው ተማሪ የአሁኑ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፤ በሰሜኑ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን ሲጨርሱ በቀጥታ ወደ ጉራጌ ዞን ምሑር ገዳም ነው ያቀኑት። በዚያም ፆመ ድጓን በጥልቀት ተምረዋል። ይህ ሲጠናቀቅ ደግሞ ጉዟቸውን ወደ አዲስ አበባ ሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ አደረጉ። ብሉይ ኪዳን ትርጓሜን በአምስት ዓመት ቆይታ፤ የሀዲስ ኪዳን ትርጓሜን ደግሞ ስድስት ዓመታትን አስቆጥረው ሁለቱን ትምህርት በ11 ዓመት አጠናቀዋል።
ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ በዘመናዊውም ትምህርትም እንዲሁ የዘለቁ ናቸው። በእርግጥ ይህ የሆነው 31 ዓመታቸው ላይ ነው። ምክንያቱም ቅድሚያ የሰጡት መንፈሳዊውን ትምህርት ነበር። ስለዚህም እድሜያቸው ሳይገድባቸው መንፈሳዊውን እየተማሩ በማታው ክፍለጊዜ ሁለተኛ ክፍል በመግባት ከታናናሾቻቸው ጋር ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ። ይህ የሆነውም በኮልፌ ሰላም በር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደሆነ ይናገራሉ። እስከ ስምንተኛ ክፍልም ትምህርት ቤቱን ተከታትለውበታል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ የተከታተሉት ኮምፕሬሄንሲፍ የሚባል ትምህርት ቤት በመግባት ዘጠነኛ እና አስረኛ ክፍልን ተማሩ። ውጤት መጥቶላቸው ስለነበር በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመግባት በሰው ሀብት አስተዳደር ትምህርት መስክ ዲፕሎማቸውን ለመያዝ ቻሉ። ከዚያ በኋላ አገልግሎታቸው ትምህርቱን እንዲቀጥሉ አላስቻላቸውምና መንፈሳዊው ሥራ ላይ አጠነከሩ።
እውነተኛው ተልዕኮ
‹‹የቤተክህነት ሰው አካባቢ የለውም፣ ያሳደጉት ኢትዮጵያውያን ናቸው። ያስተማሩትም እንዲሁ ኢትዮጵያውያን ናቸው›› የሚሉት ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፤ ያሳደገቻቸውን፣ በክብር ያኖረቻቸውን ለማገልገል ደከመኝን አያውቁትም። በተለይ ለቤተክርስቲያን ምንም የሚሰስቱት ነገር የለም። ምክንያቱም እርሷ ሳትሰስት የሰጠቻቸው ብዙ ነው። እናም በቻሉት ሁሉ ውለታዋን ለመክፈል የመጀመሪያ ሥራቸውን የጀመሩት በለጋ እድሜያቸው መሪጌታ በመሆን ነው። ያገለገሉበት ቦታ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ በወሊሶ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሲሆን፤ ሦስት ዓመታትን ያለ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሠርተዋል።
ከመነኮሱ በኋላ የጀመሩት ሥራ ደግሞ የንባብ መምህርነታቸው ሲሆን፤ በምሑር ገዳም የቆዩበት ነው። ጎን ለጎን በማህሌትና በሰዓታትም ያገለግላሉ። ከዚያ በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር ሆነው ወደማገልገሉ ገቡ። በዚህም ሦስት ዓመታትን አሳለፉ። ቀጥለው ደግሞ የብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ረዳት በመሆን ሰሜን ወሎ እንዲሰሩ ሆኑ። አብዛኛው እድሜያቸው ያለፈው በትምህርት ላይ በመሆኑ ብዙ በሥራ የተዘዋወሩበት ቦታ የለም። ይሁን እንጂ በተመደቡባቸው ቦታዎች ላይ ፍሬያማ ሥራ የሠሩ እንደሆኑ ብዙዎቹ ይመሰክሩላቸዋል። በቅርብ ባናያቸውም አሁን በሊቀ ጳጳስነት እያስተዳደሩት ያለውን አህጉረ ስብከት ማለትም ሰሜን ወሎና ከሚሴን ጨምሮ ብዙ ተዓምር ናቸው የሚያሰኙ ተግባራትን ፈጽመዋል።
ለእምነት የሚሰጠው ዋጋና ለተቋማቱ የሚሰጠው ክብር አናሳ መሆኑ ብዙ አባቶች ከሥራቸው አንጻር እንዳይገለጡ ቢሆኑም በችግር ወቅት ከወጡና ሁሉም አማኝ አባቴ የሚላቸው መሆኑም ይፋ ወጥቷል። የምዕራባውያን አሠራርና ተግባርን ትውልዱ እየወረሰው መምጣቱ የአባቶች ዋጋ እንዲቀንስ ቢያደርግም ወጣት ሽማግሌ ሳይል የሚወዳቸው አባቶች እንዳሉ ማሳያም ሆነዋል። እንደውም ሥራቸውን ሌሎች ተናገሩላቸው እንጂ እርሳቸውማ የሚሉት እንደሰሜን ወሎ የሰራነው መልካም እረኛ የሚገባውን ያህል አይደለም ነው። ነገር ግን በብዙዎች ዓይን ውስጥ ገብተዋል።
ብፁዕነታቸው እንደሚሉት፤ ችግሩ በሌሎች ቦታዎች ላይ ተከስቶ ቢሆን ኖሮ በበለጠ የሚገለጡ መልካም እረኞች ይኖራሉ። ምክንያቱም አባባሉ እንኳን ‹‹ጀግና በጦር ሜዳ ይወለዳል›› ነው። ስለዚህም ጀግና የሚገለጠው እንቅፋት ሲገጥመው እንደሆነ ሁሉ አባቶችም ሆኑ መሪዎች የሚታዩት ፈተና ሲኖር ነው። እናም ‹‹እኔ ገና ብዙ ሥራ አለብኝ፤ ብዙ አደራም። ምንም ለዚህ ክብር የሚያበቃ ነገር አልተገበርኩም›› ይላሉ ሰው ያየውን እርሳቸው ግን ገና አልሰራሁትም የሚለውን ተግባራቸውን ሲገልጹ። ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ አገር ችግር ላይ በወደቀችበት ጊዜ ለራሳቸው ሳይሰስቱ ብዙ ተግባራትን የፈጸሙ ናቸው።
መልካሙ እረኛ
በሹመት ዘመናቸው ምዕመኖቻቸውን የሚፈትን እርሳቸውንም ጊዜ የሚያሳጣ ችግር ሲገጠማቸው የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው። የመጨረሻም ያድርግልኝ ይላሉ። ምክንያቱም አሸባሪውና ወራሪው ቡድን እርሳቸው በሊቀ ጳጳስነት የሚመሩትን አካባቢ በብዙ መንገድ ጎድቶታል። ዜጎችን ጨፍጭፏል፤ አፈናቅሏል፤ ሀብትና ንብረታቸውን ዘርፏል፤ አውድሟል፤ የተረፈ ሀብት እንዳይኖር ጭምር ጭኖ ወስዷል፤ ሰዎችን አስነውሯል። በቃ ስቃዩ ብዙና አምላክ ዳግም አያሳየን የሚያስብል ነበር ይላሉ።
በጊዜው እንጨትና ከሰል ጭምር አጥተው እንደነበር የሚያነሱት ብፁዕነታቸው፤ በእግዚአብሔር ጥበቃ ተፈጥሮ እንድትመግበን አድርጎን ልናልፈው ችለናል። እንደ ሌሎቹ አገራት ቢሆን ኖሮ በሙቀት አለያም በቅዝቃዜ እናልቅ ነበር። ሆኖም እርሱ ስለሚያስብልን ተስፋይቱ ምድር ላይ ጥበቃውን ጨምሮ በተፈጥሮ አድኖናል። ውሃ እንዳጣን ጭምር ተረድቶ ምንጭን በየአካባቢው እንዲፈልቅ ያደረገበት ጊዜ ቢኖር ይህ የመከራ ወቅት ነውም ብለውናል።
ሰላም ሲታጣ ብዙ ነገሮች አብረው ይጠፋሉ። እንቅልፍ ጭምር አይኖርም የሚሉት ባለታሪካችን፤ በወራሪዎቹ እንቅልፍ ሁሉ አጥተው ከዚህ መከራ ሕዝቡን የሚያወጡበትን፤ የሚያክሙበት መንገድ ሲፈልጉ እንደከረሙ ይናገራሉ። በዚህ ውስጥ ለራሴ ብለው ያደረጉት አንድም ነገር አልነበረም። ይልቁንም በጎቻቸው እንዳይራቡ ይመግቧቸው፤ እንዳይበተኑ ይሰበስቧቸውና ከተኩላ ንጥቂያ ይጠብቋቸው ነበር። ይህንን ሲያደርጉ ደግሞ መድኃኒት ያለው መድኃኒቱን እንዲያካፍል፤ ጉልበት ያለው በጉልበቱ የደከሙትን እንዲያግዝ፤ ገንዘብ ያለው ሌላው የሚኖርበትን መንገድ እንዲከፍት በማስተባበር ነው።
ምክራቸውና ተግሳጻቸው በብዙዎች ዘንድ ሰሚነትን ያገኘ በመሆኑም ተራ ሌባን ጭምር ማስቆም ችሏል። ሳያውቁ የዘረፉትም እንዲመልሱ አስችሏል። ይህ ደግሞ የሆነው የእምነት ገደብ ጭምር ሳይኖርበት ነበር። ይህ በመሆኑም ብዙ የደስታ ጊዜያትን እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል። የመጀመሪያው በመከራ ጊዜ አብረው ማለፋቸው ሲሆን፤ በመረዳዳት መከራን ማሸነፍ እንደሚቻል አይተውበታልና ደስ ተሰኝተውበታል። የኢትዮጵያ ባህል ጠፍቷል የሚሉትንም እንዳልጠፋ ያሳዩበት ጊዜ ስለሆነላቸውም በሁነቱ ያጡት ቢኖርም የተረፈውን እንዲያስቡበት ሆነዋል። በቀጣይ ተስፋቸውን አለምልመው፣ ከችግሮቻቸው ተምረው ለሌላ የሚደርሱበትን ሁኔታ እንዲያውቁም ስላደረጋቸው ደስታቸው እጥፍ ድርብ ነው። ከሁሉም በላይ በሕይወት ተርፈው አምላካቸውን እንዲያመሰግኑት መሆናቸው በራሱ ደስተኛ ያደረጋቸው ጉዳይ ነው።
ብፁዕነታቸው ሕዝብ እንዳይንገላታ፣ ዜጎችም በረሃብ እንዳይሞቱ ለፍተዋል። ሁሉም ነገር የተዘጋባቸው ዜጎችም አባታችን ረሃብን፣ ጠማን፣ ታረዝን፣ ተከፋን እያሉ ስለሚጠይቋቸውም መልስ ለመስጠት ያልቆፈሩት ድንጋይ የለም። ምክንያቱም እርሳቸው በችግር ውስጥ ሆነው የሚሰሙት የምዕመናን ድምጽ እረፍት ይነሳል። በዚያ ላይ ገጠሩም ከተማውም በጦር ቀጠና ውስጥ ስለሆነ የእርዳታ ድርጅቶች አይገቡም። ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ለመገናኘትም አይቻልም። ስለዚህም ከአምስት ወር በላይ ሲያሳልፉ የሰውን ችግር የእርሳቸውን መፍትሔ አምጪነት ይፈልጋል። እናም ደከመኝን ሳያውቁ በብዙ መንገድ እስከቀበሌ ድረስ በአለው መዋቅራቸው እንዲሰሩ ሆነዋል።
በእርሳቸው ጥሪና ምክር በሰሜን ወሎ ውስጥ ያልሆነ ነገር አልነበረም። የመጀመሪያው ሕዝቡ ሃይማኖት ሳይለየው ይሰጣል። በዚህም ራበን ጠማን ሲሉ የነበሩ ዜጎች የእለት ጉርሳቸው ያገኛሉ። አባታችን ላይ ራበን ጠማን የሚለውም ብዙ ነው። አሁንም ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል ያሉትን መንገድ ጀመሩ። ይህም ባንክ ሳያስገቡ በየቤታቸው ብር ያስቀመጡ ካሉ ይሰጧቸው ዘንድ መለመን ነው። እርሳቸው ጠይቀው እምቢ አይባሉምና አሁንም ያሉት ሆነላቸው። ለተቸገሩትም አደረሱ።
ፈተናው በየአይነቱ የተከታተለባቸው አባት ሌላ የሚፈቱት ችግር ገጠማቸው። ይህም ቋሚ የመድኃኒት ተጠቃሚዎች መድኃኒታችን አለቀ ወደማለቱ ገብተዋል። ስለዚህም ለዚህም መፍትሔ ማበጀት ግድ ነውና ምን ማድረግ እንዳለባቸው አሰቡ። መላሹ ራሱ ሕዝቡ እንደሆነም ያውቃሉና ሌላ ጥያቄ አነሱ ‹‹ ለሌላ ቀን ይሆነኛል ብላችሁ ያስቀመጣችሁት ካለ ዛሬ ወገናችሁ ይፈልገዋልና ድረሱለት። አብሮ መድኃኒቱን ተጠቅመን አብረን እንለፈው›› አሉ። ሕዝብም አሁንም ሰማቸው። ለሁለትና ሦስት ወር ብሎ የገዛውን መድኃኒት እያነሳ ሰጣቸው። ለጊዜውም ቢሆን መድኃኒት ያለቀባቸውን ሰዎች መታደግ ቻሉ። እንዲያውም ይህንን ጊዜ ሲያስታውሱ ‹‹ለመስጠት የማይሰስቱ ኢትዮጵያውያን ሞልተዋል። በዚህም ካጣነው ይልቅ ያገኘነው በልጧል። መረዳዳትን አይተናል፣ ኢትዮጵያንም አውቀናል።›› በማለትም ነበር የገለጹት።
ፍርሃትም ድፍረትም ጠርዝ ሲለቅ መልካም አይደለም የሚል እምነት ያላቸው ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፤ ወራሪዎች ወደ ወልድያ ሲጠጉ አቡነ ኤርሚያስ እንግልት እንዳይደርስባቸው የሚፈልጉ ከአገርም ሆነ ከውጭ ያሉ ምዕመናን ‹‹አባታችን አካባቢውን ለቀው ይውጡ›› እያሉ ይጎተጉቷቸው ነበር። እርሳቸው ግን መልሳቸው ‹‹መራብና መጠማት መንገላታት እንደሚኖር ባስብም ምንም ቢሆን ስሜ እረኛ ነው። እረኛ የተባልኩት ደግሞ በእነዚህ በጎች አማካኝነት ነው። የማገለግለው ሕዝብ በተኩላ ሲበላ ማየት ደግሞ በእምነቴ ተጠያቂነቴን መጨመር ነው። የተሰጠኝን የአምላክ ክብር መካድ ነው። እናም በጎቹ በእንደዚያ አይነት አስደንጋጭ፣ የኃዘን፣ የጭንቀት ድባብ ውስጥ ሆነው እረኛው ወጥቼ ብሄድ ምንድን ነው የሚሰማቸው? እኔስ ምንድን ነው የሚሰማኝ? በእርግጥ በስጋ እፎይታን አገኛለሁ። ነብሴና ህሊናዬ ግን መቼም አያርፉም። ስለዚህም አላደረኩትም›› ብለዋል።
አቡነ ኤርሚያስ ዒላማ ሆነዋል ተብለው እንኳን የሚመጣውን ስለ እውነት ሊቀበሉ በፅናት የቆሙ ነበሩ። “መልካም እረኛ ነፍሱን ስለበጎቹ ያኖራል።›› እንደተባለው ሁሉ እርሳቸውም ይህንን አደረጉ። በጎቻቸውን ተኩላ እንዳይነጥቅባቸው ታገሉ። ተኩላው ቢበረታም እርሳቸውም በፈጣሪ እርዳታ ብዙዎችን ታደጉ። የማይተኛውን አምላካቸውን እየተማፀኑ ሳይተኙ ለዛሬዋ ቀን እርሳቸውንም በጎቻቸውንም አደረሱ።
የሽብር ቡድኑ አባላት መጀመሪያ ሲገቡ ከሕዝብ ጋር ፀብ የለንም ብሎ ነበር ያሉን ብፁዕነታቸው፤ በሕዝብ ላይ ያደረሱት ጥፋትና በደል መቼም ሰምተውትም ሆነ አይተውት እንዲሁም አንብበው አያውቁም። በዚህም መከራውን ማየትም ሆነ መስማት ከባድ እንደነበር ያነሳሉ። ከአዕምሮዬ የማይጠፋ በደሎችን አይቻለሁም ይላሉ። በጦርነት ውስጥ ብዙ ንፁሐን በተለያየ መንገድ ሊሞቱ ይችላሉ። በጦርነቱ እጃቸው የሌለበት ንፁሐን ግን በዚህ ደረጃ ሲጎዱ ማየት መቼም አይታሰብም ነበር። ግን ሲሆን እንድንመለከት ተደረግንም ብለውናል።
እርሳቸው ሊቀ ጳጳስ ናቸው። ሃይማኖታቸውን አጥብቀው ይወዳሉ፤ ያከብራሉም ይኖሩበታልም። ነገር ግን የሌላውን ሃይማኖት መንካት አይፈልጉም። በተለይም በሰውኛ አስተሳሰብ ዙሪያ ልዩነት እንዲኖር አይፈልጉም። ይህ መርሐቸው ደግሞ ክፉዎች ክፉ ነገር ቢያደርጉም እውነተኛ እረኛ እንዲያሸንፉ አድርጓቸዋል። ‹‹ሰውን መውደድ አምላክን መውደድ ነው። ምክንያቱም በዚህ ውስጥ ክፉ ቀንን መሻገር፤ በፅናት ማለፍ ይመጣልና።›› የሚሉት እንግዳችን፤ እርሳቸው መጠለያ ላጡት መጠለያ፣ መሻገሪያ ላጡት መሻገሪያ ሆነው እስከመጨረሻው የደረሱት በዚህ ምክንያት ነው።
ምንኩስና የሰጠው ክብር
ብፁዕነታቸው ነብሳቸው መንኩሳ መኖርን ትመርጣለች፣ የመነኩሴ ሕይወትን አጥብቃ ትወድዳለች። ይህ የሚሆነው ግን 50 ዓመታቸው ላይ እንደሚሆን ይገምታሉ። በለጋ እድሜያቸው ይሆናል ብለው አያስቡትም። ሰው ያስባል እግዚአብሔር ይፈፅማል ሆነና ነገሩ የእርሳቸው ፍላጎት ቀርቶ የአምላክ ሀሳብ ሆነና በ28 ዓመታቸው ታላቁን ቀንበር በብፁዕ አቡነ መልከፀዲቅ አማካኝነት ተሸከሙ። ከእኝህ አባት ምንኩስና ብቻ ሳይሆን ቅስናና ቁምስናንም ነው የተቀበሉት። ቦታውም ምድረከብድ አቦ ነበር።
ሥርዓተ ምንኩስናን ፈፀመው ዓለምን የተለዩትና የናቁት ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ፤ አሁን ብዙ ደረጃዎችን አልፈው ሊቀ ጳጳስ ሆነዋል። ይህ መሆኑ ደግሞ የእርሳቸው ዓለም የማያልፈው ዓለም እንደሆነ ይበልጥ እንዲያውቁና እየተረዱ እንዲመጡ አድርጓቸዋል። ሳይታክቱ ለነገው የነብሳቸው ድህነት የሚተጉትም ለዚህ ነው። ዛሬ ጊዜያቸውን በከንቱዋ ዓለም፣ በምትባዝነዋ ዓለም አያሳልፉም። የፈጣሪን ስም ሳያጓድሉ በሠርክ እያነሱ፤ ለምስጋና ሳይቦዝኑ በረከቱን ለምድር ይሰጥ ዘንድ ይማፀናሉ እንጂ። ይህ ደግሞ ለሁሉም ሰው እኩል እንዲደርሱና እኩል አባት እንዲሆኑ መንገድ ጠርጎላቸዋል። በብዙዎች ዘንድም ከልብ የመከበራቸውና የመወደዳቸው ምስጢር ይህ ነው።
መሠረታቸው ቤተክርስቲያን ቢሆንም ምንኩስናው ሲጨመርበት ግን በክፉ ቀን መልካም መሆንን፤ ሰው በጠፋበት ጊዜ ፀንቶ ክፉውን ቀን መሻገርንና ማሻገርን፤ መልካሙን ነገር ሁሉ ማድረግን አስተምሯቸዋልና መልካም አባትነትን ሰጥቷቸዋል። በዚህም ምዕመናኑ ሁሉ የክፉ ቀን መውጫችን እንዲሏቸው ሆነዋል። ከፈጣሪ በተሰጣቸው ጸጋ የደከመው የሚያርፍባቸው፣ መጠለያ ያጣ የሚጠለልባቸው፣ መንፈሱን የሚያበረታባቸው ምርኩዝ የሆኑትም ምንኩስናው ከሰጣቸው ክብርና ሞገስ በመነሳት በመሥራታቸው ነው።
በሰሜኑ ክፍል በተፈጠረው ጦርነት መልካም እረኝነታቸውን በተግባር የማሳየታቸው መንስኤ ይኸው በምንኩስናው ያገኙት የአደራ ውጤት ነው። በዚህም ደካማ የሚደገፋቸው፤ በክፉ ቀን ደራሽ፣ ሲርብ አጉራሽ፣ ሲታረዙ አልባሽ ሆነዋል። ምክንያቱም በክፉው ቀን ሰው የሆነን ሁሉ ልጆቼ ብለዋልና።
መልዕክት
እንደ ባለታሪካችን ማብራሪያ ዛሬ መነኩሴና አባት፤ ልጅና አዋቂ የምንልበት ላይ አይደለንም። የአምላክን ትዕዛዝ መፈጸም ላይ ብቻ የምናተኩርበት ነው። በተለይም ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ የሚለው ቃል ለዚህ ጊዜና ትውልድ የውዴታ ግዴታ የሚሆንበት ነው። ምክንያቱም ይህ ትዕዛዝ ወገን፣ ብሔር፣ ዜግነት፣ ፖለቲካ አለያም ቋንቋን አይለይም። ማንኛውንም ሰው የሆነ ፍጡርን ማገዝን ብቻ መሠረት ያደረገ ነው። ስለሆነም በጦርነቱ ምክንያት የተቸገረው ብዙ በመሆኑ ሳይለዩ ማገልገልንና ባልንጀራን መውደድን የምናሳይበት ወቅት ነውና ምንም ገደብ ሳይኖር ጊዜውን እንጠቀምበት የመጀመሪያ መልዕክታቸው ነው።
ኢትዮጵያውያን በሃይማኖት ጭምር ብንለያይም ሰሚ ነን። ለዚህም ማሳያው እንደእምነት በጎቻችን ያልተገባ ሥራ እንዳይሠሩ ገዝተን ነበር። ግዝቱን ያከበረው ግን አማኙ ብቻ ሳይሆን የሌላ እምነት ተከታዩ ጭምር ነው። በግዝቱ ምክንያት የዘረፈውን አምጥቶ ለቤተክርስቲያኑ ያስረከበ ሙስሊምና ፤ ፕሮቴስታንት እንዲሁም ሌላ ሃይማኖት የሚከተል ሰው ነበር። በተመሳሳይ ያለውን አብሮ ለመቋደስም ይሰጣል፤ ይቀበላልም። እናም የሃይማኖት አባቶች ልጆቻቸውን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የተማርንበትና በችግር ጊዜ እንዴት አብሮ ማለፍ እንደሚቻል እንደ ሕዝብም የተረዳንበት ጊዜ ነው። በዚህም ሰዎች ችግር ሲመጣ አብሮ ማለፍን ቢለምዱ፤ በማንኛውም መስክ ያሉ መሪዎች ሰውኛ ባህሪን ተላብሰው ቢሠሩ ብዙ ዓመታት ደስታ ይሆናል፤ ችግርም ድል ይነሳል ሌላው መልዕክታቸው ነው።
በጦርነቱ የተፈጠረው ችግር እስከ አሁን በሕዝቡ መደጋገፍ አልፏል። ከዚህ በኋላ ግን ሲደጋገፍ የቆየው የሚደግፈውን ይሻል። በእግዚአብሔር ጥበቃ ብዙዎች መድኃኒታቸው አልቆ ዛሬ ደርሰዋል። ነገር ግን የፈጣሪ አሠራር ልዩ ቢሆንም ቶሎ መደገፍ ግን ይኖርባቸዋል። በሽብር ቡድኑ ብዙ ስቃይ ውስጥ የገቡ ዜጎችም የስነልቦና እገዛን ይፈልጋሉ። በተጨማሪ ብዙዎች ከትምህርት ገበታቸው ተነጥለዋል። ሆስፒታልና ክሊንክም የለም። እናም ልጆቻችን ከትምህርት እንዳይርቁ፤ ጤናው የታወከ ማኅበረሰብ እንዳይፈጠርና በስነልቦናውም እንዲታከሙ ሁሉም በቻለው ልክ ሊረባረብ ይገባል ሲሉ የአደራ መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ።
ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ከፖለቲካ፣ ከብሔር ወገንተኝነትና የሰውን ልጅ ከሚያገል ስብዕና ወጥተው የማንም ጥገኞችና የሀሳብ መስጫ ሳጥን ሳይሆኑ ለአገር ሊሠሩ ይገባል። አግላይ ወገንተኝነት አገርንና ሕዝብን ያጠፋል፤ በጎችን ይበትናል፤ አስታራቂነትንም ሆነ አባትነትን ይነጥቃል። ስለሆነም ይህንን በማድረግ በጎቻችንን እንጠብቅ ሲሉ ይመክራሉ። የመንግሥት አካላትም የእምነት ተቋማትን ችላ ባይሏቸውና ድርሻቸው የጎላ እንደሆነ አስበው በተለይ በአገር ጉዳይ ላይ ቢያሳትፏቸው ይላሉም። ምክንያቱም እነዚህ አካላት ከተገፉ እምነት የሌለው ትውልድ ይፈጠራል። ይህ ደግሞ ለሰውም ለአገርም እጅግ ፈታኝ ነው። መንግሥት ይህንን እንዲያስብበት አደራ ይላሉ።
የሽብር ቡድኑ ለትግራይ ሕዝብ እሳት ጭሮ እሳት ጭኖ ወስዶለታል። ይህንን ተገንዝቦም መፍትሔ መስጠት አለበት የሚሉት ባለታሪካችን፤ ምዕራባውያን በቀጥታ መጥተው ሞክረውን ነበር። ነገር ግን አልቻሉንም። አሁን በስውር መጥተው ክፍተታችንን አይተው ነውና እያጠቁን ያሉት በቀደመ ማንነታችን መመከት ከቻልን እናሸንፋቸዋለን። በእምነትም፣ በጉልበትም መመከት የምንችል መሆናችንን ደግሞ አሁን እያሳየን ነው። ግን ማጠንከርና እርስ በእርስ መደጋገፍ አለብን፤ ማዕከላዊነት ለሁሉም ሰው ይበጃልም ሲሉ ይመክራሉ። በንግግራችን ወቅት ብዙዎቹ ሀሳቦቻቸው አንድነትን የሚሰብኩ ነበሩና እንደ እርሳቸው አይነት ታላቅ አባትን ያብዛልን ሳንል አንሰናበትምና ይህንን ተመኘን። ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥር 1 / 2014