በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ የዘንድሮው ገና በብዙ ምክንያቶች የተለየ ቢሆንም ዋና ዋናዎችን ላነሳሳ ። ገና በተነሳ ቁጥር አብረው የሚነሱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሕልውና ከአንድም ሁለት ጊዜ በአሸባሪው ሕወሓት ከተደቀነባቸው አደጋ በተዓምር ተርፈው ፤ ከውጭም ከአገሪቱ አራቱ ማዕዘናት ከመጡ ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት”ኩሉ ቤዛ !” እያሉ መከበሩ ልዩ የሚያደርገው የመጀመሪያው ምክንያት ነው ።
ሁለተኛው አገሪቱ ዳግም ከሕወሓት የአፈናና የጭቆና ቀንበር እንዲሁም ከመበታተን ተርፋ የሚከበር መሆኑ ፤ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የተደረገላቸውን ታላቅ ጥሪ ተቀብለው በአጭር ጊዜ ወደ አገር ቤት በመምጣት የሚከበር መሆኑ የዘንድሮውን ገና ልዩ የሚያደርገው ሌላው ምክንያት ነው ።
በአሜሪካ የሚመሩ ምዕራባውያን ባቀነባበሩት ሟርትና ሽብር የውጭ አገር ዜጎች ከአዲስ አበባ በለቀቁበት ማግስት ይሄን ያህል ኢትዮጵያዊ ወደ አገሩ ተመልሶ መከበሩ ምንጊዜም ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል ። ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ሊባል በሚችል ደረጃ አንድነታቸውን አድሰው ያለልዩነት ከአገራቸውና ከሕዝባቸው ጎን በኢትዮጵያዊነት መሰለፋቸው ሌላው ክስተት ነው ።
ላለፉት 47 ዓመታት ሲቀነቀን በኖረው የጥላቻና የልዩነት ፖለቲካ የተነሳ በኢትዮጵያውያን መሐከል ተገንብቶ የነበረው የባቢሎን የጥል ግድግዳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይሮ በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘው በአንድ ድምጽ እምቢ ለአገሬ ፤ እምቢ ለሕዝቤና ለወገኔ ያሉበት መሆኑ የዛሬውን ገና ልዩ ያደርገዋል ።
በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ለተጎዱ የአፋርና የአማራ ወገኖቻቸው እርዳታ መለገሳቸው ፤ ለጀግናው ሠራዊታቸው የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ማድረጋቸው የዘንድሮውን ገና ልዩ ያደርገዋል ። የጦርነቱ አካል የሆነውን የትይዩ ገበያ አሻጥር በጣጥሰው ዶላር ፣ ዩሮ ፣ ፓውንድ ፣ ወዘተረፈ በሕጋዊ መንገድ መመንዘራቸውና ያልመጡትም በሕጋዊ መንገድ መላካቸው ፤ የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም ለማስታወቅ ፤ የተከፈተባትን የዲፕሎማሲና የሚዲያ ዘመቻ ለመመከት ፤ በአደባባይ ሰልፍ በማድረግ ፣ በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎች ዘርፎች ከኤርትራ እህት ወንድሞቻቸውና ከሌላ አገር ዜጎች ጋር በመቀናጀት #በቃ ወይም #No More የሚል ዓለማቀፍ ንቅናቄ በመፍጠር ጠላቶቻችንን ዳር እስከዳር ያስደነገጠ ግልጽ መልዕክት አስተላልፈዋል ። ለዚህ ነው የዘንድሮው ገና ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያዊ ያሸነፉበት ነው ያልሁት።
ገና ወይም በዓለ ልደት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 ፣ በየአራት አመቱ ደግሞ ታህሳስ 28 ቀን የሚከበር ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓል ነው ። ገና እየሱስ ክርስቶስ የአዳምን ዘር ሁሉ ለማዳን ከሰማይ ሰማያት ወርዶ በመንፈስ ቅዱስ ከድንግል ማሪያም በበጎች ግርግም የተወለደበት ልደት የሚዘከርበት ዕለት ነው ። ለዚህ ነው የበዓላት ሁሉ በዓል ተደርጎ የሚወሰደው ። የገና ስርወ-ቃል ( መነሻ )የበዓሉ ሁሉ ንጉሥ ፣ ታላቅና ገናናነት ከሚገልጸው “ ገናና « ከሚለው ቃል የሚመዘዝ ነው ። እየሱስ ክርስቶስ በይሁዳ ቤተልሔም ሲወለደ ከነገሥታቱና ከመሳፍንቱ ከእነ ሔሮድሰ ተሰውሮ ለእረኞች ተገልጧል ።
እረኞችም ከመልአክት ጋር “ ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት …” ሲሉ ለክብሩ ዘምረዋል ። አዋቂዎቹ ሰብዓ ሰገሎች የከበረ ስጦታ ይዘው በቤተመንግሥት ሲፈልጉት በበጎች ግርግም ነበር የተገኘው ። እነዚህ ተምሳሌቶች እየሱስ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድርጎ በእግዚአብሔርና በሰው ልጅ መካከል ቆሞ የነበረውን የጥል ግድግዳ ለማፍረስ ፤ እርቅን ሰላምን ለማውረድ መምጣቱን ያበስራል ።
ዳሩ ግን ገናን በየዓመቱ በተለያየ መንገድ ከማክበር ባሻገር ብዙዎቻችን በዕለት ተዕለት ኑሮአችን አልተገበርነውም ። አልተረጎምነውም ።ገናን ለ2014 ዓመታት ጊዜ ስናከብረው ፍቅሩንና ሰላሙን ልብ አላልነውም ። አልኖርነውም ። ገናን ከቅርጫው ፣ ከስጦታው ፣ ከዳቦው ፣ ከድግሱና ሸቀጥ ከመለዋወጥ ባሻገር የልደቱን አቢይ ዓላማ አልኖርነውም ።
በተለይ ካለፈው ዓመት ወዲህ በአሸባሪው ሕወሓት ፤ በቡችሎቹ በኦነግ ሸኔ ፣ በጉሙዝ ፣ በቅማንት ፣ በአገው ሸንጎ እና በጋምቤላ ታጣቂዎች በአገራችን የተከሰተው ቀውስ ፣ ጭፍጨፋና የመረረ ጥላቻ ይሄን የሚያረጋግጥ ነው ። በተለይ የአሸባሪው ሕወሓት አብዛኛዎቹ ታጣቂዎች ማተብ አስረው ፣ መስቀል አድርገውና የጸሎት መጽሐፍ በደረት ኪሳቸው ይዘው የፈጸሙት ለመስማት የሚሰቀጥጥ ፤ ለማየት የሚዘገንን ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ሰቆቃና ግፍ ስንመለከትና ስንሰማ ፤ እውነት እነዚህ ወጣቶች እምነቱን ከሚያጠብቀው ትግራዋይ አብራክ የወጡ ናቸው !? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ አስገድዶናል ።
ትግራዋይስ ከሃይማኖታቸው ፣ ከልቦና ውቅራቸውና ከእሴቶቻቸው እጅግ ያፈገጡ ነውሮችን ባላየ ባልሰማ ከማለፋቸው ባሻገር የዚህ ሁሉ ጥፋት ጠንሳሽ የሆነውን ሕወሓት በቃ ! ለማለት ከዚህ የባሰ ምን ይምጣ ብለው ይጠበቃሉ !? እስኪ በልደት ወይም በገና መስኮት ሌሎችን ባህላዊ ወረቶቻችንና አኳኋን አከራረማችንን እንቃኝ ።
በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የሚከበሩ መንፈሳዊና ባህላዊ ሁነቶች የተሸከሙትን ግዙፍ መልዕክቶችና አንድምታዎች አለፍ አለፍ ብለን እየተመልከትን ሒሳብ እናወራርድ ። ፍቼ ጨምበለላ ፣ ቡሔ ፣ ሻደይ ፣ አሸንዳ ፣ ሶለል አይነ ዋሬ ፣ እንቁጣጣሽ ፣ መስቀል ፣ መስቀላዮ ፣ አጋመ ፣ ጊፋታ ፣ ኢ ሬቻን ፣ ጋሮ ፣ ቺሜሪ ፣ ትንሳኤ ፣ ወዘተ . በአንድም በሌላ በኩል በተለያዩ የአገራችን ማኅበረሰቦች የሚከበሩ ሃይማኖታዊ ወይም ባህላዊ ክዋኔዎች ናቸው ። ሁሉም ማለት ይቻላል ተስፋን ፣ ፍቅርን ፣ ነፃነትን ፣ አብሮነትን ፣ አንድነትን ፣ ምስጋናን ፣ እርቅን ፣ ይቅርታን ፣ እኩልነትን ፣ ወዘተረፈ . የሚያውጁ ፣ የሚለፍፉና የሚሰብኩ ናቸው ። ግን በነቂስ ወጥተን ለዘመናት በየዓመቱ በአደባባይ የምናከብራቸው የምንዘክራቸውን ያህል በዕለት ተዕለት ኑሮአችን አንኖራቸውም ። አንለማመዳቸውም ።
ይሁንና ከገጠሙን ቀውሶች ፣ ፈተናዎች መውጣት ማገገምና ማንሰራራት የቻልነው በቀሩን ሽርፍራፊ እንጥፍጣፊ ባህላዊ ንብረቶቻችን መሆኑን ልብ ይሏል ። ባለፉት 30 ዓመታት ቀን ከሌት እንደ ተሰበከው ልዩነት ፣ ጥላቻና ዘረኝነት ቢሆን ኑሮ እርስ በእርስ ተበላልተናል ። ተጨራርሰናል ። ለዚህ ነው መዳኛችን ፣ ማገገሚያችንና ማንሰራሪያችን የሆነውን ባህላዊ ወረት ወደሙላቱ መመለስ ለነገ ይደር የሚባል ጉዳይ የማይሆነው ።
ባህላዊ ወረታችን ለበጎ ዓላማ ሲውል አገርን ከጥፋትና ከእልቂት እሳት እንደሚታደግ በጋሞ አገር ሽማግሌዎች ተመልክተናል ። የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ ለበቀል ተነስቶ የነበረውን የአርባ ምንጭና የአካባቢውን ወጣት ለምለም ሳር ይዘው ተንበርክከው በመለመን ቁጣውን አብርደው መልሰውታል ።
ይህን የአገር ሽማግሌዎች ገድል በጥሞና ለተረዳው የአርባ ምንጩን እሳት ብቻ አይደለም ያጠፉት የአርባ ምንጩን ጥፋት ተከትሎ በመላ አገሪቱ ሊዛመት የነበረውን የበቀል ሰደድ እሳት ጭምር እንጂ ። ቁጣ አብራጁ ይህ የጋሞ አባቶች ልመና ( ጋሞ ወጋ ) እየጠፋ ፣ ትኩረት እየተነፈገው ያለው ባህላዊ ወረታችን ተጠብቆ ለትውልድ ሲተላለፍ አገርን እንዴት ማዳን እንደሚችል ጥሩ ማሳያ ነው ። የጋሞ አባቶች ከሦሥት አመት በፊት ልዩ የበጎ ሰው ተሸላሚ መሆናቸው በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ያለ አንዳንች ልዩነት ዳር እስከዳር አድናቆትን ተቀባይነትን ያተረፈው በዚህ እሳቤ ነው ።
ሕግን ለማስከበር ከምናደርገው ጅምር ጥረት ባልተናነሰ በየአካባቢው እንደ ጋሞ ወጋ አይነት የሽምግልና ፣ የእርቅ ባህላዊ ወረቶቻቻችንን ላይም መሥራት ይጠበቅብናል ። ከዚህ መሳ ለመሳ የአክራሪነት አዝማሚያ ፣ እኩይ አስተሳሰብ እንዲገታ ብሎም ተሸንፎ ከሰላምና ከእርቅ መንገድ ገለል ፣ ዘወር እንዲል ድልብ የሆኑ ባህላዊ ንብረቶቻችን ጥንስስ ፣ ወረት የማይተካ ሚና አላቸው ።
ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ባህላዊ ወረቶች ባለፀጋ ስለሆኑ የየራሳቸውን መዋጮ ማበርከትና ወደ ሥራ መግባት ይጠበቅባቸዋል ። በየአካባቢያችን ፣ በየቀዬአችን የምናንፀው ፣ የምናቀነቅነው ከባቢያዊ ብሔርተኝነት ወደ አክራሪነት ፣ ፅንፈኝነት የሚያንደረድር ወደገደል አፋፍ የሚገፋ ስለሆነ እነዚህን ባህላዊ ወረቶች በመጠቀም መግታት ያስፈልጋል ። የዜጎች ማንነት እሴት እንደተከበረ ወደ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የሚያደርሰንን ቀና መንገድ በቅንነት መቀላቀል ፣ መያያዝ ይገባል ። ይህ አገራዊ ብሔርተኝነትም ከገደቡ ፣ ከውሃ ልኩ እንዳያልፍ ጥንቃቄ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ ።
አይደለም ዘውጌአዊ ፣ ወንዜአዊ ብሔርተኝነት ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት በአግባቡ ካልተያዘ ፤ የጎረቤቱን የሚጎመጅ ፣ የሚመኝ ፣ የሚመቀኝ ሆኖ የመውጣት አደጋ ስላለው በብልሃት ፣ በማስተዋል ሊቀነቀን ይገባል ። በዚያድባሬ ይመራ የነበረው “ የታላቋ ሶማሊያ “ አክራሪ ብሔርተኝነት ለዚህ ጥሩ አብነት ነው ። ባህላዊ ንብረቶቻችንን እንደ ጦር ዕቃ ለብሶ እንደ ጥሩር ደፍቶ መውጣት መግባት ፣ መመላለስ ለምን ተሳነን ! ? መልሱ ቀላል ነው ። ላይ ላዩን እንከውናቸዋለን እንጂ አንኖራቸውም ።
በቃል እናነበንባቸዋለን እንጂ በልባችን አላተምናቸውም ። ባልንጀራህን ፣ ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ የሚሉ አብርሀማዊ እምነቶችን ማለትም ክርስትናን ፣ እስልምናንና አይሁድን እየተከተልን እንዴት በጥል ግድግዳ ተለያየን ! ? በአንድ አምላክ በዋቄ ፈና እያመን ኢ ሬቻን በየዓመቱ እያከበርን እየከወን ይቅር መባባል ለምን ተሳነን !? መልሱን ለማግኘት ምስጢሩን ለማወቅ ሞራ ማስገለጥ ወይም ኮከብ ማስቆጠር አያሻም ። መልሱ ቀላል ነው ። እሱም ባህላዊ ንብረቶቻችንን በሳጥን ቆልፈን እንደ ክት ልብስ በየዓመቱ በዓል ለማክበር ስለምናወጣቸው ነው ። እናከብራቸዋለንን እንጂ ሥራ ላይ ስላላዋልናቸው ( ኢንቨስት ) ስላላደረግናቸው ነው ። አገራዊ ሰላምና አንድነት እውን ለማድረግ የተቆለፈባቸውን ባህላዊ ንብረቶች ከሳጥን አውጥቶ እያንዳንዱን ዜጋ በፍጥነት ማልበስን ይጠይቃል ።
እንደ ገና ስጦታ
ባህላዊ ወረታችን ቱባነቱን እንደጠበቀ ማደግ ዘመንና ትውልድ መዋጀት ይጠበቅበታል ። አዎ ! የትውልዱንና የዘመኑን ህፀፅ የሚያርም ለምፅ የሚያነጻ ፣ የሚዋጅ መሆን አለበት ። ዘረኝነትን ፣ ጥላቻን ፣ ቂም በቀልን ፣ ደባን ፣ መከፋፈልን ፣ ወዘተ . መቤዥ ፣ መዋጀት አለበት ። ባህላዊ ንብረታችንን ይበልጥ በማጎልበት ፣ በማልማትና በማስፋት ለመጻኢ እድላችን ፣ ለነገ ተስፋችን ፣ ለእርቅ ፣ ለሰላም ፣ ለአንድነት ፣ ለሁለንተናዊ ብልፅግና ፣ ወዘተረፈ ልናውለው ይገባል ።
ስኬቶቻችንን የምናወድስበት ፣ ፈተናዎቻችንን የምንሻገርበት ነገአችንን የምንተልምበት ጭምር አድርጎ ስለመጠቀም አብክረን ማሰብ ያስፈልጋል ። የፍቅር ፣ የእርቅ ፣ የሰላም ፣ የአብሮነት ፣ የማካፈል ፣ የመተባበር ፣ የመተጋገዝ ፣ የመረዳዳት ፣ የምስጋና ፣ ወዘተረፈ . ባህሎች ፣ ልማዶች ፣ ዕምነቶች ፣ ሃይማኖቶች ከፍ ሲልም ድምር ባህላዊ ንብረቶች ባለቤት እንዲሁም የጥንታዊት አገር ባለቤት ሆነን አንድነትን በመከፋፈል ከሰዋን ፣ ፍቅር ከጎደለን ፣ እርቅ ከገፋን ፣ ሰላም ከራቀን ፣ አብሮነትን በቀዬአዊት ከተካን ፣ ማካፈልን በስስት ከቀየርን ፣ መተባበርን በመለያየት ከለወጥን ፣ ምስጋናን በእርግማን ከተካን ፣ ወዘተረፈ . ምኑን ሙሉዕ ሆነው !።
ባለፉት ሦሥት ዓመታት ያለፍንባቸው አገራዊ ውጣ ውረዶች ፣ አሳፋሪ ድርጊቶች እውነት የእነዚህ ሁሉ መንፈሳዊና ባህላዊ ፀጋዎች ባለቤት ስለመሆናችን የሚመሰክሩ ናቸው !? ከሀዲው ትህነግ በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው አሰቃቂ ግፍና ክህደት ፤ በማይካድራ ሳምሬ በተባለ የትህነግ ገዳይ የወጣት ቡድን በአማራ ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ ፤ ባለፉት አምስት ወራት በወረራ በያዛቸው የአፋርና የአማራ ክልሎች ተሰምቶም ታይቶም የማይታወቅ ግፍ ዘረፋና ውድመት ፤ በመተከል በተደጋጋሚ በዚሁ ማኅበረሰብ ላይ የፈጸመው አረመኔያዊ ግፍ ፤ ሸኔ_ኦነግ በኦሮሞና በሌሎች ማኅበረሰቦች ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ ፤ የአርቲስት ሀጫሉን ሞት ተከትሎ የተስተዋለው አውሬነት ፤ በመሐላችን እየጎነቆለ ያለ ጥላቻ ፣ ቂም በቀል ፣ ልዩነት ፣ ጎሰኝነት ፣ ወዘተረፈ በአብነት ስንመለከት የደለበ ባህላዊ ወረቶች ባለቤት ካለው ሕዝብና ታሪክ የሚጠበቅ አይደለም ። ስለዚህ ገናንም ከገና ባሻገር ሌሎች ባህላዊ ወረቶቻችንም በዕለት ተዕለት ኑሮአችን ልንኖራቸው ልንገልጣቸው ይገባል ።
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ! አሜን
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥር 1 / 2014