‹‹ እገሊት በሠላም ተገላገለች?›› ከሚለው ጥያቄ ጎን ለጎን መቼም የማይቀረው ምን ወለደች? መባባል ነው። ምላሹ ወንድ ከሆነ ታዲያ በ‹‹ጎሽ ጎሽ…›› ይደመደማል። በተቃራኒው ሴት ከሆነች ‹‹ትሁን›› ይባላል። ይሄ ከቦታ ቦታ ይለያይ እንጂ በተለያዩ ድርጊቶችና አባባሎች በሁሉም ቦታ ይገለጻል።
በአንዳንድ አካባቢ ወንድ ሲወለድ ጥይት እስከ መተኮስም ይደርሳል። የሴቶችን የበታችነት መስበክ የሚጀምሩት እንዲህ ትንንሽ የሚመስሉ ነገር ግን በነገ የልጆች ሕይወት ላይ መጥፎ አሻራን የሚጥሉ አመለካከቶች እኩልነትን በሚዘምሩ ግለሰቦች ጭምር ሲተገበሩ ቆይተዋል።
በእዚህ መልኩ የተጀመረው ልዩነት ልጆች አደግ ሲሉ በሚገዛላቸው የመጫወቻ ቁሳቁስም ይታገዛል። ለወንዱ ሽጉጥና አውሮፕላን በመግዛት መግደልም ሆነ ያሻውን ማድረግ እንደሚችል፤ አውሮፕላን ነቃቅሎ መገጣጠምም ሆነ ማብረር የሱ መሆኑን በቁስ ተደግፎ እየተነገረው ያድጋል። በሌላ በኩል ለሴቷ አሻንጉሊት በመስጠት እንዲሁም ወጥ እና እንጀራ እየሰራች እንድትጫወት ይደረጋል። በዚህም ሴት ልጅ በማጀትና ልጅ ከማሳደግ የእናትነት ሚና የዘለለ አስተዋፅዖ እንደሌላት እያሰበች ታድጋለች። የሴቶችን የበታችነት የሚያጎሉ አባባሎችም እንዲሁ በሰፊው ይነገራሉ።
ከዚህ ወጣ ብለው የተሳካላቸው ሴቶች ደግሞ «ወንድ ነሽ » ትባላለች። ይህም ‹‹ሴት በመሆንሽ ምንም ማድረግ አትችይም ነገር ግን አቅምሽ ሲጎለብት ወንድ የሚለውን የትልቅና የመቻል መጠሪያ ትጎናፀፊያለሽ›› እንደማለት ይሆናል። በማሕበረሰቡ ውስጥ የተገነባውን ይህን መሰል ከባድ አመለካከት ሰብረው በመውጣት ድልን መቀዳጀት ታዲያ ፈታኝ እንደሚሆን አያጠራጥርም።
ነገር ግን አገሪቱ አሉኝ ብላ የምትኮራባቸው ውጤታማ እንስቶች እንዳሉም አይካድም። በአፋር ክልል በርሀሌ በምትባል ወረዳ ተወልደው ዕድገታቸውን በአሰብ ያደረጉት በአፍሪካ ሁለተኛዋ በአገሪቱ ደግሞ የመጀመሪዋ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር ዓይሻ ሙሀመድ ተጠቃሽ ናቸው። እኛም በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ አልፈው ለትልቅ ኃላፊነት ከታጩት ፈገግታ ከማይለያቸው ሚኒስትር ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- እንደሌሎቹ አካባቢዎች ሁሉ እርስዎ ከመጡበት አካባቢም ሴቶች ከፍተኛ ባህላዊ ጫናዎች ስላሉባቸው ያንን ጫና አልፈው እንዴት ለዚህ ደረጃ በቁ ?
ኢንጂነር ዓይሻ፡- እኔም በዛው ጫና ውስጥ ነው ያለፍኩት። በጫናው ምክንያትም የዩኒቨርሲቲ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሆኜ እንዳገባ ተደርጌያለሁ። ከዛም ሦስት ልጆችን አፍርቻለሁ። ምንም እንኳ የወለድኩት ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ቢሆንም ሴቶችን የማስተማር ባህሉ ግን ገና ብዙ የሚቀረው እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። የትምህርትን ጥቅም አውቆ ልጆቹን ወደ ትምህርት ገበታ ሊልክ የሚችለው ቤተሰቡ ቅድሚያ ሲማር ነው። አርአያ የሚደረግ ሰው ስለማይኖር ለትምህርት የሚሰጠው ትኩረትም እምብዛም ነው። እኔ ግን ወላጆቼ ተምሬ ትልቅ ደረጃ እንድደርስ ጉጉትና ፍላጎት ስለነበራቸው ባህላዊ ጫናውን አልፌ እዚህ ደረጃ እንድደርስ አግዘውኛል።
አሁን የደረስኩበት ደረጃ እደርሳለሁ በሚል ባልማርም ቀድሞ ግን በኬሚካል ምህንድስና ዘርፉ መሰማራት እፈልግ ነበር። በዘርፉ የምርምር ሥራዎችን መሥራት ትልቁ ሕልሜ ነበረ፤ የሕይወት ጎዳና ባልታሰበ መንገድ መራኝና አጋጣሚ ሆኖ የሲቪል ምህንድስና አጠናሁ። ወደ ትምህርት ስገባ ጥሩ ሆኖ ባገኘውም አሁንም ግን በውስጤ የኬሚካል ምህንድስና ፍቅር አለቀቀኝም። በፖለቲካው ዓለም ተሳትፌ እዚህ ደረጃ እደርሳለሁ የሚል ሃሳብም አልነበረኝም። በቡድን ሥራና በውጤት ግን አምናለሁ። ከሰዎች ጋር መሥራትን እጅጉን እምፈልገውና የምደሰትበት ነው። በትዕዛዝ ስለማላምን አላዝም።
ሰርቶ በማሰራት የማምን ሰው ነኝ። አብሮ በመሥራት ስለማምንም ውጤቱ ከመጣ ማንም ይስራው ማን አያስከፋኝም። የእኔ ሥራ ነበርና አልፎኝ ሄደ ብዬም አልቆጭም። በቡድናዊ ሥራ ተግባብቶ አብሮ በመሥራት በጣም አምናለሁ። ከመታዘዙ በፊት ሰው ማመን አለበት። ይህም አንዱ የአመራር ጥበብ ነው። ሚኒስትር መሆንና አንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ ተመርጦ መቀመጥም የመጨረሻው ስኬት ነው ብዬ አላምንም።
በራሱ ጊዜ የሚመጣ ነው። ሲመጣ ግን የተሰጠን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ግዴታም መሆኑን መገንዘብ ይገባል። እኔም ይህንኑ ለመወጣት እጥራለሁ እንጂ ተሳክቶልኛል ብዬ እጄን አጣጥፌ አልቀመጥም። ለኃላፊነቱ ስታጭም በአግባቡ ሕዝብ በሚፈልገውና ተጠቃሚነቱ የሚረጋገጥበትን መንገድ ቀይሶ ለመፈፀም መሥራት ግዴታ በመሆኑም ይህን ለመወጣት እጥራለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንፃር በልጅነትዎ የነበርዎት ፖለቲካዊ ተሳትፎ ምን ይመስል እንደነበር ያስታውሱን?
ኢንጂነር ዓይሻ፡- በጣም ጠያቂ በመሆኔ ነገሮች ካላሳመኑኝ መራመድ አልችልም ነበር። ነገሮች ለምን ሆኑ? ምንስ ጥቅም አላቸው? በሚል ሳላመዛዝንና ሳልሞግት የምተገብረው አንዳችነገርም የለም። ይህም በውስጤ የፖለቲካ ስሜት እንዳለ አመላካች ይሆናል። በተለይ ደግሞ መብትና ግዴታን ለማወቅ አደርግ የነበረው ጥረት ከፍተኛ ነው። ሕዝብን እንደ ሕዝብ በቡድን ደረጃ የሚደረጉ ጅምላዊ ፍረጃዎችና ማናቸውም ተያያዥ ድርጊቶች አልደግፍም።
በግሌ ምንም ብባል ብዙም ቅር ባልሰኝም በቡድን ደረጃ ሌሎችን ማጥቃትም ሆነ ስጠቃም የማልቀበለውና የሚረብሸኝ ድርጊት ነው። የሰው ግለሰባዊ መብቶች ተከብረው ቡድናዊ መብቶች መከበር እንዳለባቸውም አምናለሁ። በግል መጥፎም ሆነ ጥሩ ሰዎች በመኖራቸው የትኛውም ማህበረሰብ በቡድን ስያሜ ሊሰ ጣቸው አይገባም። ከዚህ ጋር ተያይዞ በሰፊው የሚስተዋለው «ሴቶች እንዲህ ናቸው» በሚል ፍረጃ ውስጥ ሲገባ ነው። ይህም በጣም የሚያመኝ ጉዳይ ነው።
ስለዚህ ሴቶች አመለካከቱን ለመቀየርም ያላቸው ብቸኛ አማራጭ በሥራ ቦታ የሚሰጣቸው ኃላፊነት በብቃት መወጣት ነው። አስተሳሰቡን ትክክል እንዳልሆነ ማሳየት የሚቻለው ምናልባትም በፖለቲካ ውስጥ ተገብቶ ሊሆን ይችላል። ለእኔ የገጠመኝ ዕድል በፖለቲካ ውስጥ ሆኖ ይህንን ኃላፊነት መወጣት ነው። በልጅነቴ ግን ያን ያክል በፖለቲካ ውስጥ ገብቶ መሳተፍ ብዙም ፍላጎት አልነበረኝም። አልሜውም አላውቅም ነበር። ከሆነ ደግሞ በዛ ውስጥ ብቁ ሆኖ መገኘት እንደሚገባኝ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- መጀመሪያ ወደ ፖለቲካ ሕይወት የገቡበትን አጋጣሚ ያስታውሱት ይሆን?
ኢንጂነር ዓይሻ፡- በአፋር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶች ድምጻቸው በተደራጀ አግባብ እንዲሰማ ሊደራጁ ይገባል የሚል እንቅስቃሴ ይደረግ ነበር። ማህበርም ተቋቋመ። ማህበሩን ወክዬ የድርጅቱ ጉባዔ ላይ ተሳተፍኩ። በወቅቱም ተሳታፊዎች የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንድሆን ሲጠይቁ የድርጅቱ አባል አለመሆኔ ተነገረኝ። ይህም በጣም ስለረበሸኝ በሚቀጥለው ቀን ገና ከዕንቅልፌ ስነሳ ወደቢሮ በማቅናት የድርጅት አባል ሆንኩኝ። በኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩት አካላት ለአፋር ሴቶች አስተዋፅዖ ማበርከት የሚቻለው በዚህ መንገድ መሆን አለበት የሚል አካሄድ ነበር የተጠቀሙት። እኔም መልፋቴ ካልቀረ ለምን አባል ሆኜ ትግል አላደርግም? ትክክለኛው መንገድ ይህ ከሆነ በሚል ወደ ፖለቲካው ዓለም ልገባ ችያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከገቡስ በኋላ እንዴት አገኙት?
ኢንጂነር ዓይሻ፡- ወደ ፖለቲካው ከገባሁ በኋላ ወደ አመራርነት ለመምጣት ሦስት ዓመት መጠበቅ ነበረብኝ። በሌላ በኩል በማህበሩ ላይ ግን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲቀሩ፣ ሴቶች ወደፊት እንዲመጡ፣ የአፋር እናትና አባቶች ሴት ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ አርአያ የሚሆኑ ሰዎች መፈጠር እንዳለባቸው የተለያዩ የንቅናቄ ሥራዎችን እንሰራ ነበር። በአርብቶ አደር አካባቢ ሰርቶ ማሳየትና ሆኖ መገኘት መቻልን ለማሳየት ትልቅ ሚና አለው።
በዚህም በተለያየ መንገድ የሚስተዋሉ ኋላቀር አመለካከቶችን እንዲሁም ባህላዊ ተፅዕኖዎችን መወጣት እንደሚቻል ዘርፈ ብዙ ሥራ ይሰራ ነበር። ቀስ በቀስም ሴቶች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውና ውሳኔ ሰጪነት ላይ ያላቸው ሚና እየጨመረ መጣ። ተሳትፎው እንዳለ ሆኖ በአፋር ውስጥ ታጋይ ሴቶችም ይገኛሉ። በጣም ብዙ ዕድሉን ያላገኙ በጣም ጠንካራና ሁኔታው ቢመቻችላቸው ስኬታማ ሊሆኑ የሚችሉ ሴቶች ከክልሉ አልፎ በመላው የአገሪቱ ክፍሎች እንደሚገኙም ይታወቃል።
ውሳኔ ሰጪነት ደረጃ እንዲደርሱ ግን የይቻላልን መንፈስ ለማምጣት በወንዶች በከፍተኛ ደረጃ በቁጥጥር ሥር ያለው የተለያየ የኃላፊነት ቦታ እንዲቀር ለማድረግ ብዙ ሙከራ አድርገናል። ሴት ልጅ ዕድሉን ብታገኝ ብዙ ሥራ ልትሰራ ትችላለች። በሥራ ላይ የሚያጋጥም የሴት ልጅ ውድቀት ትርጓሜውም ብዙ ነው። ሴት ልጅ ስህተት እንደትፈፅም በማህበረሰቡ ውስጥ የተገነባው አመለካከት አይፈቀድላትም። ይህን እያሰቡ መሥራትም ይገባል። ምንም እንኳ ከቀድሞ የተሻለ ምቹ ሁኔታ እንዳለ ባይካድም አሁንም ከሚስተዋሉ ችግሮች አንዱ የሆነው ይኸው ነው።
በመሆኑም አንዳንዴ የበላይ የሥራ ኃላፊዎችን ከመጠበቅ ይልቅ በኋላ በሥራ ላይ የሚፈጠር ስህተት ሊኖር እንደሚችል አምኖ መሥራት እንደሚገባም በቆይታዬ ተረድቻለሁ። አገርን ለችግር የሚዳርግ እስካልሆነ የሚመጣውን በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ ሆኖ በኃላፊነት መሥራት እንደሚገባ ሌሎች ሴቶችም መገንዘብ ይገባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ሴቶች በከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ላይ ሲቀመጡ በብዛት አይታይም። ለችግሩም መፍትሔ ለማበጀት ምንጭ መለየት ይገባልና የችግሩ መነሻ ምክንያቶች ምንድን ናቸው ይላሉ?
ኢንጂነር ዓይሻ፡- የመጀመሪያው ሴቶች ለራሳቸው የሚሰጡት ቦታ ነው። ሁሉም የሰው ልጅ ነው በተቀመጡበት ኃላፊነት ቦታ ላይም የመምራትን ሚና መጫወት ነው የሚጠበቅበት። በዚህ ውስጥም ጥበብን መጨመር ይጠይቃል። ለጥበበኝነት ደግሞ ሴቶች ዓይነተኛ ማሳያ እንደሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ሴቶች ተፈጥሮ የቸረቻቸው በመሆኑም በአመራር ቦታ ላይ ቢቀመጡ በብቃት መወጣት እንደሚችሉ ማመን ይኖርባቸዋል። በዚህ ውስጥ ግን ክፍተቶች ያሉባቸው ሴቶች አይኖሩም ማለት እንዳልሆነም ማወቅ ይገባል።
ባህሉና ሐይማኖቱ ለሴቶች የሰጠውን ቦታ ለራሳችን አልሰጠንም እንጂ ይህን በአግባቡ ጠብቀን ብንሄድ ለሴቶች የሚሰጠው ቦታ እንዲህ አይሆንም ነበር። ለአብነት በአፋር አካባቢ ለሴት ልጅ ትልቅ ክብር ይሰጣል። በትዳር ውስጥ የሚያፈሩት ሃብት የሴቷ ነው። ቤቱ የራሷ በመሆኑም በትዳር ውስጥ መስማማት አቅቷቸው ፍቺ ቢፈፅሙ ወንዱ እንጂ ሴቷ አትወጣም። ጥቃት ሲደርስም ተመሳሳይ ነው። አንድ ሴት ልጅ የገደለ ሁለት ወንዶችን እንደገደለ ስለሚቆጠር ትልቅ ወንጀል ተደርጎ ይወሰዳል።
እንዲሁም አለመግባባት እንኳ ቢፈጠር ደብድቦ አጥንቷን መስበር የተከለከለ ሲሆን፤ ይህን አድርጎ የተገኘም ለቅጣቱ የሚጣልበት ካሳ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ባህላዊ እሴቶችን ከዘመናዊ ጋር አቀናጅቶ መፈፀም ይገባል። ወላጆች ወንድና ሴት ልጆችን የሚያሳድጉበት መንገድ ሌላኛው ለችግሮቹ መነሻ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በተለምዶ ለወንድና ለሴት ልጆች የሚሰጠው ቦታ አለ። እኛም ትክክል እንዳልሆነ እያወቅን እንኳ ልጆቻችንን ‹‹አንቺ ሴት አይደለሽ›› እንላለን። አብሮን ያደገና እኛም በባህሉ ውስጥ ያለፍን በመሆናችን አውቀንም ይሁን ሳናውቀው በምናደርጋቸው ተግባራት የምንፈጥራቸው ችግሮችም እንደ አንድ ተግዳሮት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ወኔም ያንሰናል። ጥቃቅን የሴት ልጅ ስህተቶች እንደ ስህተት ሳይሆን እንደ ውድቀት ነው የሚታዩት። ሁሉም ሰው ሲሰራ እንደሚሳሳት ቢታወቅም ሴቷ ስትሳሳት ግን ተሳሳተች ሳይሆን ‹‹አትችልም፣ አጠፋች፣ ወደቀች›› የሚል ተቀጽላ ስሞች ይሰጣታል። በዚህም ሴቶች ሊመጣ የሚችለውን ውድቀትም ሆነ ስኬት በኃላፊነት ወስዶ ሥራውን ከመሥራት ይልቅ ወደኋላ ማፈግፈግን ምርጫቸው ሲያደርጉ ይስተዋላል።
በዚህ ላይ ደግሞ የቤት ውስጥ፣ የባህልና ዕድሉን ያለማግኘትም ችግሮች ሕይወቷን ያከብዱባታል። እኛ ለእኛ ከምንሰጠው የተሳሳተ ግምት የሚጀምረው ችግር በማህበረሰቡ ላይም በሰፊው ሲንፀባረቅ ይስተዋላል። ይህም በኢትዮጵያ ብቻ ያለ ችግር ሳይሆን አደጉ ከስልጣኔ ማማ ደረሱ በሚባሉ አገራትም የሚስተዋል ነው። ለዚህም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተቀናቃኛቸው የነበሩትን ሂላሪ ክሊንተን በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅታቸው እንዴት ያደርጓቸው እንደነበር የዓለም ሕዝብ የተመለከተው ዕውነት አንድ ማሳያ ይሆናል።
ከዚህ አንፃር በአገሪቱ የሚታየው ለውጥ እንደውም የተሻለ ሁኔታ እንዳለ ያመላክታል። በአሁኑ ወቅት ያለው ጅማሮ መልካም ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውስጥ ግማሽ በመቶ የሚሆነው የሴቶች ተሳትፎ በመሆኑ በዚህ ደረጃ ከፊት ያለን ሴቶች ከኛ የተሻሉ ሴቶች እንዳሉ ተገንዝበን ‹‹ለካ ማድረግ እችላለሁ›› የሚል አስተሳሰብ በወጣት ሴቶች ላይ እንዲፈጠር የተሰጠንን ተልዕኮ በአግባቡ ለመወጣት መጣር ይኖርብናል።
የአገሪቱ ውድቀትና ስኬት የሚለካባቸው ቁልፍ ዘርፎች የሚመሩት በሴቶች ነው። ይህም ለእኛ ለሴቶች ፈታኝ ወቅት ነው። ሕዝቡ ያለውን አመለካከት እንዲቀይር አልያም ‹‹አይችሉም ብለን ነበር›› እንዲል ያደርገዋል። በመሆኑም በሥራ አሸንፈን በመውጣት ለሴቶች አርአያ መሆን ይጠበቅብናል። ካልሆነ ግን ‹‹አይችሉም›› የሚባለው ዕውነት ነው የሚል አስተሳሰብን ያስቀጥላልና ትልቅ ኃላፊነት አለብን።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የታዩት መልካም ጅማሮዎች አበረታች እንደሆኑ አይካድም። በሌሎች ሴቶች ዘንድ የሚፈጥረው መነሳሳት ምን ያክል ነው? እርስዎስ በዚህ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የተጠቀሱትን ችግሮች ለማቃለል ምን ለማድረግ አስበዋል?
ኢንጂነር ዓይሻ፡- በተቋማቱ ውጤት ለማስመዝገብ እየሰራን ነው። የቆዩ ችግሮችን ለማቃለል የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችም ይኖራሉ። ነገር ግን በተቻለ መጠን ስኬት ለማስመዝገብ እየሰሩ እንደሆነ እየታየ ነው። ኃላፊነቱ የተሰጠን ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ የአገሪቱን ሕዝብ የመምራት በመሆኑም ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ነው የምናገለግለው። ለሴቶች ብቻ ለይተን የምንሰራው ሥራ አይኖርም። ለአብነት በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ያሉ ሴቶች ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በርከት ያሉ ችግሮች ሊገጥማቸው ይችላል።
በመሆኑም የወደፊት ራዕይ እንዲኖራቸው ድጋፍ ይደረጋል። በግዳጅ አፈፃፀም ላይ ምንም ዓይነት ችግር የለባቸውም። ነገር ግን የሚያጋጥማቸው ፆታዊ ፈተናዎችና ሌሎችም ችግሮች ይኖራሉ። በመሆኑም ትልቅ ደረጃ የደረሱ ሴት የሠራዊት አባላት በማምጣትና የአሰራር ማነቆዎች ካሉ እነርሱን በማስወገድ በተለያዩ የሰላም ማስከበርና ግዳጆች ላይ የመሪነት ሚና እንዲጫወቱ የማብቃት ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል። በሚኒስቴሩ የሴቶች ጉዳይ የሚል ዘርፍም አለ። ጥቃቅን የሆኑ መፈታት የሚገባቸው ችግሮች እንዳሉም አስተውላለሁ።
በተለይ ደግሞ በሥነተዋልዶና በሥነጤና ዙሪያ ማህበራዊ ፆታዎች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች አሉ። በዚህም ላይ ወንዶች ሊያግዙ ይገባል። በአሰራር፣ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ፣ መስፈርቱን ለሴቶች የተለየ ማድረግ እንዲሁም ከገቡ በኋላ እንዳይፈተኑ ስልጠና ላይ መሠራት እንዳለበት የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር ውይይት እየተደረገ ይገኛል። የዓለም የሰላም ማስከበር ላይ ምክትል ኃይል ኮማንደር ኢትዮጵያ ልካለች። ይህንን በመያዝ ዋና ኃላፊ እንድትሆን ለማድረግ መሥራት ይገባል። በአሁኑ ወቅት በተፈጠረው አጋጣሚ ደግሞ ሴቶች ተቋሙን በመኮንነት ደረጃ እንዲቀላቀሉ በማድረግ ይሰራል። ምደባዎችም ላይ ፆታን ያማከለ እንዲሆንና አቅም ካለ ቅድሚያ እንዲሰጥ በሚል መርህ እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ወጥተው እርስዎ ለመጀመሪያ ጊዜ የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሹመት ሲሰጥዎት የተሰማዎትን ስሜት እስኪ ያስታውሱን?
ኢንጂነር ዓይሻ፡- ለምን? እና እንዴት? የሚሉ ጥያቄዎችን በውስጤ ያጫረ ወቅት ነበር። በኋላ ግን የመንግሥት አደራና ኃላፊነት ነው ወደሚል ሃሳብ መኬዱ አይቀሬ ይሆናል። የመሪነት ሚና በየትኛውም ተቋም ያለና ተመሳሳይ በመሆኑ ‹‹እችለዋለሁ? ወይስ ያዳግተኝ ይሆን? ባያስብልም እንኳ የአገሪቱን መከላከያ ሚኒስቴር መምራት ማለት አገርን መምራት በመሆኑ የዚህ ግዙፍ ተቋም መሪ መሆን ድንጋጤን ይፈጥራል።
ተልዕኮው ከባድ ነው። ይሁን እንጂ በሕግና በስርዓት የሚመራ፣ አመራሩም ሆነ ሠራተኛው ሥራውን ተረድቶ በአግባቡ ማስኬድ የሚችል፣ የራሱ የሆነ የሥራ ፍሰት ያለው እንዲሁም በቢሮ ውስጥ ተገኝቶ ሥራ ከመሥራት ባሻገር ሕይወቱን ለመስጠት የተዘጋጀ ኃይል መሆኑ ተልዕኮውን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችል መልካም አጋጣሚ ተደርጎ ይወሰዳል። ወታደራዊ ዲፕሎማሲው ከፍተኛ በመሆኑ ሌላኛው ውጪ ጉዳይ ተደርጎ በሚወሰደው በዚህ ግዙፍ ተቋም ሴት በመሪነት ማስቀመጥ ሆኖ አያውቅም።
ችግሮች ፈር መያዝና መፍትሔ የመጀመሪያው በር ይኸው ተቋም ነው። በዚህም የተቋሙ ኃላፊ በሚል ሹመት ሲሰጠኝ ለመጀመሪያ ጊዜ በፈጠረብኝ ድንጋጤ የተነሳ ለተወሰኑ ቀናት ተረጋግቼ ነበር ወደ ተቋሙ ያቀናሁት። ሌላ ተቋም ላይ ምደባ ቢደረግ ያን ያክል ብዙ ክብደት ኖሮት ባይታይም የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ተደርጎ መሾም ግን ትልቅ ኃላፊነት ነው። የኋላ ኋላም ወደ ውስጥ ሲገባ ለጥያቄዎቼ ሁሉ ምላሽ አግኝቼ አገርን ለማገልገል ከዚህ የተሻለ ቦታ እንደሌለ በማመኔ መነሳሳትን ፈጥሮብኛል።
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙን የተሻለ ለማድረግ በእርስዎ የኃላፊነት ዘመን ምን ይሰራሉ? ሕዝቡስ ምን ይጠብቅ?
ኢንጂኒየር ዓይሻ፡- መከላከያ ‹‹ቅድሚያ ለአገርና ለሕዝብ›› በሚል በሕገመንግስቱ የተሰጡት ኃላፊነቶች እንዲሁም መርሆዎችና እሴቶች አሉ። ትክክለኛ መንገድም ይህን መወጣት የሚችልና ቅድሚያ ለአገር ብሎ የተሰለፈን ሠራዊት እሴቱን ጠብቆ መሄድ የሚችልበትን ቁመና መገንባት ነው። በዚህም ምንም ዓይነት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲያጋጥሙ መሠረታዊ ፍላጎቶቹ ተሟልተውለት ግዳጅ ወጥቶ ወደ ቤቱ ባይመለስ ቤተሰቡ ምን እንደሚሆኑ ስጋት እንዳይኖርበት ማድረግ በትኩረት የሚከናወን ተግባር ነው።
ካለው አቅም ውስንነት የማይሳኩ ተግባራት ሊኖሩ ቢችሉም በቤት ውስጥ አንዲት እናት ለልጆቿ የምታደርገው አስፈላጊ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ በተቋሙም ውስጥ በተመሳሳይ መንፈስ ለሠራዊቱ አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን ለማሟላት እንደ እናት ለመስራት አቅጃለሁ። ብዛት ብቻ ያለው ሳይሆን ብቃት ያለው፣ ማድረግ የሚችል፣ በሙያው በክህሎት የበቃ ሠራዊት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረትም አግዛለሁ። በዚህም ከሃብት ማፈላለግ እስከ አሰራር ሥርዓቶች የመዘርጋት ሁኔታዎች ጥቃቅን የሚባሉ ችግሮችን በማቃለልም ሥልጣኑ በሚፈቅደው ደረጃ ሁሉ በአግባቡ በመጠቀም ተቋሙ የሚበቃበት ደረጃ ለማድረስ እሰራለሁ።
በዚህም የሰውም ሆነ ቁሳዊ ሀብት ሳይባክን በትንሽ አቅምና ጊዜ ግዳጅን መወጣት የሚችሉበት ቁመና ላይ ለማድረስ ባለኝ በቡድን የመሥራት ፍላጎት በመጠቀም ትልቅ ለውጥ እንደማመጣ አምናለሁ። የመከላከያ ሪፎርሙ እየተሰራ ያለውም ችግሮችን በለየና በዚሁ መንገድ በመሆኑ በፍጥነት እንደሚፈፀም ተስፋ አለኝ።
ለዚህም እንደ ምቹ ሁኔታ የሚወሰደው የተንዛዙ አሰራሮች አለመኖራቸው ሲሆን ይህን በመጠቀም ለውጥ እንደሚመጣ አልጠራጠርም። ሠራዊቱ ግዳጁን በሚገባ እንዲወጣ የሚያስችለው ሙሉ ቁመና እንዲኖረው ማስቻል፣ በሠላምም ሆነ በጦርነት ወቅት ውጤታማ እንዲሆኑ እሴታቸውን እንዲላበሱ፣ ያልተሸራረፈ የዴሞክራሲ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሰራ ነው። ይህም ማለት ተቋሙ በዴሞክራሲ የማያምን ከሆነ ሌሎች ሊያምኑ አይችሉምና ሁሉንም የኢትጵያ ብሔሮች ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በእኩል ዓይን የሚመለከት፣ ታዛዥና በሥነምግባር የታነፀ፣ ማንም አገሪቱን ሊመራ የመጣው ኃይል ሕገመንግስቱን እስካልጣሰና የሕዝቦችን ሉዓላዊነት እስካከበረ ድረስ የማገልገል እሴቱን ጠብቆ የሚሄድበት መንገድ ይዘረጋል። በተለያየ መልኩም ይህ እንዳይሸራረፍ ማድረግ ይገባልና በዚህ ላይ ከሌሎች በየደረጃው ካሉ ከተቋሙ አመራሮችና የሠራዊት አባላት ጋር እሰራለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለቃለመጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑልን እናመሰግናለን!
ኢንጂነር ዓይሻ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2011
በፍዮሪ ተወልደ