በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሴቶች ሰብዓዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር ተቃውሞ የጀመሩበት ወቅት ነው። በወቅቱ በኢንዱስትሪ በበለፀጉ አገሮች ዘንድ የሠራተኛው ቁጥርና የሥርዓተ ጾታው ስብጥር በከፍተኛ ደረጃ ሚዛናዊ ባለመሆኑ፤ ውስን የሆኑት ሴት የኢንዱስትሪ ሠራተኞች ለ1910ሩ ታሪካዊ ኮንፈረንስ ቅድመ ሁኔታ መሟላት ምክንያት ሆኑ። በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችና በማምረቻ ቦታዎች የሚሰሩ፤ እነዚህ ሠራተኞች ለጤና በማይስማማ የሥራ ቦታ ከመመደባቸው ባሻገር፤ እጅግ አነስተኛና የዕለት ኑሯቸውን ለመምራት በማያስችላቸው ክፍያ ይሠቃዩ ነበር። በዚህ ምክንያት ሴት ሠራተኞችና ተባባሪ ወንድ አጋሮቻቸው የሚያደርጉት አመጽ በኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ ላይ ተደጋጋሚ ኪሣራ አደረሰ።
የሠራተኛ ማህበራት መጠናከር የሴቶቹን እንቅስቃሴ በማገዙ፤ በአውሮፓ፣ በእንግሊዝ ፣ በአሜሪካና በትንሹም ቢሆን በአውስትራሊያ ሴቶች የመምረጥና መመረጥ መብታቸው እንዲከበር የሚመለከታቸውን ሁሉ ማግባባት ጀመሩ። ይህ ትግላቸው በሴቶች ላይ የሚታዩ ጭቆናዎች እንዲወገዱ ከማድረጉም በላይ በተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ በር ከፍቷል።
በኢትዮጵያም የተለያዩ ሴቶች ለመብታቸው ሲከራከሩ እና ሁሉንም መስራት እንደሚችሉ ሲያስመሰክሩ ቆይተዋል። ከተጠቃሾቹ መካከል በጉራጌ ዞን መኖሯ የሚተረክላት የቃቄ ውርድወት አንዷ ናት። እርሷም በቅርቧ ላሉ ለኢትዮጵያውያን ሴቶች የታገለች ሲሆን፤ እስከ ዛሬም እየተወራላት የገኛል። እኛም ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ108ተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ43ኛ ጊዜ የሚከበረውን ‹‹ማርች 8››ን አስመልክተን በሥራቸው አንቱ የተባሉ ለበርካታ ሴት እህቶቻችንም ተምሳሌት ሊሆኑ ይችላሉ በዛው በጉራጌ ዞን ያሉትን ኢትዮጵያዊ ሴት አርሶ አደር እንደዚህ አቅርበናል።
ሴት አርሶ አደር ወይዘሮ አየለች ኩርማ ካላቸውውድ የሥራ ጊዜ ቀንሰውም እኔ ያለፍኩበት ይሔ ነው ፤ ሴት እህቶቼ ደግሞ ከአልችልም ተላቀው በዚህ መንገድ ቢሄዱ በቀላሉ ውጤቱን ማየት ይችላሉ፤ ሲሉ ያስተላለፏቸውን መልዕክቶች አቅርበናል። በኢትዮጵያ ሴት ልጅ የመስራት አቅም ታይቶ «ጎሽ አንቺ ትችያለሽ በዚሁ ቀጥይ» ለማለት የታደልን ባንሆንም እንኳን በራስ ጥረትና ትጋት መድረስ የሚፈለግበት ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚቻል ያሳዩ ወይዘሮ ናቸው። ሥራ ወዳድ ጠንካራ የሥራ ባህል ባለቤት የሆኑት ወይዘሮ አየለች ኩርማ በጉራጌ ዞን ዕዣ ወረዳ የመንጥር ገበሬ ማህበር ነዋሪ ናቸው። ከወረዳቸው አልፈው በክልል ሞዴል የተባሉ ጠንካራ ሠራተኛ ሴት ናቸው። ወይዘሮ አየለች የሚጠሉት ነገር ቢኖር አልችለምና ደከመኝ የሚለውን አባባል ነው። ለእዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ የሥራቸው ውጤት ያደረሳቸው ደረጃ ነው።
በመንጥር ገበሬ ማህበር ውስጥ ወዳለው የወይዘሮ አየለች መኖሪያ ግቢ እንድናመራ የጋበዙን እራሳቸው ናቸው። ገና ወደ ግቢው ስንገባው ጽዳቱ መሬት ላይ መተኛትን ያስመኛል። የቤታቸው አሰራር እንደ መንደሩ አንድ አይነት ይሁን እንጂ ቤታቸውን ለማስዋብ የተጠቀሙበት ግብዓትና የሰሩበት መንገድ ግን ለየት እንዲሉ አድርጓቸዋል። በጓሯቸው ያለው የአቮካዶ፣ አፕል ፣ቡናና የእንሰት ተክል ደግሞ አጀብ የሚያሰኝ አልፎ ተርፎም የሴትየዋን ጥንካሬ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ወይዘሮ አየለች ተወልደው ያደጉት ከመንጥር ገበሬ ማህበር ወጣ ባለ ደጋማ አካባቢ ሲሆን፤ በትምህርታቸው ባይገፉም ፊደል ግን ቆጥረዋል። በኋላም ዕድሜያቸው ለጋብቻ ሲደርስ በቤተሰቦቻቸው አማካይነት ትዳር መስርተዋል።
ከትዳር አጋራቸው ጋር ሰባት ልጆችን ያፈሩት ወይዘሮ አየለች ልጆች ከማሳደግ ጎን ለጎን ቤታቸውን ከመምራት አልፈው የአካባቢውን መልክዓ ምድር ታሳቢ ያደረጉ የግብርና ሥራዎችን ልክ እንደ ወንዶቹ ጠዋት ወጥተው እስከ ማታ መስራትን ልማድ አድርገዋል። በመስራታቸው ልጆቻቸው ሳይራቡ፣ ሳይታረዙ፣ ከትምህርታቸውሳይስተጓጎሉ እንዲኖሩ አስችለዋል። «እኔ ከፍተኛ የሥራ ፍቅር አለኝ። በእርግጥ ባለቤቴም በጣም ጥሩ ሰው ነው። ጎበዝ ሠራተኛም ከመሆኑም በላይ ሀሳቤን ይሰማኛል፣ ይረዳኛል። እንዲህ እናድርግ ስለው እንወያይበት ብሎ ዕድል ይሰጠኛል። ተወያይተን በሚጠቅመን ጎኑ እንሄድበታለን፤ ይህ መሆኑ ደግሞ ከመንደሩ ነዋሪዎች ሁሉ ከፍ ብለን እንድንወጣ አስችሎናል» ይላሉ።
«በጓሮዬ በከፍተኛ ሁኔታ ቡናን አመርታለሁ እንሰትና አቮካዶም በብዛት ይመረታል አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአፕል ምርትም ጀምሬያለሁ» የሚሉት ወይዘሮ አየለች፤ ‹‹ይህ ሁሉ ሥራ ቀላል አይደለም፤ ከፍተኛ ሥራን የሚጠይቅ ነው። እኔም እንቅልፍ ያዘኝ ደከመኝ ሳልል ተግቼ ስርቻለሁ›› ይላሉ። «ሴት ነኝ ብዬ የጓዳ ሥራን ብቻ እየሰራሁ መቀመጥ አልወደም» የሚሉት ወይዘሮ አየለች፤ እንደ ወንድ በጓሮ አትክልት፣ በግብርና እንዲሁም በወረዳና ቀበሌ ተሳትፎ በሚጠይቁ ተግባራት ላይ ሁሉ የነቃ ተሳታፊ በመሆናቸው ለዚህ መብቃታቸውን ያብራራሉ።
አሁን ላይ ተሳካላቸው ከሚባሉት ሴት አርሶ አደሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚታዩት ወይዘሮ አየለች፤ ስኬታቸው ደግሞ በሥራ ላይ ብቻ ሳይሆን ልጆች ወልዶ አሳደጎ አስተምሮ ቁምነገር በማድረስም ላይም ጭምር ነው። ዛሬ ሦስት ልጆቻቸው ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ ተምረው በጥሩ ውጤት ተመርቀው በመውጣት በተለያዩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነቶች ላይም የሚገኙ ናቸው።
ዘንድሮም ሴት ልጃቸውን ለማስመረቅ እየተዘጋጁ ሲሆን፤ ሌሎቹም እየተማሩ ስለመሆናቸው በኩራት ይናገራሉ። ወይዘሮ አየለች ሥራ ይለውጣል። ሴት ትሁን ወንድ አልችልም ወይም በተለመደው ሁኔታ ሰርቼ እኖራለሁ ከማለት ይልቅ በተለየ ሁኔታ ለፍቼ ተግቼ የተሻለ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ ብለው ማሰብ እንዳለባቸው ይመክራሉ።
እርሳቸው በበኩላቸውገጠር ያፈሩት ሀብት፣ ያፈሰሱት ጉልበትና ያሳዩት ትጋት ዛሬ ለውጧቸው ወደ ከተማ ለመግባት አስችሏቸዋል። «የከተማ ኑሮን መኖር በጣም እፈልግ ነበር፤ ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች በተለይም ቤታችንና ንብረታችን ትልቅ በመሆኑ እርሱን ትቶ ለመሄድ ልጆቼም ባለቤቴም አልደገፉኝም ነበር።አሁን ግን ሁላችንም ተስማምተንና ቤታችንንም ቤት ለሌላቸው ሰዎች በኃላፊነት እንዲያስተዳድሩት ሰጥተን ወደ ከተማ ገብተናል።» ይላሉ።
እዚህ ላይ ግን ወይዘሮ አየለች የከተማ ኖሮን ለመኖር ከመጓጓት ባለፈ ከተማ ላይም ትልቅ ሥራ ሰርተው መታወቅ እንደሚፈልጉ ይናገራሉ። ይህንን ህልማቸውን ለማሳካት የደረቅ እንጀራ ንግድ፣ በገጠር ያለውን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርታቸውን ወስደው ማከፋፈል እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ የንግድ ሥራዎችን ለማከናወን እቅድ መያዛቸውን ያብራራሉ። የጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ በተለያየ ጊዜ የሥራ ትጋታቸውንና ውጤታማ ሴት መሆናቸውን ተመልክቶ የተለያዩ ሽልማቶችን እንደተሰጣቸው የሚናገሩት ወይዘሮ አየለች በጤና ዘርፍ በግብርናው እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ በኩል ከተበረከቱላቸው ሽልማቶችና እውቅና ውጪ የእዣ ወረዳ የክልል ምክር ቤት አባል ለመሆንም ችለዋል።
«በምሰራቸው ወይም በሰራኋቸው ሥራዎች አማካይነት ሞዴል በመሆኔ ወረዳው ይህንን እውቅና ሰጥቶኛል። እኔም ተቀብዬ የተጣለብኝን ኃላፊነት በታማኝነት እንዲሁም በሥራ እያስመሰከርኩ ሲሆን፤ ወደፊትም በተካተትኩበት ምክር ቤት ላይ የሴቶችን ችግር አጉልቼ በመናገር መፍትሔ በማሰጠት እንዲሁም ጠንካራ ሠራተኛ በመሆን ኃላፊነቴን እወጣለሁ» ብለዋል።
አሁን ላይ ብዙ ሴቶች በተለያዩ ተግባራት ሞዴል እየሆኑ ነው፤ እኔም መንደሬን ጎረቤቶቼን ለመቀየር እንዲሁም የመልክዓ ምድሩን ተጠቅመው እንዲያለሙ እራሳቸውን እንዲያበቁ ከኩሽና ወጥተውም አደባባይ መዋል እንደሚችሉና ከሰሩ ከተጉ የማይችሉበት ምክንያት እንደሌለ መምከር እፈልጋለሁ ብለዋል። አዎ የወይዘሮ አየለች የሥራ ትጋትና ያስመዘገቡት ውጤት እንዲሁም የቀጣይ ዕቅዳቸው ለብዙ ሴቶች በተለይም በአካባቢያቸው ላሉ ሞዴል መሆን የሚያስችላቸው ነውና ወረዳው ይህንን ተሞክሮ ማስፋት ሴቶችንም በማበረታታት ለተመሳሳይ ውጤት ማብቃት ይጠበቅበታል።
አሁን በአገሪቱ ያለው የሴቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ካለፈው ጊዜ አንጻር ከፍተኛ መሻሻል ታይቶበታል። መንግሥትም ሴቶችን እያበረታታና እየደገፈ ይገኛል። ሆኖም ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች አሉ። ይህ ቢሆንም ሴቶች በእችላለሁ ስሜት ተነስተው ራሳቸውን ማብቃት ወደ ሥራ መግባትና ሀብት ማፍራት አለባቸው። ድሮና ዘንድሮ በጣም የተለያዩ ሆነዋል። በአሁኑ ወቅት በርካታ ሴቶች በተለያየ መስክ ሥራን እየፈጠሩና ራሳቸውን ወደ በባለሀብትነት እየቀየሩ ነው። በመንግሥት በኩልም የሚደረገው ድጋፍ አበረታች ስለመሆኑ በርካቶች በመናገር ላይ ናቸው። ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀንም መነሻው እኩልነት ነውና ቀኑን ስናስብ ከእኩልነት አልፈን በልጠን መገኘት አለብን ሊሆን ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2011
በእፀገነት አክሊሉ