የተወለዱት በቀድሞ አጠራር ጎንደር ክፍለሃገር ጋይንት አውራጃ ነው። የመጀመሪያም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጋይንት ንፋስ መውጪያ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በ1976 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር ሃይል ያወጣውን ማስታወቂያ መስፈርት በማሟላታቸውና ፈተናውን በማለፋቸው ተቀጠሩና ለስልጠና ሶቭየት ህብረት ተላኩ።
ከሦሰት ዓመት በኋላ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ዳግመኛ በኢትዮጵያ አየር ሃይል ደረጃ መሰረት ሥልጠና ወሰዱ። በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተመድበው ጥቂት እንደሰሩ ግን በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ይካሄድ የነበረው ጦርነት እያየለ መጣ። በኋላም ሕወሓት አሸንፎ በትረ-ሰልጣኑን ተቆናጠጠ።
ሰራዊቱ ቢበተንም የዛሬው የዘመን እንግዳችን ግን ዳግመኛ በተቋሙ ውስጥ በመምህርነት የማገልገል እድሉን አገኙ። ይሁንና የተቋሙ አሰራር እንደቀድሞው ሁሉን በእኩል የሚያሳትፍ ሆኖ አልቀጠለም።
ይልቁንም የአንድ ብሔር የበላይነት ነገሰና የሌላውን ብሔር ተወላጆች ባይተዋር አድርጎ አገለለ። በዚህ ብቻ አላበቃም፤ እሳቸውም ልክ እንደሌሎቹ ባልደረቦቻቸው ሁሉ ሰበብ ተፈልጎ ከስራ እንዲሰናበቱ ተደረገ። አበው ‹‹ሳይደግስ አይጣላም›› እንደሚሉ እንግዳችን ቀድሞም በብቃታቸው ያውቋቸው በነበረው በኤርትራው አየር ሃይል አዛዥ ግብዣ ኤርትራ ሄደው ማስተማራቸውን ቀጠሉ።
ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ አሜሪካ የመሄድ እድሉን አገኙ። እንግዳችን አሜሪካ በስደት በቆዩባቸው ዓመታት ሁሉ ብሔር ተኮር ሥርዓት አራማጁን የሕወሓት ሥርዓት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲቃወሙ ነው የቆዩት። በተለይም ደግሞ ይህንን ስርዓት ለመጣል እንቅስቃሴ ለሚያደርጉ ድርጅቶች ያላቸውን ሁሉ በመለገስ ኢትዮጵያ ወደ ቀደመው ህብረ ብሄራዊነቷ እንድትመለስ የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸው ይጠቀሳል።
በቅርቡ ደግሞ መንግስት ያቀረበውን ጥሪ ተከትለው እሳቸውም ከህዝባቸው ጎን መሆናቸውን ለማረጋገጥ ወደ ሀገራቸው ገብተዋል። አዲስ ዘመን ጋዜጣም የቀድምው አየር ሃይል አባል ካፒቴን ክንዴ ዳምጠውን የዛሬው የዘመን እንግዳ አደርጓቸዋል። ከእንግዳችን ጋር በወቅታዊና ሃገራዊ ጉዳዮች ጋር ያደረግነው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- አየር ሃይል ውስጥ የነበሮትን ቆይታ ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር? ካፒቴን ክንዴ፡- አየር ሃይል ከሌላው መንግስታዊ ተቋም ለየት የሚያደርገው ቤተሰባዊ ስሜት እንዲሰማሽ የሚያደርግ በመሆኑ ነው።
የነበሩት መምህራኖቻችን ገና ሥልጠናችንን ስንጀምር ጀምሮ በአባላቱ መካከል ወንድማማችነት እንዲፈጠር አድርገው ነው የሚቀርፁን። በዚህ ምክንያት ልብ ለልብ ተግባብተን ነው የኖርነው ማለት ይቻላል። ከገጠር የመጣውንም ሆነ የመርካቶውን ልጅ አንድ ላይ አስተምረው ሲያበቁ መጨረሻ ላይ ወንድማማች አድርገው ያወጡናል።
በመካከላችን ምንአልባትም የትውልድ አካባቢያችን ሊታወቅ ይችላል እንጂ ስለብሄራችን የምናውቀው ነገር የለም። ቢኖርም ግድ የለንም ነበር። ስለዚህ ከሁሉ በላይ ስለዚህ ተቋም ሳስብ ከህሊናዬ የማይጠፋው ነገር የሀገርና የህዝብ ፍቅር እንዲኖረን የሚቀርፁበት መንገድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህ መተሳሰብና የሃገር ፍቅር ስሜት የደርግ መውደቅን ተከትሎ መጥፋቱ ምን አይነት ስሜት ነበር የፈጠረብዎት?
ካፒቴን ክንዴ፡- በእርግጥ መጀመሪያ አካባቢ የደርግ መገርሰስ እኔም ሆንኩኝ ሌሎች በስርዓቱ ቅሬታ የነበራቸው ሰዎች ስለነበሩ የወያኔን መምጣት ደግፈነው ነበር። ግን ደግሞ ሕወሓት ስልጣን ሊያሸንፍ የቻለው ህዝቡ ውስጥ የለውጥ ስሜት ከፍተኛ ስለነበር መሆኑን መዘንጋት አይገባም። በወቅቱ ሁሉም ሰው ለውጥ ይፈልግ ነበር።
በተለይ ከመፈንቅለ መንግስቱ ሙከራ በኋላ የምንወዳቸው ጀነራሎች መገደልን ተከትሎ አብዛኛው የአየር ሃይል አባል በደርግ ላይ ቅሬታ ውስጥ ገብቶ ነበር። ጥቂት የማይባሉትም ወደ ጎረቤት ሃገሮች ሳይቀር ተሰደው ነበር። ሆኖም ወያኔ ሲመጣ ደግሞ ሃገር ውስጥ የቀሩት የእኛ አብዛኛው አባል በግዳጅ ወደ ተሃድሶ ተቋም እንዲገባ ነው የተደረገው። እኔም ሕወሓት ስልጣን ከያዘ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደስራ እንድንመለስ ተደረገ።
በበረራ አስተማሪነት ማገልገል ጀመርኩኝ። ይሁንና ተቋሙ ቀድሞ በነበረው ኢትዮጵያዊ ቁመና መቀጠል አልቻለም። ሙሉ ለሙሉ የአንድ ብሔር ድርጅት በሚባል መልኩ ለስልጠና የሚመረጡት ሁሉ የትግራይ ተወላጆች ነበሩ። በዚህ ብቻ አላበቃም፤ የሚፈልጓቸውን ሰዎች ሁሉ እየለቀሙ እስር ቤት አስገቧቸው።
ከሰባት ዓመት ጀምሮ እስከ 20 ዓመት ድረስ ታስሮ የተፈታ አለ። ከእነዚህም መካከል በቅርቡ ህይወታቸው ያለፈው ብርሀነመስቀል አንዱ ሲሆኑ ብዙ ዋጋ የከፈሉ ሰው መሆናቸው ይታወቃል። የሚገርምሽ እኚህ ሰው ታስረው እንኳን ስለኢትዮጵያ አንድነት ከመናገር ተቆጥበው አያውቁም ነበር።
ሕወሓት ህዝብ መምራት እንደማይችል በአደባባይ ይናገሩ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ እንደእኔ ሥራ ጀምረው የነበሩ አባላቶቻችንም ታስረው ነበር። በተቋሙ ውስጥ እየተስፋፋ የመጣውን የአንድ ብሔር የበላይነት መቋቋም አቅቷቸው አውሮፕላን ይዘው የኮበለሉ አሉ።
እኔም ሶስት ኮርሶች ካስተማርኩኝ በኋላ በ1989 ዓ.ም በማላቀው ምክንያት ከስራ እንድወጣ ተደረገ። በእርግጥ እኔ ብቻ አይደለሁም የተባረርኩት፤ ሌሎች ባልደረቦችም ተመሳሳይ ድርጊት ነው የተፈፀመባቸው።
አሁን አሁን ሳስበው ግን ያኔ እኛ ላይ የተፈፀመው ነገር በዘዴ አማራ የሆነውን ብቻ ለይቶ የማጥቃት ዓላማ ይመስለኛል። ምክንያቱም ከእኔ ጋር የተባረሩት በአብዛኛው የአማራ ተወላጆች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ከስራ የተባረሩበት ምክንያት ምንድን ነበር?
ካፒቴን ክንዴ፡- ለመባረሬ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የተነገረኝ ‹‹አንተ ትግሬ ትጠላለህ›› የሚል ነው። ግን እውነታው ይህ አልነበረም። ለምሳሌ ባነሳልሽ 20 ተማሪ ለስልጠና ቢመጣ 17 የትግራይ ተወላጅ ነው።
በመሰረቱ በቀድሞ የአየር ሃይሉ መስፈርት መሰረት በዓመት ከሁለትና ሶስት በላይ አይቀበልም። ወያኔ ከመጣ በኋላ ግን ለስልጠና ከተመለመሉት ውስጥ 90 በመቶው የትግራይ ተወላጆች ነበሩ። ከዚያ ውስጥ አምስት ተማሪ እንኳን ቢወድቅ የትግራይ ጥላቻ ነው የሚመስላቸው።
ይህ የሙያ ብቃት ጉዳይ እንጂ ፈፅሞ ትግራዋይን ከመጥላት ጋር አይገናኝም። እኔም ሆንኩኝ ሌላው የትግራይ ተወላጆችን የምንጠላበት ምንም ምክንያት አልነበረንም። ሁለተኛ እንደበረራ አስተማሪ ሆነሽ ስታይው አደገኛ አካሄድ ነው ሲከተሉ የነበሩት።
ህይወትን ያህል ነገር እና ንብረትን የሚያወድም እንደሆነ እያወቁ ያለብቃታቸው ማሳለፍ ለእኔ ከባድ ነበር። አየር ሃይል ቃጫ ወይም ዳቦ ፋብሪካ አይደለም። ምንአልባት ሰዎችን ያለብቃታቸው ማሳለፍ የፋብሪካ ስራ ቢሆን ኖሮ ብዙ ችግር ላይኖረው ይችል ይሆናል፤ ያ በመደረጉ ምክንያቱም ሊከስር የሚችለው ንብረት ብቻ ነው። እዚህ ግን ቢበላሽ የሚጠፋው የሰው ህይወት ነው፤ የሚወድመው ከፍተኛ ሃብት የያዘ አውሮፕላን ነው። አጠቃላይ የመማር ማስተማሩ ሥራ በጣም ጥንቃቄ ይፈልጋል።
ከሁሉ በላይ ደግሞ ህሊና የሚባል ነገር አለ። ህሊናሽን እያወቀ ወይም እየተጠራጠርሽ ተማሪን አውሮፕላን ይዞ እንዲሄድ ማድረግ ከባድ ነገር ነው። የእድሜ ልክ የህሊና ፀፀት የምትሸምቺበት ነው። ስለዚህ ጥንቃቄ የሚፈልግ ስራ ነው። መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆንን ይፈልጋል። ተማሪ ተነስቶ በሰላም ያርፍልኛል ብለሽ በጣም መተማመን አለብሽ። ስህተት ቢፈጠር ወጪው ብዙ ነው።
ለዚህ ነው የቀድሞ አየር ሃይል በየዓመቱ በጣም ውጤታማ የሆኑትን ጥቂት ተማሪዎችን ብቻ መርጦ ያስመርቅ የነበረው። ይህንን ማድረጉ ሊመጣ የሚችለውን ኪሳራ አስቀድሞ ይቀንሳል። እርግጥነው እንደ ወያኔ ላለ አካል ይህንን ሁኔታ በጥላቻ መመንዘር ቀላል ነው። ግን ደግሞ እውነታው ግልጽ ነው። እና በዚያ ምክንያት ከስራ ወጣሁኝ።
ይሁንና ወዲያውኑ በኤርትራ አየር ሃይል ሄጄ እንድሰራ ግብዣ ቀርቦልኝ ነበር። ግን ደግሞ ለመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከኢትዮጵያ አየር ሃይል መልቀቂያ አገኛለሁ በሚል ተስፋ ምላሽ ሳልሰጣቸው ቆይቼ ነበር።
ወያኔዎች ግንእኔን ለመጉዳት ስለነበረ ሃሳባቸው መልቀቂያ ሊሰጡኝ አልቻሉም። የሚገርምሽ እነዚህ ሰዎች አንቺ ስትሰቃይ፤ ስትራቢ ማየት ደስታ ይሰጣቸዋል። ለዚህም ነው ከስራ ካባረሩኝ በኋላ ለአራት ወራት ደመወዝ እንዳላገኝ ያደረጉት።
ስለዚህ በወቅቱ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ነበረብኝ። አልያም ደግሞ ሸፍቼ ፒያሳ አንቺንም ሆነ ያገኘሁትን ሰው እየቀማሁ መብላት መቻል አለብኝ። በአጋጣሚ ሻዕቢያና ወያኔ የነበራቸው ግንኙነት በጣም ከፍተኛ ስለነበር ወደ ኤርትራ በቀበሌ መታወቂያ በአየር መንገድ ሄድኩኝ።
አዲስ ዘመን፡- ኤርትራ ታዲያ በበረራ ነው ወይስ በማስተማሩ ነው የቀጠሉት?
ካፒቴን ክንዴ፡- በማስተማሩ ላይ ነው የቀጠልኩት። ግን ደግሞ የኤርትራ አየር ሃይል ገና ከጅምሩ የሚገርም፤ የሚያስደነግጥና ክብር ያለው አቀባበል ነው ያደረገልኝ።
ይህንን ስመለከት እኔ ይህ አይነት ክብር የሚገባኝ ሰው ስለመሆኔ እስከመጠራጠር ደርሼ ነበር። ምክንያቱም እነዚህኞቹ እንደማይረባና እንዳልባሌ ነበር ጥለውኝ የነበረው። ያ አይነቱ አቀባበል ለእኔ እንግዳ ነገር ነበር የሆነብኝ። በኤርትራ ተቀጥሬ እስከ 1992 ዓ.ም ድረስ ቆየሁኝ። ሶስት ዓመት ሙሉ ኤርትራ ስንቆይ ማንም ከአጠገባችን የደረሰ አልነበረም። ጦርነቱ ተከስቶ እንኳን ለእኛ የነበራቸው አመለካከት አልተቀየረም ነበር።
በመሰረቱ ግን ሻቢያና ወያኔ እንዲጣሉ ፍላጎት ነበረኝ። በወቅቱ ታዲያ እዚህ ያለው ሃይል የጦርነት ነጋሪት ቢጎስምም አስመራ ላይ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አልነበረም። እንዳውም ሰባተኛ ዓመት የነጻነት በዓላቸውን ሲያከብሩ እኛም የአየር ላይ ትዕይንት አሳይተናል።
በመጨረሻ የአየር ድብደባው ሊጀመር አንድ ሁለት ቀን ሲቀረው የኤርትራው አየር ሃይል አዛዥ ኮማንደር ሃብተፂዮን ሃድጉ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ቢሮው ሰበሰበንና ያለውን እውነታ ነገረን። ከወያኔ ጋር ወደ ግጭት እያመሩ ስለመሆናቸውና ምንአልባትም ጦርነት ሊፈጠር እንደሚችል አስረዳን።
ይሁንና ‹‹የፈለገውን ያህል በደም የተጨማለቀ ጦርነት ቢፈጠር እናንተ ላይ የሚደርስ ነገር የለም፤ በሰላም መኖር ትችላላችሁ›› አለን። ‹‹አይመቸኝም፤ ብሄድ ይሻለኛል የምትሉ ካላችሁ አስቡና እኔን ፈልጋችሁ እንደመጣችሁ እኔው በሰላም ወደ ሀገራችሁ እሸኛችኋለሁ›› የሚል ነገር ተናገረ። ያኔ ደግሞ የአየር ትራንስፖርት ተቋርጦ ነበር። ስለዚህ ‹‹ስትፈልጉ በኬኒያ፤ አልያም በጅቡቲና በየመን አዙሬ እቤታችሁ አደርሳችኋለሁ›› ብሎ ቃል ገባልን። ውሳኔያችንንም በግል ሄደን እንድናሳውቀው እድል ሰጠን። በወቅቱ ታዲያ ከመካከላችን ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ፍላጎት የነበረው አልነበረም። ምክንያቱም ተባረን ስራ አጥተን ነበር የኖርነው። ስለዚህ ሁላችንም እንደገና ወደ ቦዘኔነት መመለስ አንፈልግም ነበር።
ወያኔዎቹም ቢሆኑ የምትበይው አጥተሽ ተቸግረሽ እንድትኖሪ ነው የሚፈልጉት። ይህንን በነገረን በሶስተኛ ቀኑ ምሳ በልተን ስንመለስ የኤርትራ አየር መንገድ ለመግባት በግምት 150 ሜትር አካባቢ ሲቀረኝ አንዳች ነገር አየሁኝ።
ይኸውም የኢትዮጵያ ሁለት ሚግ 23 አውሮፕላኖች ቦንብ ጥለው ሲወጡ ጀርባቸውን አየሁት። ዳር ይዤ እንደቆምኩኝ ፍንዳታውን ስመለከት ጦርነቱ የእውነት መሆኑን አመንኩኝ። ያንጊዜ ደስታም፤ ሃዘንም፤ ድንጋጤም ተቀላቀለብኝ። ከሁሉም በላይ ደግሞ የእነዚህ ቦንብ ጣይ አውሮፕላን አብራሪዎች የራሴ ጓደኞችና ወዳጆቼ መሆናቸው ስገነዘብ የማላውቀው ስሜት ተፈጠረብኝ። ወደ ጊቢ ሳልገባ ተመለስኩኝ። እናም በዚህ ሁኔታ ነው ጦርነቱ የተጀመረው።
አዲስ ዘመን፡- ኤርትራን ለቀው የወጡበት አጋጣሚ ምን ነበር?
ካፒቴን ክንዴ፡- በመሰረቱ ኤርትራ የቆየሁት እኔ ስራ ስላጣሁኝ ብቻ ሳይሆን አየር ሃይላቸውን ለማገዝ በእነሱ ስለተጠየኩኝ ጭምር ነው።
በተለይም የኤርትራ አየር ሃይል አዛዥ የእነሱን አየር ሃይል ልክ እንደኢትዮጵያ ጠንካራ ተቋም የማድረግ እቅድ ነበረው። ይህ ሰው የኢትዮጵያን አየር ሃይል እምቅ አቅም እንዳለው ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበር ተማሪዎቹ ውጭ ሃገር ሄደው ከሚማሩለት በኢትዮጵያ በራሪዎች ቢማሩለት ይመርጣል። ለዚህም
ነው ከጦርነቱ በፊት በርካታ ኤርትራውያን ኢትዮጵያ እየላከ ያሰለጥን የነበረው። ግን ደግሞ በወያኔ ስርዓት ግን እንዳይማሩበት ከባድ ማስጠንቀቂያ ይሰጥ ነበር።
እኔ እዛ በነበርኩበት ወቅት አስር የምንሆን ኢትዮጵያውያን አብራሪዎች በኤርትራ መንግስት ተቀጥረን እያገለገልን ብንሆንም የበለጠ ኢትዮጵያ ውስጥ የታሰሩትን በሙሉ ወስዶ ቢያሰለጥኑለት ደስተኛ ነበር። ዋና ሃሳቡም ከአፍሪካ አንቱ የተባለ የአቬይሽን ኢንስቲትዩት መክፈት ነበር። ይህንን ደግሞ ለማስፈፀም ያቀደው እዚህ በግፍ በተበተነው በኢትዮጵያ አየር ሃይል አባላት ነበር። በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለሁ ታዲያ የሩዋንዳ ተማሪዎችን የማስተማር እድል እዛው ኤርትራ ገጥሞኝ ነበር።
በእነዚህ የሩዋንዳ ተማሪዎች ምርቃት ላይ የመጣ አንድ የሩዋንዳ ባለስልጣን ጋር ተዋወቅንና ሀገራቸው አየር ሃይል የመመስረት ፍላጎት እንዳላትና ኢትዮጵያ የወደቁ አባላትን እንዳገናኘው እኔም እንድሰራላቸው ጠየቀኝ። ይህ ሰው ከፍተኛ ክፍያ ሊከፍለኝ እንደሚችል ጠቆመኝ። እኔ ግን መሄዱን ብፈልገውም የኤርትራውያኖቹን ውለታ ትቼ መሄድ በጣም ከበደኝ። ልክ እንደክህደት ነው የቆጠርኩት።
በተለይም የኤርትራው አየር ሃይል አዛዥ በዚያ መልኩ አምኖ እና አቀማጥሎ አኑሮኝ ሲያበቃ እሱን ትቼ መሄድ ክህደት ነው የመሰለኝ። ስለዚህ ሩዋንዳ ልሄድ ነው ብሎ መናገር ፈራሁ። አንድ ቀን ግን ቢሮው ገባሁና ሃብቴ ከዚህ በኋላ ኮንትራት አልፈርምም በቃኝ አልኩት። ‹‹አስቀይመንህ እንደሆነ ንገረኝ›› አለኝ። እኔ ግን ሚስቴና ልጄ አዲስ አበባ ሆነው እኔ እዚህ ብቻዬን መኖሬ ህይወት ትርጉም አልባ ስለሆነችብኝ መሄድ እፈልጋለሁ ብዬ ነገርኩት።
‹‹ለዚህ ከሆነ ቤተሰብህን እናስመጣልህ›› ቢለኝም አሻፈረኝ አልኩትና ፓስፖርት እንዲሰጠኝና ለአሜሪካ ኤምባሲ ደብዳቤ እንዲፅፍልኝ ጠየኩት። እሱም በዚያ መሰረት ሶስት መስመር ደብዳቤ ወደ አሜሪካ ለመሄድ ስለሚፈልጉ ትብብር እንዲደረግልኝ ገልፆ ላከኝ።
የሚገርምሽ ደብዳቤውን ይዤ ለአሜሪካ ኤምባሲ ስሰጣቸው አጭበርባሪ ነው የመሰልኳቸው። ስለሆነም የኢትዮጵያ አየር ሃይል ደውለው እውነታውን አረጋገጡ። እዛው እንደቆምኩኝ ቪዛ ተመታልኝ። በዚህ ሁኔታ ነው የሩዋንዳውን ጉዞ ትቼ ወደ አሜሪካ የሄድኩት። እንዳልኩሽ ሩዋንዳ መሄድ ፈልጌ የነበረ ቢሆንም ያመኑኝ ሰዎች ላይ ሸፍጥ መስራት ነው የሆነብኝ። አሜሪካ ከገባሁ በኋላም ወደ አቬየሽን ኢንዱስትሪው የመቀላቀል ፍላጎቱ የነበረኝ ቢሆንም በወቅቱ ደግሞ የመስከረም 11 ሽብር ተፈጠረና ለውጭ ዜጎች ነገሮች ሁሉ ከበዱ።
በዚያ ወቅት አውሮፕላን አጠገብ ሊያደርሱሽ ቀርቶ ለመኖር እንኳን በጣም ከባድ ነበር። ስለዚህ የተለያዩ ስራዎችን ሰርቻለሁ። በመቀጠልም ከጓደኞቼ ጋር በመሆን የራሳችንን አነስተኛ ኩባንያ ከፍተን እያንቀሳቀስን ነው የምንገኘው።
አዲስ ዘመን፡- አብዛኛው ዲያስፖራ ወያኔ ሃገሪቱን በተቆጣጠረባቸው ዓመታት ከያለበት ሃገር ሆኖ ስርዓቱን ሲቃወምና ሲታገል ነው የቆየው። እርሶ በምን ሁኔታ ላይ ነበሩ?
ካፒቴን ክንዴ፡- እኔ በመጀመሪያም ቢሆን ፖለቲከኛ አልነበርኩም፤ ነገር ግን በሃገር ጉዳይ ላይ ስሜቴን ደብቄ አላውቅም ነበር። ወያኔ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ስቃወም ነው የቆየሁት። በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ ለመከፋፈል የተጠቀሙበትን ሴራ በጣም ነበር የምፀየፈው። አሁንም ቢሆን የእከሌ ብሔረሰብ ሚዲያ ሲባል አፍራለሁ።
በሁሉም ተቋም ውስጥ ይህንን ብሔር ተኮር ስርዓት በማስፈናቸው ሙያና ስነ-ምግባር እንዲጠፋ አድርገዋል። በተለይ ደግሞ የትግራይ ፖለቲከኞች በህዝቡ ላይ የጫኑት ከፋፋይ አሰራርን በያለንበት ሃገር ሆነን እንቃወምና እናጋልጥ ነበር። በነገራችን ላይ በወያኔ ላይ ጠጠር ለሚወረውር ሁሉ ድጋፍ አደርግ ነበር። እነዚያን ተቃዋሚ ሃይሎች ሁሉ ባላውቃቸውም የገንዘብም ሆነ የሌላ ነገር ድጋፍ አደርግላቸው ነበር። ምክንያቱም እንዳልኩሽ ወያኔ ከስልጣን እንዲለቅ ፅኑ ፍላጎት ስለነበረኝ ነው። በተጨማሪም እኛ እንደአየር ሃይል ማህበር መስርተን ወያኔን ስንታገል ነበር። ህዝቡንም በማንቃት ረገድ የራሳችንን አስተዋፅኦ ስናበረክት ነበር።
እውነት ለመናገር ግን ወያኔ በዚህ ሁኔታ ይወድቃል የሚል እምነት አልነበረኝም። በህዝብ ጩኸት የሚወድቅ ከሆነ ለምን 27 ዓመት ቆየ? የሚል ጥያቄም ይፈጠርብኛል። ምክንያቱም ወያኔ ከጥቅም ተካፋዮቹ በስተቀር በህዝብ የተጠላ ድርጅት መሆኑን እናውቅ ስለነበረ ነው። ነገር ግን እንዴት አድርገው የተንኮል መረባቸውን ህዝቡ ላይ እንደዘረጉ ባይገባኝም ለረጅም ጊዜ ሥልጣን ላይ የመቆየታቸው ነገር ሁልጊዜም የሚገርመኝ ጉዳይ ነው።
እንደእውነቱ ከሆነ እነዚህ ሰዎች ይህንን ሁሉ ዓመት ስልጣን ላይ መቆየት አይገባቸውም ነበር። ግን ብዙ ጊዜ እንደሚነገረው የኢትዮጵያውያን ድክመትና አንድ ላይ አለመቆም ነው ወያኔ ይህንን ሁሉ ዓመት እንዲንሰራፋብን እድል የሰጠነው።
በመሰረቱ ብሔር ተኮር ፖለቲካ የምታካሂጂ ከሆነ አንድ የሆነ ጠላት መፍጠር አለብሽ። ይህንን ካላደረጉ የትግሬ ወይም የሆነ ብሔር ነፃ አውጪ መሆን አያስፈልግም ነበር። ከሆነ አካል ነፃ አወጣለሁ በሚል ሰበብ አንዱን ብሔር ጠላት አድርገው ማቅረብ ይገባቸው ነበር። ለዚህም ነው የተፈበረከ ፕሮፖጋንዳ ሲያሰራጩ የነበረው። ያ ጠላት ተብሎ የተሰየመው ብሔር ደግሞ ራሱን ለመከላከል ሲል የማጥቃት ዘመቻ ውስጥ ይገባል። በአጠቃላይ የብሔር ፖለቲካ አፀያፊ ነው ባይ ነኝ።
አስቀድሜ እንዳልኩሽ ደግሞ እኛ አየር ሃይል ውስጥ ያደግነው በአንድ ኢትዮጵያ ተቀርፀን በመሆኑ ይህ ወያኔ ሰራሽ ፖለቲካ ፈፅሞ ልቀበለው አልቻልኩም ነበር። ሙያና ብሄርተኝነትም አብረው ሊሄዱ አይችሉም። አዲስ ዘመን፡- ለውጡ በዚህ መልኩ ይመጣል ብዬ አልጠበቁም ብለው ሲናገሩ ምን ማለትዎ ነው? ካፒቴን ክንዴ፡- ያው ወያኔ ከዘረጋው ስርዓት አንፃር እንዲሁ በቀላሉ ይለቃል ብዬ አላስብም ነበር።
በመሰረቱ አሁንም ቢሆን የፓርቲዎቹ አደረጃጀት ብሔር ተኮር ነው። ያ ሆኖ ሳለ ስለኢትዮጵያና ስለአንድነት የሚያነሳ መሪ ሲመጣ ለብዙዎቻችን እንግዳ ነበር የሆነብን። በተለይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በምክር ቤት ያደረጉት ንግግር ለብዙዎቻችን ያልጠበቅነው ነገር ነው የሆነብን።
ግን ደግሞ የክልሎቹና የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አደረጃጀት ከብሄር ተኮር አስተሳሰብ ሊወጡ ይገባል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም የማይጠቅመን መሆኑን አይተነዋል። እኔ ኢትዮጵያዊ ከሆንኩኝ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል ተዘዋውሬ ገንዘቤን፤ እውቀቴና ጉልበቴን ኢንቨስት አድርጌ በነፃነት መኖር መቻል አለብኝ። ስፈልግ ጋምቤላ አልያም ሽሬ ገብቼ በነፃነት መንቀሳቀስ መቻል አለብኝ።
‹‹የሌላ ጎሳ አባል ስለሆንኩ እኛ ሰፈር መኖር አትችልም›› ልባል አይገባም። አለበለዚያማ ምኑን ኢትዮጵያዊ ሆንኩኝ? ለዚህ ደግሞ ወያኔ የቀረፀው ህገ-መንግስት ዋነኛው ምክንያት ነው።
በመሆኑም ይህ ህገመንግስት ካልተስተካከለ ለውጡ የእውነት መሬት ላይ እንዳይወርድ እንቅፋት ይሆንበታል ብዬ ነው የማስበው። እኛ በምንኖርበት አሜሪካ እንኳን በየትኛው የሃገሪቱ ክፍል ተዘዋውረን ብንኖር፤ የንግድ ተቋም ከፍተን ብንሰራ ማንም የሚጠይቀን የለም። በገዛ ሀገራችን ውስጥ ግን በጉልበታችን ሰርተን እንዳንኖር ነው የተደረግነው። እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደመጡ የተናገሩት ንግግር እጅግ ሆድ የሚያስብስ ልብ የሚነካ ነበር።
ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ደስታን የፈጠረ ከመሆኑም ባሻገር ትክክለኛ ሰው ሰው የሚሸት መሪ እንደሆነ ነው ለመገንዘብ የቻልነው። በእምነትም ካየሽው ፈጣሪ ችግራችን አይቶ የላከልን መሪ አድርጌ ነው የምቆጥረው። ምክንያቱም እንዲሁ በድንገት መሪ አይፈጠርም፤ ከታች ጀምሮ ኮትኩቶ ነው ማብቃት የሚቻለው። አሁንም ልጆች ላይ መስራት እንዳለብን ነው የማምነው። በዘር ፖለቲካ ተኮትኩቶ ያደገውን ትውልድ መመለስ አለብን። ምክንያቱም ምርጫ ስለሌለው የተነገረውን ይዞ ነው ያደጉት። ብዙ ነገር መስተካከል ይገባዋል።
ኢትዮጵያ ለምለም ሆና ሳለ በምግብ ራሷን መቻል ያልቻለችበት ምክንያት መመለስ መቻል አለብን። ከእኛ በኋላ የተፈጠሩ ሃገራት የትና የት ደርሰዋል። እርግጥ ነው፤ እኛ እንዳናድግ የሚታገሉን ሃይሎች አሉ። ሲታገሉንም ነው የኖሩት፤ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ከድህነት እንዳትወጣ እርስበርስ እንድንዋጋ እነሱ የቀረፁልን አጀንዳ ነው። አሁን ላይ በብሔርና በጎሳ እየተባላን ያለነው እነሱ ባበጁልን የጥፋት መስመር ውስጥ ገብተን ነው።
ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ የአባይን ውሃ እንዳንጠቀም ከፍተኛ የሆነ ሴራ ያሴሩብናል። ስለዚህ በትምህርት ቤት ደረጃ ስላሉን የውሃ ሃብቶችና ስለታሪካዊ ጠላቶቻችን ማወቅና መማር ነበረብን። በኢትዮጵያዊነትና በሃብታችን ዙሪያ ትምህርት ተሰጥቶን ብናድግ ኖሮ አይናችን ሊገለጥ ይችል ነበር።
የሚገርምሽ እኛ ለትምህርት ወደሶቭየት ህብረት ሰንሄድ ገና አሸኛኘት ያደረጉልን በመፈንቅለ መንግስቱ የተገደሉት የአየር ሃይል ምክትል አዛዥ ጀነራል አምሃ ደስታ ነበሩ።
ሲሸኙን የምንሄድበት ሃገር ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከእኛ ጋር ሊማሩ እንደሚችሉ፤ ስለሆነም ሊተናኮሏችሁ ስለሚችሉ በተቻለ መጠን በጋራ መንቀሳቀስ እንዳለብን ሁሉንም ነገር በትዕግስት ለማለፍ እንድንሞክር መክረውን ነበር። በተለይም ተልዕኮዎቻችንን አጠናቀን እዚህ የምንሰራው ስራ ስለሚበልጥና ሃገራችን ስለምትፈልገን በትግስት ማለፍ እንዳለብን ነግረውን ነበር።
በወቅቱ ታሪካዊ ጠላት ብለው ሲነግሩን የፖለቲካ ቅስቀሳ ነበር የሚመስለን። ደግሞስ ለምን እውነት ከሆነ ትምህርት ቤት አልተማርነውም? በምሁራንና በጋዜጠኞች አልተነገረንም? ለምንድን ነው ስልጣን ያላቸው ፖለቲከኞች ብቻ የሚናገሩት?።
ይህ እውነታ እንጂ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም፤ ስለዚህ ሁላችንም ታሪካዊ ጠላቶችንና ሴራቸውን አውቀን መስራት ያለብን ይመስለኛል። አዲስ ዘመን፡- ይህ አሸባሪ ቡድን ለ27 ዓመታት ሀገሪቱንና ህዝቡን ሲበዘብዝ መኖሩ አልበቃ ብሎ ከስልጣን መወገዱን ተከትሎ በመከላከያ ሰራዊትና በህዝቡ ላይ እንዲህ አይነቱን ግፍ መፈጸሙ ከምን የመነጨ ነው ይላሉ? ካፒቴን ክንዴ፡- በእውነት እንደ ሕወሓት ጥሩ እድል የገጠመው አልነበረም። ህዝቡም ሆነ የለውጡ ሃይል የዘረፋችሁትን ይዛችሁ ኑሩ ብሎ ይቅርታ አድርጎላቸው ነበር። እነሱ ግን ይህንን ጥሩ እድል መጠቀም አልፈለጉም። ልክ የደቡብ አፍሪካንአይነት የሚያስታርቅ አሰራር ነበር የለውጡ ሃይል የተከተለው። እናም ያንን እድል ባለመጠቀማቸው ነው እንዲህ አይነት ማጥ ውስጥ የገቡት። በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያን የመከላከያ ሰራዊት በሌሊት በተኛበት፤ በጭካኔ፤ በግፍ እንደዚያ ማድረጋቸው ከስህተቶች ሁሉ ትልቁ ስህተት ነው።
እኔ እንዳውም እንዲህ አይነት ባህል ከየት አመጡ? የሚል ጥያቄ ያጭርብኛል። እኔ ተወልጄ ባደኩበት አካባቢ እንዲህ አይነት ነገር ነውር ነው።
ጠላትሽን ልትገይው ሄደሽ እንኳን ቀስቅሰሽ ሱሪውን እንዲታጠቅ አድርገሽ ነው የምትገጥሚው። በተኛበት ሰው አይገደለም፤ ፀያፍ ነው። እነዚህ ሰዎች እንዲህ አይነት የሞራል ውድቀት ከየት እንዳመጡት አይገባኝም።
ቀደም ብዬ እንዳልኩት ኢትዮጵያኖች በድህነት እንድንማቅቅ ብሔር ከብሔር የሚያጋጩን፤ የሚያዋጉ፤ ይሄ ሁሉ ጥንስስ የውጭ ጠላቶቻችን እቅድና ሃሳብ ሲሆን አስፈጻሚው ደግሞ ሕወሓት ነው። እነሱ ከድህነት እንድንወጣ አይፈልጉም። ይህ ሕወሓት የፈፀመው ወንጀሎች ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ነው። ከሰውነት ስብዕና ውጭ ነው። በተለይም ያስከተለው ውድመትና የድሃ ህብረተሰብን የእለት ምግብ ሳይቀር መዝረፍ ከእኛ ከኢትዮጵያውን ባህል ውጪ ነው።
እኔ ግን ዋና ጉዳዬ ከሕወሓት ጋር አይደለም፤ ምክንያቱም እነሱ የምዕራባውያኑ አጀንዳ አስፈፃሚዎች ናቸው። እነሱ እኮ ያለቀ የነበረና ከሁለት መቶ ሺ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርገውን የጣና በለስ ፕሮጀክትን አስፈርሰዋል። በሀገር ገንዘብ ያለቀ ፕሮጀክት የምታፈርሺ ከሆነ አንቺ ከሰው ተራ ወጥተሻል ማለት ነው። ስለዚህ ትኩረታችንን የውጭ ጠላቶቻችን ላይ መሆን አለበት ባይ ነኝ። ለዚህ ደግሞ ዝግጅት ማድረግ ይገባናል።
የትኛውንም አይነት ዋጋ ከፍሎ ለሚቀጥለው ትውልድ ሃገር እንድትቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል። አዲስ ዘመን፡- መንግስት መከላከያ ሰራዊት ባለበት እንዲቆይ መወሰኑ ምን ያህል ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ? ካፒቴን ክንዴ፡-እኔ እዚህ ጉዳይ ላይ መናገር የምፈልገው ፖለቲከኞች የሚያወሩትን አይደለም።
በግሌ እንደማስበው በአሁኑ ወቅት ጥቂት የሕወሓት አመራሮች ናቸው የቀሩት፤ የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት በሌሊት ግፍ እንዲፈፀም አመራር የሰጡ የሕወሓት ሰዎች በምንም ተዓምር ለፍትህ መቅረብ አለባቸው ብዬ አምናለሁ። አሁን እኮ ጦርነቱ እየተካሄደ ያለው ከጀሌው፤ ምንም ከማያውቀውና በፕሮፖጋንዳ እየተነዳ ከመጣ ሃይል ጋር ነው። በዕፅ አደንዝዘዋቸውና በጥላቻ ልባቸውን አሳውረዋቸው ነው እያዋጓቸው ያሉት።
ስለዚህ መንግስት እኔ የምፈልገውና የምመኘው በምን ይሁን በምን እነዚህ ወንጀለኞች ማደንና መያዝ አለበት። መነጋገር ካለብን እንኳን ሊሆን የሚችለው ከእነዚህ ውጭ ከሆነው የህብረተሰብ ክፍል ጋር ብቻ ነው። እነዚህ ከምንም በፊት የሕወሓት አመራሮች ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል። ደማቸው በከንቱ የፈሰሰው የመከላከያ ሰራዊትና ንፁሃን ዜጎች ፍትህ ማግኘት መቻል አለበት።
እርግጥ የትግራይ ህዝብ ግራና ቀኙን እንዳያይ ተደርጎ ነው የተቀረፀው። አየሽ በአንድ መንገድ የምትሔጂ ከሆነ ሌላ መንገድ ያለ አይመስልሽም። የትግራይ ህዝብ ልክ እንደፈረስ ጋሪ አንድ አቅጣጫ ብቻ አይቶ እንዲሄድ ነው የተደረገው። የፈለጉትን የመናገር መብት እንኳን የላቸውም።
ትግራይ ውስጥ እኮ ነፃ ጋዜጣ እንኳን አይገባም ነበር። እነዚህ ሰዎች የሚያወዳድሩት ነገር የላቸውም። የግዴታ የተሰጣቸውን ብቻ የሚቀበሉበት ሁኔታ ነው ያለው። በመሆኑም ከፖለቲካ ይልቅ ማህበረሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ነው መሰራት ያለበት ብዬ ነው የማስበው። የህዝብ ለህዝብ ትስስሩም መጠናከር አለበት። ምክንያቱም ጭንቅላታቸው ውስጥ የገባው የጥላቻ አመለካከት በቀላሉ ማላቀቅ ከባድ በመሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና ከመከላከል አኳያ ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
ካፒቴን ክንዴ፡- በጣም የሚገርመኝ ነገር የምዕራባውያኑ ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ነው። እኛም ወደዚህ ሃገር የመጣው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አይነሳም ሲሉ ለሀገራችን ልንደርስላት ይገባል በሚል ነው።
በዚህ የችግር ጊዜ ሁሉም ዲያስፖራ የየራሱን ጠጠር መወርወር አለበት። ግን ዝም ብለሽ ስታይው አሜሪካም ቢሆን ከኢትዮጵያ በበለጠ የግብፅ ወዳጅ ነች። ለእነሱ ነው የሚያዳሉት ምንም አትጠራጠሪ። ምንም ፅንሰ ሃሳቡ ሳይገባቸው ያልገባቸው ሀገራት በአረብ ሊግ ስር ተሰብስበው ነው ከኢትዮጵያ ተቃርነው የቆሙት። እነዚህ ሀገራት እውነታውን ለማጣራት እንኳን አይሞክሩም። መሀል ለመሆን እንኳን አይጥሩም። ኢትዮጵያም በገዛ ሃብቷ መጠቀም እንዳለባት አስበው አያውቁም። ስለሆነም ኢትዮጵያኖችን የሚያከብሩን ስናከብራቸው እንደሆነ ማሳየት መቻል አለብን። ምክንያቱም ሁሉም ነገር ሚዛን ሊኖረው ይገባል።
ግብፆች እኛ በርሃብ ስንሞት ካረዱን እነሱ በውሃ ጥም ሲሞቱ ለምን እኛ እናስብላቸዋለን?። ጥቅማችን እኩል ለኩል እኮ ነው መሆን ያለበት። እነሱ ድንች እየሸጡ ለአረብ ሃገር ይሰጣሉና ኢትዮጵያኖች መራብ መቸገር አይኖርባቸውም። ስለዚህ እንዲህ አይነት የባርነት ስርዓት ሊቆም ይገባል ባይ ነኝ። አሜሪካም የውጭ ፖሊሲያቸው በዚህ ደረጃ የመውረዱ ጉዳይ ፖለቲከኞች ሊተነትኑት ይችላሉ። ግን ዝም ብዬ ሳስበው በተደጋጋሚ የሚያደርጉት ኢ-ፍትሃዊ ተግባር የኢትዮጵያ ወዳጅ ሃገር አለመሆንዋን ያረጋግጥልኛል።
በ1969 ዓ.ም ኢትዮጵያ በገንዘቧ የገዛችውን የጦር መሳሪያ ከልክለው ሱማሌን ይረዱ ነበር። ሱማሌ አዋሽ ድረስ እስኪደርሱ ድረስ የአሜሪካኖች እጅ ነበረበት። ድሬዳዋ አየር ማረፊያ ተከቦ ነበር።
የድሬዳዋ አየር ሃይል ዋናው መስራቤት ተከቦ ሱማሌዎቹ ሊቆጣጠሩ ሲሉ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ነው የመለሳቸው። እኔ አሜሪካኖች ሁሌም ለምን በችግራችን ጊዜ ከእኛ በተቃራኒ እንደሚቆሙ አይገባኝም። ግን ዋናው መፍትሄው እኛ በፅናት የሚፈለገውን መስዋትነት ለመክፈል ዝግጅት ማድረግ ብቻ ነው።
የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዛ ወይም ሌላ አጀንዳ ይኑራቸው በህብረት ልናሸንፋቸው ይገባል። አንድ ላይ ከቆምን ጠላቶቻችንን ሁሉ ማሸነፍ እንደምንችል አድዋ ትልቅ ማሳያችን ነው። በተመሳሳይ አሜሪካኖቹ ከአግዋ ተጠቃሚነት ቢያስወጡንም አሁንም በጋራ ከቆምንና ከሰራን በዚህ ምክንያት ሊመጣ የሚችለውን ችግር ማለፍ እንችላለን።
መንግስት ማስተባባር ከቻለ በሚሊዮን የሚቆጠረው ኢትዮጵያዊ ከአሜሪካኖቹ የምናገኘውን ሁሉ ሊመልስልን ይችላል። አሁን ላይ እኮ ውጭ ካለው ኢትዮጵያዊ ውስጥ አምስት በመቶው እንኳን የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ አይደለም።
በእርግጥ ዲያስፖራው አለመስጠት ፈልጎ አይደለም፤ ከፊሉ እንዴት እንደሚሰጥ አያውቅም፤ ሌላው በስራ ብዛት ሃሳቡም መረጃውም የለውም፤ አንዳንዱ ደግሞ ይጠራጠራል።
ይሄን ሁሉ ሊፈታ የሚችል መንግስት የዜግነት ግዴታ መጣል አለበት። በነገራችን ላይ እኔ እዚህ ሀገር ስመጣ የማሽከረክረው መኪና የሚሄደው አንቺ በከፈልሽው ታክስ በተሰራ መንገድ ላይ ነው። እኔ ምንም አስተዋፅኦ ሳላደርግ ነው ተንፈላስሼ የምሄደው። ለምን ይሄ ይሆናል ?።
እኔም የበኩሌን ድርሻ ላዋጣ ይገባል። እኔ በሰላም ውዬ እንዳመሽ ፖሊስ ተቀጥሯል። አንቺ በከፈልሽው ታክስ ነው ይሄ ፖሊስ የሚያገለግለው። እኔን ግን ሳልከፍል ይጠብቀኛል። ስለዚህ እኔ ለዚህ ሁሉ አገልግሎት የዜግነት ግዴታ መክፈል አለብኝ። መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ማሰብ አለበት።
ይህንን ጉዳይ ብቻ የሚሰራ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መክፈት ይገባዋል። ደግሞም በዚህ ጉዳይ ላይ መምከር ይጠበቅበታል። ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃሳብ መሰብሰብ አለበት፤ መናቅ የለበትም። ምክንያቱም ከተለያዩ ቦታዎች ጥሩ ሃሳብ ሊመጣ ይችላል። የግድ ስልጣን ስላለው አይደለም።
ከማንኛውም አቅጣጫ የሚገኘውን ሃሳብ ሊቀምረውና ስራ ላይ ሊያውለው ይገባል። በዚህ መልኩ ሁላችንም የዜግነት ግዴታችንን የምንወጣበት ስርዓት መፈጠር አለበት። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ እውነት ልንገርሽ፤ አሜሪካ ብዙ ዓመት ስኖር ከአንዱ ግዛት ወደ ሌላው ሄጄ ሆቴል በምይዝበት ጊዜ ምንም ሳላነብ የጠየቁኝ ሁሉ እከፍል ነበር።
ብዙ ኢትዮጵያውያን ያ ክፍያ ለምን አገልግሎት እንደሚውል አናየውም ነበር። አንድ ቀን ግን ስመለከት የሃገሪቱ መንግስት ከሚጥለው ታክስ በተጨማሪ የዚያ ሆቴል ያለበት ግዛት ወይም ከተማ አስተዳደርም የራሱን ታክስ ጥሎ እንድንከፍል የሚያደርግ መሆኑን ተገነዘብኩኝ።
በተቀራኒ ደግሞ እኔ ለምሳሌ ባህርዳር ስሄድ የፌደራል መንግስትንም ሆነ የከተማዋን ግብር አልከፍልም፤ ዝም ብዬ ነው ሄጄ እንደፈለኩኝ ተስተናግጄ የምመጣው። የባህርዳር ህዝብ በከፈለው ታክስ፤ ባሰራው መንገድ እኔ በነጻነት ስመላለስ ምንም አስተዋፅኦ ሳይኖረኝ እኩል እጠቀማለሁ።
ይህ ብቻ አይደለም፤ የባህርዳር ህዝብ ህብረተሰቡን እንዲያገለግል በቀጠረው ፖሊስ እኔም እጠበቃለሁ። እኔ ግን አሁንም አልከፍልም። በዚህ ሁኔታ ልንቀጥል አይገባም። የዜግነት ግዴታ መጣል አለበት። ይህ ሲባል ግን ገንዘቡ ለፖለቲካ ስራ መዋል አለበት እያልኩ አይደለም፤ ለሀገር ጥቅም እንጂ!። እኔ እድሉን ባገኝ ለሁሉም ባለስልጣን ይህንኑ መንገሬ አይቀርም።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ አጋጣሚ በሰማው የሃሰት ወሬ ተሸብቦ ወደ ሃገሩ ለመግባት ለሰጋው ዲያስፖራ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎት?
ካፒቴን ክንዴ፡– እውነቱን ለመናገር ዲያስፖራው ከመቼው ጊዜ በላይ ወደ ሀገሩ ለመግባትም ሆነ ለመደገፍ በከፍተኛ መነሳሳት ውስጥ ነው ያለው።
አሁን ላይ ሁሉም ዲያስፖራ በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ባለው ግፍና በደል ውስጡ ተቆጥቶ ነው ያለው። እንደምታይውም በየቀኑ የተቋውሞ ሰልፎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ በየትኛው የሀገሩ ጉዳይ ላይ ዘብ ቆሞ እየሞገታቸው ነው የሚገኘው።
ይህንን ሁኔታ ወደ ጥሩ አጋጣሚ መቀየር አለብን። በተለይም በጦርነቱ የተጎዱ ክልሎች የከፋ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ውጭ ያለውን ዲያስፖራ በማስተባበር በቀላሉ ልንታደገው ይገባል። አግዋም ሆነ ሌላ የውጭ ድጋፍ ሳያሻን እኛው ለእኛው መረዳዳትና መደጋገፍ እንችላለን። ለምሳሌ አማራ ክልል በራሱ ሆነ የክልሉ ተወላጆች የደረሰበትን አደጋ አስረድቶ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቋሚ ወርሃዊ መዋጮ መጠየቅ ይችላል። ግን ደግሞ እንዲሁ መዋጮ አምጡ ማለት ብቻ ሳይሆን ለዚህ የተመደበ ሰው በመቅጠር ስርዓት ባለው መንገድ ቀጣይነት ያለው አሰራር ሊከተል ይገባል።
አሁን ደግሞ ቴክኖሎጂው ስለሚመች በኢንተርኔት ብዙ ጉዳዮችን መጨረስ ይቻላል። በተጨማሪም ለሚደረገው ነገር ሁሉ እውቅና መስጠት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ይህንን ማድረጉ በራሱ ሌላውንም ስለሚያበረታታ ነው። በአጠቃላይ የሃገር ግዴታ መሆን አለበት። እንዳልኩሽ በጣም በርካታ ኢትዮጵያዊ ውጭ ይኖራል፤ ስለዚህ በጣም ቀልጣፋና ቀላል ስርዓት መፍጠር ይገባል።
ዲያስፖራውም ከያለበት ሃገር ሆኖ አንድ ቀን ለኢትዮጵያ ብቻ ብሎ ቢሰራ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። በወር 4 ሰዓት እንኳን ብንሰራ ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል። ይህንን ግን የሚያስተባብር አካል ያስፈልጋል። ለዚህም የፌደራል መንግስቱና የክልል መንግስታት ተናበውና ተጠናክረው መስራት ይገባቸዋል።
በተለይ አሁን ያለውን የዲያስፖራውን መነሳሳት እንደጥሩ አጋጣሚ ሊጠቀሙበት ይገባል ባይ ነኝ። እያንዳንዱ ዲያስፖራ በአካል ሩቅ ቢሆንም ልቡም መንፈሱም ከሀገሩ ከኢትዮጵያ ጋር ነው ያለው። እርግጥ ነው፤ ያኮረፈ አካል ሊኖር ይችላል፤ ግን ይሄ ጉዳይ የግለሰብ ወይም የፖለቲካ ጉዳይ አይለም፤ የሀገር ነገር ነው።
ስለዚህ ሁሉንም መለየት አለብን። የሀገር ጉዳይንና የፖለቲከኞችን ነገር መለየት አለብን። ሃገር ቋሚ ነች፤ አትቀያየርም። መንግስት ግን ይመጣል፤ ይሄዳል። በእኛ እድሜ እንኳን አራት መንግስት አይተናል።
ስለዚህ የሃገር ጉዳይ ሲሆን በህብረት መቆም አለብን። በሌላ በኩል በዚህ ጉዳይ ላይ ከህፃናት ጀምሮ ትምህርት መሰጠት መቻል አለበት ብዬ አምናለሁ።
እንዳልኩሽ ሲነገር እንደምንሰማው በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ኢትዮጵያኖችን በጦርነት ሳይሆን በብሔር በመከፋል ማሸነፍ እንደሚቻል ቀኝ ገዢዎች ስለመናገራቸው እንሰማን።
ያኔ በቀኝ ግዛት አፍሪካን ሲቀራመቱ ኢትዮጵያኖች በሃይል ሳይሆን እርስ በርስ የሚያባሉበትን ስርዓት ነው የዘረጉት። እሱነው አሁን ላይ እየተገበርን ያለነው። በመሆኑም ይህንን እውነታ ተገንዝበን አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል። የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገር ወዳድ እንደመሆኑ ከተባበርን ስኬታማ እንሆናለን ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈለጉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎት?
ካፒቴን ክንዴ፡- እኔ በዋናነት ማመስገን የምፈልገው የህብረተሰብ ክፍል አለ። በተለይም የቢሾፍቱ ህዝብ እኛን ስቴድየም መጥቶ መቀበሉ ፈፅሞ ያልጠበቁትና በጣም ያስገረመኝ ነገር ነው። የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ ወጣት ቢሆኑም የሚገርም ሃሳብ ያላቸው ሰው ናቸው።
በአጠቃላይ ለቀድሞው የአየር ሃይል አባላት ያሳዩንና ፍቅርና አክብሮት በጣም ነው ያስደነቀኝ። በመሆኑም በዚህ አጋጣሚ ለቢሾፍቱ ከንቲባና ህዝብ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ። በመቀጠልም የኢትዮጵያ አየር ሃይልን ጎብኝተናል።
ይህ ተቋም መስሪያ ቤቴ ብቻ ሳይሆን ቤቴም ጭምር ነበር። ዳግመኛ ይህንን ተቋም የማየት እድል ማግኘቴ በራሱ ልዩ ስሜት ነው የፈጠረልኝ። አሁን ላይ ያሉት አመራሮች ተቋሙን ለመለወጥ እያደረጉት ያሉት ጥረት በጣም የሚደነቅ ነው።
ከሁሉ በላይ ደግሞ ያስደመመኝ አመራሮቹ አንደበት አየር ሃይል ውስጥ ከዚህ በኋላ ፖለቲካና ብሔርተኝነት ምንም አይነት ቦታ እንዳማይኖራቸውና የሙያ ቦታ ብቻ እንደሚሆን መስማታችን ምንያህል ቁርጠኛ እንደሆኑ እንድንገነዘብ አድርጎኛል። በተመሳሳይ ሆሳእናን በጎበኘንበት ጊዜ የሃድያ ዞን አስተዳዳሪ ላደረጉልን መልካም አቀባበል ላመሰግን እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼ እና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ። ካፒቴን ክንዴ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 30/2014