በአገራችን ለ43ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደግሞ ለ108ኛ ጊዜ የሚከበረውን አዓም አቀፍ የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ ከሴቶች፣ ህጻ ናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ጸጋይ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- በሴቶች ላይ የሚደርሰው ተፅዕኖ አንድም ሴቷ ለራሷ ከምትሰጠው ግምት ሌላም በማህበረሰቡ የሚሰጣት ቦታ ጎታች ሆኖ ተሳትፎዋና ተጠቃሚነቷ በሚፈ ለገው ደረጃ አልሆነምና በተለይም አመለካከት ለውጥ ላይ ሚኒስቴሩ እየሰራቸው ያሉ ተግባ ራት ምን ይመስላሉ
ወይዘሮ ያለም፡- በተያዘው በጀት ዓመት ወጣት ሴቶች ላይ ማዕከል ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል። ሴቶች ነገ የአገር ተረካቢ የሆነውን ትውልድ የሚቀርፁና የሚተኩ ስለሆኑ ወጣቶች ላይ በተለያዩ የንቅናቄ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። በዚህም ለዘመናት የቆየው ‹‹ሴቶች አይችሉም›› የሚል አስተሳሰብ ሴቶች ለራሳቸው በሚሰጡት የበታችነት አስተሳሰብ ጋር ተዳምሮ የፈጠረውን ችግር ለማቃለል ‹‹እንችላለን›› የሚል አስተሳሰብ እንዲኖር የማድረግ ነው። ኋላ ቀር አመለካከቱን በእንችላለን የመቀየሩ ሥራም በአፍ ብቻ ሳይሆን በተግባር የታገዘ ነው።
በዚህም በተግባር ችለው የወጡ አርዓያ ሴቶች በማውጣት ላይ ይገኛሉ። በማህበራዊ፣ በኢኮ ኖሚና በፖለቲካ ብሎም በግብርናና በንግዱ ዘርፍ ብዙ ችግሮችንና ውጣ ውረዶችን ተሻግረው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ሴቶች አሉ። እነዚህን ሴቶች ወደፊት ማምጣትም ለሌሎች አርዓያ እንዲሆኑ ያነሳሳቸዋል። ጥሩ ውጤትና ተሞክሮ ያላቸውን ሴቶች ተሞክሮ በመቀመር ማስፋት ይገባል። ከዚህ ቀደም የነበረው ነገር ብዙ ጊዜ የሚደመጠው ሴቶች በፆታቸው ምክንያት ሲጠቁና ችግር ሲደርስባቸው በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ሲኖሩ እንደማይችሉ የነበረው ገንቢ ያልሆነ አመለካከት ተቀይሮ መልካምና ገጽታ የሚገነቡ ሥራዎች መሥራት ይገባል።
ችግሩ ከፍተኛ ትግል የሚስፈልገው ቢሆንም እንኳ ደግሞ ይህን ማነቆ ሰብረው ወጥተው በትልቅ ቦታ ላይ ያሉ የይቻላል ሕያው ምስክሮች በመኖራቸው ሴቶች ዕድሉን ካገኙ ሁሉም መሆን እንደሚችሉ ማሳያ ይሆናል። አስቸጋሪውን ፈተና በማለፍ ነገ ጠንካራ ሴት መሆን ይቻላል በሚል የመንፈስ ጥንካሬን የተላበሰች ስብዕናዋ ችግሮችን መወጣት መቻልን እንዲላበስ የማድረግ ጉዳይ በትኩረት እየተሠራ ነው።
ይህን ደግሞ ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ እንዲችሉ የማድረግ ሥራ በወሳኝነት የሚከናወን ተግባር ነው። ይህንንም ሴቶች እኛ ብቻ እንችላለን ብለን ሳይሆን የወንዶችም አጋርነት ማጠናከር ተያይዞ ይተኮርበታል። በዚህም በባህሉና በአስተሳሰቡ ይዞ ወደኋላ ያስቀራቸውን ወደፊት እንዲመጡ በማድረግ ከፍተኛ ቦታ ላይ የደረሱትን ደግሞ ማበረታታት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ሴቶች ከልጅነታቸው ጀምሮ ‹‹የእችላለሁ!›› ጠንካራ መንፈስባለቤት እንዲሆኑ ለማስቻል በቤት ውስጥ ወላጆች ካላቸው ሚና ባሻገር ትምህርት ቤቶች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ አሁንም በሴትነታቸው ምክንያት ወደ ትምህርት ገበታ ማቅናት ላልቻሉት የትምህርት ተደራሽነት ላይ ምን እተሠራ ነው?
ወይዘሮ ያለም፡- በአገሪቱ አሁን ባለው የትምህርት ተደራሽት ደረጃ በተለይ በአንደኛ ደረጃ ላይ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሴቶች የትምህርት ተደራሽነቱ 50 በመቶ መድረሱን መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህም ትልቅ ውጤት ተደርጎ ይወሰዳል። ይህም በዚህ ዙሪያ ላይ እናቶች ግንዛቤ እየፈጠሩ እንዳለ አመላካች ነው። ከቤታቸው በዚህ ደረጃ ሲመጡ በትምህርት ቤትስ እንዴት ሊቀረፁ ይገባል? የሚለው ደግሞ ሌላኛው ጥያቄ ነው። ሴቶች እንዴት የተሻለ ስብዕና ኖሯቸው በትምህርታቸው ውጤታማ ሆነው ነገ የተሻለና ጠንካራ ሴቶች ይሁኑ የሚለውን የመገንባት ሥራ ከታች ጀምሮ መከናወን ያለበት የዕለት ተዕለት ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። ተማሪዎች የሚሳተፉባቸው ክበባትንም በመጠቀም እንደሚችሉ የማድረግና የማብቃት ሥራን ይጠይቃል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት የማይሄዱ አሉ። ትምህርት ቤት ሄደውም በቂ የትምህርት አጋዥ መሳሪዎችን የማያገኙም አሉና ይህንን ለማሟላትና ለመደገፍ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሆኖ ማጠናከር ይገባል። በተመሳሳይ ልዩ ድጋፍ የሚሹና ሌሎች ሴቶችን መደገፍ ላይ ክፍተቶች እንዳሉ በመገምገሙም በዚህ ላይ ተጠናክሮ ይሠራል።
አዲስ ዘመን፡- በአገር ደረጃ በሴቶች ላይ ሲከናወኑ ከነበሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል በጤናው ዘርፍ የተሠራው ሥራ ተጠቃሽ ነው። ሚኒስቴሩ ሥራዎቹ ያስገኙትን ውጤት ገምግሟል ወይ? ቀጣይ አጠናክሮ ለማስቀጠል ምን የታሰበ ነገር አለ?
ወይዘሮ ያለም፡- በጤናው ዘርፍ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል አንድም እናት በወሊድ ምክንያት ሕይወቷ ማለፍ የለባትም የሚለው ንቅናቄ ይጠቀሳል። ይህ አገራዊ ንቅናቄ ተገምግሞም ውጤት እንዳመጣ ታይቷል። በዚህም በሚሊኒየም የዕድገት ግቦች ኢትዮጵያ ማሳካት መቻሏ ተረጋግጧል። በተለይ ደግሞ ለውጤቱ ሴቶች በየአካባቢያቸው የተደራጁበት የሴቶች የልማት ቡድን በሁሉም ዘርፍ ተጠናክረው የሠሩት ሥራ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
በዘርፉ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች ውጤትን ያስገኘና ተጠናክሮ የሚቀጥልም ነው። አሁንም ሴቶች በሁሉም ዘርፍ በልማት ቡድናቸው በጤና ነክና በሌሎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ። ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ጋርም ተቀናጅተው ይሠራሉ። በዚህ ላይ ከፍተኛ ውጤትም እየታየ ነው። በተያያዘ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በማስታከክ በጤናው ዘርፍ ላይ ትኩረት አልተሰጠውም በሚል በትኩረት መሠራት እንዳለበት የተለየው የማህፀን ችግር ያለባቸው ሴቶች ሕክምና ነው።
ከዚህ ቀደም ፌስቱላ ያለባቸው ሴቶች ሕክምና እንዲገኙ በተደረገው ንቅናቄ የተደረሰበት ውጤት አለ። የዚህ ችግር መንስዔ የሆነው በተለይ ደግሞ ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መካከል ከሚጠቀሱት ካለ ዕድሜ እና ያለአቻ ጋብቻ ለማስቀረት መሥራትን የሚጠይቅ በመሆኑ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው። በተጨማሪም የማህፀን መውጣት ችግር ያለባቸው ሴቶች ብዙ በመሆናቸው የሴቶች ቀን (ማርች 8) ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ይኸው ነው። በአገሪቱ በየዓመቱ ከ10 ሺህ ሴቶች 100 የሚሆኑት ለዚህ ሕመም ይጋለጣሉ፡ በሕመሙ የተጠቁ ሴቶች በየቤታቸው ተዘግቶባቸው ያሉ ናቸው።
አንዳንዴ ሕመሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ማህፀናቸው አጠቃላይ ወጥቶ ለመንቀሳቀስ እንኳ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰው ይታያሉ። ወደውና ፈቅደው ባላመጡት ችግርም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የሕመማቸው ሳይበቃ የሚደርስባቸው ማህበራዊ መገለልና የሥነልቦና ጉዳት ከፍተኛ ነው። ይህንንም በተለይ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የተለያዩ የንቅናቄ ሥራዎችን በመሥራት ወደ ሕክምና ሄደው ነፃ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል። በዚህም መጋቢት ወሩን ሙሉ የነፃ ሕክምና የሚደረግ ሲሆን፤ 100 ሺህ ሴቶች አገልግሎቱን ያገኛሉ ተብሎም ይጠበቃል። ምንም እንኳ ሥራው ቀኑን አስመልክቶ ይሠራ እንጂ በዘመቻ መልክ የማይቆምና ዓመቱን ሙሉ የሚከናወን ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ሴቶች ላይ የሚደርሰው ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ዓይነቱን እየቀያየረ በሰፊው የሚነሳና በርካቶች የሚያወግዙት ዕኩይ ተግባር ነው። ሚኒስቴሩ በዚህ ላይ በአንድ በኩል ችግሩ ከመከሰቱ አስቀድሞ ለመከላከል የሚከናውናቸው ተግባራት ካሉ ቢጠቅሱልን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከሕግ ተጠያቂነቱ ጋር ተያይዞ አስተማሪና ተመጣጣኝ አለመሆኑ በሰፊው የሚተች በመሆኑ በዚህ ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ካሉ ቢገልጹልን።
ወይዘሮ ያለም፡- በመጀመሪያ ሴቶች ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት እንደሚደርስባቸው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ይደመጣል። በዚህ ላይ ሦስት ሥራዎችን ለመሥራት ታቅዷል። አንደኛውና ዋነኛው የመከላከል ሥራ ሲሆን፤ ሴቶች ጥቃት እንዲደርስባቸው ማንም መፍቀድ የለበትም። በዚህም ማንኛዋም ሴት ጥቃት እንዳይ ደርስባት መላው ሕብረተሰብ ሊከላከልና ድርጊቱን በጋራ ሊያወግዘው ሊኮንነውም ይገባል። ምንም እንኳ ድርጊቱ ከመነሻው መከሰት ባይገባውም ጥቃት ደርሶ ሲገኝ ደግሞ ለተጠቂዋ የሥነልቦና ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
ድርጊቱ የተፈፀመባቸው ተጎጂ ሴቶች አንዳንዴም ከወንጀሉ አስከፊነት የተነሳ ተስፋ እስከመቁረጥ ይደርሳሉ። ከጥቃቱ ደረጃ የተነሳ ሕይወታቸው እስከማለፍም ሊደርሱ ይችላሉ። በመሆኑም ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች የማገገሚያ አገልግሎት እንዲሰጣቸው ማድረግ ይገባል። በስልጠናውም ወደ ሥራ እንዲገቡ የማስቻልና የመደገፍ ብሎም ከችግራቸው ወጥተው ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው እንዲገቡ የማድረግ ሥራ በሁለተኛ ደረጃ የሚከናወን ተግባር ነው።
ሌላኛውና ሦስተኛው ደግሞ አስፈላጊ ተመጣጣኝና አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ የመሥ ራት ነው። ይህንን ከዚህ ቀደምም በዚህ ዙሪያ ላይ የሚወሰዱ የእርምት እርምጃዎች ተመጣጣኝ አይደሉም በሚል ይተች ስለነበር የፍትሕ ፎረሙን የማጠናከር ሥራ ተሠርቷል። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ያሉበት የፍትሕ ፎረም በማቋቋም እነዚህን ችግሮች እንዴት ነው ማቃለል የሚቻለው? የትኛውስ አካል ምን ስላልሠራ ነው ችግሮቹ እየተፈጠሩ ያሉት? በቀጣይስ እንዴት ነው መፍታት የሚቻለው? በሚል ጉዳዩን በጥልቀት የሚመረምር በፌዴራል ደረጃ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሚመራው አንድ ፎረም ተቋቁሟል። በየክልሎቹም ተመሳሳይ ፎረም እየተቋቋሙ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚቀርበው የሕግ መላላት በመሆኑ ፎረሙ ሕጎች ሊሻሻሉ የሚችሉባቸው ሁኔታዎችን ፈትሿል ወይ?
ወይዘሮ ያለም፡- ፎረሙ አንዱ ሥራው ይኸው ነው። በሕግ ዙሪያ ያሉ ነገሮች ምንድን ናቸው? ምንድን ናቸው ሊሻሻሉ የሚገባቸው የሚለውን ለይቶ በቅንጅት ይሠራል። ይህንን ችግር ያቃልላል ተብሎ ይታሰባል። በተለይ ጥቃት አድራሹ ላይ አስተማሪ ቅጣት የማይጣልበት ሁኔታ ፍትሐዊም አስተማሪም አይደለም። በመሆኑም ይህንን ጉዳይ ሁሉም በጋራ ሊቃወመው ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- የሴቶች ተሣትፎና ተጠቃሚነትስ ከየት ተነስቶ የት ደርሷል?
ወይዘሮ ያለም፡- በተለይ በአሁኑ ወቅት ለሴቶች እየተሰጠ ያለው ትኩረት ጥሩ ነው። የተሻለ መነሳሳትም እየተፈጠረ እንደሆነ ይታያል። እንደ ማሳያና በሌሎች ዘንድም ሴቶች በውሳኔ ሰጪነትና በትልቅ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ቦታ ላይ መቀመጥ እንደሚችሉ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ግማሽ በመቶ ቦታ የተያዘው በሴቶች መሆኑ እንዲሁም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሴት መሆናቸው ማሳያ ነው። ነገር ግን ደግሞ ይህ ጅምር ነው። በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት የተጀመረው መልካም ጅማሮ ቢሆንም ሴቶች በሁሉም ቦታ ላይ በዚህ ደረጃ ቦታ አላቸው ወይ የሚለውን ግን ማየት ያስፈልጋል።
ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸው ላይ የማሰልጠን የማብቃት እና በዚህም በሁሉም ቦታ ብቁ ሆነው እንዲገኙ የማድረግ ሥራ ይጠይቃል። በተለይም ከሁሉም ቅድሚያ ተሰጥቶ ሊሠራበት የሚገባው ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ነው። አሁንም ቢሆን በድህነት ውስጥ ያሉ በኢኮኖሚ ጥገኛ የሆኑ ሴቶች በመኖራቸው በገጠሩም ሆነ በከተማ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ውስጥ ሕይወታቸውን ለሚገፉ ሴቶች የተለየ ድጋፍ ማድረግ ይገባል። መልካም ጅማሮውንም አጠናክሮ ለማስቀጠል ከሁሉም ዘርፎች ጋር በቅንጅት መሥራትን ይጠይቃል። ይህ ከሆነም የሚታሰበውን ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ሴቶች ብቁ ሳይሆኑ ለፆታ ተሳትፎ ብቻ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ይቀመጣሉ። ይህም እነርሱን ከማጨናነቅ ባለፈ አገርንም ይጎዳል በሚል ሲተች ይደመጣልና በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት? ወይዘሮ ያለም፡- ይህ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። ብቁ ሳትሆን ለተዋፅዖ ማሟያነት በሚል በኃላፊነት ላይ የተቀመጠች ሴት የለችም። በኮታም አናምንም። በተቃራኒው ሴቶች ዕድሉን ቢገኙ አቅሙ ስላላቸው ይሠራሉ። ይህ ትክክል በመሆኑም ነጥረው የወጡ እንስቶች ማሳያዎች ናቸው። ሴቶች በተለያየ የሥራ ኃላፊነት ላይ የሚቀመጡት ኮታ ለመሙላት ነው የሚለው አስተሳሰብ መሰበር አለበት፤ ለዚህም እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ለመሥራት ያቀዳችኋቸው ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ምን ይመስላሉ?
ወይዘሮ ያለም፡- ብዙ ጊዜ ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት እንደ ችግር የሚነሳው ብቁ ሴቶች አለመኖር ነው። ይህንንም መፈታት እንዳለበት በማመን በየደረጃው ብቁ ሴቶች እንዲኖሩ የማሰልጠን ሥራ ተጀምሯል። በዚህም ለተለያየ ደረጃ የሚሆኑ አቅም ያላቸው ሴቶች ተመልምለው በፌደራል ደረጃ ስልጠና የመስጠት፣ በየክልሉ የማብቃት ሥራ እንዲሰራ፣ ተሞክሮ እንዲወስዱ እንዲሁም ዕድሉ እንዲመቻችላቸው የማድረግ ሥራ ታቅዷል። በዚህ መሠረት አንድ ዙር ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፤ ሁለተኛ ዙር ደግሞ በቅርቡ ይገባሉ።
አዲስ ዘመን፡- ቀረ የሚሉትና ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?
ወይዘሮ ያለም፡- የሴቶች ጉዳይ በአንድ ሚኒስቴር ብቻ የሚሠራ ባለመሆኑ ሁሉም ይመለከተዋል። በሴቶች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ ሁሉም በቅንጅትና በተባበረ ክንድ እንዲሠራ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለቃለመጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑልን በጣም እናመሰግናለን!
ወይዘሮ ያለም፡- እኔም አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2011
በፍዮሪ ተወልደ